በግብርና ዘርፍ ኢንሹራንስ 230 ሚሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽሟል

አዲስ አበባ፡ባለፉት ሦስት ዓመታት 230 ሚሊዮን ብር የግብርና ምርት የኢንሹራንስ ክፍያ መፈጸሙን ተቋሙ አስታውቋል።

ፑላ አማካሪዎች እና የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ የግብርና ኢንሹራንስ ጥምረት የምሥረታ ሥነ ሥርዓት በትላንትናው ዕለት አካሂደዋል።

የፑላ አማካሪዎች የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ዳግማዊ ኃይለእየሱስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ክልል 1 ሚሊዮን አርሶ-አደሮችን የግብርና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ባለፉት ሦስት ዓመታትም 230 ሚሊዮን ብር የግብርና ምርት ካሣ ክፍያ ተፈጽሟል።

በመጀመሪያ ዙር 122ሺህ በሚደርሱ አርሶ አደሮች ላይ የሙከራ ትግበራ መከናወኑን የተናገሩት አቶ ዳግማዊ፤ ከጀርመን መንግሥት እና ከዓለም ምግብ ፕሮግራም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በመጀመሪያ ዙር 39 ሚሊዮን ብር የካሣ ክፍያ ተከፍሏል። ይሄውም በኢትዮጵያ ትልቁ ክፍያ መሆኑን ተናግረዋል።

በግብርና ኢንሹራንስ ዘርፍ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ትልቁ ችግር የፕሪሚየም የክፍያ መጠኑ እስከ 35 በመቶ መሆኑ ነው ብለዋል። ይህ ማለት 100ሺህ ብር ሰብል ያለው ሰው ለኢንሹራንስ 35ሺህ ብር ይከፍላል። ይሄ ቁጥር በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ አስቸጋሪ ያደርገዋል ሲሉ አስረድተዋል።

ለዚህም በተቋሙ መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደው በ300 ወረዳዎች አርሶ-አደሩ የአፈር ማዳበሪያ ምርትን ሲገዛ አብሮ የኢንሹራንስ ክፍያውን እንዲከፍል በማድረግ ስጋቱን ወይም ሪስኩን በ300 ወረዳዎች በማከፋፈል የክፍያ መጠኑን መቀነስ መቻሉን አብራርተዋል።

አርሶ-አደሮች በአንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ 200 ብር በመክፈል ወደ ኢንሹራንስ ሥርዓቱ እንደሚገቡም ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በዓለም ደረጃ የግብርና ኢንሹራንስ ያላቸው አርሶ-አደሮች ከ20 በመቶ በታች ናቸው። በኢትዮጵያ የግብርናው ዘርፍ ለሀገራዊ ጥቅል ምርትና ከፍተኛ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ሚና ቢኖረውም የግብርና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ አርሶ-አደሮች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው ብለዋል።

የግብርናው ዘርፍ በየጊዜው ችግሮች እንደሚገጥሙት በመግለፅ፤ በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ የግብርና ኢንሹራንስ ጥምረት የግብርና መድኅን ሽፋንን ለማሳደግ እንደሚረዳ ገልጸዋል። ጥምረቱን የጀመሩት ኢንሹራንሶች ቀደም ሲል ግብርናውን ሲደግፉ የነበሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ግብርናው በተለያየ ጊዜ በጎርፍ፣ በድርቅ፣ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ችግር ይፈተናል ያሉት አቶ ዳግማዊ፣ ይህን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ የግብርና ኢንሹራንስ ጥምረት መመሥረቱ ለአርሶ-አደሩ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ዳግማዊ ገለፃ፣ የፑላ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የሀገር በቀል ኢንሹራንስ ማኅበራትን በማገዝ እና የግብርና ኢንሹራንስ ችግሮችን በመለየት የተለያዩ አዲስ ሞዴል ፕሮግራሞችን በመቅረጽ አርሶ-አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። ኩባንያው በ20 ሀገራት ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን የግብርና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

የኢንሹራንስ ተጠቃሚ ቁጥሩን ለማሳደግና ደረጃውን የጠበቀ የግብርና ኢንሹራንስ ለመስጠት የኢትዮጵያ የግብርና ኢንሹራንስ ጥምረት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ መኸር ወቅት 3 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። በእለቱም የጋራ የስምምነት ሰነድ ከፈረሙ አጋር የኢንሹራንስ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ሌሎች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸው፤ ተቋሙም ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መክፈቱን ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የፋይናንስ ሴክተሮች ጥምረት ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፤ ትልቁን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚይዘውን የግብርና ዘርፍ በኢንሹራንስ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ጥምረቱንም በቀጣይ አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ኢንሹራንስ ጥምረት ላይ የተካተቱት ዓባይ ኢንሹራንስ፣ ኒያላ ኢንሹራንስ፣ ኦሮሚያ ኢንሹራንስ፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር እና የኢትዮጵያ መድኅን ድርጅት ናቸው።

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You