አሜሪካ የኢራንን የኒውክሌር ልማት ለዓመታት ወደ ኋላ እንደመለሰችው ገለፀች

 

አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የፈፀመችው ጥቃት የሀገሪቱን የኒውክሌር መሣሪያ ልማት ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ወደ ኋላ እንደመለሰው ገልፃለች፡፡

የአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት (Penta­gon) አሜሪካ የፈፀመቻቸው ከባድ ጥቃቶች የኢራንን የኒውክሌር ጣቢያዎች እንዳወደሟቸው ከደኅንነት መረጃዎቹ ግምገማ መረዳት እንደቻለ ይፋ አድርጓል፡፡ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሾን ፓርኔል፣ የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች የአሜሪካ ጦር በፈፀማቸው ጥቃቶች እንደወደሙ ተናግረዋል፡፡ ጥቃቶቹንም ‹‹ግልጽና የጀግንነት ዘመቻዎች›› ብለዋቸዋል፡፡ ‹‹የኒውክሌር ፕሮግራማቸውን ቢያንስ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ወደ ኋላ መልሰነዋል፡፡ የመከላከያ መሥሪያ ቤቱ የደኅንነት ግምገማዎች ያን ያሳያሉ›› ብለዋል፡፡

የእሥራኤልና ኢራን ውጊያ በተጀመረ በዘጠነኛው ቀን አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟ ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦራቸው በፎርዶው፣ ናታንዝና ኢስፋሃን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የተሳኩ ጥቃቶችን መፈፀሙንና ጣቢያዎቹን ከጥቅም ውጭ ማድረጉን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ትራምፕ ይህን ቢሉም ከአሜሪካ የስለላና ደኅንነት ተቋማት ሾልኮ በወጣ ምስጢራዊ መረጃ፣ የአሜሪካ ጥቃቶች በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያደረሱት ጉዳት ትራምፕ አክብደው በገለጹት ልክ እንዳልሆነ ተገልፆል፡፡ መረጃው የአሜሪካ ጥቃቶች የኢራንን የኒውክሌር መርሐ ግብር በወራት ብቻ ወደ ኋላ እንዲመለሱ አድርጓል ብሏል፡፡ ጥቃቱ ከተፈፀመ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሾልኮ የወጣና ለብዙ መገናኛ ብዙኃን የደረሰ የደኅንነት ምርመራ፣ ጥቃቶቹ የኒውክሌር ልማቱን ወሳኝ ክፍሎች እንዳላወደሙና ዩራኒየም የማብላላት ሥራውን የሚያዘገዩትም ለጥቂት ወራት ብቻ እንደሆነ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ትራምፕ በአሜሪካ የተፈፀሙት ጥቃቶች በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያደረሱት ጉዳት ከባድ እንዳልሆነ የሚገልጹ መረጃዎችን በአፅንዖት ተቃውመዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱና የአስተዳደራቸው ባለሥልጣናት መረጃውን አጣጥለውታል፤ መረጃውን ያሰራጩትን መገናኛ ብዙኃንንም አብጠልጥለዋቸዋል፡፡

ትራምፕ ‹‹የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል›› ሲሉ በቁጣ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹በታሪክ ውስጥ ስኬታማ ከሆኑ ወታደራዊ ጥቃቶች አንዱን ለማሳነስ ሙከራ አድርገዋል›› ሲሉ መገናኛ ብዙሃንን ወቅሰዋል። የመከላከያ ሚኒስትሩ ፔት ሄግሴት ‹‹እናንተ መገናኛ ብዙኃን ትራምፕ ሲሳካላቸው አትወዱም፡፡ ለትራምፕ የምታሳዩት ምቀኝነት በደማችሁ ውስጥ የሰረፀ ነው፡፡ ትራምፕ እንዲሳካላቸው አትፈልጉም›› በማለት መገናኛ ብዙኃኑንና ዘገባዎቻቸውን በከባድ ኃይለ ቃላት ወርፈዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ደግሞ ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት የሚያስችል ዩራኒየምን እንደገና በወራት ጊዜ ውስጥ ማበልፀግ ለመጀመር የሚያስችል አቅም እንዳላት ይፋ አድርጓል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ፣ አሜሪካ በሦስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ያደረሰችው ድብደባ ከባድ ቢሆንም አጠቃላይ ውድመት አለመድረሱን ገልጸዋል። ‹‹እውነቱን ለመናገር አንድ ሰው ሁሉም ነገር እንደወደመ እና ምንም የቀረ ነገር የለም ብሎ መናገር አይችልም፡፡ በወራት ጊዜ ውስጥ ጥቂት ማብላያዎችን በማሽከርከር የበለፀገ ዩራኒየም ያመርታሉ፡፡ የኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ አቅሞችን ይዘዋል፡፡ ስለዚህ ከፈለጉ ይህንን እንደገና መጀመር ይችላሉ›› ሲሉ ግሮሲ ተናግረዋል። ይህ የዋና ዳይሬክተሩ ሃሳብ ዶናልድ ትራምፕ ‹‹የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል›› ሲሉ ከተናገሩት መረጃ ጋር ይቃረናል።

ኢራን በበኩሏ የኒውክሌር ጣቢያዎቿ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰባቸው እርስ በርሳቸው የሚጋጩ መረጃዎችን አስተላልፋለች። አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ‹‹ጥቃቱ ምንም ፋይዳ የለውም›› ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አባስ አራግቺ ግን ‹‹ከመጠን በላይ እና ከባድ›› ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ጋር ያላትን ትብብር ለማቋረጥ የሚያስችሏትን ርምጃዎች እየወሰደች ነው፡፡ የኢራን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀገሪቱ ከኤጀንሲው ጋር ያላትን ትብብር እንድታቆም ወስነዋል፡፡ ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዝሽኪያንም የሀገሪቱ ምክር ቤት ባወጣው ሕግ ላይ ፈርመዋል፡፡ በሕጉ መሠረት የኤጀንሲው ባለሙያዎች ከኢራን ብሔራዊ የደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ፈቃድና እውቅና ውጭ የኒውክሌር ጣቢያዎችን መጎብኘት አይችሉም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኢራን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎችን ለመጎብኘት ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አድርጋዋለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ‹‹የግሮሲ በቦምብ የተደበደቡ ጣቢያዎችን የመጎብኘት ጥያቄ ጎጂና ትርጉም የለሽ ነው፡፡ ኢራን ሕዝቧን፣ ሉዓላዊነቷንና ጥቅሟን ለመጠበቅ ማንኛውንም ርምጃ የመውሰድ መብት አላት›› ብለዋል፡፡

ኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎቿን ለኤጀንሲው ክፍት እንድታደርግ አሜሪካ ጠይቃለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ፣ ኢራን ከኤጀንሲው ጋር የነበራትን ትብብር ለማቋረጥ መወሰኗ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ የፈረንሳይ፣ የጀርመንና የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ ደግሞ፣ ኢራን የኤጀንሲውን ዋና ዳይሬክተር ጥያቄ ውድቅ ማድረጓን አውግዘው፣ ለኤጀንሲው ሙሉ ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡

ከሁለት ሳምንታት በፊት እሥራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማትና ወታደራዊ ጣቢዎች ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ለ12 ቀናት የዘለቀ የአየር ውጊያ አካሂደዋል፡፡ እሥራኤል በፈፀመቻቸው ጥቃቶች በርካታ የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች መገደላቸው እና ወታደራዊ ተቋማት መውደማቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ኢራንም በወሰደቻቸው የአፀፋ እርምጃዎች በእሥራኤል ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡ በጥቃቶቹ ሰላማዊ ዜጎችና የመኖሪያ አካባቢዎች ሰለባ እንደሆኑም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

አሜሪካም ከእሥራኤል ጎን ተሰልፋ በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ፈፅማለች፡፡ ኢራን አሜሪካ በኒውክሌር ጣቢያዎቿ ላይ ለፈፀመችባት ጥቃት ኳታር በሚገኘው አል-ኡዴይድ የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት በመፈፀም የአፀፋ ምላሽ ሰጥታለች፡፡ ከጦር ሰፈሩ ጥቃት ጥቂት ሰዓታት በኋላ ሁለቱ ሀገራት ተኩስ ለማቆም መስማማታቸው ተገልፆ የ12 ቀናቱ የአየር ላይ ውጊያ እንደቆመ ይታወሳል፡፡

በአንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You