የስኳር ልማት ኢንዱስትሪ በሀገራችን ከግምሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋ ኢንዱስትሪ ነው። ሆኖም ኢንዱስትሪው እድሜውን በሚመጥነው ልክ እድገት አላሳየም ። ኢንዱስትሪው በሚፈለገው ፍጥነት ባለማደጉም የስኳር ምርት እጥረት በሀገር ውስጥ እንዲከሰት አንዱ ምክንያት ሆኗል ። ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ካለማደጉም ባሻገር በአፍሪካ በህዝብ ቁጥር ሁለተኛ በሆነችው ሀገራችን እየተመዘገበ ያለው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እድገት እና ስኳርን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር መበራከት የሀገሪቱ የስኳር ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር አስገድዷል።
የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግር እየሆነ መጥቷል ። ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥት ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድ ጀምሮ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሰራባቸው ዘርፎች አንዱ የስኳር ኢንዱስትሪ ልማት ነው ። ዕቅዱ ከተጀመረ ወዲህ የሀገሪቱ የስኳር ኢንዱስትሪ ለማስፋፋትና ለማዘመን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወጪ የተደረገበት ዘርፍ ነው።
በዚሁ መሰረት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተካሂዷል ። አንዳንዶቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን አንዳንድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች መጓተት ታይቶባቸዋል ። በአጠቃላይ ሲታይ በስኳር ልማት ዘርፍ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ማሳካት አልተቻለም ። በተለይም የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ለማሳካት የተያዘውን ግብ ካላሳካቱ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ።
የሀገሪቱን የስኳር ፍላጎት ከማሟላት አልፎ ለሀገሪቱ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ግብ ተቀምጦለት ነበር ። ከዚያ ባሻገር የሥራ እድል በመፍጠር እና በአካባቢው የሚኖረውን የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ህይወት ለመለወጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም የተቀመጠለትን ግብ ሳይመታ ቀርቷል ።
ሳይጠናቀቁ የቆዩት ላይ መንግሥት ጥናት በማካሄድ ግንባታቸው ተጠናቆ ምርት ወደ መስጠት እንዲሸጋገሩ ለማስቻል ጥረቶች ተደርገዋል ። የለውጥ አመራር ወደ አመራር ከመጣበት ማግስት ጀምሮ የፕሮጀክቶችን ችግሮች ለመለየትና ለችግሮቹ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ተደርጓል ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተወሰዱት እርምጃዎች አንዳንድ የስኳር ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ ገብተዋል ። ከረጅም ጊዜ መጓተት በኋላ በመንግሥት በተወሰዱት ቆራጥ እርምጃዎች ወደ ምርት ከተሸጋገሩት መካከል የበለስ ስኳር ልማት ቁጥር አንድ ፕሮጀክት እና የኦሞ ኩራዝ ሁለት እና ሶስት ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው ።
ሆኖም እስካሁን ተጠናቀው ምርት ወደ ማምረት ያልገቡ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችም አሉ፤ ከእነዚህም መካከል ፕሮጀክቶች በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኙ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ነው ። እነዚህ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ስኳር እጥረት ለመቅረፍ እንዲሁም ሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ነበሩ ። ከነዚህ ፋብሪካዎች መካከል በዞኑ በሰለማጎ ወረዳ የሚገኘው ኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት አንድ በቀን 24 ሺህ ቶን አገዳ እንዲፈጭ ታቅዶ ነው ወደ ግንባታው የተገባው።
ግንባታውን ብረታ ብረትና ኢንጂነርንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ነበር ሲያከናውን የነበረው። ሜቴክ የፋብሪካውን ግንባታ 84 በመቶ ካደረሰ በኋላ ግንባታው ቆሟል ። ግንባታው የቆመው ደግሞ የፋብሪካውን ወሳኝ እና ቴክኒካል የሆነውን ክፍል ቡድን መገንባታ ባለመቻሉ ውሉ መቋረጡን ጠቁሟል። ሆኖም ውሉ ከተቋረጠ ወዲህ ምንም አለመሰራቱን በፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የደቡብ ኦሞ አካባቢ ተወካይ በየካቲት 15 /2014 ዓ.ም በተካሄደው ሶስተኛው አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የኦሞ ኩራዝ አንድ እና አምስት ስኳር ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ የተያዘውን እቅድ አስመልክቶ ጥያቄ ባነሱበት ወቅት ገልጸዋል ።
ፕሮጀክቱ በተያዘላቸው ጊዜ ካለመጠናቀቁም ባሻገር መንግሥት የፕሮጀክቱን ችግር በጥናት ከለየ በኋላ ራሱ የፕሮጀክቱ ግንባታ ሊካሄድ አለመቻሉ እና የአካባቢው ህዝብና ሀገሪቱ ከፕሮጀክቱ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም ማግኘት አለመቻላቸው እንደ ሀገር ኪሳራ መሆኑን ነው ያነሱት።
ሌላኛው በደቡብ ኦሞ ዞን በኛንጋቶም ወረዳ የኦሞ ስኳር ፕሮጀክት ቁጥር አምስት የግንባታ ሥራ JJIEC በተሰኘ የቻይና ኩባንያ ከህዳር ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን የቆየ ሲሆን በቀን 24 ሺህ አገዳ ይፈጫል ተብሎ ታቅዶ ነው ሲገነባ የነበረው። ኩባንያው የፋብሪካውን ግንባታ 25 በመቶ ብቻ ሰርቶ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ቆሞ እንደሚገኝና ይህም ሀገርና የአካባቢውን ህዝብ ከፕሮጀክቶቹ ማግኘት ያለበትን ጥቅም ማግኘት እንዳይችል ማድረጉን የአካባቢው የህዝብ እንደራሴ በቅርቡ በፓርላማ ተናግረዋል ።
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት የዋና ፕሮጀክቱ ግንባታው ከመቆሙ ባሻገር የፕሮጀክት የመስኖ ካናል ግንባታው የፌዴራል ውሃ ሥራዎች ግንባታ ድርጅት ጀምሮ የነበረ ሲሆን የመስኖ ካናል ግንባታም ቆሟል። የኦሞ ኩራዝ አንድና አምስት እንዲሁም የመስኖ ካናል ባለመጠናቀቁ ፕሮጀክቱን ተከትሎ የሰፈሩ የኛንጋቶችምና የሰለማጎ ወረዳዎች ነዋሪዎች የቅሬታ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን የህዝብ እንድራሴው ጠቁመዋል ።
የነዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ በአንድ በኩል እየጨመረ ያለውን የሀገሪቱን የስኳር ፍላጎት ለማሟላት ፋይዳው ከፍ ያለ ሲሆን በሌላ በኩል ለዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር ስለሆነ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከአካባቢው ህዝብ ተወካይ ለተነሳው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በርካታ የስኳር ፋብሪካዎች በተመሳሳይ ጊዜ መጀመሩ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቁ ምክንያት ሆኗል።
የለውጥ ኃይሉ ወደ አመራር ከመጣ ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች ተጓተው የነበሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ሥራ ማስጀመር መቻሉን ጠቁመዋል ። በለስ ፣ ኦሞ ሁለትና ሶስት አልቆ ሥራ ጀምረዋል ። ይህ እንደ ትልቅ ድል የሚወሰድ ነው። አንድና አምስት በፋይናንስ ምክንያት መጓተቱን ጠቅሰው ግንባታውን ለማጠናቀቅ የፋይናንስ ችግሩ መቀረፍ አለበት ብለዋል ። ፕሮጀክቱ ተጠናቆ የአካባቢው ህዝብና ሀገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን መንግሥት ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል ነበር ያስገነዘቡት ።
ኦሞ ኩራዝ አንድ እና አምስት ለማጠናቀቅና ወደ ምርት ለማስገባት እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ ከአዲስ ዘመን ጥያቄ የቀረበላቸው የስኳር ኮርፖሬሽን ቃል አቃባይ አቶ ደመቀ ረታ እንደተናገሩት ፤ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሊገነቡ ከታቀዱ አራት ስኳር ፋብሪካዎች መካከል ሁለቱ ማለትም ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት እና ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ መደበኛ ምርት የገቡ ቢሆንም፤ የቀድሞው ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (METEC) የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ግንባታን ለማከናወንና በ18 ወራት አጠናቆ ለማስረከብ በ2004 ዓ.ም ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ውል ቢፈጽምም በታየው ከፍተኛ የግንባታ መጓተት ሳቢያ ውሉ በ2010 ዓ.ም እንዲቋረጥ ተደርጓል። ውሉ በመቋረጡ በአሁኑ ወቅት ለኩራዝ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ለምቶ የነበረ የሸንኮራ አገዳ ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት እና ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች እየቀረበ ይገኛል።
በሌላ በኩል በሁለት ምዕራፍ የሚገነባውና ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ በቀን 24 ሺህ ቶን አገዳ ይፈጫል ተብሎ የሚጠበቀው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ስኳር ፋብሪካ የግንባታ ሥራ JJIEC በተሰኘ የቻይና ኩባንያ ከህዳር ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን የነበረ ቢሆንም ባጋጠመው የፋይናንስ ዕጥረት ምክንያት ግንባታው ሊቋረጥ ችሏል። የፋብሪካው የመጀመሪያ ምዕራፍ የግንባታ ሥራ በተቋረጠበት ወቅት አፈጻጸሙ የአካባቢው የህዝብ እንድራሴ በፓርላማ ከጠቀሱት በላይ መሆኑን ያነሳሉ። ግንባታው 27.1 በመቶ ደርሶ እንደነበርም ጠቁመዋል ።
በአሁኑ ወቅት የፋብሪካ ግንባታቸው ተቋርጦ የሚገኘውን የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ እና ቁጥር አምስት ስኳር ፋብሪካዎችን ግንባታና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በመንግሥት ድጋፍ አማካይነት ከተለያዩ ምንጮች ፋይናንስ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው ። እስካሁን ድረስ ግን በተለያዩ ምክንያቶች የፋይናንስ ምንጭ ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግረዋል ። በመሆኑም ፕሮጀክቶቹን ለማስቀጠል የሚያስፈልግ ፋይናንስ መገኘት እንደተቻለ ሥራዎች እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።
በኦሞ ኩራዝ ፋብሪካ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ያደረጉ ከፋይናንስ በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም አሉ። የኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ‘ጣፋጭ ራዕይ’ እና ተግዳሮቶች መካከል የሚገኘው ፕሮጀክት በሚል ርዕስ በቤኔዲክት ካሚስኪ በተሰኘ ምሁር ተፅፎ ታንዲፍ ኦንላይን በተሰኘ ድረገጽ ላይ የታተመው የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው ፤
በታችኛው የኦሞ ሸለቆ የሸንኮራ አገዳ ልማት እና የስኳር ልማት ላይ የታዩት ችግሮች የተለያዩ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ ። ፕሮጀክቱ የሚገነባበት ቦታ ርቀት እና ተያያዥ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት እጦት ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ አንዱ ምክንያት ሆኗል ።
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሳያደርግ በመንግሥት ግፊት የመጀመሪያ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አንድ ላይ ግቦችን ለማሳካት ተብሎ መጀመሩ ለፕሮጀክቱ መጓተት ሌላኛው ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ደካማ እቅድ፣ የተሳተፉት ቁልፍ እቅድ አውጪዎችና ተቋራጮች ልምድ አነስተኛ መሆን በፕሮጀክቱ ላይ በመጠን እና በማቀነባበር አቅም ላይ ከፍተኛ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ምክንያት ሆኖ ነበር። በተጨማሪም ግንባታው ከተጀመረ በኋላ በውጭ አማካሪዎች ምክር መሰረት መቀየር ያለባቸው ነገሮች ስለነበሩ እነዚህን መቀየር ተጨማሪ ወጪ እና ጊዜ መጠየቁን ጥናቱ ያሳያል።
ከዚያ ባሻገር በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ለስኳር ፕሮጀክቶች መንግሥት የሰጠውን አይነት ልዩ ትኩረት በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን አለመስጠቱ ፕሮጀክቶቹ እንዲጓተቱ መንስኤ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የመንግሥት ስትራቴጂክ ትኩረት ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመሸጋገሩ የስኳር ኢንዱስትሪው ዝቅተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል ። የመንግሥት ትኩረት መቀነሱ ለፋይናንስ እጥረቱ አንዱ መንስኤ ነው።
መንግሥት የኦሞ ኩራዝ ሁለት እና ሶስት ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የበለስ ስኳር ፕሮጀክቶችን ከገባበት ቅርቃር በማውጣት ወደ ምርት እንዲሸጋገር የወሰደውን አይነት ቆራጥ እርምጃዎች በመውሰድ ቁጥር አንድ እና አምስትን በማጠናቀቅ ወደ ምርት ለማሸጋገር ቆራጥ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014