ኢትዮጵያ ያልተነካ በርካታና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ:: ያላትን የሰው ኃይል እና የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም አለመቻሏ ድህነቷን ካባባሱባት ምክንያቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታመናል:: በሁሉም አቅጣጫ ገና ብዙ ያልተነካና ያልተሠራበት ዘርፍ ስለመኖሩም እንዲሁ:: ታድያ አገሪቷ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ሰፊ ቁጥር ካለው የሰው ኃይል ጋር በማቀናጀት ለውጥ ለማምጣትና ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የተጠናወታትን ድህነት ከሥሩ መንግላ ማውጣት እንድትችል መንግሥት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ይስተዋላል::
ለአብነትም አገሪቷ ያላትን እምቅ ሀብት አውጥታ መጠቀም እንድትችል ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸውን ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ማሰማራት መቻል አንዱ ነው:: ለዚህም መንግሥት ወጣቶችን በየአካባቢያቸው በማደራጀት በፈለጉት የሙያ ዘርፍ ተሰማርተው መሥራት እንዲችሉ ሁኔታዎችን ሲያመቻች መቆየቱ ይታወቃል:: በተለይም አምራች ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት የማምረቻና የመሸጫ ቦታ እንዲሁም የሥራ ማስኬጃ የፋይናንስ ብድር እና ሌሎችንም ድጋፎች በማድረግ ወጣቱ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርለት ሲያደርግ ቆይቷል:: መንግሥት ያደረገውን ድጋፍ በመጠቀም እራሳቸውንና አካባቢያቸውን መለወጥ የቻሉ እንዳሉ ሁሉ በርካቶችም መንግሥት ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጪ ሆነው ለኪሳራ የተዳረጉ አልታጡም::
በዛሬው የ‹‹ ስኬት ›› አምዳችን እንግዳ ያደረግነው ያለውን ዕውቀት ተጠቅሞ ከመንግሥት ባገኘው የመሥሪያ ቦታ በዶሮ እርባታ ውጤታማ ስለሆነው ግለሰብ ነው:: ግለሰቡ ተወልዶ ባደገበት ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቅቋል:: ከትምህርት በኋላም ሥራ መሥራት እንዳለበት በማመን ቢሾፍቱ በሚገኝ አንድ የዶሮ እርባታ ድርጅት ውስጥ ከመኪና ረዳትነት አንስቶ ሾፌር ሆኖ አገልግሏል:: አለፍ ሲልም የመኪና ሾፌርና ረዳት ሆኖ ባገለገለበት ትልቅ የዶሮ እርባታ ድርጅት ውስጥ ለሥራ ካለው ፍላጎትና ጉጉት የተነሳ በዶሮ እርባታ ዘርፉ ውስጥም ቆይቷል::
ቢሾፍቱ ከተማ ሥራን ‹‹ሀ›› ብሎ በመኪና ረዳትነት የጀመረው እንግዳችን አቶ ሰለሞን ጌታቸው ዛሬ ላይ ታዋቂ ለሆኑ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች እንዲሁም ሱፐርማርኬቶች የዶሮ ሥጋ አቅራቢ ከመሆኑ አስቀድሞ የ120 ብር ደመወዝተኛ እንደነበር አስታውሶናል:: በ120 ብር ደመወዝም መንጃ ፈቃድ አውጥቶ ወደ መኪና ማሽከርከር ማደግ ችሏል:: በዚህም የፍሪጅ መኪና ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ አበባ ተበልቶ የተዘጋጀ የዶሮ ሥጋና እንቁላል ጭምር እያጓጓዘ ለደንበኞች ተደራሽ የማድረግ ሥራ ሰርቷል:: ይህም አካባቢንና ሰዎችን የመተዋወቅ እድል ፈጥሮለታል:: እንዲህ እንዲህ እያለ ለስምንት ዓመታት በድርጅቱ ሲቆይ ካገኘው የሥራ ልምድና ዕውቀት በበለጠ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ትልቅ አቅም የሆነው ደንበኞችን ማግኘት መቻሉ እንደሆነ ይናገራል::
ተቀጥሮ ሲሰራበት በነበረው የዶሮ እርባታ ድርጅት ውስጥ ያገኘውን እውቀት ተጠቅሞ የግሉን የዶሮ እርባታ ሲጀምር የገበያ ችግር ያልገጠመው አቶ ሰለሞን መነሻ ካፒታል 15 ሺ ብር አስመዝግቦ እንደ ጀመረ ያስታውሳል:: በወቅቱ አምስት መቶ ጫጩቶችን በመግዛት ዘርፉን ሲቀላቀል አንድ ኪሎ ዶሮ 62 ብር ሂሳብ በመግዛት ነበር:: ለአምስት ሺ ጫጩቶችም 40 ሺ ብር አካባቢ ወጪ ያደረገው መሆኑን ያስታወሰው አቶ ጌታቸው፤ ካፒታሉን ያገኘውም ከጓደኞቹና ከቤተሰቡ በብድር መልክ ነበር::
‹‹የትምህርት ደረጃዬ 10ኛ ከፍል በመሆኑ ይህን ብሰራ ያን ብሰራ ብዬ ማማረጥ አልችልም›› የሚለው አቶ ሰለሞን ፤ ነገር ግን ከመቀጠር ይልቅ በግል መሥራት አዋጭ እንደሆነ ለማወቅና ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትምና በቀላሉ ዘርፉን መቀላቀል ችሏል::
ሥራው አዋጭ ለመሆኑም በድርጅቱ የነበረው ቆይታ ከበቂ በላይ ዕድል የሰጠው በመሆኑ ወደ ሥራው ሲገባ ለአዋጭነቱ ሙሉ ዕምነት ነበረው:: በተለይም ተቀጥሮ በሚሰራበት ወቅት የሚያውቃቸውን ደንበኞች ቀዳሚ የገበያው መዳረሻ ማድረግ መቻሉ በአጭር ጊዜ ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል::፡
ከመነሻ ካፒታሉ በላይ ለበርካታ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ፈተና የሆነው የማምረቻ ቦታ ጥያቄውን መንግሥት የመለሰለት ሲሆን፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በመደራጀት የማምረቻ ሼድ አግኝቷል:: ከመንግሥት ባገኘው ሼድ ውስጥም የዶሮዎቹን ምግብ በአግባቡ መግቦና ጤናቸውን ጠብቆ ለ45 ቀናት በማቆየት የሥጋ ዶሮን እያረባ ለገበያ ማቅረብ ዋና ሥራው ሆነ:: በዋናነት የሥጋ ዶሮን በማርባት አዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የተለያዩ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች እንዲሁም ሱፐርማርኬቶች ያቀርባል::
ዶሮዎቹ አስፈላጊው እንክብካቤ ከተደረገላቸውና ጤናቸው ተጠብቆ ምግባቸውን በአግባቡ ካገኙ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘትና ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ያጫወተን አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ የሚያረባቸው የሥጋ ዶሮዎች ለገበያ የሚያቀርባቸው በእርባታ ቦታው ላይ ታርደውና ተበልተው እንደሆነም ይናገራል:: ደንበኞች በሚፈልጉት መንገድ የሚዘጋጀው የዶሮ ሥጋ ሙሉ ዶሮውን ለሚፈልግ ሙሉ ዶሮው የሚዘጋጅለት ሲሆን የዶሮዎቹን የተለያየ ክፍል የሚፈልገውም የፈለገውን አካል በማዘጋጀት ያቀርባል:: የዶሮ ሥጋ በብዛት የሚጠቀሙት በርገር ቤቶች እንደመሆናቸው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚገኙት ታዋቂ በርገር ቤቶች ያቀርባል::
ለዶሮ እርባታ ሥራ የፍሪጅ መኪና ወሳኝ ነው የሚለው አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ ካለፍሪጅ መኪና የዶሮ እርባታ የማይታሰብ ሥራ እንደሆነም ይናገራል:: ታድያ ቀደም ሲል ይህን ለሥራው ወሳኝ የሆነው መኪና ከግለሰቦች ተከራይቶ ሲሰራ ከቆየ በኋላ በአሁኑ ወቅት ግን የግሉን ባለፍሪጅ መኪና መግዛት ችሏል:: ከጊዜ ወደ ጊዜ የማምረት አቅሙን እያሳደገ በመምጣትም በአሁኑ ወቅት በሳምንት እስከ ሶስት ሺ የሥጋ ዶሮዎችን አምርቶ፣ አርዶና በልቶ ለደንበኞቹ ያከፋፍላል:: ከዚህም በተጨማሪም አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ በሚገኘው የመሸጫ ሱቅ ከፍቶ የሥጋ ዶሮዎቹ ይሸጣሉ::
በዋናነት ከተሰማራበት ሥራ በተጨማሪ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን በመሸጫ ሱቅ ያቀርባል። በአማራ ክልል ጎጃም አካባቢ የሚገኙ አርብቶ አደሮች የሚያመርቱትን ወተትና የወተት ተዋጽኦ ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ዕድል ፈጥሮላቸዋል::
በከፍተኛ የዶሮ እርባታ ድርጅት ውስጥ በመሥራቱ በዘርፉ የመሰማራት ዕድሉን አስፍቶ ዛሬ ላይ ከግለሰቦች ጀምሮ ትላልቅ ለሆኑ ድርጅቶች ጭምር ምርቱን በትስስር ለገበያ የሚያቀርበው አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ በዘርፉ 10 ለሚደርሱ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል:: በቋሚነት ከፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ጫጩቶችን በሚረከብበት ጊዜም ጊዜያዊ ሠራተኞችን ይቀጥራል::
ዘርፉን ፈታኝ ከሚያደርጉት ተግዳሮቶች መካከል ጫጩቶቹ ከውጭ አገር በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ በመሆናቸው በስፋት ለማምረት አስቸጋሪ እንደሆነና በተለይም ጫጩቶቹ በተወሰኑ አስመጪዎች እጅ መሆኑ ፈታኝ ያደርገዋል:: ምንም እንኳን በዘርፉ ከፍተኛ ዕውቀትና ልምድ ያካበተ ቢሆንም ቅሉ ጫጩቶቹን ከውጭ አገር ለማስገባት ከፍተኛ ካፒታል ሊያውም የውጭ ምንዛሪ መጠየቁ ሥራውን በሚፈልገው መጠን ማስኬድ እንዳላስቻለው አቶ ጌታቸው ይናገራል::
ከውጭ የሚገቡት እንቁላል ጣይ ጫጩቶቹ ሲገቡ ከአንድ ጊዜ በላይ እንዳይባዙ ተደርገው መሆኑ የዘርፉ ትልቅ ችግር ነው:: እንቁላል ጣይ ዶሮዎቹ ከውጭ ሲገቡ አንድ እንቁላል አንድ ጊዜ ብቻ ከጣለች በኋላ በቀጥታ ወደ ሥጋነት ተሸጋግራ አገልግሎቷን ታበቃለች:: ዋጋውም ቢሆን አንድ ጫጩት በአንድ መቶ ብር የሚገዛ ሲሆን ጫጩቶቹ ይደጉም አይደጉም አይታወቅም። እንዲሁም ከዘርፉ ችግሮች አንደኛው ከውጭ የሚገቡት ዶሮዎች የሚራቡ አለመሆናቸው እንደሆነና ለዚህም መንግሥት በቻለው አቅም ድጋፍ ቢያደርግ በዘርፉ ያለውን ችግር ማቃለል የሚቻል መሆኑን ይናገራል ::
ጫጩቶቹ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልጉ ሲሆን፤ ከምግባቸው ጀምሮ ህክምናቸውንና አጠቃላይ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ በማድረግ በ45 ቀናት ውስጥ ዶሮዎቹ ለሥጋ ይደርሳሉ በማለት ከአበሻ ዶሮዎች ጋር ሰፊ ልዩነት ያላቸው መሆኑን የገለጸው አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ አንድ የሀበሻ ዶሮን ለሥጋ ለማድረስ ከሶስት እስከ አራት ወራት የሚቆይ በመሆኑ የሀበሻ ዶሮዎችን ማርባት አዋጭ አለመሆኑን በማስረዳት በአጠቃላይ የሥጋ ዶሮ በአገር ውስጥ ማርባት የማይቻልና ከውጭ የሚገባ መሆኑን ተናግሯል::
በሥራ ዓለም ውስጥ በቀዳሚነት የተዋወቀውን የዶሮ እርባታ ተቀላቅሎ እራሱንና ቤተሰቡን መለወጥ የቻለው አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ በ40 ሺ ብር የጀመረው ሥራ በአሁኑ ወቅት ከመኪናውና ከተለያዩ ንብረቶች ውጭ በጥሬ ገንዘብ ብቻ ስምንት ሚሊዮን ብር ካፒታል መድረስ ችሏል:: መንግሥት ዜጎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በተለያየ የሥራ ዘርፍ መሰማራት እንዲችሉ በሰጠው እድል ከተደራጁ ኢንተርፕራይዞች መካከል አንዱ የሆነው አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ መንግሥት ባስቀመጠው አሰራር መሰረት በአምስት ዓመታት ውስጥ ሥራውን አሳልጦ፣ ሀብት አፍርቶና ውጤታማ መሆን በመቻሉ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ሽግግር ማድረግ ችሏል::
መንግሥት ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ያሸጋገራቸውን ኢንተርፕራይዞች በቀጣይ የማምረቻ ቦታ ለመስጠት ቃል የገባ መሆኑን የጠቀሰው አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ መንግሥት በገባው ቃል መሰረት መሬት ማቅረብ ከቻለ በቀጣይ የሥጋ ዶሮዎችን በስፋት ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ በአሁኑ ወቅት ያለውን ሙሉ አቅም አሟጦ እየተጠቀመ ሲሆን መንግሥት ደግሞ ባለው አቅም ላይ ሌላ አቅም መፍጠር ከቻለ የበለጠ አምርቶ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል አስረድቷል::
በቅርቡም የሚከበሩ በዓላትን አስመልክቶ አጠቃላይ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የዶሮ ሥጋ እንዲሁም ወተትና የወተት ተዋጽኦዎችን በስፋት ለገበያ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን የገለጸው አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ ደንበኞቹ በፈለጉት አይነት በማዘጋጀት ያስረክባል:: ሙሉውን ዶሮ የሚፈልግ እንዳለ ሁሉ እግር፣ መላላጫ፣ ታፋና ሌሎችንም እንደ ደንበኛው ፍላጎት የሚሸጥ ሲሆን የዶሮ እግር ማለትም ጥፍሮቹን ቻይናውያን አብዝተው የሚፈልጉት እንደሆነም አጫውቶናል::
ከሀበሻ ዶሮዎች ይልቅ የበለጠ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው የውጭ ዶሮዎች እንደሆኑ የሚናገረው አቶ ሰለሞን ጌታቸው፤ በዘርፉ ረዘም ላለ ጊዜ በመቆየቱ በሽታ ከያዛቸው እንደሚሞቱና ኪሳራ ውስጥ እንደሚገባ ጠንቅቆ በማወቁ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሁሉ ያደርጋል:: በመሆኑም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተሰማራበት የዶሮ እርባታ እስካሁን ይህ ነው የሚባል ችግር ያልገጠመው ቢሆንም ጫጩቶቹ በውስን ሰዎች እጅ ውስጥ ብቻ መሆናቸው ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ እንደሆነ ተናግሯል::
በአገሪቱ የዶሮ እርባታውን ጨምሮ በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የጎላ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ መንግሥት የጀመረውን የማበረታታትና የመደገፍ ሥራው አጠናክሮ ቢቀጥልና ተኪ ምርቶችን በስፋት መጠቀም መልካም ነው:: በማለት አበቃን::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014