ለርዕሱ የሰጠነውን ብሂል እንደተናገሩ የሚታመነው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (ከ144 – 1919 ዓ.ም) ናቸው። ብልህነታቸውና ፍትሕ አዋቂነታቸው ደምቆ የሚመሰከርላቸው እኒህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጎምቱ አባት ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ እስከ ዘመነ ዘውዲቱ ተከብረውና አንቱታን አትርፈው ያለፉ “የአገር አድባር” ይሏቸው ዓይነት የዘመናቸው “የሹሞች ቁንጮ” ነበሩ።
በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን መካከል ተፈጥሮ የነበረው የፖለቲካ ሽኩቻ ግራ ያጋባቸው ሀብቴ አባ መላ፤ የአልጋ ወራሹን ፖለቲካዊ ሴራ አስመልክተው ያንን ዘመን ተሻጋሪ ብሂል ለትዝብታቸው ማዋዣ እንደተጠቀሙበት በታሪክ ድርሳናት ሳይቀር ተመዝግቦ ተላልፎልናል። መቼም ሕዝባዊ ሥነ ቃል “አባ ከና” የሚባል ባለመብት ባይጠቀስለትም አልፎ አልፎ ግን እንዲህ ጠቋሚ መረጃ ሲገኝ “እከሌ እንደተናገረው” ብሎ ዋቢ ማመላከት አግባብ ስለመሆኑ የዘርፉ ሙያ ይመክረናል። “የለም ይህ አባባል በሌሎችም አንደበት ተነግሯል” የሚል ሞጋች ከቀረበም ለአሜንታው አንከራከርም። ሀብቴ አባ መላን ያስታወስናቸው የርዕሳችን “ባለ መብት” መሆናቸውን ለመግለጽ እንጂ ዝርዝር ግለ ታሪካቸውን ለመዘከር ስላልሆነ መንደርደሪያውን እዚህ ላይ ገታ አድርገን ወደ ዋናው ጉዳያችን እናዘግማለን።
ተቀምጠን ሰቅለናቸው ቆመው የገረፉን አበሳዎቻችን፤
ሀገራዊ መከራዎቻችንን እንዴት ስናስተናግድ እንደኖርን በውሱን የቃላት ትዝብት እንግለጽ ከተባለ ለውክልና የሚመጥነው አባባል “አታምጣው ነው እንጂ መቼስ ምን ይደረግ” የሚለው የ“ልበ ሰፊነታችን” ዳተኝነት እንደሆነ ጸሐፊው አጠንክሮ ያምናል። ዝርዝሩ በአግባቡ ይብራራል።
“ዳቦ በዋጋም በተደራሽነትም ብርቅ እስከ መሆን ደረሰ፣ ስኳር ለሞት መድኃኒትነት ቢፈለግ እንኳን መገኘት ስለመቻሉ አጠራጠረ፣ የጤፍ ዋጋ ናረ፣ ሽንኩርት ለሽታ እንኳን ጠፋ፣ ዘይት የወርቅ ያህል ተወደደ፣ የአንድ ኪሎ ሥጋ ከጠቦት መግዣ ዋጋ ጋር ተቀራረበ ወዘተ.” እያልን ስንጮኽ “መንግሥታችን” ያለ ዕውቀትና ያለ ብቃት በስልጣን ማማ ላይ አሽቀንጥሮ ያጎናቸው “ፊት አይቶ አደር” ሹሞቻችን አያፌዙ ሲዘባነኑብን ደጋግመን አድምጠናቸዋል።
የዓለም ኢኮኖሚ ሥርዓትን እየጠቀሱ፣ በወቅቱ የምንዛሪ ምንትስ እያመካኙ ፣ የመጓጓዣ ችግርን እያጦዙ፣ የጋራ ተጠቃሚ የሆኑበትን የደላሎች ሴራ እያወገዙ፣ ጉዳዩን ከእነርሱ ራስ ላይ በማውረድ ሌሎች የመንግሥት ሹመኞችን እየወቀሱ ወዘተ. ሕዝብን እየሸነገሉ መደለልን በሚገባ ተክነውበታል። ድርጊታቸውን እያወቅን እንዳላወቅን ስንሆንም “በሕዝባዊ ጅልነታችን” ተሳለቁብን።
መከረኛው ሕዝብ መዘባነናቸውን እየሰማ በሆድ ይፍጀው ትዝብት ቀን የሚገፋው “አያምጣው እንጂ መቼስ ምን ይደረግ” በሚል ቆሽት አብጋኝ ትዝብት ናላው እየዞረ መሆኑ አልገባቸውም። ለስንቱ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን “መቼስ ምን ይደረግ!” በማለት ቁዘማ የሰርክ ባህላችን፣ እምባችን ቀለባችን ሆኖ እስከ መቼ እንደምንዘልቅ ግራ ተጋብተናል። ለነገሩ እየኖርን ነው ማለታችን እስትንፋሳችን ስላልወጣ እንጂ “ከቆሙት በታች ከሞቱት በላይ” መሆናችን የብዙኃኑ የኑሮ ገመና በሚገባ ያረጋግጥልናል። ለዚህ ሁሉ ያበቁን አጨብጭበን መርጠን፤ እያለቀስን ማውረድ የተሳነን የቢሮክራሲው ዘዋሪዎች እንደሆኑ በሚገባ ከገባን ሰነባብቷል።
ጽሑፌን ለአፍታ ያህል ገታ አድርጌ የአገሬን “ካብ አይገባ ቢሮክራሲ” በማሰብ እየተብሰለሰልኩ ባለሁበት ቅጽበት የአንድ ዕድሜ ጠገብ እናት እሪታ በእዝነ ህሊናዬ ውስጥ ሲያቃጭል ተሰማኝ። ጉዳዩ ግነት ወይንም ፈጠራ አይደለም። ይህንን ታሪክ ዛሬ አብራርቼ እገልጸዋለሁ እንጂ ከአሁን ቀደም ስሜቱ ትኩስ በነበረበት ወቅት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተሰበረ መንፈስና በሚቃትት ስሜት ጠቀስ አድርጌ ማለፌን ልብ ይሏል።
እኒህ እናት በወንዝ ዳር በሚገኘውና መጠነኛ ስፋት ባለው ጓሯቸው ውስጥ ጎመን እየተከሉ በመሸጥ ኑሯቸውን መደጎማቸውን ሲናገሩ ያደመጥናቸው ከራሳቸው አንደበት ነው። ያችንው ያመረቷትን ጎመን የሚሸጡትም በንፋስ የተበጣጠሰች ሸራ ከልለው ደጃፋቸው ላይ በመቸርቸር እንደሆነ ሲናገሩ የነበረው ከሞጭሟጫ ዓይናቸው ላይ የሚያዠውን እምባ እያበሱ ነበር። ይህ ጸሐፊ ያገኛቸውም ከባለቤቱ ጋር አገልግሎት ለመጠየቅ በሄደበት የወረዳ ጽ/ ቤት ውስጥ ነበር።
እኒህ እናት ገርጥተዋል። ከሰውነት ተራ በመውጣትም አጽም መስለዋል። ንግግራቸውም የህመማቸውን ጥንካሬ በሚገባ ይገልጻል። በመስታወት ውስጥ አፍጥጦ ወደሚመለከታቸው የወረዳው ሠራተኛ ቀረብ በማለት፤ “ልጄ! እኔ የምኖረው ጎመን ቸርችሬ ነው። ሰሞኑን የንግድ ግብር ካልከፈልሽ እያሉ ጤና ነስተውኛል። ምኔን ልክፈል? ጦቢያ የምትበለጥገው የጎመን ግብር እየተሰበሰበ ነው? ይኼው ለእናንተ ግብሬን፤ ለፈጣሪ እምባዬን አፍስሼ ሞቴን እጠብቃለሁ።” በእጃቸው የያዟትን የተጨማደደች አስር ብር ወርውረውለት እብስ አሉ። የግብራቸውን እዳ መክፈላቸው መሆኑን ልብ ይሏል።
ይህንን ትዕይንት ያስተዋለውና በዕለቱ “በሥራ ጠል ደመወዝተኞች” ሲጉላላ የነበረው ተገልጋይ እንባውን ያፈሰሰው በገሃድ በሚታየው ዓይኑ ብቻ ሳይሆን በልቡም ጭምር ነበር። የዚህ ጽሑፍ ባለቤት ያንን የክፉ ቀን ክፉ አጋጣሚ ባነሳች ቁጥር ዛሬም ድረስ እምባ ይተናነቃታል። በአንጻሩ ያ “ተቃላቢ” ደመወዝተኛ ተብዬ በአሮጊቷ ድርጊት ተገርሞ ሲገለፍጥ ማስተዋል የትራዤዲው ሁለተኛ ገቢር ነበር። “ጦቢያ የምትበለጥገው በእውነት የጎመን ግብር እየተሰበሰበ ነው?” የእኒያን እናት መሰል ድምጾች ዛሬም አየሩ ላይ ቢፈተሹ ይጠፋሉ ማለት አይቻልም። በግብር ጉዳይ ላይ ጫን ያልኩት “የበጎ ፈቃድ የታክስ አምባሳደር” የሚል አደራና ተቀጥያ በስሜ ላይ የተጫነብኝ መሆኑን በማስታወስ ጭምር ነው።
የንግድ ስርዓቱን የሚያስተዳድሩት መንግሥታዊ ተቋማትና መሪ ተብዬዎቹ ቢሮክራቶች “ቁጭ ብለው ሰቅለው፤ ቆመው ለማውረድ የተቸገሩበትን” ዋና ጉዳይ ላስከትል። ሥጋና ጤፍ ወደፊት መገኛቸው ገበያ ላይ ሳይሆን አንድም ዝርያቸው እንዳይጠፋ ታስቦ በሚቀመጡበት “በዘረ መል” የምርምር ማእከላት ውስጥ ሄዶ መጎብኘት፤ ሁለትም “በዜግነታቸው ክብር” የመጀመሪያው ረድፍ ላይ በተቀመጡና ሀብታቸው ዋስትናቸው በሆነ “ጥቂት ምርጥ ዜጎች” ማዕድ ላይ፣ ሦስትም ፖለቲካው በሚያቀማጥላቸው ሹመኞች ቤቶች ውስጥ ብቻ እንደሚሆን ብንተነብይ አባይ ነብያት ልንባል አይገባም። ለተከራካሪ ተሟጋቾች ማሳያችን የሚከተለው ነው።
ለምሳሌ፤ መንግሥታዊ ተቆራጭ ደመወዙ ሁለት ሺህ ብር የሆነ አንድ ምስኪን ግለሰብ በስድስት ሺህ ብር ጤፍ የሚሸምተው የስንት ወር ደመወዙን ከመስሪያ ቤቱ አስቀድሞ መበደር ቢችል ነው? መልሱን መስጠት ያለባት የደመወዝ ጣራውን እንጂ የኑሮውን ሰማይ እንዳላየ አይታ “የደመወዛችሁ የስኬል ጣሪያ ይህን ያህል ነው” ብላ በሕግ የቀፈደደችው አገር ራሷ መሆኗን አስ ምረን እናልፋለን።
በክርስትናው ሰፈር ፆም ገድፈውም ሆነ ሃይማኖታዊ ቀኖናው እኛን አይመለከትንም በሚሉ ግለሰቦች በዋናው የኩዳዴ ቀናት ውስጥ አንድን ኪሎ ሥጋ በአንድ ሺህ ብር ከገዙ፤ ነገ ጠዋት ፋሲካ ሲጠባ ዋጋው ስንት ሊደርስ ይችላል? ለሙስሊም ወገኖቻችንም የኢድ አል ፈጥር (ረመዳን) ጨረቃ ብቅ ብላ የሁሉም የሃይማኖት ቤተሰቦች ምዕመናን ከልኳንዳ በራፍ ላይ መኮልኮል ሲጀምሩ ለአንድ ኪሎ ሥጋ ምን ያህል ሺህ ብር ሊጠየቁ እንደሚችሉ መገመት ከባድ አይሆንም። ፆማችንን በምስር እንገድፋለን የሚሉ ዜጎችም የአንድ ኪሎው ስፍር ከመቶ ብር ዘሎ ስንት እንደደረሰ ሁሉም ስለሚያውቀው ብዙ ብንጽፍበት ለቀባሪ የማርዳት ያህል ስለሚያስገምት እናልፈዋለን።
ገበያውና ኑሯችን አቅሉን ስቶ ሲሰቀል ቁጭ ብለው ያስተውሉ የነበሩና ይመለከተናል ባይ “ምን ግዴዎች” ዛሬ በየሚዲያው “ኡኡታ!” እያሰሙ አድምጡን ቢሉ “ተቀምጣችሁ የሰቀላችሁትን ቆማችሁ ማውረድ
ከተሳናችሁ ወንበራችሁን ለቃችሁ ለሌላ አስረክቡ” ብለን ሰላማዊ ሰልፍ ብንጠራ ብሶት የወለደው እርምጃ ስለሚሆን ተቆጭዎቻችን ላያመሩብን ይችላሉ። ሰሞኑን “የተከበሩ እያልን የምንሽቆጠቆጥላቸው” አንዳንድ የክልልና የፌዴራል ሁነኛ ፖለቲከኞች “ሕዝቡ ምሬት እያሰማበት ያለውን የኑሮ ውድነት በዘጠና ቀናት ውስጥ እናረጋጋለን” እያሉ በጋዜጣዊ መግለጫ ሲረባረቡ እያስተዋልን ነው። ከሆነማ እሰየው! ምን ከፋን። ችግሩ ጸጋዬ ገብረ መድኅን እንደተቀኘው መሆኑ ነው፤
“ርሃብ ቀጠሮ ይሰጣል?
ወይንስ ቀን ቆጥሮ ይፈጃል?
“የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል”
ይባላል ድሮም ይባላል፣
ይዘለዝላል ይከትፋል፣
ብቻ እስከሚጨርስ ድረስ፤ ሆድ ለሆድ ጊዜ ይሰጣል።
ስንት ሰዓት ነው የራብ አቅም?
ለእኔ ብጤማ ትርጉሙ፣
የሁለት ፊደል ድምጽ ነው፤ “ራብ” የሚሉት ከነስሙ።
“አይነጋ መስሏት…” ይላል ብሂል አዋቂው የሀገሬ ሰው። ከሆነላቸው አሜን! ዕልል በቅምጣችን ብለን “ዘጠና ቀኗን” እንደ ርሃብ ቀን ሰብል ተግተን በጉጉት እንጠብቃለን።
እኒህን መሰል ቁጭ ብለው የተሰቀሉ፤ ነገር ግን ቆመን እናውርዳቸው ቢባል አቅምንም ሆነ ሥልጣንን የሚፈታተኑ አገራዊ ጉዳዮቻችን ብዙ የሚባሉ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ባህር አሸዋ ሊቆጠሩ የማይችሉ እንደሆኑ ደጋግመን ጽፈናል፤ በየስብሰባውና በየሚዲያውም የሰሚ ያለህ እያለን ጮኸናል። ሲብስብንም የጥላሁን ገሠሠን ዜማ ተውሰን እያንጎራጉርን መተከዝን ስራችን ብለን ተያይዘነዋል። ካሻቸው አንባቢያንም ሊተክዙበት ይችላሉ።
“ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣ ዘንድሮ፣
የስንቱ ተወርቶ የስንቱ ተነግሮ – ዘንድሮ።
በዚያኛው ተገርመን ጥቂት ሳንቆይ፣
የዚህኛው መባስ አያስቅም ወይ።
ብዙ ዓመት በድብቅ ሲጓዝ ከረመና፣
ዘንድሮ ላይ ሲደርስ ሸክሙ አጋደለና፣
ተዝረክርኮ ወድቆ በግልጽ ብናየው፣
የዘንድሮን ነገር ዘንድሮ አወቅነው።
“ቁጭ ብለን ሰቅለን ቆመን ለማውረድ ያስቸገረን ሌላው እንቆቅልሻችን” ድምጻችንን ሰብስበን በመስጠት ለወንበርና ለከፍተኛ ሹመት ያበቃናቸው “ኃያላን” ተመራጭ ፖለቲከኞቻችን ከመረጣቸው ሕዝብ ርቀውና ድምጻቸውን አጥፍተው የመሰወራቸው ጉዳይ እያሳሰበን ነው። እንደምንሰማው ከሆነማ ከመረጣቸው ሕዝብ ይልቅ የግል ድሎታቸውና ጥቅማቸውን በማስቀደም መንግሥት የትም ይሁን የት መኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው እየተማጠኑ ስለመሆኑ በተሟጠጠ ትዝብታችን “የከሌን ጉድ ሰማህ ወይ? ሰማሽ ወይ?” እየተባባልን ግርምታችንን መገላለጣችን አልቀረም። የደረጃውና የሥልጣኑ ከፍታና ዝቅታ ልዩ ጥቅም እንደሚኖረው ባይጠፋንም፤ “ትንሽ ትልቁ” ወደ ሥልጣን ኮርቻ ጠጋ ባለ ቁጥር የመረጠውን ሕዝብና በቅርበት የሚያውቀውን ወገኑን “አንተ ብትመርጠኝም አላምንህም፤ ለደህንነቴም ስጋት አለብኝ” ብሎ መንግሥት ቤት እንዲሰጠው ሲማጠን መመልከት ብዙ የሚባልለት ነው። አንድም፣ አንድም፣ አንድም … እያልን በአንድምታ የምንዘረዝራቸውን በርካታ ምክንያቶች መጠቃቀስ ቢቻልም ለጊዜው እዚሁ ላይ አቁመን በትዝብት ማለፉ ይበጃል። ሰላም ይሁን!!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014