የተወለዱትና ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ መሳለሚያ በሚባለው አካባቢ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸው ሙስሊሞች ቢሆኑም ቄስ ትምህርት ቤት አስገብተዋቸው ፊደል ቆጥረዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በዝብዝ ካሳ፣ ኢኑሪትማን፣ ብላታ አየለ፣ ሸኖ እና የካቲት 23 በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረው ነው የተማሩት፡፡ በመድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
በመቀጠልም ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው መማር ቢጀምሩም በጤና ማጣት ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ኢኩል ቴክኒክ በተባለና በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ በተቋቋመ ኮሌጅ ገብተው ለሁለት ዓመት በኢንጅነሪንግ ዘርፍ ከተማሩ በኋላም በተመሳሳይ ይህንንም ትምህርት አቋረጡ፡፡ በዚህ ግን ተወስነው አልቀሩም፤ አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ገብተው በፐርቼዚንግና ሰፕላይ ማኔጅመንት ተምረው ዲፕሎማቸውን አገኙ፡፡
ይሁንና በተማሩበት ሙያ ገፍተው አልሄዱም፤ የቤተሰብ ንግድ ሥራ ላይ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ተሰማሩ።የንግዱን ዘርፍ ባህሪ መረዳት ባለመቻላቸውም ከቤተሰብ ጋር ተስማምተው መስራት ተሳናቸው። ለሃይማኖታቸው ቀናዊ እሳቤ ያላቸው እኚሁ ሰው ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን የእስላምና አስተምህሮዎችን ወደ ማጥናት አደረጉ፡፡ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ትምህርቶችና ፅሁፎችን መፃፍና የኦዲዮ-ቪዥዋል ሥራዎችን እያዘጋጁ ለምዕመኑ ማድረስ ጀመሩ፡፡ እንዲሁም በርካታ መንፈሳዊና ዓለማዊ የትርጉም ሥራዎችን በጋዜጦች ላይ ይፅፉም ነበር፡፡
እንግዳችን 130 የሚደርሱ የቪሲዲ ሥራዎች በህትመት መልክ አቅርበዋል፡፡ ሥርጭታቸውም ጥሩ የሚባል ነበር። በትርጉም ሥራ ለህትመት ካበቋቸው ፅሁፎች መካከልም <<ሲሲሊያዊው>> የተሰኘው መፅሐፍ ተጠቃሽ ነው፡፡
የሚፅፏቸው ፅሁፎች መንፈሳዊ ቢሆኑም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልን ጭምር የሚያናግሩ ናቸው፡፡ በተለይም ስነ-ምግባር የሚባለው ነገር ሃይማኖታዊ ምንጫቸው አንድ መሆኑ ሙስሊሙንም ሆነ ሌላውን የእምነት ተከታይ ትኩረት የሚስቡ፤ የሚያወያዩ ነበሩ፡፡ በተለይ 1983 ዓ.ም አካባቢ በኢትዮጵያ ውስጥ የትርጉም ሥራ በእጅጉ የተስፋፋበት ወቅት ስለነበር የእሳቸውም ሥራዎች ከፍተኛ እውቅና አግኝተው ነበር፡፡
በጋዜጦቶችና መፅሔቶች ላይ በሚያቀርቧቸው ሥራዎች ጥሩ ተቀባይነትም ያገኘሁበት ወቅት መሆኑ ደግሞ የራሳቸውን ኦዲዮቪዧል ተቋም ለመክፈት እንዳስቻላቸው ያነሳሉ፡፡ በዚህም አላበቁ አፍሪካ ሚዲያ የተባለ የሃይማኖት ቴሌቪዥን ጣቢያ እስከመመስረት ደረሱ፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የቴሌቪዥን ጣብያውን በማማከር ድጋፍ የሚሰጡ ሲሆን የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በመስጠት ሙስሊሙ ህብረተሰብን የማነፅ ሥራ በስፋት እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ከአወሊያ ትምህርት ቤት ጋር የተነሳውን አለመግባባት ለመፍታት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ እንዲመሰረትና ችግሩ ዘላቂ እልባት እንዲያገኝ ያደርጉት በነበረው ትግል ይታወቃሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቀደመው መንግሥት ታስረው በወህኒ ቤት ሲንገላቱ ከነበሩ ሙስሊም ወገኖች መካከልም አንዱ ነበሩ፡፡ በዚህና በሌሎችም ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ኡስታስ ሀሰን አሊን የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ እንደሚከተለው ይዟቸው ቀርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- 2003 ዓ.ም ሙስሊሞች ያነሱት ጥያቄ በተለይ የአወሊያ እንቅስቃሴ ውስጥ የእርሶ ተሳትፎ ምን እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችን እንጀምር?
ኡስታዝ ሃሰን፡- እንደሚታወቀው በአወሊያ የመጀመሪያውን እንቅስቃሴ ያነሱት ተማሪዎች ነበሩ። ትንሽ በሃይማኖታዊ ሥራዎች ወጣ ያልን ሰዎች ይህ ሁኔታ በዚህ መቀጠል የለበትም በሚል በተደራጀ መልኩ ከስሜታዊነት ወጥቶ ለመንግሥት ቀርቦ መፍትሔ የሚገኝበት ነገር ነበር አስበን ስንሰራ የነበረው፡፡ በተለይም ህብረተሰቡ ጋር ፊት ለፊት የነበርን ሰዎች ሰብሰብ ብለን ያንን እንቅስቃሴ ወጥ በሆነ መልኩ ለመንግሥት የሚደርስበትን መንገድ ስንቀይስ ነበር። በዚህ መሰረት መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ከተዋቀረ በኋላ ጥያቄዎቻችንን ለመንግሥት አቀረብን፡፡ ጥያቄዎቹ በዋናነት ሶስት ናቸው፤ አወሊያ የሚባል ትልቅ ተቋም አለ፤ ይህ ትምህርት ቤት ለበርካታ ዓመታት የህዝበ-ሙስሊሙ ልጆች የሚማሩበት መንፈሳዊም፤ አካዳሚም፤ የእርዳታ ሥራዎችን አካቶ የሚሰራ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ያንን ተቋም ይደግፉት የነበሩት አካላት በሚሄዱበት ወቅት መንግሥት አንስቶ ለመጅሊሱ ሰጠው፡፡ አንዱ ጥያቄ መጅሊሱ ሊያስተዳድረው አይገባም የሚል ሲሆን ከዚያ ይልቅ ከህብረተሰቡ የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ሊያስተዳድሩት ይገባል የሚል ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የነበረው መጅሊስ አንደኛ በህዝብ አልተመረጠም፤ ጊዜውም አብቅቷል፤ የአወሊያ ጉዳይ ከተነሳ በኋላ የሚወስዷቸው አንዳንድ እርምጃዎች ህዝቡን ለቁጣ በጣም አነሳስቶት ነበር፡፡ በመሆኑም በዋናነት የህዝቡ ጥያቄ የነበረው አወሊያ ህዝቡ በሚመርጠው አካል ይተዳደር የሚል ነበር፡፡
ሁለተኛ ‹‹አህባሽ ›› የሚባል የሃይማኖት ክፍል በመንግስት ጭምር መደገፉ ተገቢ አይደለም የሚል ቅሬታ የነበራቸው አካላት ነበሩ፡፡ ይህ ድጋፍና ጣልቃ ገብነት ሊቆም ይገባል የሚል ሃሳብ አንስተውም ነበር፡፡
ሶስተኛው ደግሞ ህዝበ-ሙስሊሙ በአጠቃላይ ራሱ በመረጣቸው አካላት ሊተዳደር ይገባል የሚል ጥያቄ ነው ለመንግሥት የተነሳው፡፡ ይሁንና እነዚህ ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉበት አግባብ በጣም ቀላል ሆኖ ሳለ፤ በወቅቱ መንግሥት ሊፈታው አልፈለገም፡፡ እኛ ከመታሰራችን በፊት ጉዳዩ በሰላም እንዲፈታ ሽማግሌዎችን አዋቅረን ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ስንንቀሳቀስ ነበር፡፡ በእነዚህ ሂደቶች ሁሉ እጅግ የሚያሳዝን ሁኔታ ነበር ይፈፀም የነበረው፡፡ አንዱ ችግር በሃገሪቱ የሚሰማ መንግሥታዊ አካል ባለመኖሩ አዘቅት ውስጥ እየገባች መሆኑን ነው፡፡ የነበረው ችግር በይፋ እንዲታወቅም አልተፈለገም ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ሽምግልና ኢትዮጵያን ካቆያት ባህላዊ እሴቶች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በተለይም ሃይማኖትና ባህል በሽምግልና መልክ ተገልፀው ነው ይህችን ሃገር ያሸጋገሯት እንጂ ዘመናዊ የተባለው ህግ ለሁሉም ተደራሽ ሆኖ አይደለም፡፡ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ባህላዊ በሆነ ሽምግልና ነው ነገሮችን ሲፈታ የነበረው። ተመሳሳይ ጥያቄዎች በ1957 ዓ.ም ባሌ ላይ እኛ በተከሰስንበት መንገድ የተከሰሱ ሰዎች ንጉሱ ጋር ቀርበው ችግሩ በሽምግልና የተፈታበት ታሪካዊ ገጠመኝም አለ፡፡ ድሮም ቢሆን በጎሳና በሃይማኖት ውስጥ ግጭት ነበር፤ ባለፉት 27 ዓመታት የመጣ አይደለም፡፡ ግን ችግሮቹ የሚፈቱበት መንገድ ነው ሃገሪቱን ምስቅልቅል ውስጥ የከተታት፡፡ የኢህአዴግ ትልቁ ስህተት ነባር እሴቶችን ገንድሶ አለመተካቱ ነው፡፡ ህጉ ተደራሽ ሆኖ ፍትህ ይሰፍናል ብለን እንዳናምን በትክክል አይተገበርም፤ ይልቁንም ከነአካቴው ተጨመላልቆ የባሰ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እንዳውም ህግ አስፈፃሚ አካላት ራሳቸው ህጉን እንዳሻቸው የሚበዘብዙት ነው የሆነው፡፡ ህጉ ተጠናክሮ መውጣት አልተቻለውም፡፡ እዚህ ሃገር የሆነው ህጉ የፖለቲካ ማስፈፀሚያ ነው፡፡
እኔ በታሰርኩበት ጊዜ በቦረና ፤ በሱማሌና በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች በጅምላ ይታሰሩ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ጋር በቅርበት ስንነጋገር የተረዳሁት ነገር ገጠር ያለው ማህበረሰብ ከዚህ ቀደም ሲገዛበትና ሲተዳደርበት የነበሩበት እሴቶች ሁሉ እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ነው፡፡ በህብረተሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የነበራቸው የሃገር ሽማግሌዎችና የእምነት አባቶች ተቀባይነት እየጠፋ መጥቷል፡፡ መንግሥት እነዚህን የሃገር ሽግሌዎችና አባቶች ወደፊት ሲያመጣቸው የነበረው ችግሮችን ለመፍታት አይደለም የተጠቀማቸው፤ የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት እንጂ፡፡ በዚህ ምክንያት በሂደት ከህብረተሰቡ ነጠሏቸው። ጥቅመኛ ሆኑ፤ ህብረተሰቡ እዳውም ይህን በደምብ በመገንዘቡ አገለላቸው፡፡ ትልቁ ኪሰራ የሆነው ህብረተሰቡ በጣም የሚያከብራቸውን ሰዎች እዚህ አምጥተሸ በጥቅማ ጥቅም በመደለል ጥሩ ፊት እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው፡፡
የሃይማኖት አባቶች ላይም የሚታየው ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁን ላለንበት ችግርም ነፀብራቁ እነሱ ናቸው፡፡ እነዚህ የሃይማኖት አባቶች ከፖለቲካ ካድሬ ምንም የማይለዩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ የነበራቸው ተቀባይነት እየተመናመነ ሄዷል፡፡ የነበራቸውን ተሰሚነት ለራሳቸው ጉዳይ ማስፈፀሚያ ነው ያደረጉት፡፡ ስለዚህ አሁን የሃይማኖት አባት የሚለውን ማንም የሚሰማ የለም፡፡ ምክንያቱም ለህዝቡ አርዓያ መሆን አልቻሉም፡፡ በተለይ ከህግ ስርዓቱ መላሸቅ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ እጅግ ልንወጣ የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ እነዚህ እሴቶች ሃገሪቱን እንደካስማ ይዘውት የቆዩ ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚያደርጋቸው ጣልቃ ገብነቶች የራሱን እድሜ ለማራዘም ነው ሲሉ የሚተቹ ሰዎች አሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ? መነግሥት በተለይ ይህንን የሚያደርገው አክራሪና ፅንፈኛ የሚላቸው ሰዎች ስለነበሩ ወይስ ከበስተጀርባ ድብቅ አላማ ስለነበረው ነው?
ኡስታዝ ሃሰን፡- እንዳልሽው ያለፈው መንግሥት አክራሪነትና ፅንፈኝነት አለ ብሎ ራሱ ብዙ የሽብር ሥራዎችን ሲሰራ ነበር፡፡ አለፍ ሲልም የአልቃይዳ ክንፍ አለ የሚል ሃሳብ በምክር ቤት ሳይቀር የተናገሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ግን በዚህ ሰበብ የታሰሩት ሰዎች ማንነት ይታወቅ ነበር፡፡ይህንን ስል በደምሳሳው ፅንፈኛ አመለካከት ያላቸው ፖለቲከኞችና የሃይማኖት ሰዎች የሉም በሚል አይደለም፡፡ ፅንፍ የወጡ የፖለቲካ አቋሞች፣ የሃይማኖት አስተሳሰቦች፣ የጎሰኝነት አመለካከቶች አሉ፡፡
የሌለ ነገር አይደለም፡፡ እንግዲህ ፅንፈኝነቱ ከነበረ ታዲያ ይህንን ለማስወገድ መንግሥት ከማን ጋር ተነጋጋረ? ብለሽ ብትጠይቂ መልስ አታገኚለትም፡፡ በተመሳሳይ ያ ወቅት ለምን እንደመረጠም ጥያቄ የሚፈጥር ነገር ነው፡፡ ለ30 ዓመታት ሙሉ ፅንፈኝነት እየተስፋፋ ከነበረ መንግሥት ምንም አይነት መፍትሄ ለምን መውሰድ እንዳልቻለም ግልፅ አይደለም፡፡ ከህብረተሰቡም ጋር ለመወያየት የተደረገ ጥረት የለም፡፡ ከነአካቴውም ጉዳዩም አልነበረም።
እኛ ፅንፈኛ የምንላቸው ነገሮች ባሉበት ጊዜ ሁሉ አሳሳቢ በመሆኑ ለመንግሥት ጥቆማ ሰጥተን ነበር። ለምሳሌ የ‹‹ሃዋሪጅ›› እንቅስቃሴ አደገኛ በመሆኑ ቶሎ መፍትሔ እንዲፈለግ ተናግረን ነበር፡፡ ግን መንግሥት ጆሮውን ሊሰጠን አልፈለገም፡፡ እንዳውም የእነዚህ ነገሮች መኖራቸው በራሱ የመንግሥት ሰዎች ይፈልጓቸው ነበር። እንዲኖሩም ከለላና ድጋፍ ይሰጣቸው ነበር፡፡ ጉዳዩ ግን በወቅቱ ከነበሩ የሃይማኖት አባቶችና አመራሮች ሊያልፍ የማይገባው ነበር፡፡ ግን እንዲፈታ አይፈልጉም ነበር።፡ ከዚያ ይልቅ የአልቃይዳ ሴል ታይቷል አሉ።
እነሱ እንደሚሉት እዚህ ሀገር አልቃይዳ ካለ በተለይ ለምን ላለፉት ሰባት ዓመት ሙሉ ራሱን አልገለፀም?።ይልቅ ያሉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ‹‹ሱፊያ›› የተባለው እንቅስቃሴ ጎልቶ የሚታይበት ባሌ አካባቢ እንኳን የዚህ እምነት ተከታዮች እምነታቸውን በቀናዊነት ከመከተል ባለፈ ሰላማዊ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ሌሎች ሃገር ላይ በሚታይ መልኩ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ የሚጥል አይነት እንቅስቃሴ አያደርጉም፡፡
በመሰረቱ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአልቃይዳ ሴል ኢትዮጵያ ውስጥ ታይቷል ብለው ያሰሯቸው ሰዎች ፈፅሞ እንዲህ አይነት እንቅስቃሴ ውስጥ ያልነበሩ ናቸው፡፡ ይልቁንም አስቀድሜ እንዳልኩሽ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ በወቅቱ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ አክራሪነት መዋጋት ፋሽን ስለነበር ዓለምአቀፍ ተቀባይነት ለማግኘት ተብሎ ነው፡፡ እንደተባለው ደግሞ የራስን ስልጣን ማራዘሚያ ከመሆን ውጭ ሌላ አላማ አልነበረውም፡፡
እውነት እሱ እንዳሉት አልቃይዳ ቢኖር ኖሮ በተለይ በዚህ ወቅት ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ ራሱን እንዳሻው የሚገልበት እድል ነበረው፡፡ አበድኩ ያለ ሁሉ ሊተኩስ የሚችልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ዙሪያችን ያሉት ሃገራት አብጃለሁ ብትዪ ሳያቅማሙ ነው መሳሪያ የሚሰጡሽ፡፡ በተለይ እነግብፅ እና ሱዳን ቀጥታ ጥቅማችን ላይ ቆማችኋል ብለው ነው የሚያስቡት፡፡ ስለዚህ ማንኛውንም ተቃዋሚ ኃይል ከመርዳት አይቦዝኑም፡፡ በመሆኑም በዚያ መልኩ የተደራጀ ካለ ራሱን የማይገልፅበት ምክንያት ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ግን ደግሞ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ችግር ይህ ነው ብዬ አላስብም፤ ከዚያ በላይ የባሰ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ያነሱት በቀድሞው ስርዓት ውስጥ የነበሩ ችግሮች አሁን በየእምነት ተቋሙ ለሚታየው ግጭትና ምስቅልቅል ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ?
ኡስታዝ ሃሰን፡– እኔ አሁን ያለው ሁኔታ በጣም እንዲጎላ ያደረገው የፖለቲካው ጣልቃ ገብነት ነው። ምክንያቱም ችግሩ ሃይማኖታዊ ከሆነ መፈታት ያለበት በሃይማኖት ተቋማቱ ነው፡፡ ደግሞም ከተቋማቱ በላይ የሆነ ችግር አለ ብዬ አላምንም፡፡ ሚዛናዊ የሆኑ የሃይማኖት አባቶች እርስበርስ ባላቸው ግንኙነትም ሆነ ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶች በውይይት መፈታት የሚችሉ ናቸው፡፡ ደግሞም ተፈትቶ ያውቃል። ግን አሁን ፖለቲከኞቹ እጃቸው ገብቷል።
አሁን ትልቁ ችግር ፖለቲከኞቹ እጃቸውን በመክተት የራሳቸውን ተቀባይነት ማሳደግ ነው አላማቸው፡፡ ለምሳሌ አንቺ ያነሳሽው የኢህአዴግ ፓርቲ በሁሉም አደረጃጀት ውስጥ ገብቶ የሚፈተፍትበት ሁኔታ በጣም ሰፊ ነበር፡፡ እነዚህ ተቋማት ራሳቸውን በሌላ መልኩ እንዲገልፁ አይፈልግም፤ ምክንያቱም በራሱ ጨቋኝ ስለሆነ ነው፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩሽ በ27 ዓመታት ብዙ ነባር እሴቶቻችንን እየሸረሸረ ስለመጣ ከስልጣን ከወረደም በኋላ እስከዛሬ አይተናቸው የማናውቃቸው ችግሮች እንዲከሰቱ ሆኗል። ያም ቢሆን መፍትሔ የሌለው ነገር የለም፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን ችግር ለመፍታት የተማረ ሰው እጥረት የለባትም፡፡ እኛ ሃገር ያለው ችግር ሌሎች ሃገሮች ያላለፉበትም አይደለም፡፡ በርካቶች በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፈዋል፤ አሁንም በዚያ ውስጥ ያሉ እንዲሁም ብትንትናቸው የወጣ ሃገራት አሉ፡፡ ትልቁ ችግር ተማረ የሚባለው ሰው ራሱ የጥፋቱ አካል መሆኑና ምሁርነቱን ክዶ በዚህ ችግር ውስጥ ተዘፍቆ የሚታይበት ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ የሆነ ፖለቲካ ወይም ጎሳ ውግንና ይዞ ነው የሚወጣው፡፡ እንደመፍትሔ ይሄ ነው ብለው የሚያቀርቡት ነገር የለም፡፡ *እኔ በይቅርታ አምናለሁ፤ ያለይቅርታ ችግሮችን መሻገር እንደማይቻል እረዳለሁ፤ ግን ደግሞ በጅምላ ይቅርታ መጠየቅ መፍትሔ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለምሳሌ ዶክተር ዐቢይ እንደመጡ በፓርቲያቸው ስም ይቅርታ መጠየቃቸው መልካም ሆኖ ሳለ ግን ደግሞ ያጠፋው አካል ራሱ ጉዳት ያደረሰበትን የህብረተሰብ ክፍል ፊት ለፊት ወጥቶ ይቅርታ ቢጠይቅ የተሻለ ውጤት ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ልክ ደቡብ አፍሪካ እንደተደረገው የይቅርታ ዋስትና ተሰጥቶ አጥፊው ወጥቶ የሚናገርበት እድል መፈጠር ነበረበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ አጥፊዎቹ አሁንም ድረስ ጥፋታቸውን አምነው ባልተቀበሉበት ሁኔታ ይህ እርሶ የሚሉት ነገር እውን ይሆናል ተብሎ እንዴት ይታሰባል?
ኡስታዝ ሃሰን፡- ልክ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢህአዴግ ላጠፋው ጥፋት ይቅርታ መጠየቃቸው ትክክል ነው፡፡ ግን ደግሞ በ27 ዓመታት ውስጥ በደል የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ቅሬታቸውንና ሃሳባቸው መጠየቅ ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም የተፈፀሙት በደሎች መልካቸውም ሆነ ባህሪያቸው ፈፅሞ የተለያየ ነው፡፡ ይቅርታ ሲጠየቅም እንዳው ሁሉንም በደምሳሳው ሳይሆን ያለበት በተጨባጭ ስለተፈፀሙት በደሎች መሆኑን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ የህዝቡን ችግር መፍቻ የሆነውን የኖረ እሴት የሸረሸሩት ሰዎች አሁንም በሕይወት አሉ፤ በዚያ ስርዓት ተጠቅመዋል፤ ግን እስቲ ይቅረቡና በደላቸውን አምነው ይቅርታ ህዝቡን ይጠይቁ፡፡ ይህንን ማድረጋቸው ደግሞ ጥፋቱ እንዳይደገም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብዬ አምናለሁ። አዲሱ ዓመራር ሲመጣ ጉዳዩ ተመሳሳይ መንገድ ውስጥ እንዳይሄድ ያስተምረዋል፡፡
እንዳልሽው አጥፊዎቹ አሁንም ድረስ ስለጥፋታቸው አምነው አልተቀበሉም፡፡ እንዳውም የ27 ዓመቱ አልበቃ ብሏቸው ነፍጥ አንስተው በመዋጋት ሃገርና ህዝብን ምንአይነት ችግር ውስጥ እንደከተቷት የሚታይ ነው፡፡ ግን እነሱ ብቻ አልነበሩም ጥፋተኞቹ፤ አሁንም ጉያችን ተሸሽግው የተቀመጡ አሉ፤ አንዳንዶቹ አቅም አንሷቸውና ተገደው መፈፀማቸውን ሲያወሩ ይደመጣሉ፡፡ ግን እነዚህ ሰዎች በይፋ ስለጥፋታቸውም ሆነ ላጠፉት ነገር ይቅርታ ሲጠይቁ አላየንም፡፡ ዝም ብለው መቀመጣቸው የሚቀጥለውን ትውልድ ጭምር ይጎዳል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ይህንን የምለው እነዚህን ሰዎች ይታሰሩ ከሚል አይደለም፤ ግን ደግሞ በቀጣይ በኃላፊነት የሚመጣው ሰው ተመሳሳይ ጥፋት እንዳያጠፋ ማስጠንቀቂያ ይሆነዋል፡፡
ትልቁ የእኛ ሃገር ችግር ግልፀኝነት የለም እንጂ የምንቧደናቸው ቡድኖች ጥሩ ለመስራት ሳይሆን ሌሎችን ለማጥቃት እንደሆነ እሙን ነው፡፡ አሁን ላይ በጎሳ ተቧድነን የምናጠቃቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ነገ እኛ ላይ መነሳታቸው አይቀርም፡፡ በመሆኑም ያለፈውን በግልፅ ኮንነን እንዳይደገም ካላደረግን በስተቀር ዘላቂ የሆነ ሰላም ማምጣት አይቻለንም፡፡ እነሱማሌና ሶሪያ ከእኛ በተሻለ የሚያመሳስሏቸውና የሚያስማማቸው ነገር ቢኖርም ሃገራቸውን ከመበታተን ማዳን አልቻሉም። ይህም የሆነው ያጠፋው ጥፋቱን አውቆ በመመለስና በይቅርታ ችግራቸውን መሻገር ባለመቻላቸው ነው፡፡
እኛን እንደእብድ ገላጋይ በማንኛውም ጉዳይ እየገቡ ሊያፋጁን የተዘጋጁ በርካታ ኃይሎች አሉ። ለእነሱ ህልውና መቀጠል የእኛን መጋደል የሚፈልጉ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ባሉበት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት የተለየች አይደለችም፡፡ ብዙ ጎሳ፤ ብዙ ሃይማኖት፤ ብዙ የፖለቲካ አመለካከት ነው ያለው፡፡ በዚያ ላይ በጣም አደገኛ የሚባሉ ጎረቤቶች ነው ያሉን፡፡ ጠዋት ከእኛ ሆነው ከሰዓት ከሌላ ጋር የሚያወሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ አንፃር በዚህ ዘመን ላይ ያለ የመንግሥት ባለስልጣን፤ የሃይማኖት መሪ እና ምሁር ከሌላው ጊዜ በተለይ ድርብ ኃላፊነት አለበት፡፡ የእኔ ጉዳይ ይቆይ የሚል አመራር ካልፈጠርን ሃገርን ማሻገር አንችልም፡፡ ሁሉም የራሱን ጉዳይ ብቻ ለማስፈፀም መሯሯጡን የሚቀጥል ከሆነ ነገ ቁጭ ብለን የምንነጋገርባት ሃገር አትኖረንም፡፡ አሁን ላይ እኮ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሶሪያዊ በሃገሩ አይኖርም።
ዛሬ እነዚህ ሰዎች ወደሃገራቸው መመለስ ቢፈልጉ እንኳን የእኔ የሚሏት ሃገር የላቸውም፡፡ ሊብያውያን ‹‹ሀገራችን እንደምትፈርስ አስቀድመን መገመት ብንችል ኖሮ መሃመድ ጋዳፊ እስከልጅ ልጆቹ ለዘላለም እንዲነግስ እንፈቅድ ነበር›› ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው የመንግሥት አመራርና ዜጋ ከሌላው ጊዜ በተለየ ኃላፊነቱን መወጣት መቻል አለበት፡፡
አሁን ላይ የኢኮኖሚው ችግር እየተባባሰ ከመምጣቱ የተነሳ ብዙ ሰው የሌላው እጅ ጠባቂ ሆኗል፡፡ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ሲርበው እየቀማ የሚኖር ዜጋ እየተበራከተ ይመጣል፡፡ በእስልምና ለምሳሌ ‹‹የሰረቀ እጁ ይቆረጣል›› ይላል፤ ግን ደግሞ ይህ ህግ ተግባራዊ የማይሆንበት አጋጣሚ አለ፤ ከእነዚህም መካከል በድርቅና በርሃብ ጊዜ ሰርቆ የበላ ሰው እንደሃጥያተኛ ላይታይ ይችላል፡፡ ስለዚህ ባለሃብቶች የሚኖሩትን ማህበረሰብ ማዕከል ያደረገ ሥራ መስራት ይገባቸዋል፡፡ ይህች ሃገር እንድትቀጥል ከተፈለገ በተለይ ባለሃብቱ እነዚህን ወገኖች መደገፍ አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ግን ያከማቸውን ሃብት የሚበላበት ሃገር አትኖረውም፡፡ ሁሉም ሰው በተለያየ ነገር ሊበደል ይችላል፤ ተበድሏልም፤ ግን ደግሞ ከራሱ በላይ ሃገርንና ህዝብን ማስቀደም ካልቻለ ኢትዮጵያን ካለችበት ችግር ሊያወጣትም ሆነ ሊያሻግራት አይችልም። ዛሬ እኔ ልጎዳ ሃገር ትዳን ማለት መቻል አለብን፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልን ቁጭብለን የምንጨቃጨቅበት ሃገር እንኳን ይናፍቀናል፡፡
ያለፈው ስርዓት ሌላው ትልቁ ችግር የሃይማኖት ሰዎችን ሰብስቦ ማሰሩ ነው፤ ይህ ብቻ አይደለም ቁጭ ብሎ ለመነጋገርና ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት ያለመኖሩ ለዚህች ሃገር ከፍተኛ ኪሰራ አስከትሏል ባይ ነኝ፡፡ የሃይማኖት አባቶች ችግሩ እንዲፈታ ሲሉ በገቡበት ቢሮ ሁሉ ሞራላቸውን ነክተው ነው የመለሷቸው፡፡ አንዳንድ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶችም በመንግሥትና በእምነት ተቋማት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ከመፍታት ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም ያደሩ ሆነው ነው የተገኙት። እውነታውን መናገርና ፊት ለፊት ለመጋፈጥ ደፋሮች አይደሉም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ትውልዱን ከመታደግ አኳያ የሃይማኖት ተቋማት ቀጣይ የቤት ሥራ ምን መሆን አለበት?
ኡስታዝ ሃሰን፡- አሁንም ቢሆን ትክክለኛ የሆኑ የሃይማኖት አባቶች የሚሰብኩት ሰላምን ነው፡፡ በተለይ በቀደሙት ዓመታት ህዝቡ መረጃ የሚያገኝበት እድል ስላልነበረው የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነት ከፍተኛ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ብዙ ተወዳዳሪ አለባቸው። ኢትዮጵያ የሃይማኖት ሃገር ናት፤ ሃይማኖተኞች ግን አይደለንም፡፡ ምክንያቱም የአንድ ሃይማኖት ተቋም ተከታይ መሆንና እምነትን በህይወት መተግብር የተለያዩ ነገሮች በመሆናቸው ነው፡፡ አሁን ላይ በቁጥር ብዙ የሚባለው ወጣት ሃይማኖት ውስጥ ቢኖሩም ሃይማኖታዊ መርሆን ተከትሎ የሚንቀሳቀስ አይደለም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የሃይማኖት አባቶቹ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ባለማስተማራቸው ነው፡፡ በመሰረቱ ትውልዱ በአደገኛ ሁኔታ በመበላሸቱ ጥሩ ለሆኑት አባቶች እንኳን ፈታኝ እየሆነ ነው ያለው፡፡
ስለዚህ መጀመሪያ መደረግ ያለበት ብዬ የማስበው የሃይማኖት ተቋማቱ ከስልጣን ሽሚያ አስተሳሰብ ወጥተው ተቀባይነት ላላቸው የእምነት ሰዎች እድሉን ሊሰጡ ይገባል፡፡ ለምሳሌ በእኛ ቤተ-እምነት ሁሉም በየጎራው የተከፋፈለበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዱ አንዱን መስኪድ ይዞ ሌላውን እንዳያስተምር ይከላከላል፤ ያኛውም ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈፅም ይስተዋላል፡፡ ይሄ ተገቢ አይደለም። ለሁሉም እድል መሰጠት ያስፈልጋል። ለምዕመኑንም ሁሉንም የሚያደምጥበት እድል ሊኖረው ይገባል፡፡ ማንም ሰው በየመስኪዱ እየመሸገ እገሌ አትድረስብኝ ማለት አይገባውም፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ደግሞ በምእመኑ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘትና የጥቅም ግጭት በመኖሩ ነው፡፡
ለሁሉም እኩል መድረክ በመስጠት በሚያስተምረው ነገር እንዲመዘን ማድረግ ይቻላል። ነፃነት በሰጠን ቁጥር ህዝቡ ራሱ ያሻውን ይመርጣል። በከለከለን ቁጥር ግን ግጭቱ እየተባባሰ በመሄድ ሃገራዊ አደጋ ይዞ ሊመጣ ይችላል። መስኪዶች የሰላም ቦታ እንዲሆኑ ከተፈለገ በግልፅ መነጋገር ብቻ ነገሩን ይፈታዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድ መስኪዶች ላይ ይህ ተሞክሮ በተጨባጭ ለውጥ አምጥቶ አይተናል። በፊት የፀብ መነሻና የፍትጊያ ቦታ የሚባሉት እነዚሁ መስኪዶች ሁሉንም ያሳተፈ ስርዓት መዘርጋት በመቻላቸው ችግሮች ተፈተዋል፡፡ አለበለዚያ ግን ሁሉም እጁን ያስገባበታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሃገር አቀፍ የተስፋፋው የሙስና አስተሳሰብና ድርጊት በእምነት ተቋማት ውስጥም ጎልቶ የወጣበት ሁኔታ መኖሩን እንሰማለን፡፡ ለመሆኑ የዚህ ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
ኡስታዝ ሃሰን፡- ለዚህ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ በመንግሥት የኃላፊነት ቦታ የሚመ ደበው ሰው በመጀመሪያ ለቦታው መመጠኑንና ብቁ መሆኑን ከማረጋገጥ ይልቅ የመጣበት ጎሳ ወይም ሃይማኖቱ ነው የሚታየው።፡ ይህ የሚደረገው የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀጠልና በሌላው ላይ ጫና ለመፍጠር በማለም ነው። ለእኔ የጥቅም መስመሩ በዚህ 30 ዓመታት ውስጥ በውግንና በተዘረጋው ስርዓት መምጣቱ ነው ለሙስና መስፋፋት ምክንያት ነው ብዬ የማስበው። ሁሉም ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል ብቻ የሚከፈለውን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ የራሱን ሰው ማሾም ነው የሚፈልገው።
በሌላ በኩል ደግሞ አስቀድሜ እንዳልኩሽ ነባር እሴቶቻችን መሸርሸራቸው ለሙስናም ሆነ ለስነ-ምግባር ብልሹነት መስፋፋት ምክንያት እየሆነ ነው ያለው። አሁን ላይ ትውልዱ የሃይማኖት አባቶችን የመስማት ፍላጎቱ በመቀነሱ መክሮ የመመለሱ ጉዳይ ጊዜ የሚወስድ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ለዚህ ችግር ሆነኛ መፍትሔ ነው ብዬ የማስበው የህግ የበላይነትን ማስፈን ነው፡፡
አሁን ላይ እኮ አብዛኛው የመንግሥት ሹመኛ ሥራውን እያበላሸ ‹‹አቅቶኛል›› ብሎ የሚለቅበት ሁኔታ አናይም፡፡ የሚመለከተው አካልም ያንን ሰው ሲያባርረው አናይም፡፡ ምክንያቱም በተቆጠረ ሥራ አይመዘንም፡፡ እዚህ ሃገር ህዝብን መበደልና መበዝበዝ እንደመብት ነው የሚቆጠረው፡፡ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር መብራት ለ20 ደቂቃ ጠፋ ብሎ 20 ደቂቃ አጎንብሶ ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አሁን እኮ ወደ ጎንም ወደ ታችም ተቧድነው ነው ህዝብን የሚበዘብዙት፡፡ ቅሬታ ብታቀርቢ እንኳን በጥቅም ሰንሰለት የተሳሰሩ በመሆኑ የሚሰማሽ አታገኚም። አሁን በየወረዳው የምንሰማው ነገር በጣም አሳፋሪ ነው። ሰዎች ገንዘብ ከፍለው ስልጣን የሚያገኙበት ሁኔታ መኖሩን እንሰማለን፡፡ ይህ ለቀጣዩ ትውልድ ጭምር የሚተርፍ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ሌሎች ሃገራት እንዲህ አይነቱን ችግር የፈቱት ህብረተሰቡን በማንቃትና የጋዜጠኝነት ባህል በማጎልበታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ግልፀኝነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር በሁሉም መልኩ መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በመንግሥት ብቻ የሚፈታ አይደለም፤ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ አንቂዎች ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል። የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተለይ የህዝብ ተወካዮች ለህዝቡ የቀረበ ሥርዓት መፍጠር የህዝብ የልብ ትርታ ማዳመጥ መቻል አለባቸው፡፡
የእምነት ተቋማት ውስጥም ሙስና እንዲስፋፋ ያደረገው በሃገር ደረጃ ያለው ብልሹ አሰራር ነው። የቀደሙት የመንግሥት ኃላፊዎች በእምነት ተቋማት ውስጥ ያለው ጥቅም ተካፋዮች ናቸው፡፡ ስለዚህ የእምነት ሰዎች ለሚያጠፉት ጥፋት ከለላ የሚሰጣቸው የመንግሥት አካል አለ፡፡ በአንድ ወቅት ከሃጂና ኡምራ ጋር ተያይዞ ግጭት ተፈጠረና እኛ እንፍታ ብለው የገቡ የመንግሥት ሰዎች በትክክል የሚገኘውን ጥቅም ሲያውቁ ችግር ሲፈጥሩ ከነበሩት የሃይማኖት አባቶች ጋር የጥቅም ድርድር ውስጥ ገቡ፡፡
ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የድርሻቸውን ተደራድረው አስጨምረው ወጡ፡፡ እኛም ዳግመኛ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ እንዳናነሳ አስፈራርተው ነው የመለሱን፡፡ ስለዚህ የሙስና ሰንሰለቱ እዚህም ሆነ እዚያ የተዘረጋ ነው። በመሆኑም ችግሩ መፈታት የሚችለው ከመንግሥት በኩል ብቻ ሳይሆን በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያለውን የጥቅም ሰንሰለት ማቋረጥ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሔ የሚሆነው የህግ የበላይነትን በተጨባጭ ማስፈን ስንችል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ኡስታዝ ሃሰን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1 /2014