ልጆች!
እንዴት ናችሁ? ትምህርት ቆንጆ ነው? መቼም ጥሩ ነው የሚል ምላሽ እንደምትሰጡ አስባለሁ። ምክንያቱም ጠንካራ አንባቢና ባለራዕዮች ስለሆናችሁ። ልጆች ጊዜው ትምህርታችሁን አጠናክራችሁ የምትማሩበት ነው አይደል? ከፈተና ተመልሳችሁ ቀጣዩን የትምህርት መንፈቅ ዓመት ጀምራችኋል። በመሆኑም በሚገባ ትምህርታችሁን እየተከታተላችሁ፣ከጓደኞቻችሁ
ጋር አብራችሁ እያነበባችሁ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።
ይህ ካልሆነም ቤተ መጽሐፍት በመግባት እንደምታነቡ እገምታለሁ። ወደ ቤታችሁ ስትሄዱ ደግሞ የየቀኑን ትምህርት ታጠናላችሁ። ይህ ደግሞ ፈተና ሲመጣ እንዳትጨናነቁ ያግዛችኋል። ስለዚህም በርትታችሁ ይህንን ልምዳችሁን ማጠንከር ይገባችኋል። ልጆች! ዛሬ ከእስከዛሬው ለየት ያለ ነገር ነው ይዤላችሁ የቀረብኩት። ይህንን የትምህርታችሁን ሁኔታ በደንብ የሚያጠነክርላችሁና ከማህበረሰቡም ሆነ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ ጋር እንዴት መቀራረብ እንደምትችሉ የሚነግራችሁ ነው።
ልምዳችሁን እንዴት ማጎልበት እንደምትችሉም በተግባር ያስተምራችኋል። በተለይም ወደፊት መሆን የምትፈልጉትን በሚገባ እንድትተገብሩት ይረዳችኋል። ሁላችሁም ትምህርታችሁን ስትጨርሱ መሆን የምትፈልጉት ምኞት አላችሁ አይደል? አዎ እንዳላችሁ እገምታለሁ። ስለዚህ ይህ ዝግጅት ለፍላጎታችሁ በሚገባ መልስ ይሰጣል። ነገር ግን እናንተ መስራት የሚጠበቅባችሁ ነገር አለ። ጥናቱን ያቀረበው አቶ ስምኦን ተሰማ ይባላል። የተለያዩ የሂሳብ ስራዎችን በመስራት ይታወቃል።
ለዚህ ጥናቱ መንስኤ የሆነችው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ተማሪ ልጁ ናት። ምን መሆን እንደምትፈልግ ሲጠይቃት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን መሆን እንደምትፈልግ ነገረችው። በዚህ ጊዜ ደግሞ በጣም ደነገጠ። ምክንያቱም ዶክተር አብይን ለመሆን በሁሉም አቅጣጫ በሳል፣ ንግግር አዋቂ፣ የፖለቲካ አቅሟ የተገነባ፤ የትምህርት ደረጃዋም ፣ የስነምግባርና ሌሎች ነገሮቿ የተስተካከሉ ፣ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አቋም ያላት መሆን አለባት። እናም በድንጋጤ አይን ስትመለከተው ከቆየች በኋላ « ምነው ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አትችልም?» ስትል ጠየቀችው። እርሱ ምን እንዳላት ታውቃላችሁ? በደንብ ትችላለች።
ይሁንና ብዙ ነገሮችን ማሟላት አለባት። ስለዚህ አንቺ በዚህ ሁኔታ ተገንብተሽ ስታድጊ ነው ይህንን መሆን የምትችይው አላት። ለዚህም ከቤተሰብ የጀመረ ስራ መስራት እንዳለበት አሰበና ይህንን ጥናት አደረገ። ደስ ይላል አይደል? ፍላጎቷን እውን ለማድረግ ደግሞ የእርሱ ሥራ ብቻ ውጤታማ እንደማያደርግ ስላመነበት ወደ ትምህርት ቤቷ ሄደ። በዚያም ጥናቱ እንዲተገበር የተለያዩ ተግባራትን ፈጸመ። ይህ ተሞክሮ ደግሞ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ዘንድ ቢተገበር ጥቅሙ የጎላ በመሆኑ ስለጥቅሙ ለመንገር እኛ ዘንድ መጣ።
እናም ልጆች የራስን ፍላጎት እውን ለማድረግ መደረግ ያለበትን ዝርዝር መረጃ ነግሮናል። ወላጆችም ይህንን አንብበው ለልጆቻቸው ውጤታማነት እንዲሰሩ ያደርጋል ብለንም ለንባብ አቅርበነዋል። አቶ ስምኦን እንዳለው፤ መጀመሪያ ልጆች ፍላጎታቸውን እንዲያሳኩ ከቤት የጀመረ ተግባር ያስፈልጋቸዋል። ቤተሰብ የልጅን ፍላጎት መግታት የለበትም ብለዋል። ልጆች የተገቱ ከመሰላቸው ቤተሰብን ማሳመን ላይ መስራት አለባቸው። ቤተሰቦቻቸውንም በሚፈልጉት ነገር እንዲያግዟቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ትምህርት ቤቶች በየክበባቱ ውስጥ ነጻና ፍትሃዊ የምርጫ ሂደቶችን ተከትለው ተግባራትን እንዲያከናውኑ መፍቀድ አለባቸው።
ይህ ደግሞ በተማሪዎች መተግበር ይኖርበታል። ተማሪዎች ፍላጎታቸውን ለማሳካት በትምህርታቸው ጠንካራ ተማሪ መሆን አለባቸው፤ ከሰዎች ጋር በፍቅር መስራትም ይጠበቅባቸዋል። ስነምግባር ያላቸውና ሁሉን ነገር ለማወቅ የሚጥሩም መሆን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ የራስ ተነሳሽነት ያስፈልጋል። ለቤተሰብ መታዘዝ፣ የአካባቢን ችግር በመመልከት ችግሮችን ለመፍታት መሞከር፤ ተባብሮ መስራትን መልመድ ግድ ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ ደግሞ ማድረግ ያለባቸው በመሰረታዊነት በክበባት ውስጥ መሳተፍና የምርጫ ስርዓትን መልመድ ነው።
ለመሆኑ ልጆች የምርጫ ስነስርዓትን ማወቅ ለምን እንደሚጠቅም ታውቃላችሁ? እንደ አቶ ስምኦን ጥናትና ማብራሪያ የተለያዩ ጥቅሞች አሉት። የመጀመሪያው መመረጥንና መምረጥን እንዲለምዱ ያደርጋቸዋል። ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ስርዓት ምን ማለት እንደሆነ በተግባር እንዲረዱ ያስችላቸዋል። የምርጫ ቦርድ ስርዓት ምን እንደሚመስል እንዲያውቁም ያደርጋቸዋል።
በተመረጡበት ጊዜ ደግሞ ኃላፊነትን መውሰድን እንዲለማመዱ ያስችላቸዋል። ማህበራዊ ትስስራቸውንም በእጅጉ እንዲያጠናክሩበት ይረዳቸዋል። ምክንያቱም ተመራጭ በመሆናቸው ከሰዎች ጋር ቀርቦ የመስራት ልምድን፤ በጋራ መተባበርን ባህላቸው ያደርጋሉ። በተለይ ምርጫቸው ትምህርት ተኮር ስለሚሆን ለትምህርት ቤታቸው ብዙ አበርክቶ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል። በተመሳሳይ በሰሩ ቁጥር የተለያዩ የልምድ ባለቤቶች የመሆን እድላቸውን ያሰፋዋል። መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበትም የምርጫ ስርዓትን ማወቃቸው ይጠቅማቸዋል።
የማይሰራን ማውረድ፣ የሚሰራን ማበረታታት ይህ የምርጫ ስርዓት በትምህርት ቤት ውስጥ ተግባራዊ መሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ምክንያቱም የማይሰሩ ከሆኑ እነርሱም ላለመጣል እንዲሰሩ ያደርጋቸዋልና ነው። ልጆች በዚህ የትምህርት ቤት ምርጫ ስርዓት ውስጥ ተመራጮች ሌላም የሚጠቀሙበት መሰረታዊ ነገር አለ። የንግግር ብቃታቸውን ያሳድጉበታል። ምክንያቱም የምረጡኝ ተግባርን በተማሪው ፊት ያደርጋሉ። የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችንም ለመመረጥ ሲሉ ይተገብራሉ። ይህ ደግሞ የበለጠ የስራ ፍቅር እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። ይህ ደግሞ የብዙ ሙያዎች ባለቤት የመሆን እድላቸውን ያሰፋዋል።
ልጆች ይህ ግን የሚሆነው በተለያዩ ክበባት የምርጫ ስርዓት ተግባራዊ ሲደረግ እንደሆነ አቶ ስምኦን ይናገራሉ። ለአብነትም የቱሪዝም፤ የሳይንስ፣ የቋንቋና ስነጽሁፍ፣ የስፖርትና የመሳሰሉት አይነት ክበባት ላይ ሁለት ሁለት ተማሪዎች መመረጥ ቢችሉ ማህበረሰቡንም ሆነ ራሳቸውን በተለያየ መንገድ እንዲያግዙ ይሆናሉ ብለዋል። ለዚህም በምክንያትነት ያነሱት ሁለት ነገር ሲሆን፤ የመጀመሪያው የአካባቢን ባህል እንዲያውቁና ያንን ለመተግበር እንዲተጉ ማድረጉ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሁልጊዜ ፍላጎታቸውን መሰረት አድርገው ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ለዚያ ነገር እንዲሰሩ ብሎም ማህበራዊ ትስስር ያለውን ዋጋ ተረድተው በስነምግባራቸው የበቁ ዜጎች እንዲሆኑ እድል መስጠቱ ነው። ልጆች ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ግን ተያያዥ ችግሮች
ሊያጋጥሙ እንደሚችሉም ነግረውናል አቶ ስምኦን። በዋናነት ሊገጥም የሚችለው ችግር ሙሉ ትኩረታቸውን ለተመረጡበት ተግባር የሚያደርጉ ከሆነ መደበኛ ትምህርታቸውን በሚገባ መከታተል አይችሉም። ስለዚህም ውጤታቸው ዝቅ ሊል ይችላል። ሆኖም ተማሪዎች እነዚህ ምርጫዎች ላይ ሲሳተፉና ተመራጭ ሲሆኑ ማድረግ ያለባቸው በጥበብ ሥራዎችን ማከናወን ነው ብለዋል። ትምህርታቸው ላይ ምንም አይነት መደራደሪያ ማቅረብ የለባቸውም። ነገር ግን ፍላጎታቸውን መገደብ እንደሌለባቸውም ገልጿል።
ልጆች ሌላ አቶ ስምኦን ምን እንዳሉኝ ታውቃላችሁ? የምርጫ ቀን በትምህርት ቤቶች እንደ ውሃና የባንዲራ ቀን መከበር ቢችል መልካም ነው። ስለዚህም እናንተ በየትምህርት ቤታችሁ ይህ እንዲደረግ መምህራንና የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ ማሳመን ላይ መስራት አለባችሁ። ምክንያቱም ከላይ በምርጫ መሳተፍ ያለውን ጥቅም አይታችኋል። ሌላው ማድረግ ያለባችሁ ምርጫው በክበባት አማካኝነት የሚከናወን ስለሆነ መረጃችሁን ስለሚያጠነክርላችሁ ለተግባራዊነቱ መትጋት ነው። በመጨረሻ የአቶ ስምኦን ልጅ ማዕዶት ስምኦን ያለችኝን ልንገራችሁ። ተማሪዎች ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚያግዳቸው ነገር የለም።
ራሳቸውን ለፍላጎታቸው መተግበር መስጠት ከቻሉ። ስለዚህም እኔም ዶክተር አብይ አህመድን ለመሆን ተግቼ እሰራለሁ። አሁን የኬጅ 3 ተማሪ ነች። እስካሁንም አንደኛ ደረጃነቷን ሳትለቅ ነው እዚህ የደረሰችው። ስለዚህም በቀጣይም ቢሆን ይህንኑ አቅሟን ለማሳደግ እንደምትፈልግ ነግራኛለች። ለዚህም ደግሞ የቤተሰቦቿ እገዛ የበረታ ነውና አትፈራም። ሌሎች ልጆችም ይህንን ማድረግ እንዳለባቸው ትመክራለች። ለፍላጎታቸው መሳካት በትጋት መስራት እንዳለባቸው። ሌላው ያለችኝ «ዶክተር አብይን ባያቸው በጣም እደሰታለሁ።
አንድ የምጠይቃቸው ነገርም አለኝ። እንዴት እርሳቸውን መሆን እንደምችልና በሁሉም ነገር የተሳካለት ለመሆን ምን ያስፈልገኛል የሚለውን ከአንደበታቸው መስማት እፈልጋለሁ» ብላለች። ተስፋም አላት በምትማርበት ትምህርት ቤት ማለትም በኢትዮ ብሔራዊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መጥተው እንደሚያዩዋት። እኛም መልካሙን ተመኝተን ልጆችም እንደእርሷ መሆን እንዳለባቸውና አቶ ስምኦን የመከሯቸውን መተግበር እንደሚገባቸው ጠቁሜ ለዛሬ የያዝኩትን ቋጨሁ። መልካም እለተ ሰንበት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 8/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው