ሰዓሊ በቀለሙ ዓለምን ይተረጉማል። በብሩሹ ስለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ግኝቶች ሁሉ በተገለጠለት ጥልቀት ይገልፃል። ስዕል ከፍ ያለ ክህሎት ከነጠረና ጥልቅ ሀሳብ ጋር ተዋህዶ በአንድ ገጽ የሚታይበት ጥበብ ነው። ከሌሎች የኪነጥበብ ዘርፎች ቀዳሚ የኪነ ጥበብ ዘርፍ መሆኑ የሚነገርለት ስዕል የታሪክ አሻራን በጉልህ አድምቆ የማሳየትና ዘመናትን ተሻግሮ የመታየት አቅሙ ከፍተኛ ነው።
ሸራን ወጥረው ቀለምን አዋህደውና የታያቸው ረቂቅ ሀሳብ በብዙ የሚገልፁት ሰዓሊያን የኪነ ጥበቡ ድምቀቶች ናቸው። እነዚህ ልዩ ጥበበኞች በተናጥል ከሚያደርጉት ጥረት የሚያገኙትን ለውጥና ውጤት ይበልጥ ከፍ ለማድረግ በማሰብ ጥምረትን እንደ አንድ መንገድ ይወስዱታል። የኢትዮጵያ ሴት ሰዓሊያን ማህበርም ለዚሁ ጥምረትና አብሮ መስራት ተሰባስቦ የጋራ አላማ ለማሳካት የሚደረግ ጥረት አንዱ ማሳያ ነው። በዛሬው የዘመን ጥበብ ገፃችን የማህበሩ ኪነ ጥበባዊ እንቅስቃሴ ለመዳሰስ ወደናል መልካም ንባብ።
በአገራችን የስዕል ጥበብ ቀድሞ የመጀመሩ ያህል ዛሬ ካለበት ደረጃ ጋር ሲነፃፀር አዝጋሚነቱ ፍንትው አድርጎ ያሳያል። አልያም በሚፈለገው መልኩ አድጎና ሰዓሊው ተጠቃሚ አድርጎ መጓዝ አልቻለም። በእርግጥ ስዕል ጥበብ እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ ያለውና በኪነጥበባዊ ጠቀሜታው የጎላ ቢሆንም የጥቅሙ ያህል እድገቱ የተፋጠነ አይደለም። ለዚህ ደግሞ በዘርፉ የሚስተዋለው ችግር ለእድገቱ ማነቆ ተደርጎ ይወሰዳል።
በዘር የሚታዩ ችግሮችን በጋራ በመቋቋም የተሻለ ስራ ለመስራትና የስዕል ጥበብ ለማሳደግ የሚተጋው የሴት ሰዓሊያን ማህበር የተመሰረተው በ1988 ዓ.ም ነው። ከዘርፉ ከባድነትና ካሉበት ውስብስብ ችግሮች አንጻር ለየብቻ ከመጋፈጥ በጋራ በማህበር ተደራጅቶ መስራት መፍትሄ ነው ብሎ የተደራጀው የኢትዮጵያ ሴት ሰዓሊያን ማህበር፤ በሰዓሊ መምህር እመቤት አወቀ ሀሳብ አመንጪነት ነው የተቋቋመው። ማህበሩ ሴት የስዕል ባለሙያዎችን በጋራ በማደራጀት በዘርፉ ተወዳዳሪና በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዲችሉ የማድረግ አላማ ሰንቋል።
ማህበሩ ይህ ታላቅ አላማ በመያዝ ዛሬ ላይ ከስዕል ትምህርት ቤት ወጥተው ወደ ስዕል ሙያ መቀላቀል ለሚፈልጉ ሴቶች መንገድ አመላካች፣ ልምድና ተሞክሮን አጋሪ፣ የጀመሩትን አዲስ ስራ ወደ ሕዝብ ማቅረቢያ ምቹ ሁኔታ ፈጣሪ ሆኗል። አንጋፋና ወጣት ሴት የስዕል ባለሙያዎችን ያቀፈው ማህበሩ በሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ በአገሪቱ የስዕል ጥበብ ላይ የራሱን አሻራ በማሳረፍ ላይ ይገኛል።
ሴት ሰዓሊያኑ ማህበር መስርተው በጋራ መስራታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኘላቸው ቢሆንም ያለሙትን ለማሳካት በስዕል ሙያ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች ፈተና ሆኖባቸዋል። ሴት ልጅ ካለባት ድርብ ኃላፊነት በተጨማሪ ያላትን ተስጥዖ ለማውጣት እንድትችል ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን የሚናገሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንት አርቲስት ስናፍቅሽ ዘለቀ ዓላማው ለማሳካት ብዙ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።
ሴት ሰዓሊያን ከተቋማት ጋር በመነጋገር የስዕል ስራዎቻቸው የሚያቀርቡበት መድረክ በማዘጋጀት ከሕዝብ ጋር እንዲገናኙ የማድረግ ስራ እየሰራ እንደሆነና የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም በዚህም ሰዓሊያኑ ተጠቃሚ እንዳደረገም ይናገራሉ።
በተለይ ሴቶች የመስራት አቅም እያላቸው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለሕዝብና ለራሳቸው ማበርከት የሚችሉትን እንዳይወጡ የሚያደርጋቸውን ምክንያቶች በመቅረፍ በአንድ ላይ ሆነው ለጠንካራ ስራ እንዲበቁና ለኪነጥበቡም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያደርጋል። ማህበሩ በዚህ ሁሉ ጥረቱ የሚፈልገውን ማድረግ እንዳይችል ጋሬጣ የሆኑበት ችግሮች መኖራቸውም በማሳያነት ያነሳሉ።
ከተመሰረተ ከ24 አመት በላይ የሆነው ይህ ማህበር ዛሬ ድረስ ቋሚ የሆነ የሰዓሊያኑ መገናኛና መቀመጫ ቢሮ፣ የሰዓሊያን የጋራ መስሪያና አውደ ርዕይ ማሳያ ቦታና ለስዕል ጥበብ የሚረዱ የተለያዩ ግብዓቶች የሚያገኝበት መንገድ የለውም። በዚህም በዘርፉ ነጥሮ ለመውጣትና የማህበርተኞችን አቅም ለማሳደግ የዘርፉ ችግሮች ፈተና እንደሆነባቸው ይገልፃሉ።
የማህበሩ አባል የሆኑ ሴት ሰዓሊያን ስራዎቻቸው በተለያየ መንገድ በራሳቸው በግል ጥረትና ምቹ ባልሆነ ሁኔታ የተሰራው ስዕል ማሳያ ቦታ በማጣትና የማህበሩ አባላት ይህን ችግር ተቋቁመው የተሰሩት ስራ ገበያ ማጣት የማህበሩ ዋንኛ ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው።
በዓመት ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ በስዕል አውደ ርዕዮች፣ መደበኛ የስዕል ማሳያና መሸጫ ጋለሪዎችና በሚዘጋጁ በልዩ ልዩ መሰል መርሀ ግብሮች ላይ የማህበሩ አባላት ስዕልና የእደ ጥበብ ውጤቶችን ለሕዝብ ያቀርባሉ። እጅግ ውስን በሆነ ቦታና ጊዜ መቅረቡ ደግሞ ተደራሽነቱን ይቀንሰዋል። ሰዓሊው በአዳዲስ ፈጠራ ሀሳቦች መሪነት የሚያዘጋጀው ስዕል ቋሚ የሆነ ማሳያና መሸጫ ቦታ አላገኘለትም። ይህ ችግር የማህበሩ አባላት የተሻሻሉ አዳዲስ ስራዎችን ሰርተው ወደ ሕዝቡ ማቅረብ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል::
ሰዓሊ፣ የስዕልና ግራፊክስ ዲዛይን መምህርና የማህበሩ አባል የሆነችው ወይዘሮ ሩት አድማሱ የሴት ሰዓልያን ማህበር ለ5 አመት ያህል በፕሬዚዳንትነት መርታለች። ስዕል የሰዎችን ውስጣዊ ጥልቅ ሀሳብ ማሳያ ልዩ ጥበብ መሆኑንና በአንጻሩ ግን ጥበበኛው በሚፈለገው መልክ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ትገልፃለች።
የስዕል ጥበብ እንደ አገር ሲታይ በግለሰብ ደረጃ እድገቱ እጅግ አስገራሚ የሆነ ለውጥ እንዳለው የምትገልጸው ሩት ይህ በሁሉም መሰባሰቦች ውስጥ እንዲታይ ግን በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች መቅረፍ ይገባል። ስዕል ማበርከት የሚገባውን የላቀ ጠቀሜታ እንዲሰጥ ሁኔታዎች ምቹ መሆን አለባቸው የምትለው ሰዓሊና መምህርትዋ ሩት ችግሮቹ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያዊያን ጥበበኞች ናቸው። ለዚህ ማሳያው የቀደሙ አባቶቻችን የጥበብ አሻራቸው ያሳረፉባቸው አክሱም፣ ላሊበላ፣ፋሲል ግንብ፣ በእምነት ተቋማትና ታሪካዊ ቦታዎች ላይ በልዩ ልዩ ቀለማት ተስለውና ተቀርጸው ዛሬ ድረስ የሚያስደምሙ ስራዎቻቸው ማስረጃ ነው።
ስዕል በቂ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ እንዳይሰጥ እንዲሁም መሰል የስዕል ማህበራትና ሳዕሊያን እንዳይጠቀሙ ያደረገበት ምክንያት ሩት ታስረዳለች። በአገር ደረጃ ለስዕል ጥበብ ትኩረት ተሰጥቶ አለመሰራቱ፣ ለስዕል ስራ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ላይ የበዛ ቀረጥ መጣሉ፣ የስዕል ማሳያ ቦታዎች በቂ አለመሆንና አሁን ላይ እየተገነቡ ያሉ ፓርኮች ላይ ያሉ ጋለሪዎች ለሙያተኛው ምቹ በሆነ መልኩ ስራዎቹን እንዲያሳይና እንዲያቀርብ ዕድል አለማግኘቱ ወይም ለሙያተኛው ምቹ ሁኔታ አለመፈጠሩ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው።
ማህበረሰቡ ለስዕል ስራ ያለው አተያይም ሌላው ቀጥተኛ ባይሆንም በስዕል ሙያ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪው ጉዳይ ነው። ሰዓሊ እራሱን የጣለ፣ ፀጉሩን ያንጨባረረ፣ ስለ ሰዎችና የሚኖርበት ዓለም ጉዳይ የማይሰጠውና ተራ ሕይወትን የሚመራ አድርጎ በተሳሳተ መልክ ማሰቡ በሚዲያ ተፅዕኖ የመጣ እንጂ እውነታው ሌላ መሆኑን ሙያተኞቹ ይገልጻሉ። በምናያቸው ድራማዎች፣ ፊልሞችና የስነ ጽሁፍ ውጤቶች ሰዓሊያን የሚሳሉበት ገጸ ባህሪ ህብረተሰቡ ሙያውን በተሳሳተ መንገድ እንዲረዳው አድርጎታል።
የኢትዮጵያ ሴት ሰዓሊያን ማህበር ፕሬዚዳንት ስናፍቅሽ ዘውገ፣ ስዕል ጥበበኛ እጆች የታደሉ ባለሙያዎች የሚገኙበት ዓለም መሆኑና ለዚህ ትልቅ መስክ የሚገባውን ሊደረግለት እንደሚገባ ያነሳሉ። የስዕል ታላቅነት ትልቅ ደረጃ በተለያየ መልኩ ይንፀባረቃል የሚሉት ፕሬዚዳንትዋ በማሳያነት በአገራችን ብሎም በዓለም ታዋቂ የሆኑትን የጥበብ ሰው እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ይጠቅሳሉ።
ዘመን ተናጋሪና ታሪክ አስረጂ የሆነውን የስዕል ጥበብ ለማሳደግና ማህበረሰቡ ለስዕል ጥበብ የሚሰጠው ክብርና ፍቅር ከፍ እንዲል ከትምህርት ቤት ጀምሮ ህጻናት የስዕል ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ቢቻለልና በስዕል ጥበብ ትልቅ ቦታ የደረሱ ኢትዮጵያዊያንን የማስተዋወቁ ስራ ቢሰራ መልካም መሆኑንም ይነገራል።
ለሕዝብ ጠቃሚ የሆነውን ጥበብ ለሚያፈልቀው ሰዓሊ የሚገባውን ማግኘት ይገባዋል የሚል የጸና እምነት አላቸው። ጥበብ ለሽያጭ ተበሎ የሚከወን ወይም የሚሰናዳ ባይሆንም የጥበበኛው ህያውነት የሚያረጋግጡ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ግድ ይላል። አንድ ሰዓሊ ስዕል መተዳደሪያና የገቢ ምንጩ ነውና ሕይወቱን ለመምራትና የተሻሉ ስራዎችን ሰርቶ ለህዝብ ማቅረብ እንዲችል ቀድሞ ያቀረባቸው ስራዎቹ ሊሸጡለትና የድካሙን ያህል ሊያገኝበት ይገባል።
ሰዓሊው አንድ የተዋጣለት ስራ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሶስት ወርና ከዚያ በላይ ይወስድበታል። ስዕሉን ለመስራት የወሰደበትን ጊዜ፣ ለስዕል ስራው ያወጣውን ወጪና ስዕሉን ለመስራት የተጠቀመበት እውቀት፣ ሀሳብና ክህሎቱን ተጠቅሞ ለሕዝብ ያቀረበውን ስራ ጥረቱን በሚመጥን መልኩ ገዢ ካላገኘ ሌላ ፈጠራ የታከለበት የነጠረ ስራ ለመስራት አቅምና ሞራል ያሳጣዋል።
ማህበረሰቡ በሚዘጋጁ የስዕል አውደ ርዕዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ ልምዱ ቢዳብር፣ ለሰዓሊ የስዕል ማሳያ ቦታዎች ቢመቻችለት፣ ሰዓሊው ለስዕል ስራው የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎች ቀረጥ ቢቀንስና ለዘርፉ መነቃቃት አሉታዊ ሚና ይጫወታል እንደ ስዕል ባለሙያዎቹ ሀሳብ።
በባለሙያዎቹ ለስዕል ጥበብ ማበብ እንደ መፍትሄ ከተቀመጡት ውስጥ አንዱ ዘርፉ ከቱሪዝም ጋር ማገናኘትን ነው። ቱሪዝም ከስነ ጥበብ ጋር የጠበቀ ቁርኝት አለው። ስዕል ደግሞ የቱሪስት መስህቦችን በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ድርሻ አለው። አገራችን በቱሪዝም ሀብት የታደለች መሆንዋ ደግሞ ለዚህ ምቹ ያደርጋታል። የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ላይ የተለያዩ ደረጃቸው የጠበቁ የስዕል ጋለሪዎቸ ቢመቻቹና አሁን ላይ በስፋት እየተሰሩ ያሉ ጋለሪዎች ለባለሙያው ምቹ ቢሆኑ የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል።
በሌላ በኩል ያልታየው ዋንኛ ጉዳይ ስዕል ሰፊ ተደራሽነት ያለው መስክ ስለሆነ ለውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገድም ሊሆን ይችላል። ሰዓሊው ስራዎቹን ቢያቀርብ ለአገር የውጭ ምንዛሬ ምንጭም መሆን ይችላል።
ማህበሩ ከስዕል ስራ በተጨማሪ በተለያዩ ማህበራዊና አገራዊ ጉዳዮች በመሳተፍ አገራዊ ኃላፊነቱም በመወጣት ላይ ይገኛል። በተለይ የስዕል ጥበብን ለሌሎች በማስተማር፣ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ስልጠናዎችን መስጠትና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችም በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የስዕል ጥበብ በራስ እይታ የተለያየን የፈጠራ ስራ በቀለም አድምቆና ልዩ ውበት ሰጥቶ ለማህበረሰቡ ማቅረብ በዚያም የላቀ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማስገኘት ነው። የኢትዮጵያ ሴት ሰዓሊያን ማህበር ልምድና ተስጥኦ ያላቸው ድንቅ ሰዓሊያን ስራዎቻቸው ምቹ ሁኔታ አግኝተው ለገበያ ቢቀርብላቸው ከራሳቸው አልፈው ለአገር ኢኮኖሚ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል።
ሰዓሊ የስዕልና የግራፊክስ ዲዛይን መምህር የሆኑት ወይዘሮ ሩት አድማሱ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ልምድ ቢወሰድ ለዚህ መልክም መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህም የጀርመንዋ ከተማ በርሊን እና የቻይናዋ ቤጂንግ ማሳያ አድርገው ያነሳሉ። ከተሞቹ የጥንት መንደሮቻቸውን ለይተው ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በመስጠት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ቅርሶችን እየጠበቁና እየተንከባከቡ የራሳቸውን ስራ እንዲሰሩና የሰሩትን የኪነ ጥበብ ስራ ማሳያ እንዲሆን ይደረጋል።
በዚህም አገራቱ የጥንት መንደሮችና ታሪካዊ ቦታዎች የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን በማልማት ለቱሪዝም ዘርፍ እድገትና ለገቢ ምንጭነት ማዋል እንደቻሉ ይጠቁማሉ። ይህንን ተሞክሮ ወደ አገር ቤት በመመለስ ዘርፉንና ቱሪዝሙን ማጠናከር የሰዓሊያንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ህልም ማሳካት ችግሮችም መቅረፍ ያስችላል።
አሁን ላይ በከተማችን አዲስ አበባ እየተሰሩ ያሉ የስዕል ማሳያ ጋለሪዎች መዘጋጀታቸው መልካም ቢሆንም የጋለሪዎቹ ባለቤት ተለይቶና ለሰዓሊያን ምቹና ቀላል ተደርገው ቀርበው ለማሳየትና ስራዎቻቸው ከሕዝብ ጋር የሚያገናኙባቸው መድረኮች ቢሆኑ መልካም እንደሆነ አስተያየትዋን ትሰጣለች።
የስዕል ጥበብ አገራዊ ፋይዳው የጎላ ነውና በዘርፉ የተነሱ ዋና ዋና ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል። አገርናና ሕዝብን የመቀየር ታሪክናና ማንነትን የማሳየት ትልቅ አቅም ያለው የስዕል ጥበብ ሙያተኞቹን በማገዝ ለፈጠራቸው ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ለእድገቱ ሊሰራ ይገባል መልዕክታችን ነው።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2014