በአገራችን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ተጃምለው የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የዕለት ተዕለት ኑሮ አሳር እያደረጉት ነው። ከኢኮኖሚያዊ ቀውስነት ባሻገር ወደ መልካም አስተዳደርና ፖለቲካዊ ጥያቄ እያደገ ነው። በደምሳሳው የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ችግሮ አደባባይ አውጥተዋል። ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአንድ በኩል በአቦሰጥ የኑሮ ውድነቱን የፈጠረው የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ነው ይለንና መፍትሔው ምርታማነትን ማሳደግ ነው ቢልም፤ ግብርናውን የሚመለከተው ተቋም ደግሞ የምርት እጥረት የለም በማለት፤ ምርት በየአመቱ እየጨመረ መሆኑን አኃዛዊ መረጃዎችን እየጠቀሰ ይሞግታል።
በሌላ በኩል አርሶ አደሩ የገብያ ትስስር አልተፈጠረልኝም እያለ ሲያማርር በሚዲያ ይደመጣል። ከአዲስ አበባ በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቀት ሽንኩርትና ቲማቲም በአስራ ምንአምን ብር እየተሸጠ፤ አዲስ አበባ ሲደርስ ከእጥፍ በላይ የሚሸጥበትና ሲብስም ከገበያ የሚጠፋበት ምክንያት ብዙውን ሸማች ግራ ያጋባል። በዚህ መልኩ ኢኮኖሚውን ተብትበው የያዙት ችግሮች እንዳሉ ሆነው፤ በአምራቹና በሸማቹ መካከል የተፈጠረው የገብያ ሰንሰለት መርዘም፤ ከማሳ፣ ከጉልት አንስቶ እስከ ጅምላና የውጭ ንግድ የተሰገሰገው እንደ እንጉዳይ የፈላ ደላላ ለኑሮ ውድነቱ ግንባር ቀደም ተከሳሽ ሲሆን ከውጭ የሚገባው ንግድ በጣት በሚቆጠሩ አስመጪዎች እጅ መውደቁና ምርትን መያዝና ገበያውን ማሻጠር ሌላው ተወቀሽ ሆኖ ይነሳል።
ያም አለ ይህ ኢኮኖሚው የሥርዓትና የሕጋዊነት በገበያ መርህ የመመራት መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር ያለበት መሆኑ አያጠያይቅም። 80 በመቶ አርሶና አርብቶ አደር ባለበት አገር የምርት አቅርቦት ችግር አለ ቢባል ውሃ አያነሳም። ሆኖም ግብርናችን በተበጣጠሰ መሬት ሜካናይዝድ ባልሆነ አግባብ በአለበት ሲረግጥ መኖሩ የሚካድ አይደለም። ዳሩ ግን ከአምራቹና ከሸማቹ ቁጥር የማይተናነሰው ደላላ ገበያውን አንቆ አላላውስ ከማለት አልፎ በመዳፉ ስር ማድረጉ በእንቅርት ላይ ቆረቆር ሆኗል። በነጻ ገብያ ስም ገበያው ስድ መለቀቁና የትርፍ ሕዳግ አለመወሰኑ እና የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ አለመተመኑ ሌላው ችግር ነው።
የአገራችን ኢኮኖሚ በአዳም ስሚዝ የኢኮኖሚክስ ሀ ሁ በፍላጎትና አቅርቦት ሳይሆን በደላላ የሚዘወር ነው። ገበያው ካለበት መዋቅራዊ ችግር ባልተናነሰም በገበያው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ክፍተት መኖሩ ችግሩን አወሳስቦታል። በዓለማችን ባልተለመደና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአገራችን የተሰገሰገው ደላላ በገበያውና በኢኮኖሚው ላይ አዛዥና ናዛዥ ሆኗል። ደላላው በመንግሥት ውስጥ ያለ የገበያ መንግሥት ሆኗል። ምንም አይነት ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔ ቢቀመጥ ደላላውን ከኢኮኖሚ መዋቅር ማስወጣትና በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ካልተደረገ ከዚህ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት አዙሪትና ቀለበት ሰብሮ መውጣት አይቻልም።
“አራተኛው መንግሥት “(The Fourth Estate) የሚለው ስያሜ ሀረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው የዛሬ 234 ዓመታት በሀገረ እንግሊዝ ነው። አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ደግሞ ከዚህ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቀድሞ እንደነበረም ያወሳሉ። በዛ ጊዜ ሶስቱ መንግሥታት በመባል ይታወቁ የነበሩት፤ 1ኛ.ቤተ ክርስቲያኗ፣ 2ኛ.መሳፍንቱ፣ 3ኛ.ተራው ሕዝብ ሲሆን፤ 4ኛ.ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን ነበሩ። አራተኛው መንግሥት የሚለውን አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙት የታላቋ ብሪታኒያ የፓርላማ አባል ኤድሞንድ ቡርክ ሲሆኑ፤ አመቱም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1787 እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ከትበው አቆይተውናል።
ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት ንግስቷ፣ የሕግ ባለሙያዎች (lawyers) እና ዝቅተኛው መደብ (ላብ አደሩ /proletariat) እንደ አራተኛ መንግሥት ይቆጠሩ ነበር። ከጊዜ በኋላ ስያሜው ወደ ጋዜጠኞችና ሚዲያ ቋሚ መጠሪያነት ተሸጋግሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሒደት ሶስቱ መንግሥታት ቀደም ሲል ከነበራቸው ስያሜ ወደ ሕገ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚ እና ሕግ አስፈፃሚ መለወጣቸውን እነዚሁ ድርሳናት ያስረዳሉ።
እነዚህ የመንግሥት አካላት መንግሥታቸውን የመቆጣጠሪያ ሚዛንና የመመዘኛ መድለው(check & balance) በመሆን ያገለግላሉ። ሚዲያው አራተኛው መንግሥት መባሉ በአንድ አገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳይ ምን ያህል ከፍ ያለ ቦታና ሚና እንዳለው ያሳያል።
በምዕራባውያን በተለይ በእንግሊዝና በአሜሪካ ሚዲያው ከሶስቱ የመንግሥት አካላት ተርታ መሰለፍ ችሏል። በአህጉራችን በደቡብ አፍሪካ፣ በጋና እና በናይጄሪያ እንዲሁም በተወሰነ ደረጃ በኬንያ፣ በኮት ዲቯር እና በሌሎች አገራት ሚዲያው የአራተኛው የመንግሥት አካልነት ሚናቸውን፣ ኃላፊነታቸውን ከነውስንነተቻው እየተወጡ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ አገራችን የጎለበተ፣ ጥንታዊ የአገረ መንግሥት ልምምድ ቢኖራትም ሚዲያችን ግን አራተኛው የመንግሥት አካል ለመባል ገና ብዙ ብዙ ይቀረዋል።
ስለሆነም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የመንበሩን አለመያዝ ተረድተው ይመስላል በአንድ መድረክ በአገራችን የገነገነውን ሙስና አራተኛው መንግሥት በማለት እንደገለፁት ሁሉ፤ እኔም በአገራችን አሉታዊ ተፅዕኖው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣውን፤ በጊዜ ሀይ ካልተባለ ለአገራችን ህልውና አደጋ እየደቀነ ያለውን፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከጉልት እስከ ጅምላ ንግድ፤ በአጠቃላይ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ ሕይወታችንን እየናጠ ያለውን፤ አደገኛ እየሆነ የመጣውን፣ በሰዓት የተጠመደ ቦንብ (time bomb) ይገልፅልኛል ብዬ ስላመንሁ”ድለላ!?”ን ሳልወድ አምባሻ ሳልቆርስ “አራተኛው መንግሥት!?” ብየዋለሁ።
አዎ ! ከላይ ስለ ሀረጉ ስረወ ቃል ሳትት ፅንሰ ሃሳቡ በቀደመው ዘመን ንግስቷን፣ የሕግ ባለሙያን፣ ሰራተኛውን ለመግለፅ ይውል እንደነበረው ሁሉ፤ እኔም ዛሬ ድለላ በአገራችን ከደቀነው ወቅታዊና ከቡድ ተፅዕኖ አኳያ አራተኛው የመንግሥት አካል ብለው ያንስበት ይሆን እንደሁ እንጅ አይበዛበትም። እንዲያውም ከሕግ አውጭው፣ አስፈፃሚውና ተርጓሚው እንዲሁም ከሚዲያው በላይ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ ጓዳ ጎድጓዳችንን አንዳንድ ጊዜም አልጋ ተጋሪያችንን፣ አንሶላ ተጋፋፊያችንን እስከ መወሰን ከፍ ሲልም ውሃ አጣጫችንን እስከመምረጥ ስለተሸጋገረ “ድለላ!?” 1ኛው የመንግሥት አካል ቢባል ያንሰው ይሆናል እንጅ አይበዛበትም። አዎ! ደላላ ስንበላ የሚበላ፣ ስንጠጣ የሚጠጣ፣ ስንለብስ የሚለብስ፣ ስንገዛ የሚገዛ፣ ስንሸጥ የሚሸጥ፣ ስንከራይ የሚከራይ፣ ስንወስብ የሚወስብ፣… ምን አለፋችሁ ስንሰራ ካለመስራቱ፣ ስንራብ ካለመራቡ፣ ስንታረዝ ካለመታረዙ፣ በችጋር ስንገረፍ ካለመገረፉ፣ በኑሮ ወድነት ስንሰቃይ ካለመሰቃየቱ፣ በዋጋ ግሽበት ኪሳችንንና ቦርሳችን ሲገለበጥ ካለመገልበጡ በስተቀር የማይገባበት የሕይወታችን ቅንጣት፤ የማያንኳኳው በር የለም። ታዲያ አይደለም 4ኛው፣ 1ኛው መንግሥት ቢሆን ይበዛበታል!? ደላላ በሶስቱም የመንግሥት አካላት ማለትም በሕግ አውጭው፣ ተርጓሚውና አስፈጻሚው እንዲሁም በሚዲያው የሰራ አካላት የተሰራጨ አደገኛ ሕመም ነው።
በእያንዳንዳችን ሕይወት አዛዥ ናዛዥ የሆነው “ድለላ!?” የቃሉ ትርጉም ምን ማለት ይሆን!? ምንም እንኳ በሥነ ልሳን አስተምህሮ በስያሜውና በተሰያሚው መካከል የባህሪ ግንኙነት እንደሌለ ቢበየንም፤ የቃሉ ግብርና ምግባር ስለተማታብን፣ ስለተጣረሰብን ትርጉሙን እንመልከት። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ “ደላላ”ን፦ ‘ገንዘብ እየተከፈለው ተፈላላጊዎችን (ሻጭና ገዥን፣ አከራይና ተከራይን፣…) አገናኘ፣ አስማማ፤’ በማለት ይተረጉመዋል። በመደለል ስራ ላይ የተሰማራ ሰው፤ አታላይ፣ በውሸት አግባብቶ ለማሳመን የሚሞክር፤ “ድላል”ን ደግሞ ለደላላ የሚከፈል ገንዘብ በማለት ይተረጉማል። የደስታ ተክለወልድ ዘሀገረ ወግዳ በ1970 ዓ.ም የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ፤ ደለለ፦ አሞኘ፣ አታለለ፣ ሸነገለ፣ የማያደርገውን አደርጋለሁ አለ፤ ደላላ፦ አመልካች፣ ጠቋሚ፤ ድላል፦ ለጠቋሚ፣ ላስማሚ የሚሰጥ ገንዘብ ሲል ይተረጉመዋል። ይሄኛው ትርጉም ከቀደመው ይልቅ የአገራችንን ደላላ ቁልጭ አርጎ ይገልፀዋል።
የእንግሊዝኛውን ትርጉም ‘broker’ ስረወ ቃል ስንመለከት “brocour” ከሚለው የፈረሳይኛ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቋንቋው አካል መሆኑን ሜሪያም ዌቢስተር የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ያወሳና ትርጉሙም፦{bro·ker: a person who helps other people to reach agreements, to make deals, or to buy and sell property (such as stocks or houses)} ነው ይለናል።
የአማርኛውም ሆነ የእንግሊዝኛው መሰረታዊ ትርጉም ተቀራራቢ ቢሆንም፤ “ድለላ” ሲነሳ አብሮ ማታለል፣ መሸንገል፣ ማሞኘት፣ በውሸት አግባብቶ ማሳመን፤ የሚሉ አሉታዊ አንድምታዎች ግዘፍ ከመንሳት አልፈው “ድለላ” በተነሳ ቁጥር ቀድመው ወደ አዕምሯችን የሚመጡት እነዚህ አሉታዊ ብያኔዎች ናቸው። በአገራችን ያለውን አብዛኛውን ደላላም ይገልፁታል ተብሎ ይታመናል። ሆኖም እጅግ ያነሱና በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ታማኝ፣ ሀቀኛና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ደላሎች መኖራቸው ግን ሊዘነጋ አይገባም። ድለላን ከመንግሥት አካላት ተርታ ከማሰለፍ አልፌ እንደ 1ኛው መንግሥት የቆጠርሁበትን አብይት መግፍኤዎችንና መገለጫዎችን ላነሳሳ፤
1.ኢኮኖሚያዊ፦
ኢኮኖሚያችን ከሌሎች አገራት ለየት ያደርገዋል ብዬ ከማምንባቸው ግርምቶች ቀዳሚው፤ በአዳም ስሚዝ የኢኮኖሚክስ ሀ ሁ ዝቅተኛ መስፈርት በሆኑት ፍላጎት/ demand እና አቅርቦት/supply አለመዘወሩ ነው። ከጉልት እስከ ጅምላ ንግድ፣ ከጎጥ እስከ ፌዴራል፣ ከሽንኩርት ማሳ እስከ አትክልት ተራ፣ ከሚዛን ተራ እስከ እህል በረዳ፣ ከአንድ ክፍል ጭቃ ቤት እስከ ተንጣለለ ቪላና ፎቅ፣ ከአንድ ጥማድ መሬት እስከ ጋሻ መሬት፣ ከአራጣ ብድር እስከ ባንክ ብድር፣… ከታች እስከ ላይ በተሰገሰጉ ህልቁ መሳፍርት ደላሎች ሳምባ የሚተነፍስ ኢኮኖሚ መሆኑ ነው።
አንድ ወዳጄ በዚያ ሰሞን እንዳጫወተኝ ከሆነ የደላላ እጅ ሀይ ባይ በማጣቱ እረዝሞ እረዝሞ በአንድ ወቅት አገራችን በምትፈርማቸው ብድርና እርዳታ ሳይቀር ፈርቅ እስከመያዝ ደርሶ ነበር። እግራችን እስኪቀጥን ብንዞር የደላላ እጅ ያልገባበት የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም። ከላይ ከትርጉሙ እንደተመለከትነው የድለላ ስራ ሻጭና ገዥን ማገናኘት ለዚህም ድላል (የአገልግሎት ክፍያ) መቀበል ቢሆንም፤ የአገራችን ደላላ ግን በዓለም ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ ዋጋ ቆራጭ፣ ተማኝ፤ ገብያ መሪ እስከመሆን ደርሷል።
አሁን ያለው የእህል፣ የአትክልት፣ የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ፤ የመኪና የንግድም ሆነ የኪራይ ቤት ክፍያ፣ የመሬት ዋጋ፣… የተቆረጠው፣ የተተመነው በገበያ ሳይሆን በደላላ ነው። በዚህም ገበያ አመጣሽ ሳይሆን፤ ደላላ ዘራሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አስከትሏል። በዚህ የተነሳ ዜጋው በኑሮ ውድነት ፍዳውን እያየ ነው። የሸቀጡ፣ የምርቱ፣ የአገልግሎቱ አምራች፣ አቅራቢም የሚገባውን ጥቅም እያገኘ አይደለም።
ከሸማቹም፣ ከሻጩም በሁለት ቢላዋ እየበላ ያለው ሕገ ወጥ ደላላው ነው። ዛሬ በመላው አገራችን ያሉ አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጥያቄ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውና ለምርታቸው፣ ለገበያ ከሚቀርቡ እንስሳትም ሆነ ተዋጽኦ ተገቢውን የድካማቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ሲወተውቱ፣ ሲማፀኑ በየሚዲያው ብንሰማም፣ ብንመለከትም መፍትሔ ባለማግኘታቸው ዋጋ የሚቆርጥላቸው ደላላው ነው። በምርቱ ተጠቃሚዎች እነሱ ሳይሆን ደላላው ነው። አርባ ምንጭ ገበሬው ኪሎ ሙዝ ሰባት ብር እንዲሸጥ፤ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ 40 ብር እንዲሸጥ የወሰነው ገበሬው ሳይሆን ደላላ ነው። አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የድካሙ፣ የላቡ ተጠቃሚ ካለመሆኑ ባሻገር፤ ደላላ አመጣሽ የሆነው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት የኢኮኖሚውን ወደለየለት ቀውስ እያንደረደረው ነው።
ሕገ ወጥ ደላላው ያለ አዛዥ ናዛዥ ገበያውን በብቸኝነት መቆጣጠሩ፤ መንግሥት በነፃ ኢኮኖሚ ስም መነሻ ዋጋ ተመን እና የትርፍ ሕዳግን / profit margin/ አለመወሰኑ፤ ከሕገ ወጥ ደላላው ጋር እሳትና ጭድ ሆኑ የኑሮ ወድነቱን እያቀጣጠለ፤ በዜጋው ላይ ብሶትን፣ ምሬትን ተስፋ መቁረጥን እየከዘነ ይገኛል። በዚሁ ከቀጠለ ወደለየለት ፖለቲካዊ ቀውስ የማያመራበት ምክንያት የለም። በዓለማችን የነፃ ገበያ አባት የምንላቸው ምዕራባውያን ሳይቀሩ የትርፍ ሕዳግንም ሆነ የመነሻ ዋጋ ደረጃን እየወሰኑ፤ ገበያውን እየተቆጣጠሩ ባለበት፤ እኛ ለዛውም ያልሰለጠነውን ኢኮኖሚ ስድ መልቀቃችን ዛሬ ለምንገኝበት ምሬትና እሮሮ ዳርጎናል።
2.ማሕበራዊ፦
ባለፉት ዓመታት ምሳሌ፣ አርዓያ የሚሆን ቤተሰብ፣ ተቋም፣ መሪ በየደረጃው አለመፈጠሩ፤ የግብረ ገብ ትምህርት አለመሰጠቱ፤ ፈሪአ እግዚአብሔር (ፈጣሪ) ያለው ትውልድ አለመታነፁ ዛሬ ለምንገኝበት የማሕበራዊ ቀውስ አፋፍ አድርሶናል። ውሸት፣ ሌብነት፣ ዘረፋ፣ ማጭበርበር፣ መካድ፣ ጥሎ ማለፍ፣… ነውር መሆናቸው ቀርቶ የሚያሸልሙበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። የዚህ ትውልድ፣ ማሕበራዊ ቀውስ ውጤት የሆነው አብዛኛው ደላላም መዋሸትን፣ ማታለልን፣ በአቋራጭ መክበርን ሙያ እስከማድረግ ተግቷል። ገንዘብ እስካገኘ ድረስ ለዜጋው ለወገኑ ደንታ ቢስ ሆነ። እህት ወንድሞቹን በማይጨበጥ ተስፋ እየደለለ ለስደት፣ ለመከራ ዳርጎ በበርሀ፣ በባህር አለቁ። በአረመኔዎች እጅ ወድቀው የአካላቸውን ክፍል አጡ። ሕገ ወጥ ድለላው በዚህ የሚያበቃ አይደለም።
በአገራችን እየተስፋፋ በመጣው የወሲብ ንግድም ግንባር ቀደም ተዋናይ ነው። ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ልጃገረድ ሕፃናትን ሳይቀር ለሕገ ወጥ የወሲብ ንግድ እስከማቅረብ፣ የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን ለዚህ ሕገ ወጥ ተግባር እየመለመለ የፎቶ አልበም አዘጋጅቶ የሚያቀርብ አረመኔ ደላላ በየዩኒቨርሲቲዎቻችን በሮች ማግኘት እየተለመደ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ዛሬ ዛሬ ደግሞ አዲስ የድለላ ዘርፍ ማለትም ስለ የማህፀን ኪራይ /surrogacy/ ደላሎች መስማት ከጀመርን ውለን አደርን፤ ልጅህን ለልጄ ማለት እየቀረ ተጋቢዎች ራሳቸው ወስነው ትዳር መመስረት እየተለመደ ቢመጣም፤ አሁን ሶስት ጉልቻ በደላላም ተጀምሯል። ምን አለፋችሁ ድለላ ያልገባበት የሕይወታችን ቅንጣት የለም።
በእንቅርት ላይ እንዲሉ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች እየተሸረሸረ በመጣው ማሕበራዊ ተራክቦ ላይ ሥነ ምግባር የሌለው ሕገ ወጥ ደላላ በአናቱ ተጨምሮበት ቀውሱን እያባባሰው ነው።
3.ፖለቲካዊ፦
ሕገ ወጥ ደላላው በኢኮኖሚው የሚስተዋሉ መዋቅራዊ፣ ተቋማዊ ችግሮችን በማበባስ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ፈታኝ እያደረገው ይገኛል። በዓል በመጣ ቁጥር የሚስተዋሉ እጅግ የተጋነኑ የዋጋ ጭማሬዎችን እዚህ ላይ በአብነት ማንሳት ይቻላል። በቋሚነት የኑሮ ወድነቱን፣ የዋጋ ግሽበቱን በማባባስ ዜጋውን ለብሶት፣ ለምሬት እየዳረገ ነው።
እዚህም እዚያም ለሚስተዋሉ ግጭቶች በአንድም በሌላ በኩል የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ የፈጠረው ተስፋ መቁረጥ እንደ ክብሪት ሆኖ በማገልገል ላይ መሆኑን የተለያዩ አካላት እያነሱ መሆኑ፤ የሕገ ወጥ ደላላ እጅ ከኢኮኖሚው አልፎ በማሕበራዊ መዋቅራችን ከፍ ሲልም ከሌሎች መግፎኤዎች ጋር ተዳብሎ አገራዊ ቀውስ በመለፈፍ፣ በመጥራት ላይ መሆኑን ተገንዝቦ ከዚህ በላይ ሳይረፍድ፣ ሳይቃጠል በቅጠል ሊባል ይገባል።
እንደ መውጫ
ራሳቸውን ሕጋዊ ብለው የሚጠሩትም ሆነ ሕገ ወጥ ደላላዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በዜጋው፣ በአገሪቱ ላይ እያሳደሩት ያለውን አሉታዊ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ለማስወገድ መንግሥት የዘነጋውን፣ ችላ ያለውን ኃላፊነቱን ዛሬ ነገ ሳይል መወጣት ሊጀምር ይገባል። በድለላ የሚዘወረው ኢኮኖሚ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆነው ሸማች፣ ሕዝብም ኢኮኖሚውን ከድለላ ምርኮ ነፃ ለማውጣት የድርሻውን ማበረከት ይጠበቅበታል። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የሚመለከታቸው የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን መጠየቅና ከጥልቅ እንቅልፋቸው መቀስቀስ ይጠበቅበታል። የዘርፉ ልሒቃንም የአደጋውን ስፋት በጥናት ተንትነው ሊያስረዱ ይገባል።
ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት በየደረጃው ከጎጥ እስከ ፌዴራል፣ ከሽንኩርት፣ ከቲማቲም እስከ ጅምላ ንግድ ገበያውን፣ የንግድ ሥርዓቱን በኔት ወርክ ተደራጅቶ እያተራመሰ ያለውን ሕገ ወጥ የድለላ ኃይል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቃህ!!! ሊለው ይገባል። መንግሥት በአጭር ጊዜ መሰረታዊ ሸቀጦችን አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ከደላላ ነፃ በማድረግ፤ ሸማቹና ሻጩ ያለደላላ በገበያ ሥርዓት በቀጥታ እንዲገበያዩ መደላደሉን ሊፈጥር ይገባል። ከዚህ በመቀጠል የገበያ ሰንሰለቱን ከሕገ ወጥ ደላላ መዳፍ ፈልቅቆ ነፃ አውጥቶ ሕግን ማስከበር ይጠበቅበታል። በመቀጠል ሕጋዊ ደላላው የሚገዛበት ሕገ ደንብ እና እንደአስፈላጊነቱ የሥነ ምግባር መመሪያ ሊዘጋጅ ይገባል። የደላላ ክፍያና ድለላ የሚፈቀድባቸውና የሚከለከልባቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በሕግ በማያሻማ ሁኔታ መለየት አለባቸው።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2014