በቅርቡ አንድ ልብ የሚነካ ንግግር በአንድ የቴሌቪዥን መስኮት ተመለከትኩ። ‹‹በግድ ብሉ እያልኩ አሞላቅቄ ያሳደኳቸውን ልጆች ምግብ ፈልገው ሲያለቅሱ የምሰጣቸው አጣሁ›› የሚል። ንግግሩ የተደመጠው ከመኖሪያ ቀያቸው በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ አንዲት እናት አንደበት ነው። ልጅ ራበኝ ብሎ ምግብ ሲጠይቅ ቆርሶ አልያም ፈትፍቶ ለመስጠት እጅ ከማጠር በላይ ለእናት ምንም የሚያስጨንቅ ነገር እንደሌለ ለመረዳት እናት መሆን ግድ የሚል አይደለም።
የእኚህ እናት ንግግር ለሚዲያ ስለበቃ ለአብነት አነሳነው እንጂ፤ አሁን አሁን በኢትዮጵያ መሰል አሰቃቂ ድምጾች በየቦታው ከፍ ብለው መደመጥ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ችግሩ ጎልቶ የሚታየው በጦርነትና በድርቅ በእጅጉ በተፈተኑ አካባቢዎች ቢሆንም፤ በአገሪቱ በተፈጠረው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ምክንያት የአብዛኞቻችን ጓዳ በችግር እየፈተነ ነው። በተለይም በዝቅተኛ ደመወዝ ተቀጥረው ለሚሰሩ እና በአነስተኛ የጡረታ፣ እንዲሁም ያለምንም ገቢ የሚኖሩ ወገኖች የሕይወት መራራነት ከዕለት ዕለት ማየሉን ቀጥሏል።
“ልጆቼን ምን ላብላቸው”፣ “ይህን ገንዘብ ምኑን ከምን አድርጌ ልኑርበት”፣ “የቤት ኪራይ ከየት አምጥቼ ልክፈል”፣ “ጎዳና መውደቄ ነው”፣ የሚሉና ሌሎችም የሰቆቃ ድምጽ ለጆሯችን እንግዳ፤ ለሕይወታችንም ሩቅ አልሆኑም። በቅርቡ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ገለጻ አድርገው ነበር። ምክንያቱም እርሳቸው ባቀረቡት ገለጻ መሰረት፤ ከሁለት ዓመታት በፊት የወጣው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ ይቋቋማል ይላል። ሆኖም እስካሁን ድረስ ቦርዱ ተቋቁሞ የተቀመጠ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ባለመኖሩ፤ ከአንድ ሺህ ብር በታች ደመወዝ የሚከፈላቸው ሰራተኞች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም።
ይህ ገንዘብ ደግሞ የቤት ኪራይ መክፈል፣ የምግብና ተያያዥ ወጪዎችን መሸፈን ቀርቶ አምስት ሊትር ዘይት እንኳን መግዛት አያስችልም። በመሆኑም ብዙ ሠራተኞች ምሳ ቋጥረው መሄድ ስለማይችሉ ጾማቸውን ሥራ መዋል እየተገደዱ ነው። ከዚህም ባለፈ አብዛኛው ሰራተኛም በአሁኑ ወቅት ዝቅተኛ የቤት ኪራይ ፍለጋ ከመስሪያ ቤቱ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ርቆ ይኖራል። ይህ አይነቱ ሰራተኛ ከመኖሪያ ቤቱ ማልዶ ወጥቶ ሥራ ውሎ ምንም አይነት ምግብ ሳይበላ ወደ ቤቱ ሲመለስ የግለሰቡ ሕይወት ምን ያህል አሰልቺና አሰቃቂ እንደሆነ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይደለም። አኗኗራችንም ወደየት እያመራ እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው።
በቅርቡ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች የደብረ ብርሃን እና ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጎብኝተው ነበር። በዚህ ወቅት የሠራተኞች ሮሮን ልብ ብሎ ላዳመጠ ሰው ምናልባትም ሥራ አለኝ ለማለት ካልሆነ የእነዚህ ሰዎች ገቢ ከሥራቸው አንጻር ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው። ሠራተኞቹ “…እጃችን ላይ እየደረሰ ያለው ከአንድ ሺህ ብር ያልበለጠ ገንዘብ ነው፤ በዚህ ገንዘብ የቤት ኪራይ ከፍለን፣ የምግብና ሌሎችንም ወጪዎች ሸፍነን ለመኖር ፈተና ሆኖብናል” ሲሉ ነበር የተደመጡት። የሚመለከተው አካል ሕይወታቸውን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ይፈልግላቸው ዘንድም በምሬት ነበር የተናገሩት።
የእነዚህን ሰራተኞች ድምጽ ያደመጡትና ምላሻቸውን የሰጡት የየፓርኮቹ ኃላፊዎች ደግሞ፤ የሠራተኞችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ባለመቀመጡ ይህ ጉዳይ እንዲሻሻል ለማድረግ ፈተና እንደሆነባቸውም ነው ሲገልጹ የተሰማው። ይህ ደግሞ ለችግሩ ከፍ ባለ አካል መለስ ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳየ ሲሆን፤ መንግሥት እነዚህን ዜጎች መስማት ከፈለገ የግድ አደባባይ እስኪወጡ መጠበቅ የለበትም። በወቅቱ ገበያ አምስት ሊትር ዘይት ለመግዛት አቅም በሌለው ደመወዝ ሕይወታቸውን እየገፉ ያሉ እልፍ ዜጎችን ጥያቄ ለመመለስም ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት መሥራት ይኖርበታል።
ዜጎች አገሪቱ ያለችበትን አጣብቂኝ ከግምት በማስገባት የልጆቻቸውን የማያባራ የዳቦ ጥያቄ፣ የራሳቸውንም በልቶ የማደር ትግል ተቋቁመው መንግሥት መፍትሔ እስኪሰጣቸው በትዕግስት እየጠበቁ ነው። ይሁን እንጂ ጊዜ ለማይሰጠው ጥያቄ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጡ የሚጠበቅባቸው አንዳንድ የሥራ ኃላፊዎች ግን ከስግብግብ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር የሕዝብን ሸክም እያከበዱ ነው የሚል ቅሬታም ይሰማል። በቅርቡ በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የክልል ከተሞች በተደረጉ የሕዝብ ውይይቶች አመራሩ የሕዝቡን የኑሮ ጫና ከማቃለል ይልቅ አባባሽ እየሆነ ነው የሚል ወቀሳ ተደጋግሞ መደመጡም የዚህ ብሂል አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው አንደኛው ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለልና የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል ተጨባጭ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ቃል ገብቷል። ይሄን መነሻ በማድረግ ከጉባኤው ማግስት ለፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ቀርቦ ለማዳመጥ እንዲቻል በየደረጃው ሕዝባዊ ውይይቶች ተደርገዋል። በዚህ ወቅት በርካታ ችግሮች የተነሱ ቢሆንም የኑሮ ውድነት መፍትሔ ይበጅለት፣ እና ከሁሉም በፊት የዜጎች የመኖር ዋስትና ይረጋገጥ የሚሉ ሀሳቦች ሚዛን ደፍተው ተስተውሏል። መንግሥትም ለዜጎች ጥያቄ በሂደት መፍትሔ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።
ይሁን እንጂ ብዙዎች መንግሥት በተለያየ ጊዜ እርምጃ እንደሚወስድና ለሕዝቡ እንደሚያሳውቅ ቃል የገባቸው አያሌ ጉዳዮች የውሃ ሽታ ሆነው በመቅረታው፤ አሁን ላይ የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር ስለመቀየራቸው ስጋት አላቸው። ይህ ስጋት ደግሞ ያለምክንያት አይደለም፤ ይልቁንም የሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በጊዜው ተተግብረው መፍትሄ የማይመጣ ከሆነ የቤት ኪራይ መክፈል ካልተቻለ ወደ ጎዳና፣ የቤተሰቡን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አዳጋች ሲሆንም ወደ ዝርፊያና ሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ሊያመራ ከሚችል አሳሳቢ ጉዳይ በመነሳት ነው።
በመሆኑም የኑሮ ውድነት እንደ ከዚህ ቀደሙ በእናጣራለን እና እርምጃ እንወስዳለን ሸንጋይ ቃላት ሊታለፍ የሚችል አይደለም። መንግሥት ለሕዝቡ በገባው ቃል መሠረት በአጭርና በረጅም ጊዜ ሊሠሩ የሚገባቸውን የቤት ሥራዎች በመሥራትና ሕዝቡን በማስተባበር የገባውን ቃል ወደ ተግባር ለማሸጋገር ዛሬውኑ የሚታይና የሕዝቡን ሸክም ሊያቀል የሚችል ተግባራዊ እርምጃ መጀመር አለበት። “የሚበላውን ያጣ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል” እንዲል፣ ይህ ካልሆነና ሕዝቡ የእለት ጉርሱን ማግኘት ሲያቅተው በቀላሉ ለችግር ፈጣሪ ኃይሎች ፊት መስጠቱ፤ የእለት ጉርሱን ማሟላት ሊያገኝበት በሚችለው አግባብ መሰማራቱ፤ ገፋ ሲልም ለአመጽና ተቃውሞ መነሳቱ እንደማይቀር ከጎረቤት አገራት ልንማር ይገባል። እናም የሕዝብ ብሶት ገንፍሎ አደባባይ ሳይወጣ የሚጨበጥ ለውጥ ሊመጣ የግድ ይሆናል። ለዛሬው አበቃሁ፤ ቸር ያቆየን፤ ሰላም!
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2014