2ኛው የአፍሪካ ቴኳንዶ ቻምፒዮና እና ኢንተርናሸናል የአሰልጣኝነት ስልጠና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ራስ ኃይሉ ጅምናዚየም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ሳቦም ጌታቸው ሽፈራው አስታውቀዋል።
በውድድር እና ስልጠናው ከአስራ አምስት በላይ የአፍሪካ አገራት እንደሚሳተፉ ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ስልጠናው ከትናንት በስቲያ መጋቢት 26/2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን ከሁለት መቶ አርባ በላይ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ ተገልጿል። ከሰልጣኞች ውስጥ ሃያ አምስት የሚሆኑት በሚወስዱት ፈተና የዳን እድገት እንደሚያገኙም ታውቋል። ከሰልጣኞቹ መካከል ኢትዮጵያዊው ሳቦም ወጋየሁ ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የማስተርነት ማዕረግ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪ 2ኛው የአፍሪካ ቴኳንዶ ቻምፒዮና ሚያዝያ 01 – 02/2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ታውቋል ።
ከዚህ ጎን ለጎን ከነገ በስቲያ መጋቢት 30/2014 ዓ.ም 4ኛው የአፍሪካ ቴኳንዶ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
በውድድሩና በስልጠናው እንዲሁም በጉባኤው ለመሳተፍ እና ለመምራት የኢንተርናሸናል ቴኳንዶ ፌዴሬሸን ፕሬዚደንትና ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባ ገብተዋል ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28/2014