እርግጥ ነው ይህ ያለንበት ወቅት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ያሉበት፤ በተሰራባቸው ቦታዎች ምርት በስፋት የሚታይበት (የእነ ዘይት ገበያ ቅጡን ቢያጣም)፤ በሥራ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራው ዘርፍ የወጣቶች ተሳትፎ እየተበራከተ የመጣበት፤ የባንዲራ ግድባችን እፍታውን የፈነጠቀበት ወዘተ ወቅት ነው። ይሁን እንጂ እንደ ሀገር አሁን ያለንበት ሁኔታ ደስ የሚል አይደለም። በዚህ ሲሉት በዛ፤ በዛ ሲሉት በዚህ እየሆነ ግራ እያጋባን ይገኛል። ምንም ሆነ ምን ግን የሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ የችግሩ ባለቤቶች እኛው ነን። የምእራቡ እጆች ድጋፍ ቢኖርም አጥፊ አውዳሚዎቹ እኛው ነን።
ሳይቸግር ጤፍ ብድር እንዲሉ፣ ምንም ሳይጠፋ፣ እዚህም እዛም እርስ በርስ የምንጋጭበት እየበዛ በሟችና ገዳይነት ተከፋፍለን በየእለቱ (ሳንወደውም ቢሆን) “ተጨፈጨፉ …”፣ “…ተገደሉ”፤ “ወደመ”፣ “ተቃጠለ…”፤ “… መሳሪያ ተያዘ ….” የሚሉ ዜናዎችን ከመስማት፤ እስር፣ ስቃይ፣ የጅምላ ግድያ፣ የመብት ረገጣና ንጹሃን ዜጎችን እንግልት ዘገባዎችን ከማንበብ አምልጠን አናውቅም። አሁንም፣ ጌትነት እንየው የአገሪቱን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ፊት ለፊቱ ቁጭ አድርጎ ባማረና ወቃሽ ግጥሙ እንዳለው “እኛው ነን”።
ከዚህ ሁሉ ሰብዓዊ ስቃይ ውስጥ የሰሞኑ አገራዊ ርእሰ ጉዳይ የሆነውንና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት እጃችን የገባውን መረጃ መነሻ አድርገን ስለ “ጅምላ ግድያ” እና “ጅምላ መቃብር”፣ (ድርጊቱን ከማውገዝና እንዳይደገምም ከመማፀን አኳያ) የተወሰኑ ሀሳቦችን እራሳችን ከራሳችን ጋር እንነጋገርበት ዘንድ እናንሳ።
በመሰረቱ “ጅምላ ግድያ”ም ሆነ “ጅምላ መቃብር” ሰብዓዊ ተግባራት አይደሉም። የዝቅጠት፣ የህሊናቢስነት፤ የሂትለራዊነት ….. ማሳያ የመጨረሻ ጥግ እንጂ በምንም መልኩ የጀግንነት መለኪያ፣ የወታደራዊ ሳይንስ ምጥቀት ማሳያዎች አይደሉም። በምንም መልኩ የተሸናፊነትን እንጂ የአሸናፊነት ስነ ልቦናን አያጎናፅፉም። በምንም መንገድ “አበጀህ”፣ “ጎሽ” … የሚያስብሉ፤ ደረት አስነፍተው አደባባይ የሚያቆሙ፤ የሚያሸልሙ ሥራዎች አይደሉም። በታሪክም ቢሆን በጀግንነት ተግባር ሳይሆን በአረመኔአዊነት ስር የሚያስፈርጁ ናቸው። መግደል እራሱ የግፈኞችና ጨካኞች ተግባር ሆኖ ሳለ እንደገና የገደሉትን በዚህ መልኩ ጅምላ መቅበር የሰው ልጅ ወጉ አይደለም። በተለይ ለአበሻ በፍፁም አይመጥነውም።
ግን ምን ያደርጋል፣ ጉዳዩ ዘመን አመጣሽ ነውና ሆነ። ንፁሀን ተቀጠፉ፣ እናቶች ተደፈሩ፣ ህፃናት ያልሆኑት ያልተደረጉት የለም። የአገር ሀብት ንብረት ሁሉ ወደመ። የተገኘው እርካታ ምን እንደ ሆነ ለጊዜው ለራሳቸው እንተወውና ድርጊቱ ግን በማንኛውም መመዘኛ ጭካኔ የወለደው መሆኑን ሳይናገሩ ማለፍ አይቻልም። ወደ መነሻው እንሂድ።
በወቅቱም “የማይካድራ ከተማ ከንቲባን አቶ ቸሩ ሀጎስ፣ የቀበሌ 01 ሊቀመንበር እና የከተማዋን ነዋሪዎች ጠቅሶ ጌቲ ኢሜጅስ በምስል አስደግፎ ባሰራጨው መረጃ ላይ እንደተገለጸው፤ እ.አ.አ ማርች 05 ቀን 2020 በአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን የጅምላ መቃብር ውስጥ ከ1ሺህ 300 በላይ የአማራ ብሄር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች አስከሬን ተገኝቷል።” የሚል ዜናን ሰማን። ሁሉም ደነገጠ። “አዘነ” የሚለው ሊገልፀው ከሚችለው በላይ ሁሉም ማዘን ብቻ ሳይሆን በያለበት ክው ብሎ ቀረ። ምክንያት? ይህንን መሰል ዘግናኝ ተግባር ለኢትዮጵያና ህዝቧ እንግዳ የመሆኑ ጉዳይ ነው።
እንደ ቡድን “ሳምሪ”ና የስምሪቱ ባለቤት ይህንን አይነት ተግባር ሲፈፅሙ ምክንያታቸውን በውል መረዳት ቢቸግርም ተግባሩ ፍፁም ኢሰብአዊ መሆኑን ሳያውቁት አይደለም፤ ወይም፣ አያውቁትም ማለት አይቻልም። ድርጊቱ ለማንም፤ ማሰብ ለሚችል ሰው ሁሉ ዘግናኝ ነው።
የሽብር ቡድኑ በአንድ ቀን (በጳጉሜ ወር 2013 ዓ.ም) ብቻ በቆቦ ከተማ 89 ሰዎችን ገድሎ በጅምላ መቅበሩን ሰምተናል። ከዛ በፊትም፣ ወይም ገና ግጭቱ እንደ ተጀመረ “በማይካድራ የጅምላ መቃብር ተገኘ፤ በህወሓት የተገደሉት ቁጥር …” የሚለውም ሳይዘገይ ነበር ለጆሯችን ሲበቃ የነበረው። እንስማና እናውግዘው እንጂ ቡድኑ እስከዛሬም ድረስ ከተግባሩ አልተቆጠበም።
ማርች 29 2021 ለጆሮና እይታ የበቃው “የማይካድራን የጅምላ መቃብር ማን ይዘግብ? ሁመራ አየር መንገድ ተቀብረው የተገኙ የጅምላ መቃብር ማን ይናገር?” የሚለው እሮሮ ዛሬም ድረስ በየጆሮአችን ላይ ድምፁ እንደተንጠለጠለ ነው። ችግሩ በዛው ያበቃል ብለን ነበር። ያ ሳይሆን ቀርቶ ከሰሞኑ “ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች የተጨፈጨፉባቸው በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸው ተገለፀ” የሚል ዜና ሰማን። ይህን ዜና ከሌሎች ለየት የሚያደርገው እንደ ሌሎቹ ገለጥ ገለጥ እየተደረገ የተገኘ ሳይሆን በሳይንሳዊ ጥናት ላይ በመመስረት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያገኘውና ሰሞኑን የይፋ ያደረገው መሆኑ ነው። ድመት መንኩሳ … እንዲሉ ቡድኑ ከድሮ እስከ ዘንድሮ እዛው ስለ መሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው።
ዜናው በመግቢያ አንቀፁ “የህወሓት ቡድን ከ1975 ጀምሮ በርካታ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ላይ የዘር ፍጅት የፈጸመበት ’ሀለዋ ወያነ’ በመባል የሚታወቁ የጅምላ እስር እና የጅምላ ቀብር የሚፈጸምባቸው ቦታዎችን ማግኘቱን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን አስታወቀ።” የሚለውን በማስነበብ የእነ ሳምሪንና የስምሪቱን ባለቤቶች ማንነትና የኋላ ታሪክ ይነግረናል።
ይህ ብቻ አይደለም፤ “የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ በርካታ የቡድኑ የጉድጓድና የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶች ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ከተጠቆሙት የጅምላ መቃብሮች መካከል ለሙከራ አምስቱን አስቆፍሮ ጭካኔ በተሞላበት ግፍ የተረሸኑ ንጹሃንን አፅም አስወጥቷል።” የሚለውና ሌሎችም ከዜና ባለፈም የእርስ በርስ መወያያ አጀንዳዎች ናቸው። “አካባቢውን የጀርመኑ ናዚ 1ሚሊዮን 400ሺ በላይ እስራኤላውያንን ከጨፈጨፈበት ’ኦሽዊዝ’ የተባለ ማጎሪያ ጋር አነጻጽረው ’የኢትዮጵያው ኦሽዊዝ’ ሲሉ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አባላት፤ ’ገሃነም’ በተባለው የትህነግ የድብቅ እስር ቤት በርካታ ሺህ ንጹሃን ማለቃቸውን በወቅቱ በእስር ላይ የነበሩና ከሞት የተረፉ የወራሪ ቡድኑ የጥቃት ሰለባዎችን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል።” የሚለውም እንደዚሁ የመነጋገሪያ አጀንዳ በመሆን እያነጋገረ ይገኛል።
“ለመሆኑ ይህን ድርጊት የፈፀመው አካል ለምን ይህንን ቦታ መረጡ?” የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ካለ ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ጥናት “ህወሓት ይህን ድብቅ እስር ቤት የመረጠበት ምክንያት አካባቢው ሰው ከሚኖርበት ርቆ የሚገኝ ዙሪያው በከፍተኛ ሰንሰለታማ ተራራ የተከበበ ከመሆኑም ባሻገር በኃይል ይዟቸው የነበሩትን የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች አማካኝ ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከሁሉም አካባቢዎች ንጹሃንን እያፈነ ወስዶ ለማጎርና ለመጨፍጨፍ ምቹ በመሆኑ ነው” የሚል መልስ ይሰጠዋልና ምክንያቱን ለማወቅ እሩቅ አይሄድም።
እውነቱ፣ ያለንበት ገሀዱ ዓለም ይህንን ይመስላል። አሁን ጥያቄው “እንደ ህዝብና ዜጋ እንዴት አድርገን ከዚህ አዙሪት እንውጣ?” የሚለው ነው። ይህ ደግሞ የሚመለከታቸውን ቅን ዜጎች ርብርብ ሁሉ ይፈልጋል። በመሆኑም ከችግሮቻችን አዙሪትና ከክፋቶቻችን ለመውጣት የጋራ መፍትሄ ፍለጋውን አሁኑኑ ልንሄድበት ይገባል። የእኛው ችግር መፍትሄ እኛው በመሆናችን ከወደቅንበት እንድንነሳም የሰውነት ልካችንን፤ የሞራል ከፍታችንን ፈልገን ማግኘትና መመለስ ይኖርብናል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መጋቢት 28 /2014