ዓለም ተሰርቶ ያለቀ ምንም ነገር የላትም። ሁሉም ኩነት፣ ሁሉም ምኞት በጊዜ ሂደት ውስጥ እንዲፈጠር ሆኖ የተሰራ ነው። እኛም እንኳን ቀስ በቀስ የምንሰራ የጊዜ ባሪያዎች ነን። ከትናንት ዛሬ ሌላ ነን። ነገ ደግሞ ከዛሬ የተሻልን የምንሆንበት በርካታ አጋጣሚዎች አሉ።
ይሄን ጽንሰ ሃሳብ ወደ አገርና ትውልድ ስናመጣው ከፍ ያለ ትርጉም ያለው ሆኖ እናገኘዋለን። ሰው ራሱን ሳይቀይር፣ አስተሳሰቡን ሳይገታ የሚፈጥረው አንዳች በጎ ነገር የለም። አገራችንን ለመፍጠር መጀመሪያ ራሳችንን መፍጠር አለብን።
ከራሳችንና ከሃሳባችን ጋር መስማማት አለብን። አገር ማለት ትርጉሙ ሳይገባን ለከፍታ የምንኖረው ቅንጣት ሕይወት የለንም። ሁሉም ነገራችን ልክ የሚመጣው አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያወቅን ሰሞን ነው። ዛሬ ላይ እንደ አገር፣ እንደ ማሕበረሰብ ብዙ ነገሮች ተበላሽተውብናል። የዛሬን ተስፋና ብርሃን ወደ ጎን ብለን የትናንትን ጨለማ የምንማትር ብዙ ነን። እጃችን ላይ ያለውን አሁናዊ በረከት ችላ ብለን ከአምና ማህጸን ውስጥ ጠጠርና ፋንድያ የምናስስ ብዙ ነን። ይህ ማለት ራሳችንን አልፈጠርንም ማለት ነው። ሰው ራሱን ሲፈጥር በዙሪያው ላሉት ሁሉ እንደ ራሱ የሰላምና፣ የእውነት አለቃ መሆን ይጀምራል።
ሰው በአስተሳሰቡ ሲዘምን ወደ ትናንት አይመለስም፤ ዛሬው ላይ ለራሱም ሆነ ለአገሩ የሚሰራው በርካታ ቁም ነገር ስላለው ያለፈን አይበረብርም። ሰው የአገር ፍቅር ስሜት ሲገባው ስለአሀገሩና ስለወገኑ ይሞታል እንጂ አገሩን ለማፍረስ ከተሰማሩት ጋር አያብርም።
ሰው በአእምሮ ሲበረታ አገሩን ማፍቀር ነው የሚጀምረው። አብዛኞቹ መከራዎቻችን ትናንትን እያስታወስን የቆሰቆስናቸው ናቸው። እስኪ ወደ አሁን እንመለስ። ትናንትን የመርሳትና በይቅርታ የመሻገር ጥበብን እንማር። ለምንድነው ዓለም የቻለው ለእኛ የከበደን? ለምንድነው በሃሳብ መዘመን ሲገባን በስይጥንና የዘመንነው? ለምንድነው በጋራ ሃሳብ የጋራ አገር መፍጠር ያቃተን? ለምንም ነገር ጦርነትና መገፋፋትን መፍትሄ አድርገን እስከ መች እንዘልቃለን? ጊዜው የእርቅ ነው። ጊዜው በአንድ ሃሳብ ለአንድ አገር የምንለፋበት እንጂ የተለያየ አመለካከትን ይዘን ጽንፍ የምንረግጥበት አይደለም።
ዓላማችንን አገር ካደረግን ክፉ ሃሳብ አይኖረንም። መዳረሻችንን ትውልድ ካደረግን በሀጥያት የምንጀምረው ጎዳና አይኖርም። አሁን ላይ አንድ መሆን ያቃተን የጋራ አገርና ትውልድ ስላልገነባን ነው እላለሁ። ትናንትን እየበረበርን፣ ያለፈውን ጊዜ እየመለስን ለመገፋፋት ምክንያት የምንፈጥረው ከእኔነት የላቀ ሁሉን አቃፊ ሰውነት ስለሌለን ነው። ሰው በሃሳቡ ካልዘመነ፣ ሰው በሰውነቱ ከፍ ካላለ ሌላ የከፍታ ጥግ አለው ብዬ አላስብም። ሰውነት ስፍራው ሁሉ አገር ነው።
ሰው ለአገሩ ካልሞተ፣ ሰው ለትውልዱ ካልተጨነቀ ያኔ ከሰውነት ርቋል ማለት ነው። እያንዳንዱ አገር በዜጎች የተፈጠረ ነው። ዓለም ላይ የምንቀናባቸው የአውሮፓ አገራት በዜጎቻቸው የአንድነት ሃሳብ አገር የሆኑ ናቸው። እኛም በአንድ ሃሳብ፣ በአንድ ልብ የጋራ አገራችንን ልንፈጥር ይገባል። የእስካሁኑ እርምጃችን ትርፍ ካላመጣልን የሄድንበትን ጎዳና ለምን እንደግመዋለን?
መጀመሪያ በሃሳብ እንጀምር። መጀመሪያ አገር ማለት ትርጉሙ ይግባን። መጀመሪያ ችግሮቻችንን ሁሉ በውይይትና በእርቅ የመፍታት ጥበብን እንማር። ከነችግሮቻችን ተቀምጠን የምናመጣው የአንድነት ሃሳብ፣ የምንፈጥረው የአንድነት አገር የለም።
መጀመሪያ በመተው ማሸነፍን፣ በይቅርታ መሻገርን መርህ እናድርግ። አባቶቻችን ዓድዋ ላይ ታሪክ ሲሰሩ ሊወራቸው ከመጣው የጣሊያን ወራሪ ሃይል በብዙ ነገር ያነሱ ነበሩ። ግን አንድነት፣ የአገር ፍቅር፣ የተባበረ ክንድ ነበራቸውና አፍሪካን የፈጠረ ታሪክ ሰሩ። የአገር ታሪክ የእኔና የእናተ ታሪክ ነው። የአገር ታሪክ የግለሰቦች ታሪክ ነው። ዛሬ ላይ በምንሆነው በእያንዳንዱ ነገር ነገ ላይ ትውልድ ገልጦ የሚያነበውን ታሪክ እየጻፍን ነው። ምንድነው እየጻፍን ያለነው? እያንዳንዱ ትውልድ፣ እያንዳንዱ ማሕበረሰብ በእኛ የተፈጠረ ነው።
እኛ በትናንት አባቶቻችን እንደተፈጠርን ሁሉ መጪው ትውልድም የተሻለ አገርና ተስፋ እንዲኖረው ሰላምና ፍቅርን በምናውቅ በእኛ መፈጠር አለበት። ከዚህ ሁሉ ነባራዊ እውነት በመነሳት አገራችንን በፍቅርና በእርቅ መገንባት የሁላችንም ቀጣይ የቤት ስራ ነው ብዬ አምናለሁ።
አባቶቻችን አፍሪካን መፍጠር ከቻሉ እኛ እንዴት አገር መፍጠር አቃተን? አባቶቻችን ዓለምን ከፈጠሩ እንዴት እኛ ኢትዮጵያን መፍጠር ተሳነን? ይሄ ጥያቄ የምንጊዜም ጥያቄዬ ነው። የአባቶቻችን ልጆች፣ የዛ ትውልድ አብራክ ሆነን አንድነት ማጣታችን ይገርመኛል። የዓለም መደነቂያ፣ የአፍሪካ የትንሳኤ ደብር ሆነን ባህር አሻጋሪ መጠበቃችን ይገርመኛል። እኛ እኮ ለአፍሪካ ሙሴን ነን። እኛ እኮ አፍሪካን ከጨለማ ወደ ብርሃን ያሸጋገርን ብርሃናማ ነፍሶች ነን።
እኛ እኮ ዓለምን ያስደነገጥን፣ አይበገሬዎችን ያርበደበድን የይቻላል የጽናትና የይቻላል ልጆች ነን። ዛሬ ላይ ያ መቻላችን ወዴት ገባ፣ ለአንድ አገር፣ ለአንድ ባንዲራ የመጽናታችን የአባቶቻችን የመቻል መንፈስ ወዴት ተሰወረ? ያኔም አሁንም ያለችው ኢትዮጵያ ናት። እኛ እንጂ ኢትዮጵያ አልተቀየረችም።
አንድ ሃሳብ፣ አንድ ልብ አጣን እንጂ ሁሉም ነገር እንደነበረ ነው። ያጣነው ተነጋግሮ መግባባት ነው። ያጣነው ትናንትን ረስቶ ዛሬን መኖር ነው። ያጣነው ከብሄርና ከጎሳ አመለካከት የነጣ አእምሮና ልብ ነው። ያጣነው በሁሉም ነገር ኢትዮጵያን ያስቀደመ ሰውነት ነው።
አሁን ጊዜው አርቆ የማየት ነው። እኔነትና ብሄርተኝነት ከሞቱ ዘመን የላቸውም። ትናንትን እየደገምን እንደ ትናንቱ አይነት ጥፋት የምንሰራበት ጊዜ ላይ አይደለንም። ጊዜው የፍቅር ነው… ጊዜው በተግባቡና በታረቁ ሃሳቦች አገር የመፍጠሪያ ነው። ጊዜው ለድርድር በጠረጴዛ ዙሪያ የምንቀመጥበት እንጂ ጦርና ጎራዴ ይዘን ጫካ የምንገባበት፣ በሃይል መብቶቻችንን የምናስከብርበት አይደለም። ጊዜው በበላጭ ሃሳብ የተበላሸችውን ኢትዮጵያ የምናስተካክልበት እንጂ ትናንትን መልሶ መላልሶ የምንደጋግምበት አይደለም።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዛሬም ድረስ ያልተደፈነ ሰፊ የመለያየት ቀዳዳ አለ። ዛሬም ድረስ የለያየን ያ ቀዳዳነው እላለሁ። ያን ቀዳዳ መድፈን አቅቶን በውሸትና በማስመሰል ቀዳዳው እየሰፋን ዛሬ ላይ ደርሰናል። ያ ቀዳዳ መደፈን አለበት። ያ የብሄር ቀዳዳ፣ ያ የእኔነት ቀዳዳ፣ ያ የተረኝነት ቀዳዳ፣ ያ የማን አለብኝነት ቀዳዳ፣ ያ የውሸትና የማስመሰል ቀዳዳ መደፈን አለበት። እነዛን ቀዳዳዎች ተጋግዘን ካልደፈንን ኢትዮጵያን ለመፍጠር አቅም አናገኝም። እስከዛሬ ድረስ ተነጋግረን ያልተግባባመነው፣ ሮጠን ያልቀደምነው፣ ሞክረን ያልተሳካልን እነዛን ነውረኛ ቀዳዳዎች ስላልደፈንን ነው እላለሁ።
አሁን ጊዜው እነዛን የመለያየት ቀዳዳዎች ደፍነን አገር የምንፈጥርበት፣ ትውልድ የምናሻግርበት ነው። ዘመኑ ያልዋጀውን ኋላ ቀር የፖለቲካ አስተሳሰባችንን ቀይረን ወደ ፊት የምንልበት ነው። አድዋን የፈጠሩ… ኢትዮጵያዊነትን የኳሉ እነዛ ሰማንያና ከዛ በላይ የሆኑ የአንድነት መልኮቻችን እርቅን ይሻሉ። ምንም ባልነበረበት በዛ ዘመን… ከዘመን ዘምነው፣ ከጊዜ ገዝፈው ነጻነትን የፈጠሩልን እነዛ ብሩካን ልቦች አንድነትን ይሻሉ።
አገር ለመፍጠር ሲሉ ከማይችሉት ጋር ተጋፍጠው በሞትና በጉስቁልና ክብርና ሉዓላዊነት የተውልን እነዛ ወርቃማ ነፍሶች ፍቅር ይሻሉ። እኛ የአባቶቻችን ጸአዳ መልኮች ነን… በጥላቻና በመገፋፋት ያን ውብ መልካችንን ማጠልሸት የለብንም። ኢትዮጵያዊነት የሚያምረው በጋራ ነው። ሀበሻነት የሚደምቀው በህብረ ብሄራዊነት ነው። በተለያየን ቁጥር እያነስን ነው የምንሄደው። በተገፋፋን ቁጥር እየሳሳን ነው። በተጋፋን ቁጥር እየኮሰስን ነው። በራስ ወዳድ ሰውነቶች በውሸትና በፈጠራ ትርክት የእውነት መስለው የተሰሩ ድራማዎቻችን የሚፈርሱበት ጊዜ ላይ ነን።
መከራ ወለድ ከሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ወጥተን መፍትሄ ወለድ ወደ ሆነ አዲስ አስተሳሰብ መሸገጋገር ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ውስጥ ቀዳሚው መስፈርት ነው እላለሁ። እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አብዛኞቹ መከራዎቻችን ፖለቲካ ወለድ ናቸው። አብዛኞቹ ትናንትናዊም ሆኑ አሁናዊ ቁርሾዎቻችን እውነትና ፍትህን ባልተላበሱ የአገዛዝ ሥርዓት የመጡ ናቸው።
እኚህንና የመሳሰሉ የችግር ምንጮቻችንን በእርቅና በአገራዊ ምክክር አድርቀን ከፍ ወዳለ የልዕልና ስፍራ መሄድ ከሁላችንም ይጠበቃል። ልዩነትን ወደ ጎን ብሎ ለጋራ ጥቅም በጋራ መስራት የዚህ ዘመን የሥልጣኔ ቀንድ ስለመሆኑ የሚጠራጥር አለ ብዬ አላስብም። እኛም በዚህ ቀንድ ላይ ተንጠልጥለን ልዩነቶቻችንንና ሲያኳርፉን የነበሩ ቁርሾዎቻችንን በባህላዊና በሳይንሳዊ መንገድ እልባት ሰጥተን ቀና ማለት ይኖርብናል። ፍቅር በራቀው ልብ፣ ሰላም ባጣ መንፈስ እስከ መች አጎንብሰን እንዘልቀዋለን? በእልህና በአልሸነፍ ባይነት መድረስ ካለብን ሳንደርስ እስከ መች ኋላ ቀርተን እንችለዋለን?
በአዲስ አስተሳሰብ ከፍ እንበል። በአዲስ አስተሳሰብ አገር እንፍጠር። የሚበጀን እሱ ነው። በአንድ አይነት አስተሳሰብ፣ በአንድ አይነት ፖለቲካ ዘመን ተሻግረናል… እስኪ አሁን ደግሞ በታደሰ ልብና አእምሮ ኢትዮጵያን እንስራ። እስኪ ደግሞ ለሰላም፣ እስኪ ደግሞ ለእርቅ በጥላቻ የከረቸምናቸውን ልቦቻችንን እንክፈት። እኛ ሳንለወጥ የምንለውጠው አገር የለንም። እኛ ሳንለወጥ የምንፈጥረው ብርቱ ትውልድ የለም። ሁሉ ነገራችን ያለው በእኛ ለውጥ ውስጥ ነው።
አገር ለመፍጠር መጀመሪያ እኛ በሃሳብ እንለወጥ። የሃሳብ ለውጥ የድርጊት ለውጥ ነው። የድርጊት ለውጥ ደግሞ የውጤት ለውጥ ነው። በሃሳባችን ከተቀየርን አገር የመፍጠር ሃይል ይኖረናል። የሃሳብ ለውጥ የሰላም ለውጥ ነው። የሃሳብ ለውጥ የእርቅና የሕብረት ለውጥ ነው። የጠፋችብንን ኢትዮጵያ የምናገኛት በሰላም ውስጥ ስንፈልጋት ነው። ያጣንውን ነገር ሁሉ የምንመልሰው ይቅር በመባባል ውስጥ ስንገኝ ነው።
ኢትዮጵያን በመፍጠር ሂደት ውስጥ መጪው ትውልድ ሌላ ዓድዋ ያስፈልገዋል። በእኛ የተሰራ፣ በእኛ የተጻፈ አዲስ የማንነት ዓድዋ ግድ ይለዋል። እስከዛሬ ታሪክ ስናወራ፣ ታሪክ ስንደግም ኖረናል አሁን ግን በእርቅና በተባበረ ክንድ ከመለያየት ወጥተን አገር በመፍጠር ገድል ውስጥ መሳተፍ አለብን።
ብዙ አንድ አይነት አለላ መልክ እያለን፣ የምንዋደድባቸውና የምንፋቀርባቸው እንዲሁም ደግሞ የምንተቃቀፍባቸው አንድ መአት የጋራ እሴቶች እያሉን ግን ደግሞ ነውር ነቃሽ ሆነን እዛና እዚህ ቆመናል። እስከ መቼ? አገራችን ኢትዮጵያ ፊተኛ ናት… ሕዝባችን ታሪኩ ቀደምት ነው… በፖለቲከኞቻችን ራስ ወዳድነትና እልህኝነት የክብር ስፍራችንን ማጣት የለብንም። ለዘመናት በማይመጥኑን ድሕነትና ኋላ ቀርነት አጎንብሰን ኖረናል። አንድ አይነት ነገር እየደጋገምን አዲስ ነገር አጥተን ከርመናል። ለምን? በቃ እንታረቅ… በቃ ስለኢትዮጵያ ስንል በልዩነት ውስጥ አንድ አይነቶች እንሁን።
በአሁኑ ሰአት ለአገራችን ምን እንደሚያስፈልጋት ሁላችንም እናውቃለን። በአሁኑ ጊዜ ለሕዝባችን እንዲሁም ለትውልዱ ምን እንደሚበጀው ይሄንንም እናውቃለን። ግን ማድረግ እየቻልን አላደረግንም። ትልቁ ክፍተታችን እዚህ ጋ ነው። የሚበጀንን ነገር እናውቃለን ግን ያን ነገር ለማግኘት ስንለፋ አንታይም። የሚያስፈልገንን እናውቃለን ግን ዛሬም ድረስ ለማይቅሙን የምንለፋ ነን። የሰላምን ዋጋ እኮ ከእኛ በላይ የሚያውቅ የለም። የአንድነትን ሃይል ከእኛ በቀር የደረሰበት የለም።
የቆምነው ግን ከዚህ እውነት በራቀ መንገድ ላይ ነው። ስፍራችንን እንወቅ… ወደሚጠቅመን የጋራ ህልም እንጓዝ። አገራችን ለጀመረችው የእርቅና የምክክር ጉባኤ ሁላችንም ልባችንን ከፍተን ወደ ሰላም መሄድ አለብን። የሁሉንም በር በሚያንኳኳው አገራዊ ምክክር ፍሬ እንደምናፈራ ተስፋ አለን። በዚህ የተስፋ ፍኖት ውስጥ ቆመን ለትውልድ የሚቆይ የአባቶቻችንን አይነት የጋራ ታሪክ እንደምንጽፍ ጽኑ ተስፋ አለኝ። ከቅያሜ ወጥተን በእርቅና በመከባበር ስሜት፣ በአባቶቻችን የአንድነት መንፈስ የምንናፍቃትን ኢትዮጵያ መፍጠር አለብን።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 27 /2014