ደላሎች ብዙ ወጪ ሳያወጡ ግን ደግሞ ላይ ታች ብለው፤ ወጥተውና ወርደው፤ አንዱን ካንዱ አገናኝተው ዋጋ ተምነው የማሳመን ሥራን በብዙ ሰርተው፤ ጠቀም ያለ ገቢ ያገኛሉ።
ማንኛውንም የግል ንብረት ለመሸጥ ከደላላ ውጭ አይሞከርም። ቢሞከርም አንድ እርምጃ ወደፊት መንቀሳቀስ ካለመቻሉም ባለፈ ትርፉ ድካም ይሆን እንጂ የሚገኝ ውጤት አይኖርም። መሸጥ ብቻ አይደለም ገዢውም በገዛ ገንዘቡ ብድግ ብሎ ከደላላ ውጭ ያሻውን ነገር መግዛት አይችልም። ደላላ ከመግዛትና ከመሸጥ ባለፈም ዋጋ ይተምናል ፤ ያስተምናል። ሻጩም እንዲሸጥ ገዢውም እንዲገዛ ደላላ የመሀል ቤት ዳኛ ይሆናል።
በእኛ አገር ያለው ደላላ ዳኝነቱን ሕጋዊ ዕውቅና ሰጥቶ በሀቅና በፍትሐዊነት ባይሰራም ደላላ በውጭው ዓለም ከሙያ ዘርፎች መካከል አንዱና ዋነኛው በመሆኑ ደንበኛው የሚፈልገውን ምርት ወይም አገልግሎት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በተፈጠረው ምቹ ሁኔታም የተራራቁ ግን ደግሞ ተፈላላጊዎችን ይገናኛሉ።
በሰለጠነው ዓለም የሰለጠኑ ደላሎች የሰዎችን ድካም ከማቅለል ባለፈ የመሸጥ የመለወጥ ሥራን በቀለጠፈ መንገድ በማከናወን ቀልጣፋና ወቅታዊ አገልግሎት ይሰጣሉ። በእኛ አገር ያሉት ደላሎች ደግሞ ከቀልጣፋ አገልግሎታቸው ይልቅ ቅጥፈታቸው ያይላልና በሰላ ምላሳቸው ያለውን እንደሌለ፤ የሌለውን ደግሞ በእጃቸው የጨበጡት ያህል ተማምነው ያሳምናሉ።
እርግጥ ነው ብዙዎች በደላሎች አማካኝነት የፈልጉትን አገልግሎት አግኝተው ይሆናል። ነገር ግን ‹‹በደላላ ሰው ተጉላላ›› እንዲሉ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የበዛ እንግልት የደረሰባቸው ለመሆኑ አንድ ሺ አንድ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል።
ፈረስ ያስጋልባል ያሉት ቤት አንድ አልጋ የማያዘረጋና የአይጥ ጉሬ ሲሆን፤ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽ በደጃፍህ እያለፈ ንጽህናው ለጉድ እኮ ነው በማለት ማሳመን። በአየር ካርታ ላይ የማይታይ ቤትም ሆነ ቦታ ካርታ አለው በማለት ምሎ መገዘትና ከባለንብረቱ ውጪ ሌላ ዋጋ ተምኖ የአካባቢው ዋጋ ነው በማለት ማሳመን የደላላ ዋነኛ ሥራ ነው። ይሁን እንጂ የማይሆነውን አይሆንም የሌለውንም የለም በማለት በታማኝነትና በቀናነት አገልግሎት የሚሰጡ ደላሎችም በጣት ቢቆጠሩ እንጂ አይታጡም።
በማንኛውም የንግድ መስመር ውስጥ የሚገኘው ደላላ በተለይም በአሁኑ ወቅት ሰው ሰራሽ እየተባለ ለሚንቆለጳጰሰው የዋጋ ንረት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል። ነጋዴውም ደላላ፤ ደላላውም ያው ነጋዴ ነውና እጃቸው ላይ ባለ ምርት ያሻቸውን ዋጋ ለጥፈው ሕዝቡን በፈለጉት መጠን እያማረሩት ይገኛሉ። አሁን አሁንማ በአገር ውስጥ ከሚሰማው ኮሽታ በላይ በውጭው ዓለም ያለውን ግርግር ሁሉ ምክንያት በማድረግ ኑሮውን ያንሩት ጀምረዋል።
አንድ ወር ባስቆጠረው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ምክንያት ስግብግብ ነጋዴም በለው ደላላ ከጦርነቱ አስቀድሞ በእጁ በያዘው ዕቃ ላይ ያሻውን ዋጋ ጨምሮ የዋጋ ንረቱን በማባባስ ሕዝቡን አስጨንቀው ይይዙታል። ምንም አማራጭ የሚሆን ምርጫ የሌለው ሕዝብም ሕገወጥ ነጋዴውም ሆነ ደላላው ያደረገውን ይሆናል።
እርግጥ ነው ዓለም አንድ መንደር ናትና የአንዱ ሰላም ማጣት ሌላውን ሊያተኩሰው የግድ ነው። ነገር ግን ሁሉም ነገር በራሱ ሚዛን ካልተመዘነ የሚያስከትለው አደጋ ከባድ ነውና ደላሎች አሻሽጠው ከሚያገኙት የገንዘብ ቁጥር በላይ ማሕበረሰቡን ቢያስቡ መልካም ነው። የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለመሸጥና ለማሻሻጥ የጎላ ሚና ያላቸው እነዚህ ደላሎች ታዲያ ምንም አይነት እሴት ባልጨመሩበት ምርት ከፍተኛ ተጠቃሚ ሲሆኑ መመልከት የተለመደ ነው።
ይሁንና እንዲህ አይነቱን የንግድ ሥርዓት በሕግ አግባብ ሥርዓት ማስያዝ እንዲቻል መንግሥት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም ችግሩ ዛሬም ድረስ ተባብሶ ቀጥሏል። ስለሆነም ረጅም የሆነውን የግብይት ሰንሰለት በማሳጠር በቀጥታ አምራቹንና ሸማቹን የማገናኘት ሥራ መሥራት ለነገ የሚተው ሳይሆን ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጊዜ አሁን ነው።
የችርቻሮ ንግድን ጨምሮ ጅምላ አከፋፋይና አስመጪውም ጭምር ንግዱን እያቀላጠፈ ያለው ያው በደላላ ነው። በእያንዳንዱ የንግድ እንቅስቃሴ ሂደት የደላላው ሚና የጎላ ድርሻም ጉርሻም አለውና ማንኛውም ምርት ሸማቹ ጋር ሲደርስ ከሸማቹ የመክፈል አቅም በላይ ሆኖ ሕዝቡን እያማረረ ይገኛል። የደሃ ሽሮ ሳትቀር በደላላ እጅ መግባቷ አግራሞትን ከመጫር አልፎ ደላላ በደሃ ጉሮሮ ላይ የሚቆመው እስከ መቼ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። የደላላ ነገር ዘንድሮ ከጥያቄም አልፎ ነፍጥ ሳያስነሳ አይቀርምና ቢታሰብበት መልካም ነው።
ሕዝቡ ኮሶ የመጠጣት ያህል የመረረውን የኑሮ ውድነት የማር ያህል ማጣፈጥ ባይቻል እንኳ ማረጋጋት እንዲቻል ዛሬ መሬት የነካ ነገር መሥራት የግድ ነው። መሽቶ በነጋ ቁጥር እየተባባሰ ለመጣው የዋጋ ግሽበት በሕገወጥና በስግብግብ ነጋዴዎች እንዲሁም በደላሎች ምክንያት ነው ከማለት ባለፈ ህገወጥ ንግዱንም ሆነ ደላላውን ሕግና ሥርዓት ማስያዝ ለመንግሥት ለምን ተሳነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
ሕዝቡ በማያባራ የኑሮ ውድነት ውስጥ እየዳከረ ባለበት በዚህ ጊዜ የሚሰማው ሁሉ ሰበብና ምክንያት ብቻ ነው። ምክንያት መደርደር ደግሞ ከችግር አያወጣም። የችግሩ ስፋትና ጥልቀት መኖሩ እስከማይቻልበት ጥግ አድርሶታልና ሕዝብ ዛሬ ምክንያት ሳይሆን መፍትሔን አጥብቆ ይሻልና የመፍትሔ አካላት ከወዴት ናችሁ ይላል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በከፍተኛ መጠን የእህል አምራችና ላኪ የሆኑት ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ላይ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ከተሸከመችው ችግር የገዘፈው ችግር ተጋርጦባታል። ስለዚህ በሰፊው ማሰብ ያስፈልጋል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያነሳሉ። በጦርነቱ ምክንያት በዓለም የሚፈጠረው የምግብ እጥረትና የዋጋ መወደድ ኢትዮጵያንም በእጅጉ ያሳስባታልና በተለይም የዋጋ መወደድን ከግምት ያስገባ መፍትሔ ማፈላለግና መዘጋጀት ካሁኑ የሚጠበቅ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
እርግጥ ነው መንግሥት በደላላ እንዲሁም በህገወጥና ስግብግብ ነጋዴ አማካኝነት የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በሚል በተለያየ ጊዜ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል። በሚወስዳቸው እርምጃዎችም ከፍተኛ የወጪ ጫና ውስጥ እንደሚገባና የበጀት ጉድለት የሚያጋጥመው መሆኑም ይታመናል። ለአብነትም ዘይት ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ በመፍቀዱ ያጣቸው ቢሊዮን ብሮችን እንዲሁም ሌሎችን መጥቀስ ይቻል ይሆናል ነገር ግን መንግሥትም ከገንዘቡ ሳይሆን ሕዝቡም የዘይት ጥሙ ሳይረካ ዛሬም ድረስ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል።
ይህ ሁኔታም በዚሁ ከቀጠለ መንግሥት የበጀት ጉድለቱ ሰፍቶ ማጣፊያው እንዳያጥረው ያሰጋልና ከመቼውም ጊዜ በበለጠኑ ወቅት አማራጮችን በመጠቀም መፍትሔውን መሻት ከመንግሥት የሚጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ ሲሆን፤ በተለይም የተዝረከረከውን የንግድ ሥርዓት መልክ በማስያዝ በደላላ እየተጉላላ ያለውን ሕዝብ ሊታደገው ይገባል በማለት አበቃን!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 27 /2014