በርካታ ተመልካቾች ያሉት የአውሮፓ ቻምፒዮንስሊግ ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ታቅዷል። ከዋንጫው ጋር ዝነኛው አውሮፓዊ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋችና አሰልጣኝ እንደሚመጣም ታውቋል።
በዓለም ዙሪያ ተወዳጅና በርካታ ተመልካቾችን ያፈሩት የአውሮፓ እግር ኳስ ውድድሮች በኢትዮጵያም ከፍተኛ አትኩሮትን ማግኘት ችሏል። የአህጉሩ ትልቁ ዋንጫ የሆነውና ታላላቅ ክለቦች የሚዋደቁለት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ደግሞ በእግር ኳስ ቤተሰቡ ዘንድ ተጠባቂ ከሆኑት መካከል ነው። ዋንጫው በተለያዩ የዓለም ሃገራት እየተዘዋወረ የሚጎበኝ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም ከመዳረሻዎቹ የአፍሪካ ሃገራት መካከል አንዷ ናት። በመሆኑም በመጪው ሚያዚያ 02 ቀን 2014 ዓ.ም ባለ ትልቅ ጆሮው ዋንጫ በአዲስ አበባ ለስፖርት ቤተሰቡ እይታ የሚቀርብና ፎቶ የመነሳት መርሀ ግብር እንደሚዘጋጅ ሃይንከን ኢትዮጵያ፣ በውጪ ግንኙነትና ሰስቴኔብሊቲ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ በሻህ በኩል አስታውቋል።
ከዋንጫው ባሻገር ከአውሮፓ የቀድሞ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ክላረንስ ሴዶርፍ በአዲስ አበባ የአንድ ቀን ቆይታ የሚኖረው መሆኑም ታውቋል። በተዘጋጀው መርሃ ግብር መሰረት በሸራተን አዲስ ሆቴል እና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከአድናቂዎቹ ጋር በቅርበት የሚገናኝበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ተጫዋቹ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በሚኖረው ቆይታም ከኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን ጋር ጨዋታ ያደርጋል። ይኸውም የሚሆነው የመጀመሪያውን ግማሽ የጨዋታ ሰዓት ከአንደኛው ቡድን ጋር ቀሪውን ደግሞ ከሁለተኛው ቡድን ጋር በመጫወት ነው።
አቶ ፍቃዱ በመግለጫቸው፤ ተቋማቸው ብሄራዊ ቡድኑን ከማገዝ ጀምሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲያድግ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ ወጣት ተጫዋቾች እንዲነቃቁና ምሳሌ የሚሆናቸው የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት አርዓያ እንዲሆናቸው የማድረግ ስራ ይከናወናል። ተጫዋቹ ከወጣት ቡድኑ ጋር በሚያደርገው ጨዋታም የቡድኑ አባላት ተነሳሽነትና በእርሱ መንገድ እንዲቀረጹ ይረዳቸዋል። የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫው በመላው ዓለም በሚያደርገው ጉዞ 31 ሃገራትን ያዳርሳል። በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታም የእግር ኳስ አፍቃሪው አስደሳች ጊዜ እንደሚያሳልፍ አመላክተዋል።
ድርጅታቸውም መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪያን የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫንና የጨዋታውን ኮከብ በቅርበት የማየትና የማግኘት ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል። ዋንጫውን የማስጎብኘቱ መርሃ ግብር የ13 ዓመታት ታሪክ ያለው ሲሆን፤ በአፍሪካ፣ እስያ እንዲሁም ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ አህጉራት በሚገኙ የተለያዩ ሃገራት ይዞራል። የዘንድሮው ጉዞም ‹‹ውዳሴ ለሁሉም የኳስ አፍቃሪያን፤ ውዳሴ ለኳስ ተጠባቢያን›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ዋንጫው በአፍሪካ አራት ሃገራት ቆይታ ሲኖረው በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮን ኪንሻሳ፣ በሞዛምቢክ ማፑቶ፣ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ እንዲሁም ናይጄሪያ ሌጎስ እና አቡጃ ከተማዎች ላይ ለእይታ ይቀርባል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ፤ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ከማሳደግ ከፌዴሬሽኑ ጋር በአጋርነት ከሚሰሩት አካላት መካከል ሃይንከን ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኑን ጠቁመዋል። የተጫዋቹ መምጣትም በተለይ በወጣቶች ዘንድ ትልቅ የሆነ መነቃቃትን ይፈጥራል። በመሆኑም የእግር ኳስ ቤተሰቡ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዲገኝ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ሆላንዳዊው የቀድሞ የእግር ኳስ ኮከብ ሴዶርፍ ከተጫዋችነቱ ባለፈ በአሰልጣኝነትም ይታወቃል። ተጫዋቹ በሪያል ማድሪድ፣ ኢንተርሚላን እና ኤሲሚላን ክለቦች በተለይ የሚታወቅ ሲሆን፤ በሁለቱ ክለቦች ሶስት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን አንስቷል። የቻምፒዮንስ ሊጉ ምርጥ የመሃል ሜዳ ተጫዋችነት ክብርንም አግኝቷል።
በዚህ መልኩ የአውሮፓ እግር ኳስ ከዋክብትን ወደ ኢትዮጵያ ሲያስመጣ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አለመሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በዚህ መርሃ ግብር ብራዚላዊው የባርሴሎና ኮከብ ተጫዋች ሮናልዲኒሆ ጎቹ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከአድናቂዎቹ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም መገናኘቱ የሚታወስ ነው። በሪያል ማድሪድ እና በቼልሲ ክለቦች የሚታወቀው የቀድሞ የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ክላውድ ማካሌሌም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታን ከደጋፊዎች ጋር መመልከቱ የሚታወስ ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014