ኢትዮጵያዊ ትህትና፣ አክብሮት፣ ኩራትና ፍቅርን የተጎናጸፉ መልከ ቀና ሰው ናቸው። ስብዕናቸውም ቢሆን ከጥንቱ ኢትዮጵያዊ የባህል ቱባ የተመዘዘ ለመሆኑ ነገረ ሥራቸው ሁሉ ይመሰክራል። ከደንበኞቻቸውና ከሠራተኞቻቸው ጋር ያላቸው ቀረቤታም እንዲሁ ቤተሰባዊ የሆነ ጥብቅ ትስስር ያለው ለመሆኑ በነበረኝ ቆይታ መገንዘብ ችያለሁ። ልጆች መልካም ስብዕናን ይዘው ለማደጋቸው ትልቅ ድርሻ ካለው ቤተሰብ ፍቅርን፣ መልካምነትን፣ አክብሮትንና ለሌሎች መትረፍን በብዙ ተምረዋል። ለትውልድ የሚተርፍ መልካም ሥራን መሥራት የሰብዓዊነት ጥግ ስለመሆኑም ኖረውት አድገዋል።
በመልካም ስብዕና ለማደጋቸው ቀዳሚ ተምሳሌት ቤተሰቦቻቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። በተለይም ከወላጅ እናታቸው የወረሱት መልካምነት ፍሬ አፍርቶ ዛሬ በብዙ እጥፍ እየመነዘሩት እንደሆነ የሚነግሩን የዕለቱ እንግዳችን በጤና፣ በትምህርትና በምግብ ኢንዱስትሪ ተሰማርተው ትርጉም ያለው ሥራ እየሠሩ ለብዙዎች በርካታ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ባለሀብት ናቸው – አቶ ዳዊት ኃይሉ። በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ ለገጠሟቸው ደንቃራዎች እጅ ሳይሰጡ ለስኬት በቅተዋል። ታዲያ ስኬት ማለት ለእርሳቸው ሰዎች ያቀዱትን ማንኛውንም ነገር ለሚገጥማቸው እንቅፋት ሳይበገሩ ማሳካት መቻል ነው ብለው ያምናሉ።
ወላጅ እናታቸው በሕይወት ባይኖሩም በልጆቻቸው ላይ የዘሩት መልካም ፍሬ ግን በእጥፍ ያፈራ ስለመሆኑ የሚናገሩት የዕለቱ እንግዳችን አቶ ዳዊት ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ መሀል ፒያሳ ላይ ነው። የአካውንቲንግና የሶሾሎጂ ትምህርታቸውን ተከታትለው በአሁኑ ወቅት በንግዱ ዘርፍ ተሰማርተዋል። አሁን ላይ በጤና፣ በትምህርትና በምግብ ዘርፍ ሦስት ድርጅቶችን ቢመሩም መነሻቸው የባህል አልባሳት መሸጥ እንደነበር አጫውተውናል።
በተማሩት ትምህርትም ሆነ በሌላ ተቀጥረው ያልሠሩት አቶ ዳዊት፤ ከሠርጋቸው በተረፈ ገንዘብ በቀዳሚነት በባለቤታቸው ስም ውዳሴ የባህል ዕቃዎች መሸጫን ከፍተው ነበር። ወደ ንግዱ የገቡበት አጋጣሚም ሠርጋቸውን እጅግ መጠነኛ በሆነ ድግስ በቀበሌ አዳራሽ ውስጥ ከማድረጋቸው ባለፈ የመጠነኛ ድግሱ ወጪም ቢሆን በዘመድ አዝማድ መሸፈን በመቻሉ ወደ ንግዱ እንዲገቡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ባገኙት አጋጣሚ የባሕል ዕቃዎች መሸጫን ከአንድ ወደ ሁለት ከሁለት ወደ ሦስት ቅርንጫፍ በማሳደግ፣ በማምረትና ወደ ውጭ በመላክ በዘርፉ ውጤታማ መሆን ችለዋል።
ተጨማሪ ሥራን ሲያስቡ ታዲያ በወቅቱ በጤናው ዘርፍ ያለውን ክፍተት በማጥናት የሲቲ ስካን አገልግሎት በአገሪቱ አለመኖሩን በመገንዘብ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከልን አቋቋሙ። ቀጥለውም ቢሾፍቱ ከተማ ላይ ከኬጂ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውና አንድ ሺ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለው ጆርጎ ትምህርትን ከፍተዋል። ጆርጎ የቅድመ አያታቸው ስም መሆኑን እና የኦሮሚኛ ቃል እንደሆነ የገለጹት አቶ ዳዊት፤ ትርጉሙም ትልቅ ፍሬው የከበደው ዛፍ ማለት ነው። ስለዚህ እነርሱም እንደ ጆርጎ ዛፍ ፍሬያቸው በዝቶ ለሌሎች ጥላ ለአገር መከታ ለመሆን ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ትምህርት ቤቱን ጆርጎ አካዳሚ ብለው እንደሰየሙ አጫውተውናል።
በተጨማሪም ቴክኖሎጂ ላይ የሚሠራ ፍቱን ከቴክኖሎጂ እንዲሁም የሕክምና መሣሪያዎችን የሚያቀርብ ኤልስ ሜድ የተባለ ድርጅትን በመክፈት የንግድ ሥራቸውን ማቀላጠፍ የቻሉት አቶ ዳዊት፤ አሁን ደግሞ በምግብ ኢንዱስትሪው በስፋት እየታወቁ መጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት በስፋት እየታወቁበት ያለው አኮ ቡና ሲሆን ‹‹አኮ ›› የወላጅ እናታቸው መጠሪያ ስም ነው። አኮ ቡናም ወላጅ እናታቸውን ይበልጥ የሚያስታውሱበት እንደሆነ ይናገራሉ። አኮ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ ምግቦችን በጥራት የሚያቀርብና በተለያዩ አካባቢዎች ሦስት ቅርንጫፎች ያሉት በቅርቡም አራተኛውን ቅርንጫፍ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ሲሆኑ በእህት ኩባንያዎቻቸው በጠቅላላ አንድ ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
በሕይወት ጉዟቸው ሁሉ ውጤታማ የመሆናቸው ምስጢር ከወላጅ እናታቸው የተገኘ ስለመሆኑ ሲናገሩ እናታቸው የብዙዎች እናት አልባሽና አጉራሽም ነበሩ። ይህን መልካምነት እየተመለከቱ ያደጉት አቶ ዳዊት፤ ዛሬ የእናታቸውን ፈለግ መከተል አላዳገታቸውምና በሚያስተዳድሯቸው ድርጅቶች ሁሉ የወላጅ እናታቸውን መርሆ በመከተል እንግዳ ተቀባይ ሆነው ደንበኞችን እንደየፍላጎታቸው ያስተናግዳሉ።
‹‹አኮ የልጅ ልጆቿ ሲመጡ የማይሆን ነገር አታቀርብም፤ ምርጥ የተባለውን ሁሉ ታቀርባለች›› የሚሉት አቶ ዳዊት እርሳቸውም ለደንበኞቻቸው የማይሆን ነገር እንደማያቀርቡ እና ደንበኞች አኮ ቡና ገብተው ምንም የሚያጡት ነገር እንደሌለም ይናገራሉ። አገልግሎታቸው ለ24 ሰዓታት የሚቋረጥ አይደለም ለዚህም ወላጅ እናታቸው በሕይወት በነበሩ ጊዜ እርሳቸው ጋር ገብቶ ሳይበላ ሳይጠጣ የሚወጣ ሰው እንደሌለና ምግብ ባይበላ እንኳ እንግዳ ሆነው የገቡ ሴቶች ሽቶ ተቀብቶ ይመለሱ እንደነበርም ለአብነት አንስተዋል።
የተጀመረ ነገር ፍጻሜ እንዲኖረው እናታቸው የሚመክሩትን ምክር ሁሌም በማስታወስና ተግባር ላይ ለማዋል ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ ‹‹ልጆቼ አንድን ነገር ከመጀመር ይልቅ መፈጸም መልካም ነውና የጀመራችሁትን ነገር ፈጽሙት›› የሚለውን ንግግር በድርጅታቸው ግርግዳ ላይ ከፍ አድርገው አስቀምጠዋል። ከንግግራቸው ባለፈም ሙሉ የቤተሰቡን አባላት የያዘው ፎቶግራፍ አይን የሚይዝ ቦታ ላይ መሰቀሉም አኮ ቡናን ለየት ያደርገዋል።
አኮ ቡና ውስጥ ታዲያ እናታቸው የሚታወሱባቸው በርካታ ድርጊቶችና ምስሎች መኖራቸው በዋናነት ለማስታወስ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዳዊት፤ ከሌሎቹ ድርጅቶች በተለየ አኮ ቡና የወላጅ እናታቸውን መልካም ባህሪና ማንነት ሊያንጸባርቅ የመጣ ድርጅት እንደሆነም ይናገራሉ። በአኮ መሶብ ውስጥ ምንም የሚታጣ ነገር አልነበረምና ፍራፍሬን ጨምሮ ዳቦ፣ ጭኮ፣ ቆሪና ሌሎችም ባህላዊ ምግቦች ሁሌም አሉ። ይህን መነሻ በማድረግም በአኮ ቡና ባህላዊ የሆኑ ምግቦችን ጨምሮ የጾምና የፍስክ፣ ቡና በዓይነት በዓይነቱ፣ ጣፋጭ ኬኮችና የተሟላ የምግብ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ድርጅት ነው።
ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው አኮ ቡና ቅርንጫፍ ሲከፈት ለሰዎች በጎ ነገሮችን እያስተማረ መሆኑን አቶ ዳዊት ይናገራሉ። ሁለተኛው ቅርንጫፍ ሲከፈት ድርጅቱን የመረቁት የመቄዶንያ ሰዎች ሲሆኑ በፕሮግራሙም አረጋውያኑን በአክብሮትና በትህትና ዝቅ በማለት እግራቸውን አጥበውና ስመው ተቀብለዋል። ቀጥለውም አረጋውያኑን ጋቢ አልብሰው ምግብ በጋራ በልተው የአረጋውያኑን ምርቃት ተቀብለው ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆነ ባህል ድርጅቱን መርቀው ከፍተዋል።
ይህ ለድርጅቱ ትልቅ ትርጉም አለው የሚሉት አቶ ዳዊት፤ ከዚያም ባለፈ እንግዳ ተቀባይነት የኢትዮጵያውያን መገለጫ በመሆኑ ነው። እግር ማጠብ ትህትና በመሆኑ ትህትና የሌለው ሥራ ደግሞ ውጤታማ አይሆንም። ስለዚህ የአረጋውያኑን እግር በማጠብ የትህትናን ጥግ እግር በመሳም ደግሞ የፍቅርን ጥግ ማሳየት በመቻላቸው ልጆቻቸውን ጨምሮ ለሠራተኞቻቸውም አርአያ መሆን ችለዋል።
ሦስተኛውን አኮ ቡና በከፈቱበት ወቅት ደግሞ 150 የሚደርሱ ማየት የተሳናቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ከየአቅጣጫው በማሰባሰብ የምሳ ግብዣ በማድረግ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዳዊት፤ ማየት የተሳናቸውን የመረጡበት ምክንያትም ከማኅበረሰቡ የተገፉና የተረሱ በመሆናቸው ለማስታወስ ነው ይላሉ። ሌላው ቀርቶ እነሱን መጋበዝ ቀላል ሥራ እንዳልሆነና ለእነሱ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ እንደሚገባ ለማስታወስ ጭምር መሆኑን ይናገራሉ።
ቤት መመረቅ እርዳታ መሰብሰቢያ መሆን የለበት የሚል ዕምነት ያላቸው በመሆኑ ከተለመደው የሆቴል ምርቃት ወጣ በማለት በረከትና ምርቃት ከሚገኝባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ኢትዮጵያዊ በሆነ ባህል መገናኘቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር ልምድ በማድረጋቸው ተጠቃሚ እንደሆኑና ሥራቸው እንደሚባረክም ያምናሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሲሆን ለአብነትም በውዳሴ ዲያጎንስቲክ ማዕከል በየዓመቱ ጳጉሜ ከአምስት እስከ ስድስት ቀናት ነፃ ሲቲ ስካንን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ማናቸውንም ሕክምና ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል አመቻችተዋል። በማንኛውም ጊዜም የመክፈል አቅም ለሌላቸው ሰዎች ነፃ አገልግሎት ይሰጣሉ። በአጠቃላይ በ12 ዓመት የሕክምና ጉዟቸውም 50 ሺ ለሚደርሱ አቅመ ደካሞች የነፃ አገልግሎት ሰጥተዋል።
ሁሉም እህት ድርጅቶች እርስ በእርስ ተደጋግፈው የሚጓዙ ስለመሆናቸው ያነሱት አቶ ዳዊት፤ ድርጅቶቹ የተሟላ አገልግሎት ምክንያታዊ በሆነ ዋጋ ያቀርባሉ። የሚሰጧቸው አገልግሎቶችም ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በመላበስ በፍጹም ትህትናና አክብሮት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሳቸውም ከቤተሰብ የወረሱት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ጨምሮ ባለቤታቸው ትልቅ ድርሻ ያላቸው መሆኑን በማንሳት በዋናነት ግን ‹‹እኔ ማነኝ የተፈጠርኩለት ዓላማ ምንድነው ›› ብለው እራሳቸውን ጠይቀው ለጥያቄያቸውም መልስ በመሻታቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
‹‹ገንዘብ ያላቸውና ካፒታላቸውን ማሳደግ የቻሉ ሁሉ ስኬታማ ናቸው ማለት አይቻልም። ስኬት ማለት ሰዎች የተፈጠሩለትን ዓላማ ፈልገው ሲያገኙ፣ ሲያሳኩና ለዚያ ዓላማም መኖር ሲችሉ ነው›› የሚሉት አቶ ዳዊት፤ በተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ሁሉ ውጤታማ ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ልክ ስኬታማነታቸው የሚለካ እንደሆነና ሥራቸው ፍሬ አፍርቶ ለሌሎች መትረፍ ሲችሉ እንዲሁም ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለአገርና ለወገን መከታ መሆን እያሳኩት ያለ የተፈጠሩበት ዓላማ እንደሆነ ይናገራሉ።
በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ከአስር ዓመት በላይ የተጓዙት አቶ ዳዊት በጉዟቸው ሁሉ የተለያዩ መሰናክሎች ይገጥሟቸው እንደነበር፣ አሁንም ችግሮች እንዳሉና ወደፊትም ሊገጥማቸው የሚችል እንደሆነ በማመን ነገር ግን ማንኛውንም ችግር በጥረት ማለፍ ይቻላል ይላሉ። በቀጣይም የሚገጥማቸውን ፈተናዎች ሁሉ በመቋቋም በተለይም ድርጅቶቻቸውን በማጠናከርና ሌሎች ቅርንጫፎችን በመክፈት ተደራሽነታቸውን የማስፋት ዕቅድ አላቸው።
ጆርጎ አካዳሚንም እንዲሁ የማስፋፋት ዕቅድ ያላቸው ሲሆን የውዳሴ ዲያጎንስቲክ ማዕከል አገልግሎትን በክልል ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ጅማ ከተማን ቀዳሚ በማድረግ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሲሆን በፈረንጆቹ 2025 ለአራት ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም አቅደው እየሠሩ ነው።
‹‹ወጣቱ በህልምና በራዕይ መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል›› የሚሉት አቶ ዳዊት፤ ህልም ዓይን ተጨፍኖ የሚታይና ሥራ የማይፈልግ በመሆኑ ወጣቶች ሥራ የሚፈልገውን ራዕይ ዕውን ማድረግ እንዲችሉ ዓይናቸውን ገልጠው ማሰብ፣ ማሰላሰልና ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ይመክራሉ። እኛም አስተማሪ ታሪክ ካላቸው እንግዳችን ወጣቶች ብዙ እንደሚያተርፉ በማመን ከህልም ዓለም በመውጣት ባለራዕይ እንሁን በማለት አበቃን ሰላም!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014