የቤቱ አባወራ ትጉህና ጠንካራ አባት ነው። ቤተሰቦቹን ለማኖር ቤቱን በወጉ ይመራል፤ ሚስቱን አክባሪ ልጆቹን ወዳድ ስለመሆኑም አገር ጎረቤት ይመሰክራል። አመታትን የዘለቀበት ትዳር ለበርካቶች ምሳሌና አርአያ እንደሆነ ዘልቋል።
ከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ። አቶ ሲሳይ ዲዳና ከትዳር አጋሩ ስምንት ልጆችን አፍርቷል። ተግባቢና ቅን አሳቢ ነው። ባለቤቱን ጨምሮ ለሚያስተዳድረው በርከት ያሉ ቤተሰብ ሌት ተቀን ይለፋል። . ሲሳይ የመንግስት ሰራተኛ እንደመሆኑ ተቀጥሮ አመታትን ባገለገለበት የመንገድ ስራ ከባልደረቦቹ ጋር ተግባብቶ በመስራት ይታወቃል።
መልካም ምግባሩን የሚያውቁ ሁሉ ስለእሱ ያላቸው ምስክርነት ከአክብሮት ጋር ነው። የመስሪያ ቤቱ አለቆች በሲሳይ ጉብዝና ይተማመናሉ ። ሁሌም ጠንከር ያለ ስራን ከኃላፊነት ጋር ያስረክቡታል ። ብርቱው ባለሙያ ለስራ ካሉት ቀልድ አያውቅም። ግዳጁን በታላቅ ውጤት አጠናቆ ለቀጣዩ ተግባር ይዘጋጃል። አቶ ሲሳይ ጥርሱን በነቀለበት ሙያው ታምቶ አያውቅም ። ለስራው ተገዢና ሟች ነው ።
አንዳንዴ አቶ ሲሳይ ከዋና መስሪያ ቤቱ የሚያርቅ ስራ ያጋጥመዋል። ይህ አይነቱ የመስክ ቆይታ ቀናትና ሳምንታትን አልያም ወራትን ሊፈጅ ይችላል። በእንዲህ አይነቱ ግዴታ ስራውን በብቃት የሚወጣው ሲሳይ ከስራው መልስ ከኃላፊዎቹ አድናቆትን ይቸራል፡፤
የሲሳይ አለቆች ሁሌም በጠንካራው ሰራተኛቸው ብቃት ይተማመናሉ። እንዲህ መሆኑ ሲሳይን ወደተለያዩ ወረዳዎች ያመላልሰዋል። ትዕዛዝ አክባሪው ሰው ለተሰማራበት የመንገድ ስራ ሁሌም ዝግጁ እንደሆነ ነው። በየደረሰበት የተጠቃሚውን ችግር ለመፍታት ከልቡ ይተጋል። ይህ ትጋቱ ሁሌም በውጤት ያሳጅበዋል፡፤ በመልካምነት ያስጠራዋል።
የመንገድ ባለሙያው ክረምት ከበጋ በማይቋረጥ ግንባታ ላይ ይሰማራል። እሱ በሚሳተፍባቸው የገጠር አካባቢዎች ከፍተኛ ድልድዮችና የመንገድ ግንባታዎች ይሰራሉ። እሱ ችግር አለባቸው በተባሉ ስፍራዎች አስቀድሞ ይገኛል ። ለሲሳይ የአናጺነትና የግንበኝነት ፣ ሙያዎች ከእጁ የራቁ አይደሉም። አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ተገኝቶ ስራውን ይመራል፣ይቆጣጠራል። አንዳንዴ በእጁ ያለውን ስራ ትቶ ወደሌላ ቦታ እንዲሄድ ይገደዳል። ለመስሪያ ቤቱ ወሳኝና አስፈላጊ ነውና በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ተከፍቶ አያውቅም። የተሰጠውን ሊፈጽም ፣በቀና ልቦና ወደተባለው ቦታ ይሄዳል።
የሲሳይ ቤተሰቦች የስራ ባህርይውን ጠንቅቅው ያውቃሉ። ወደ መስክ ሲወጣ በወጉ ይሸኑታል። ሲመለስ ጠብቀው በደስታ ይቀበሉታል። ባለቤቷን የምታከብረው ወይዘሮ የአባወራዋን በሰላም ወጥቶ መግባት ትመኛለች። በስስት የሚያዩት ስምንት ልጆችም ስለአባታቸው የተለየ ቦታ አላቸው። አባታቸው ለእነሱ አባት ብቻ አይደለም። የጓደኛ ያህል ነው ። በተለየ ፍቅር ይቀርባቸዋል።
ሲሳይ ወደመስክ በወጣ ጊዜ የእጅ ስልኩ አያርፍም። ለቤተሰቦቹ ይደውላል። ለባለቤቱ ሁኔታውን ያስረዳል። ለአለቆቹ ስለስራው ሪፖርት ያደርጋል። ሚስቱና ልጆቹ ከመነሻው ጀምሮ እስከሚያርፍበት ድረስ ደህንነቱን ያረጋግጣሉ። ለእነሱ በሰላም መድረሱ እፎይታቸው ነው።
አንዳንዴ አቶ ሲሳይ የሚሄድበት ስራ ሊያቆይ፣ሊያከርመው ይችላል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ሆቴል ከማረፍ ቤት መከራየትን ይመርጣል። ቆይቶ በሚሰራበት አካባቢ ከምግብ ቤቶች ከፍሎ ይመገባል። ስራውን ሲጨርስም ወደመጣበት ይመለሳል። የስራ ባህርይው ሆኖ የመንገድ ግንባታው ከሌሎች ጋር ያገናኘዋል። ከስራ ባልደረቦቹ፣ከአካባቢው ነዋሪና ከሌሎች ጋር በሰላም ውሎ መለያየት ልማዱ ነው።
ሲሳይን የሚቀርቡት ስለመልካምነቱ ተናግረው አይጨርሱም። የዋህና ቅን መሆኑን፣ ለብቻው መብላት፣ መዝናናት ያለመውደዱን ይመሰክራሉ። ታታሪው አባወራ ከመስክ ስራ መልስ ደከመኝን አያውቅም። ሚስትና ልጆቹን ለማስደሰት ከቤት ደርሶ የቻለውን ያደርጋል። ይህ ልማዱ ለመላው ቤተሰብ አይረሴ ትዝታ ነው።
ሲሳይ ለጎረቤቶቹና ለአካባቢው ነዋሪ ታዛዥና ቅን አሳቢ ነው። በታቻለው ሁሉ ከሁሉም ጋር በሰላም መኖርን ይሻል። ይህን ባህርይ የሚያውቁለት ስለእሱ ከበሬታና ፍቅር አላቸው። ትዳሩን አክባሪ ቤተሰቡን ወዳድ በመሆኑ ለብዙዎች መልካም ምሳሌ ሆኖ ይጠቀሳል።
ታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓም…
ሲሳይ በማለዳ ከቤት የወጣበት ስራው ላይ አርፍዷል ። ከመስሪያ ቤቱ ደርሶ የዕለት ግዴታውን ሲወጣም ውሏል። ከምሳ በኋላ በነበረው ጊዜ ከቅርብ አለቆቹ የስራ ትዕዛዝ ደረሰው። እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ለታታሪው ሰራተኛ አዲስ አይደለም። የተሰጠው ስራ ከቢሮው ተቀምጦ የሚሰራው አይደለም። ከቆይታ በኋላ በሚጓዝበት ወረዳ ጊዜያትን ፈጅቶ የሚቆይበት ስራ እንዳለ ከቀናት በፊት ተነግሮታል።
ሲሳይ የስራ ስምሪቱን እንዳወቀ የሚጓዝበት መኪና ተመደበለት። ለወጪው የሚያስፈልገው ውሎ አበል፣ ለስራው የሚያግዙት ቁሳቁሶችና ሌሎችም ዝግጁ ሆኑለት። ለስራው ጓዙን የሸከፈበት አካባቢ ከመኖሪያው ይርቃል። ለስራ ትዕዛዝ የተቀበለበት የአዲዮ ወረዳና ነዋሪው በክረምረቱ ቆይታ በመንገድ ጉዳይ ሲቸገር ቆይቷል። ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ ለመስጠት ከተመረጡት ባለሙያዎች አንዱ አቶ ሲሳይ ሆኗል።
አባወራው ከቤቱ ደርሶ ስለሚሄድበት ስራ ከቤተሰቡ አወጋ። ጊዜ በሚፈጀው የመንገድ ስራ መመለስ የሚታሰብ አይደለም። ለዚህ መፍትሄ ስራው እስኪጠናቀቅ በከተማው ቤት ይከራያል። ከቆይታ በኋላ ሻንጣውን ይዞ ሚስትና ልጆቹን ተሰናብቶ ከቤት ወጣ። ሁሉም በፍቅር ዓይን እያዩ ከደጅ ወጥተው ተሰናበቱት።
ከቀኑ አስር ሰአት ሲሆን ባለሙያዎቹን የጫነው የመስሪያ ቤቱ መኪና ግቢውን ለቆ ወጣ። ሰራተኞቹ ቦንጋንና አካባቢውን ርቀው ኪሎ ሜትሮችን ተሻገሩ። ሁሉም በየድርሻቸው የተመደቡበት የሙያ ዘርፍ ተሰጥቷቸዋል። ሲሳይ ከመስሪያ ቤቱ የጀመረው የማስፋፊያ ስራ ቢኖርም አንገብጋቢ ነው ወደተባለው ቦታ ሊሄድ ግድ ብሏል።
አቶ ሲሳይ በጉዞ ላይ ሳለ የእጅ ስልኩን አነሳ። ለባለቤቱ መንገድ መጀመሩን አሳውቆ ጥቂት አወራት። የትዳር አጋሩ በቸር ደርሶ እንዲመጣ ተመኘችለት። ከታሰበው ለመድረሰ የመኪና ፍጥነት ቀጥሏል። መንገዱ ወጣ ገባ የገጠር ጎዳና ነው። ለስራ የሚሄድበት ኦዲዮ ወረዳ ደግሞ ከዚህ የባሰ ውጣውረድ ይቆየዋል። በሀሳብ እየተብሰለሰለ መነሻውን ወደ ኋላ ትቶ ወደፊት ተጓዘ።
ሰአቱ ለዓይን መያዝ እንደጀመረ የመኪናው ተጓዦች ካሰቡት ወረዳ ደረሱ። አቶ ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች ሻንጣቸውን አውርደው ማደሪያቸውን አሰቡ። ሲሳይ ለስራ እንደሚዘልቅ በማወቁ የኪራይ ቤት አዘጋጅቷል። ጓዙን ይዞ ወደማረፊያው አቀና። ቤቱ ደርሶ ጥቂት ከማረፉ የእጅ ስልኩ አቃጨለ። የቤተሰቡ ጥሪ ነው ።
በሰላም መግባቱን ጠየቁት። ሁሉም ሰላም መሆኑንና ነገ ስራውን እንደሚጀምር አሳወቃቸው። ከቤተሰቡ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎችን ተቀበለ። ሁሉንም በምስጋና አሰናብቶ ሞባይሉን ተጫነና ሰአቱን ተመለከተ። ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ከሰላሳ ይላል። ወደከተማ ዘልቆ እራት መብላትና ጓደኞቹን ማግኘት እንዳለበት አሰበ። ጊዜ አልፈጀም። ከእጁ ያለውን አስቀምጦ ጃኬቱን ደረበና ወደባልንጀሮቹ መገኛ አመራ።
ጊዜው እየመሸ ነው። ሲሳይ ለአካባቢው አዲስ ቢሆንም እንግድነት አልተሰማውም። ባልንጀሮቹ ያሉበትን ሆቴል ነግረውታል። ጥቂት ተራምዶ እነሱ ካሉበት ደረሰ። ጠረጴዛ ከበው ተቀምጠዋል። ሰላም አላቸውና ወንበር ስቦ እነሱን መሰለ። ሁሉም የአንድ ድርጅት ባልደረቦች ናቸው። ሲገናኙ ጨዋታው ደራ። ስለስራ ፣እያነሱ፣ ስለህይወት እያወጉ ቆዩ።
ከምሽቱ አንድ ሰአት ከሰላሳ ከማለቱ የሲሳይ የእጅ ስልክ አቃጨለ። ሴት ልጁ ነች። ስለመንገዱ ጠየቀችው ። በሰላም መግባቱን መለሰላት። ጥቂት ቆይቶ ከሚጠጣው እንዲጨመር ታዘዘ ። ባልንጀሮቹ እየተጫወቱ ከመጠጡ ደጋገሙ። ሲሳይ የጓደኞቹን ሂሳብ ለመዝጋት ፈልጓል። በኪሱ ያለውን ሂሰብ አሰበው። ሙሉን ወጪ የሚሸፍን አይደለም። ቤት ደርሶ አሟልቶ ለመክፈልና እራቱን ጭምር ለመብላት ፈለገ። ይህን ለማድረግ ተመልሶ ከተከራየው ቤት መሄድ አለበት።
ሲሳይ ቤት ገብቶ ያሰበውን ይዞ ሲመለስ ከምሽቱ ሁለት ሰአት አልፎ ነበር። ገንዘብ ተቀባይዋ ዘንድ ደርሶ ሂሳቡን ዘጋና ወንበር ስቦ ተቀመጠ ። የቤቱ ባለቤት በክፉ ዓይኖቹ አተኩሮ እያየው ነው። ጸጉረ ልውጥ መሆኑና ተመልሶ መምጣቱ የተመቸው አይመስልም። ሰውዬው እንግዳውን በግልምጫ እያነሳ ወደ ገንዘብ ተቀባይዋ ተጠግቶ ስለ ማንነቱ ጠየቃት።
ገንዘብ ተቀባይዋ ሂሳብ ለመዝጋት ተመልሶ መምጣቱንና አሁንም እየተስተናገደ መሆኑን ተረጋግታ መለሰችለት። የሆቴሉ ባለቤት የሲሳይን ድርጊት በበጎ አላየውም። እንደተናደደ እጁን ጨብጦ ከፊት ለፊቱ ተገተረ። ሲሳይ ሁኔታው ቢያስደንቀው ምክንያቱን ለመጠየቅ ሞከረ። ሰውዬው ለምላሹ ጊዜ አልነበረውም። ዓይኑን አፍጥጦ፣ ጥርሱን አግጥጦ አንገቱን ለማነቅ ተንደረደረ ። አንዳች ትንፍሽ ያላለው እንግዳው ሲሳይ የእጁን ብርጭቆ አስቀምጦ ወደውጭ ለመውጣት ተነሳ። ይህን ያስተዋለው የሰውዬው የቅርብ ጓደኛ ከወደጓሮ ብቅ ብሎ እንዳይንቀሳቀስ አገደው። ሌሎች ሁለት ሰዎች ተጨምረውም ራሱን እንዳይከላከል እጆቹን አጥብቀው ያዙ።
ሲሳይ ወጥቶ ከመሄዱ በፊት ድንገት በተነሳው አለመግባባትና ግጭት የቤቱ ሁኔታ ተረበሸ ። ገላጋይ መሳዮቹ ሰዎች ሲሳይን እያንገላቱ ለቤቱ ባለቤት አሳልፈው ሰጡት። ግርግር፣ ጩኸትና ወከባው አየለ። በዚህ መሀል ሲሳይ በአንዳች ነገር ጀርባው ጠልቆ ሲወጋ ተሰማው። ስቃዩን ችሎ ራሱን ለማስለቀቅ ታገለ። ብዙ አልቆየም ። በቀኝ ጭንቅላቱ በኩል ተመሳሳይ ጥቃት ሲያርፍበት ራሱን ስቶ ተዘረረ።
ታህሳስ 5 ቀን 2010 ዓም…
ማለዳ ከዕንቅልፏ የተነሳችው ወይዘሮ እንደወትሮዋ የዕለት ስራዋን ልትከውን ጥድፊያውን ይዛለች። በዚህ ሰዓት ከቤት ወደየጉዳዮቻቸው ለመውጣት ለሚዘጋጁ ልጆቿ ቁርስ ለማድረሰ ትባትላለች። በሌሊት ልብሷ ነች። ድንገት በሩን ከፍታ ወደውጭ አስተዋለች። አካባቢው ባልተለመደ ሁኔታ በሰዎች ተጨናንቋል። በሁሉም ፊት ላይ ሀዘንና ጭንቀት እየተነበበ መሆኑ ቢገባት ክፉኛ ደነገጠች ። በቦታው ምን እንደተፈጠረ እስክታውቅ እግሯቿ ብርክ ያዛቸው። የምታያቸው ሁሉ ወደእሷ ቤት እየተመለከቱ ነው። ውስጧ በፍርሀት ራደ፣ተንቀጠቀጠች።
ተመልሳ ወደቤት ገባችና ሴት ልጇ ለወንድሞቿ እንድትደውል አጣደፈቻት። ልጅቷ ቀድማ ለአባቷ ደወለች። ስልኩ አይመልስም። እየተጣደፈች አንደኛው ወንድሟ ዘንድ ደወለችና የሚያውቁት ነገር እንዳለ ጠየቀች። በቂ ምላሽ አላገኘችም። ቤት የነበረው ወንድሟ ከሌላው ወንድሙ ጋር በስልክ እያወራ ከቤት ወጣ። ክፉኛ ተረብሸዋል።
የአባቱ መስመር ባለመስራቱ የተጨነቀው ወጣት ድንገት ከአንድ ሰው የደረሰው የስልክ መልዕክት ይበልጥ አስደንግጦታል። ደዋዩ የአባቱ የስራ ባልደረባ ነው። ለማንም ሳይናገር መስሪያ ቤት እንዲመጣ ነግሮታል። ወጣቱ ሌሎች ሰዎችን አስከትሎ ከተባለው ስፍራ ደረሰ። ለጉዞ የተዘጋጁ መኪኖች እነሱንና ጥቂት ባልደረቦችን ይዞ ወደ አዲዮ ወረዳ አቅጣጫ ተፈተለከ ።
የአቶ ሲሳይ ልጆች ካሰቡት ደርሰው አባታቸውን ሊያገኙ ቸኩለዋል። በድንገት መጠራታቸው ብዙ እያሳሰባቸው ነው። ሲሳይ ለስራ ከወጣ ገና አንደኛ ቀኑ ነው። ከማንም እንደማይጋጭ፣ እንደማይጣላ ያውቃሉ። ምንአልባት ትንሽ አሞት ሊሆን ይችላል። ታዲያ ስልኩ ለምን አይሰራም?ለምንስ አላወራቸውም ? ክፉኛ ተጨንቀዋል።
በአዲዮ ወረዳ – ከፖሊስ ጋር
ከቦንጋ የተነሳው የድርጅቱ መኪና አዲዮ ወረዳ ሲደርስ የአካባቢው ፖሊሶች ተቀበሏቸው። ልጆቹና አብረዋቸው ያሉት ፊትና ኋላ ሆነው ፖሊሶቹን ተከተሉ። ሁሉም በቅርብ ርቀት በርከት ያሉ ሰዎች መኖራቸውን አስተውለዋል። ፡የልጆቹ ዓይኖች እነሱን አሻግሮ ሌላውን ተመለከተ። አባታቸው ከአንድ ቦይ ላይ በጀርባው ተንጋሎ ወድቋል ። እየተጣደፉ አጠገቡ ደረሱ። ደግመው ፣ደጋግመው አዩት፣አላያቸውም። እየጮሁ፣እያለቀሱ ወዘወዙት፣ ጠሩት ፤አልሰማቸውም።
ትናንትና ምሽት..
ለሆቴሉ ባለቤት አግዘው ሲሳይን ለጥቃት የሰጡት ሰዎች ለአገሩ እንግዳ የሆነውን ሰው ተባብረው በስለት ወግተውታል። ሁኔታውን ያስተዋሉ ጥቂቶች ለመገላገል ዕድል አላገኙም። ህይወቱ ማለፉን የተረዱት ግለሰቦች በድኑን ከስፍራው ለማሸሽ የአካባቢው መብራት ዕንቅፋት ሆኗቸዋል። አስከሬኑንም ለሰአታት በኮሪደሩ አቆይተው ከመንገድ ለመጣል በመስማማት እንዳሰቡት አድርገዋል።
ሌቱ ነግቶ ጸሀይ መውጣት ስትጀምር በከተማው የታየው እውነት ብዘዎችን አስደነገጠ። ለነዋሪው በስለት ተወግቶ ከጎዳና የተጣለውን ሰው መለየት ቀለል አልሆነም። እንግዳው የመንገድ ሰራተኛ ህይወቱን የተነጠቀው ከተከራየበት ቤት ለአንድም ቀን ሳያድርና የመጣበትን ሥራ በወጉ ሳይጀምር ነበር ።
የአካባቢው የጸጥታ አካላት የሟችን ማንነትና የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለማወቅ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ተጠርጣሪዎቹን በህግ ቁጥጥር ስር አዋሏቸው። የወረዳው መርማሪ ፖሊሰ ረዳት ሳጂን በላቸው በዛብህ የሁለቱን ሰዎች ቃል ለመቀበል ከፊታቸው ቀረበ። ተጠርጣሪዎቹ የፈጸሙትን የነፍስ ግድያ ወንጀል አልካዱም። ለስራ ጉዳይ በወረዳው የተገኘውን የመንገድ ስራ ባለሙያ ተባብረው በግፍ መግደላቸውን አመኑ። መርማሪው ቃላቸውን በበቂ ማስረጃዎች አስደግፎ ለቀጣዩ የክስ ሂደት መዝገቡን ለዓቃቤህግ አስተላለፈ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2014