51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በሐዋሳ ስቴድየም እየተካሄደ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ይዟል። ቻምፒዮናው ነገ በተለያዩ ርቀቶች በሚካሄዱ የፍጻሜ ውድድሮች ይጠናቀቃል። በቻምፒዮናው የመጀመሪያ ሁለት ቀናት ስድስት አዳዲስ ክብረወሰኖች መሰበራቸው በቀጣይ ቀናት ውድድሮችም በርካታ ክብረወሰኖች እንደሚሻሻሉ ተስፋ የሰጠ ቢሆንም እስከ ትናንት በተካሄዱ ውድድሮች አንድ ተጨማሪ ክብረወሰን ብቻ ነው መሻሻል የቻለው።
በቻምፒዮናው ሦስተኛ ቀን ውሎ ከአስር አመት በኋላ የወንዶች ዲስከስ ውርወራ ክብረወሰን ተሻሽሏል። በ2004 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በመከላከያው አትሌት ምትኩ ጥላሁን 44.33 ሜትር ተይዞ የቆየው የኢትዮጵያ ክብረወሰን ዘንድሮ በሲዳማ ቡናው አትሌት ማሙሽ ታዬ ተሻሽሏል። አትሌቱ ክብረወሰኑን ያስመዘገበውም 45.09 ሜትር በመወርወር ነው። በዚህ ውድድር አትሌት ገበየሁ በእየሱስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 43.77 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ሆኖ ያጠነቀቀበትን ውጤት ሲያስመዘግብ አብዲሳ ገመቹ ከአዳማ ከተማ 42.85 ሜትር በመወርወር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።
ምንም ክብረወሰን ባልተመዘገበበት የቻምፒዮናው አራተኛ ቀን ውሎ ትናንት የተወሰኑ የፍጻሜ ፉክክሮችን ተካሂደዋል። በተለይም በሦስት ሺ ሜትር መሰናክል በሁለቱም ጾታ የተካሄዱ ውድድሮች ትልቅ ትኩረት ያገኙ ሲሆን የርቀቱ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኖችም ተለይተውበታል። በዚህም በሴቶች አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው ከመከላከያ በ09፡41.79 የርቀቱ ቻምፒዮን ስትሆን በወንዶች ሳሙኤል ፍሬው ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ በ08:22:48 የኢትዮጵያ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል።
በሴቶች መካከል የተካሄደውን ውድድር መቅደስ አበበ ከአማራ ክልል 09:43:72 በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ስታጠልቅ፣ የሲዳማ ቡናዋ ዘርፌ ወንድማገኝ በ09:44:85 የነሐስ ሜዳሊያውን የግሏ አድርጋለች። በተመሳሳይ በወንዶች ቻምፒዮኑን ተከትሎ በመግባት ኃይለማርያም አማረ ከፌዴራል ማረሚያ 08፡24.53 ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ታደሰ ታከለ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 08፡26.01 ሦስተኛ በመሆን አጠናቋል።
ጥሩ ፉክክር እየተስተናገደባቸው በሚገኙት የሜዳ ተግባራት ፉክክሮች ርዝመት ዝላይ በወንዶች ትናንት ፍጻሜ ሲያገኝ፣ ኡመድ ኡኩኛ ከሲዳማ ቡና 7.47 ሜትር በመዝለል አሸናፊ ሆኗል። ድሪባ ግርማ ከመከላከያ 7.33 ሜትር በመዝለል ሁለተኛ ሲሆን በቀለ ጅሎ ከኦሮሚያ ክልል 7.29 ሜትር ዘሎ ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል። የከፍታ ዝላይ የወንዶች ውድድርም በጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ አትሌት አበራ አለሙ አሸናፊነት ተፈጽሟል። አትሌቱ ቻምፒዮን የሆነው 4.10 ሜትር ከፍታ በመዝለል ነው። 4:00 ሜትር ከፍታ የዘለለው የመከላከያ አትሌት ሳምሶን በሻ ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ አበበ አይናለም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ 3.90 ከፍታ በመዝለል ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።
በቻምፒዮናው ሦስተኛ ቀን ውሎ ከትናንት በስቲያ ፍጻሜ ካገኙ ውድድሮች አንዱ በሆነው የሴቶች ምርኩዝ ዝላይ ውድድር የጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ አትሌቶች የወርቅና የብር ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል። የነሐስ ሜዳሊያውን ማሸነፍ የቻለ አትሌት በሌለበት በዚህ ውድድር ሲፈን ሰለሞን 2.10 ሜትር ከፍታ በመዝለል የወርቁን ሜዳሊያ ስታሸንፍ ሜቲ ቤኩማ 2.00 ሜትር ከፍታ ዘላ የብሩን ሜዳሊያ ወስዳለች።
በተመሳሳይ የሴቶች ርዝመት ዝላይ ውድድር ኪሩ ኢማን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 5.75 ሜትር በመዝለል ስታሸንፍ፣ ማሬዋፒዶ ከመከላከያ በ5.68 ሜትር ተከታዩን ደረጃ ይዛ ፈጽማለች። አርያት ዴቪድ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ 5.68 ሜትር ሦስተኛ ሆናለች።
በ110 ሜትር መሰናክል ወንዶች ማረሰ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 14.06 ሰዓት የርቀቱ የ2014 ዓ. ም ቻምፒዮን ሲሆን ኬሪዮን ሞርቴ ከኦሮሚያ ክልል 14.43 ሰዓት፣ ሮድ ቾል ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ በ14.76 ሰዓት ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በቻምፒዮናው ያለፉት አራት ቀናት ውሎዎች እንደወትሮው በርካታ ውድድሮችን ማሸነፍ ያልቻሉት ኦሮሚያ ክልልና መከላከያ በመቶ ሜትር ሴቶች መሰናክል ውድድር ሁሉንም ሜዳሊያዎች አሸንፈዋል።
በተለይም ኦሮሚያ ክልል ውድድሩን 14.08 ሰዓት ቀዳሚ ሆና ባጠናቀቀችው ሂርጰ ድርባ የወርቅ ሜዳሊያውን ሲወስድ የብር ሜዳሊያውንም 14:17 በሆነ ሰዓት ባጠናቀቀችው አለሚቱ አሰፋ አማካኝነት የግሉ ማድረግ ችሏል። ቀሪውን የነሐስ ሜዳሊያም ምህረት አሻሞ 14.28 በሆነ ሰዓት አጠናቃ ለመከላከያ አስመዝግባለች።
ቻምፒዮናው ነገ የሚጠናቀቅ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ከማለዳ ጀምሮ በሁለቱም ጾታ የሚካሄዱ የሃያ ኪሎ ሜትር ርምጃ ውድድሮችን ጨምሮ በርካታ የሜዳ ተግባራትና አጭር ርቀት የፍጻሜ ፉክክሮችን እንደሚያስተናግድ ከወጣው መርሃግብር መረዳት ተችሏል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2014 ዓ.ም