ወንዝ ተሻግሮ፣ ሀገር ቆርጦ፣ ከሩቅ ተጉዞ የሚመጣ የመርዶ መልዕክተኛ ብዙውን ጊዜ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ነው የሚደርሰው። ይህ ጥንት የነበረ ዛሬም ያለ ነው። «እንዲያው ናፍቃችሁኝ ከረማችሁና…»እያለ በድንገተኛ እንግድነቱ የተደናገጡትን ዘመዶች «በእንዴት ሰነበታችሁ» የሚያረጋጋው ያ መልዕክተኛ የመርዶ አደራውን እንደጠበቀ ሲጫወት ያመሻል።
«ለመሆኑ እነአባዬ ፣ እነእምዬ ደኅና ናቸው?» እየተባለ ይጠየቃል። እርሱም «አዎን ደኅና ናቸው» ይላል። አንዳንዴም የሞተው ላይ ሲደርስ ከአንደበቱ ደንቀፍቀፍ እያለ በሆዱ ያምቀዋል። እንዲህ በጥያቄ ልቡ ሲወልቅ ሞትን በሕይወት እየለበጠ፣ እውነትን በሐሰት እየለወጠ ያድርና በማግስቱ ጎሕ ከመቅደዱ በፊት ብድግ ብሎ የኅልፈት ደውሉን ያሰማል። የሟችን ስም እየጠቀሰ ለቅሶውን ራሱ ይጀምረዋል። እነዚያ አሉ የተባሉት በአንድ ጀምበር ሞተው ይገኛሉ።
«አቶ እንቶኔ፣ እመት እገሊት አርፈዋል» ብሎ መግለጽ የሚከብደው ያ መርዶ ነጋሪ እንዲህ በዜማ እያቆነጀ ለቅሶውን ሲነዛው ብዙውን ጊዜ ስሞቹን የሚጠቅሰው በመጀመሪያው የእዬዬ ምዕራፍ አይደለምና ማን እንደሞተ ለማወቅ የሚሹት ተረጂዎች በእጅጉ ነው የሚጨነቁት። «ማነው የሞተው ንገረንና እንወቀው እንጂ» እየተባለ በእጅጉ ሲወተወት ነው አርጂው በዜማ የሟችን ስም የሚጠራው። ከዚህያም ወዲያ ተቀባይና ተቀባባይ እየበረከተ ዋይታው ይበረታል።
አንዳንድ መርዶ ነጋሪ ደግሞ ማታ እንደ ምንም ሲቀለማምድ ያመሽና አልያም ከጭንቀቱ ለመዳን መኝታ ፈልጎ ሌላ ቦታ ያድርና ገና ሰማይና ምድር ሳይለቅ በማለዳ ይመጣና እንዴት እንደሚያረዳቸው ቃሉም እንጉርጉሮውም ይጠፋዋል። ታዲያ እንዲህ ካሉቱ አንዱ ብልኃቱ ቢቸግረው «አያ እንዴት ከረምክ… አያ እንዴት ከረምክ…» እያለ በለቅሶ ያዜም ገባ ይባላል። «ሙት እንዴት ከረምህ» ተብሎ ጤንነቱ መጠየቁ ቢገርምም! የለቅሶ ነገር እንደ ሀገሩ፣ እንደ አህጉሩ፣ እንደ ዕድሩ የተለየ መልክ አለው። ብዙ ጊዜ የተጻፈበትን፣ የተተቸበትን ሥርዓተ ለቅሶ አቆይተን በሀገራችን የሚስተዋለውን የመርዶ ወግ ጠለቅ ብለን ለመመርመር ብንቃጣ ከማዘን በቀር የምንጨምረው አይኖር። ነገር ግን አሳዛኙ መርዶው ራሱ ሳይሆን ወጉና ሥርዓቱ ነው።
«ለመሆኑ ሞት አዲስ ነው ወይ? መቼና የት ተጀመረ?» በመሠረቱ ልደት እንዳለ ሁሉ ሞትም ይኖራል። ሕይወት እንደመኖሩም ኅልፈት አለ። ይህን መሻር አይቻልም። ከተፈጥሯዊ ሕግጋት አንድ ተብሎ የሚቆጠር ነው። «ከቶ አይቀርም ሞቱ ምንም ቢታከቱ» ይባላል። ሰው ቁም ስቅል እንዳያይ በቁሙ በደዌና በድህነት እንዳይማቅቅና እንዳይወዳድቅ ይጣጣራል እንጂ በዘመነ ሕይወቱ አበሳ እንዳይቆጥር፣ ፍዳ እንዳይዘረዝር ይደክማል እንጅ ሞት አይቀርለትም። «ዙሮ ዙሮ ከቤት… ኖሮ ኖሮ ከመሬት» ይላሉ አበው።
ይሁንና ሰው እሞታለሁ ብሎ የዕለት ተግባሩን ከማከናወን አይታቀብም። ይልቁንም «እከርማለሁ እኖራለሁ» እያለ ነው በስፋት የሚወጥነው። ይህ ትክክል ነው። የሰው ልጅ ተስፋውን ብሩኅ አድርጎ በፍኖተ ሕይወት የሚጓዘው እኖራለሁ በማለት ነው። በእርግጥ ደግሞ የሞትኩ እንደሆነ ልጆቼን ሚስቴን ችግር ውስጥ ከመዝፈቅ ጥቂት ነገር ላቆያቸው ብሎ ሲጥር የሚታይም ሞልቷል። ከአንዳንድ ራስ ወዳድ ደንታ የለሽ በቀር እንዲህ የሚያስቡ ብልኆች አሉ።
ይህንን በምንመለከትበት ጊዜም አንድ ታላቅ ቁም ነገር ይከሰታልናል። ይኸውም ለሞት መሰናዶውም ቢሆን ጥረት ማስፈለጉን ነው የምናየው። ለሀገርና ለወገን አኩሪ ታሪክ ማስፈለጉን ነው የምናየው። ለሀገርና ለወገን አኩሪ ታሪክ ትቶ ለመሞት፣ መልካም ዝና ትቶ ለመሞት፣ ለቤተሰብ የተደላደለ ሕይወት ትቶ ለመሞት ብዙ መሥራት፣ እጅግ መልፋት፣ መጣር፣ መጣጣር እንደሚያሻ መሆኑን ነው የምንገነዘበው። እንዲህ ሲሆንም የሕይወትና ኅልፈትን ተደጋጋፊነት ነው የምንረዳው።
ሞት በርግጥ አዲስ አይደለም። ይህንንም አውቀናል። ዳሩ ግን የዘመድ አዝማድ የወዳጅ ሞት ሲሰማ ከአሁን በፊት ታይቶ እንዳልታወቀ ትኩስ ሥርፀት ይቆጠራል። እንደ ደራሽ ውሃ ያስበረግጋል። አሮጌነቱ ይረሳል። በተለይም ይህ ጽሑፍ ያተኮረበት የመርዶ ነገር አንድ ራሱን የቻለ ጉዳይ ነው።
መቼም ሰው ሆኖ የአባቱንና የእናቱን የእህቱንና የወንድሙን፤የሚስቱንና የባልን፤ የልጆቹንና የዘመዶቹን ሞት በደስታና በሆታ፣ በዕልልታ አይቀበለውም። እንኳን በሥጋ ልደት በጋብቻ ውኅደት የተቆራኘውን፤ የተዛመደውን እንኳን ከልቡ የተወደደውንና የተጎዳኘውን ሰው ሞትና የማያውቀው ግለሰብ በኅልፈተ ሕይወት መሰናበት ያሳዝነዋል። ይህ ሰብዓዊ ባሕርይ በሰውነታቸው በታመኑት ዘንድ የደነደነ ነው።
በሰው ሞት የሚስቅ፣ በኅልፈተ ሕይወት የሚሳለቅ፣ በሰው ጥርኝ አፈርነት የሚፈነድቅ፣ ሰው አለ ሊባል አይቻልም። ሞት በእውነት የሚፈራ መሆን የለበትም። ይህ ስለተባለ ደግሞ የተድላ ብሥራት ነው ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ሞት ያሳዝናል፣ ያስለቅሳል፣ ያስተክዛል። ቢሆንም ለሁሉም ልክ ሊበጅለት የሚያስፈልግ መሆኑን መቀበል ሊገደን አይገባም።
ለምሳሌ ይህ ጽሑፍ ያተኮረበትን ሥርዓተ መርዶ ብንፈትሽና «እርማችሁን አውጡ» ከሚባልበት ከማለዳው ሰዓት እንኳ ብንነሣ ብዙ ብዙ ነው የምንገነዘበው። የተኛ በግድ ተቀስቅሶ፣ የታመመ ካለም በሽታው ታድሶ፣ ሕፃን አዋቂ ሳይባል ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የአካባቢ ነዋሪ በጫጫታና በዋይታ ታምሶ፣ ሠፈሩና መንደሩ በሁከት ተተራምሶ ነው ለቅሶው የሚከናወነው። ይህ አንድ ራሱን የቻለ ድንገተኛ ግርግር ነው የሚመስለው። ቃጠሎ የተነሳ፣ ሽብር የተነዛ ነው የሚመስለው።
የአንድ ሀገር ባህል ወጉ፣ ሥርዓቱ የመሳሰለው እየተመረመረ ከጊዜ ጋር የማይራመደው ተኮንኖ እየወደቀ ይቀራል። ከወቅት የሚዛመደውና ከሥልጣኔ የሚዋኃደው ተመዝኖ እየጸደቀ ይዳብራል። በኢትዮጵያችን የሸመገለውን፣ ሸምግሎም ያልሞተውን ይበልጡንም እያሸተ የተራመደውን የመርዶ ወግ ተንከባክቦ ማቆየቱ ከምን ሊቆጠር ይችል ይሆን?
ይህን ጥያቄ ያነሣሁት እንዲሁ ያለ ምክንያት አይደለም። የመርዶው ወግ ይበልጥ እያደገ ከዱሮው በላቀ ሁኔታ ለእድገቱ ዋስትና እየተሰጠው የሄደ ይመስላል። ከጥንት የመርዶ ሣልሰት በአመዛኙ እንዲህ እንዳልነበር ተረድተናል። ዛሬ ግን እንደቀብር ሣልሰት መርዶው በተነገረ በ3ኛ ቀን የቀጠሮ ለቅሶ ይካሄዳል። ሙሾ አውራጅ አቁመው ደረት እየደበደቡ ሆሆውን የሚነኩት ጥቂት እንዳልሁኑ አይተናል። የሴት ዕድሮች ለትርዒት ጭምር የሚያቀርቡት ድቁስና ሰናፍጭ ሳይቀር ሶስት ቀን ሙሉ ዋናው ዕድር በተከለው ድንኳን አምሮበት ይሰነብታል። የዕድር ነገር ከተነሳ ዘንድም አንድ ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነጥብ አለ። ጥንት በአብዛኞቹ ዕድሮች ያልነበረ ደንብ ዛሬ ወጥቷል። ይኸውም ለመርዶ የሚከፈል ተብሎ ገንዘብ ተተምኖ መገባቱ ነው። ይህ እንግዲህ ለእድገቱ ለብርታቱ የቱን ያህል እንደታሰበለት ነው የሚያመለክተን።
የቀረው ቀርቶ ለአክስትና ለአጎት ጭምር የሚከፍሉ ዕድሮች እንዳሉ ይነገራል። እህቴን፣ ወንድሜን ተረድቼ…የሚሉትማ ሥፍር ቁጥር እንደሌላቸው ነው የሚወራው። እንዴት ተዋልደው ወይም ማ ቢወልድ ማ ተብለው ሲጠየቁ አንዳንድ ዕድሮች የዘመዶቻቸውን ስም ዝርዝር አስታውቀን ብለው ጽፈው በመዝገብ ያስቀመጡ እንዳሉም ተረድተናል። ይሁንና አንድ ሰው በየክፍለ ሀገሩ በየዳር ሀገሩ ያለውንም የሌለውንም ወንድሜ እህቴ እያለ ቢያስመዘግብ እንዴት ብሎ የሚቀናቀነው አይኖርም። ቁጭ ብሎ ያስወለደ የለምና መርዶው ሲመጣ ይከፈለዋል።
ይህን ሁሉ በምናይበት ጊዜ እንግዲህ ዕድሮች የመርዶን ባህል ለማደርጀት ያበረከቱትን ግዙፍ አስተዋፅኦ ለመመስከር የምንቸገር አይመስለኝም። ይህን በዚህ እንለፈውና ወደማለዳው ዋይታ ዘወር ብለን ጥቂት እንመርምረው።
ለመሆኑ አንድ መርዶ ነጋሪ ራሱ እንዲያ ተጨንቆ ሰውን አስጨንቆ በማለዳ ተነሥቶ እገሌ ሞቷል የሚልበት ምክንያት ለምንድን ነው? ከሆነስ ሌላ ሰዓት በረፋዱ፣ በቀትሩ ወይም በምሽት ዋዜማም ቢሆን አይነግረውም? የተጻፈ ደብዳቤ ካለስ ለምን ወደ ሥራው ቦታ ወይም አደባባይ ፈልጎ አልያም አንድ የሆነ ሥፍራ በማንኛውም ጊዜ አይሰጠውም? ለምንድን ነው ሰው ማለዳ የሚያውከው?
የባሕር ማዶ ሰዎች በየትኛውም ጊዜ በማንኛውም ሰዓት ፖስታ ሲቀበሉ፣ ቴሌግራም ተልኮላቸው ወይም ኢሜይል ከፍተው ሲረዱ አይተናል። በስልክ ሲነገራቸውም ሰምተናል። እዚህ በአዲስ አበባችን እንኳ የመልዕክት ሳጥናቸውን ሲከፍቱ «ዜና ዕረፍት» የሚል ደብዳቤ ያገኙና ዓይናቸውን በመሐረም ጠራርገው ወረቀቱን ኪሳቸው ከተው ሲሄዱ አይተናል።
ፀጥታ ሳይነሱ፣ ቀዬ ሳያተራምሱ ረጋ ብለው ከልብ የሚያለቅሱትን አይተናል። ምናልባት በሰው ሀገር ስለሆነ ነው እንዳይባል ደግሞ በዚያው በሀገራቸውም ተመልክተናል። ነገሩም ያው ነው። ያው ፖስተኛ ብቻ እንጅ «አንጥፉ፣ ጎዝጉዙ በማለዳ ጩሁ» የሚል የለም። እንደውም ጩኸት በእጅጉ አስነዋሪ ነው። እንኳን መርዶ መጣብኝ ብሎና ሬሳ ቢወጣም በዚህ ምክንያት የሚታመስ፣ ሠፈር የሚተራመስበት ምክንያት የለም።
ምናልባት ይህን መሳይ ባህል በለመድነው ሀገራዊ ዕድር ገብቶ ሊሠራ አይችልም ብለው የሚሟገቱ እንደ ማይጠፉ እናውቃለን። አንድ የሆነ ሥፍራ «ዘመድህ ሞተ» ተብሎ ለአንዱ ቢነገረው ይደነግጥና በሽታ ላይ ይወድቃል የሚሉም አይታጡም። ነገር ግን ለእነዚህ ሁለት መከራከሪያ ነጥቦች አርኪ ምላሽ ለማግኘት የሚቸግር አይደለም።
በቅድሚያ መቀበል ያለብን አንድ እውነት አለ። ይኸውም ያን ጊዜ ያለፈበትን ወግ፤ ያን ከወቅት የማይታረቅ፤ ያን ሥልጣኔ ባዘመነው ማኅበረሰብ የማይጸድቅ ጎታች ባህል አዝለን ለመኖር ጀርባችን የጠና ሊሆን እንደማይችል መረዳት ይገባናል። ዛሬ ማለዳ ለግንባታ የምንነሳበት እንጂ ማለዳ ለመርዶ፣ ማለዳ ለለቅሶ እያልን ሙሾ የምንቀባበልበትን የዋይታ ፕሮግራም የምንነድፍበት ጊዜ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። የሥራ ክቡርነት የጊዜ ወርቅነት ባልታወቀበት ዘመን የነበረውን ጎታች ወግ ይዘን እንሰልጥን ማለትም አንችልም። የሥልጡን መሳቂያ ከመሆን በቀር!!
«ዘመድህ ሞተ» ተብሎ ሲነገረው ይደነግጣል የሚባለው ግን ጥቂት የሚያሳስብ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ለማለዳው ትርምስ በቂ ምክንያት ሆኖ መቅረብ አይችልም። በመጀመሪያ የተረጂውን የጤና ሁኔታ መመርመር ያሻል። ይህ ከሆነም ቀስ ብሎ በእርጋታ ነው። ወይም ሁለት ወዳጆቹን አማክሮ ቢሮም ይሁን ቤት ሊነገረው ይችላል። ይህም እንደተረጂው ሁናቴ ይለያያል። አንዳንዱ እንዲያውም ጠንካራ ይሆናል። እነዚያ ወግ ጠባቂዎች የግድ ቤቱን በማለዳ እየወረሩበት ቢያስቸግሩት እንጂ እርሱ ራሱ በቀትር ስልክ ተደውሎለት ቢሰማው የሚፈቅድ ሊሆንም ይችላል።
በተረፈ ደግሞ በደብዳቤ ከሆነ እጅግም አያስጨንቅም። ምክንያቱም አንድ ሰው ወረቀት ሲመጣለት ዘወትር ማሰብ ያለበት ደግ ደጉን ብቻ መሆን የለበትም። ሁሌ የሠርግ ጥሪ እንደማይመጣለት ማወቅ ይገባዋል። ሁሌ የተድላ ብሥራት መጠበቅ አይኖርበትም። ሁሌ ልደትን፣ መልካም ሕይወትን ብቻ ማሰብ የለበትም።
አደጋን፣ ሕመምና ኅልፈትን ጨምሮ ማሰብ የግድ ነው። ሰው የሚደነግጠው በሕልሙም በውኑም ያላሰበው ነገር ሲደርስበት ነው። በአመዛኙ እንዲያ ነው። ሞት ደግሞ ከትውልድ አብሮ የኖረ የማይቀሩበትም ስለሆነ ይህን ከማለዳው አውቆ መሰናዳት ብቻ ነው የሚጠቅመው። ደግሞም አንድ ነገር አለ። ፈረንጅ እንዲያ መንፈሱን ጠንከር አድርጎ ማዘን ከቻለ የእኛ ከእርሱ እንዴት ያንሳል?
በመሠረቱ እንዲያውም ማዘን አለማዘን በሚለው ሀሳቤ ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን ቀዬ በማለዳ ማበጡም፣ ሆነ ለቅሶ መቀመጡ እንዲሁ ወግ አክባሪነትን ለማሳወቅ እንዲያ ሲልም ከሐሜት ለመዳን ያህል ነው የሚመስለው። ለውዳሴ ከንቱ መደረጉን ነው ብዙ ጊዜ የሚያመለክተው።
ዛሬ በቴክኖሎጂ በገፋው አህጉር የሚገኘው ኅብረተሰብ በየሰዓቱ ማን ልመርምር ምን ልመራመር? ምን ልፍጠር? እያለ ነው የሚሽቀዳደመው። እኛም አቅማችን በፈቀደ መጠን ስንጥር ስንግር እንታያለን። ሆነልንም አልሆነልንም ብዙ እንደክማለን። ብዙ እንለፋለን ረሀብን በሽታን መሐይምነትን ድህነትን ለማጥፋት ነው የምንጥረው። ትግላችን ለዚህ ነው። እንዲህም ሲሆን «ማለዳ ለግንባታ» ካልን ብቻ ነው የትግላችን ውጤት ፍሬያማ የሚሆነው። «ማለዳ ለዋይታ» ከሆነ ግን የምናተርፈው ብዙ ያለ አይመስለኝም። ያንኑ ድህነታችንን ብቻ እንጂ!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 6 /2011
አሸናፊ ዘደቡብ