ጥንታዊ መሠረት ካላቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ ፈረስ ስፖርት ነው። ይህ ስፖርት በርካታ የውድድር ዘርፎች ያሉት ሲሆን፤ እአአ ከ1900 ጀምሮ ከኦሊምፒክ ስፖርቶች መካከል አንዱ ሊሆን ችሏል። ይህ ስፖርት በኢትዮጵያ ከጥንታዊና ባህላዊ ስፖርቶች መካከል ይመደባል። በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች በዓላትን ተንተርሰው ከመካሄዳቸው ባለፈ በኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ዕውቅና ካገኙና ውድድርም ከሚካሄድባቸው ስፖርቶች መካከል አንዱ ነው።
ከዚህ ባሻገር በሌላው ዓለም የሚዘወተረውና ዘመናዊ የሆነው ስፖርት በኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን አማካኝነት ይካሄዳል። በአገሪቷ ከሚገኙ ስምንቱ የስፖርት አሶሴሽኖች መካከል አንዱ የሆነው ፈረስ ስፖርት የተለያዩ ክለቦችን በስሩ ያቅፋል። በተለያዩ ጊዜያት በአሶሴሽኑ አዘጋጅነት በጃንሜዳ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይም ከክለቦቹ ባሻገር ኤምባሲዎችና የውጪ አገራት ዜጎችንም በማሳተፍ ይታወቃል። በርካታ የፈረስ ዝርያዎች ያሏት አገሪቷ ለስፖርቱ ምቹ ሁኔታዎች በስፋት መኖራቸውም በባለሙያዎች ይነሳል።
ኢትዮጵያ በፈረስ ሃብት ከመታደሏ ባለፈ፤ በመጓጓዣነት፣ በጦር እንዲሁም በመዝናኛነት ሰፊ ድርሻ አለው። ይሁንና አገሪቷ እስካሁን ካልተጠቀመችባቸው ሃብቶቿ መካከል አንዱ መሆኑን ተከትሎ እንቅስቃሴውም ከአገር ውስጥ እምብዛም ያልዘለለ ሆኖ ቆይቷል። ከሰሞኑ በአፍሪካ ደረጃ በተካሄደ አንድ ውድድር ግን በስፖርቱ አዲስ ታሪክ እንዲሁም አበረታች የሆነ ተስፋ ታይቷል። በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያ አስተናጋጅ በሆነችበት አህጉር አቀፍ የፈረስ ስፖርት ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያዊው ታዳጊ ለአገሩ ሜዳሊያ ሊያስመዘግብ ችሏል። በውድድሩ ላይ አገሩን ወክሎ የተሳተፈው ብሔራዊ ቡድን ወደ አገሩ ሲመለስም አቀባበል ተደርጎለታል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ ውድድር ከሚካሄድባቸው የሕጻናትና የታዳጊዎች ወጣቶች ዘርፍ ተሳታፊ ስትሆን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ከኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የተገኘው መረጃ ያስረዳል። እድሜቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ 7 ታዳጊዎች በብሔራዊ ቡድኑ ታቅፈው አገራቸውን የወከሉ ሲሆን፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በውድድሩ ተካፋይ ለመሆን አሶሴሽኑ ሲዘጋጅ ቆይቷል። ከመጋቢት 14-16/2014 ዓ.ም በተካሄደው ውድድርም ከ12-14 የዕድሜ ክልል በተካሄደው የመሰናክል ዝላይ ታዳጊው ፈረሰኛ ፈጠነ ተሾመ አሸናፊ በመሆኑ ለአገሩ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል። የቤካ ፈርዳ ክለብ ጋላቢው ፈጠነ በአገር ውስጥ በሚካሄዱ ሻምፒዮናዎች ተሳትፎውም በውጤታማነቱ ይታወቃል።
ውጤቱ ተስፋ ሰጪ በመሆኑም ልዑኩ ወደ አገሩ መመለሱን ተከትሎ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዲሁም የአሶሴሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገዋል። በአቀባበሉም ላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በታሪክ በፈረስ ግልቢያም ሆነ በፈረስ ውጊያ በጦር ሜዳ ብዙ ታሪክ የሠራች በመሆኑ በዚህ ውድድር ታሪክ የተደገመበት ታላቅ ጀብድ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን ውጤታማ የሆኑ የስፖርት ማኅበራትን ወደ ስፖርት ማዕከል ለማስገባት መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራም መጠቆማቸውንም ሚኒስትሩ በድረገጹ አስነብቧል።
የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ቸርነት በበኩላቸው፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ከፈረስ ጋር ወጥተው ተሸንፈው አይመለሱም፤ የጊዜና የቴክኖሎጂ ልዩነት ቢኖርም አባቶቻችን በወጡበት መስክ ሁሉ ከፈረስ ጋር ታሪክ ሠርተው እንደሚመለሱ ይህ አንዱ ማሳያ ነው›› ብለዋል። አምባሳደሩ አክለውም የፈረስ ስፖርት አሶሴሽን በአፍሪካ መድረክ በውጤት መጀመሩ የሚበረታታ ስለሆነ ሁሉም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የመጨረሻ ግብ የአገር ባንዲራ ከፍ አድርጎ ማስጠራት እስከሆነ ድረስ ተግተው ሊሠሩ ይገባል። መንግሥት የተገኘውን ድል መነሻ በማድረግ በሌሎች ውድድሮችም ጠንካራ ሆነው እንዲገኙ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረግጠዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 /2014