ኢትዮጵያና ጀግንነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ልክ እንደ እጅና ጓንት፣… ከዘመን ዘመን ከትውልድ ትውልድ ስማችን በኩራት ሲጠራ ቆይቷል። አርበኝነት ከታሪክነት ባለፈ በእያንዳንዳችን ነፍስ ላይ የበቀለ የኢትዮጵያዊነት አለላ መልክ ነው። ብዙ ትላንትናዎችን የፈጠረ የዘመን ቀለማት። ለዚህ ደግሞ በተለያየ ጊዜ በጠላት ላይ በወሰድነው የበላይነት ያስመዘገብናቸው አኩሪ ብሄራዊ ድሎች ምስክር ናቸው። ከነዚህ እሙን የታሪክ ድርሳን ውስጥ አርበኞቻችን ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ።
የትላንቷ ኢትዮጵያ የዛሬዋም መልካም ምድር በአርበኞቻችን እንባና ደም የተቀለመች ናት። ሲነኳቸው በሚቆጡ፣ ሲደፍሯቸው በህብረት በሚነሱ ጥቁር ህዝቦች የጸናች ናት። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም ከተጻፉ ክቡር ስሞች ውስጥ አርበኛ የሚለው ቃል ቀዳሚው ቃል ነው እላለው። በዘመናት የጥቁሮች ታሪክ ውስጥ ፋና ወጊ ሆኖ ዛሬም ድረስ በክብር ይጠራል። ከአፍሪካ አልፎ በዘመናዊው የአውሮፓ ሥልጣኔ ውስጥ የሃያላኖቹ የእግር እሳት ሆኖ ዛሬም ድረስ አለ። የቆምነው በዚህ ታላቅ እውነት ውስጥ ነው። ኢትዮጵያን ያቆማት ይሄ ስም ነው።
ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ፋና ወጊዎች ሆነን ቀደምት ስልጡን ህዝቦች በመባል የምንጠራው በአገራቸውና በርስታቸው ቀልድ በማያውቁት አባቶቻችን ደምና አጥንት ነው። ከትላንት እስከዛሬ ለአገርና ህዝብ ክብር ሲሉ ራሳቸውን እንደ ሻማ ያቀለጡ በርካታ አባቶች አሉን። ርስቴን አልሰጥም፣ የአገሬን ዳር ድንበር አላስነካም ሲሉ የሞቱ፣ የተንገላቱ ብዙ የአገር ባለውለታ አርበኞች በትላንትና በዛሬ ውስጥ አሉ። እኔና እናንተም የነዚህ ባለውለታ አርበኞቻችን የደም ፍሬ ነን። የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዚህ ልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጎልታና ታፍራ እንድትታይ ያደረጉት እነሱ ናቸው።
በአድዋና በካራማራ፣ በኡጋዴንና በአንባላጌ ታላቅ ገድልን በመፈጸም የማይሞትና የማያረጅ ዘላለማዊ ክብርን የሰጡን ባላደራ ትውልዶች ነበሩን። ቋያ በታጠቁ ጥቁር ክንዶች፣ ጽናት ባነገቱ ህያው ነፍሶች ከባርነት ወጥተናል። ዘመን በማይሽረው የአርበኝነት ተጋድሎ ብዙ የጠላት ወረራዎችን በድል አልፈናል። በአባቶቻችን ደም፣ በአርበኞቻችን አጥንት በዓለም ላይ ታላቋን የነጻነት ምድር ኢትዮጵያን ፈጥረናል።
እኔም እናንተም የአባቶቻችን የድል ፍሬዎች ነን። ክብራችን ሳይጎድል፣ ነጻነታችን ሳይነካ ዳር ድንበራችን ሳይደፈር ከትላንት እስከዛሬ በክብር የምንጠራው ነፍሳቸውን ለአገር በሰጡ አባቶቻችን ሞት ነው እያልኩ ነው። ሁላችንም የሞት ፍሬ ነን። የዛሬው እኛነታችን በዚህ ልክ የተገኘው ሞት በተከፈለበት የዛኛው ትውልድ ጀብድ ነው። በአባቶቻችን ደም የበቀልን በአጥንታቸው የታፈርን የብዙ ተጋድሎ ውጤቶች ነን።
ብዙዎች በሚናፍቁት ማንም በሌለው አገራዊ ታሪክ ውስጥ የምንኖር ሕዝቦች እንዲህም ነን። በታላቅ ክብርና ሞገስ ከትላንት እስከዛሬ ተራምደናል። ለኢትዮጵያ ክብርና ነጻነት ደማቸውን ባፈሰሱ እውነተኛ የሕዝብ ልጆች ከጭቆና ወተን አንገታችንን ቀና አድርገናል። ኢትዮጵያን ተባብረው በገነቧት ጽኑ ክንዶች ታቅፈን ወደ ሚደነቅ ብርሀን ተሸጋግረናል። በአባቶቻችን ብዙ ሞትና መከራ አርነት ወጥተን ስማችንን በታሪክ ድርሳን ላይ ጽፈናል። ክብር ለዛኛው ትውልድ ይሁንና..።
ከእውነት ሁሉ እውነት አገር ናት። አገር የሁላችን ክብር ናት። የደስታችን አጥቢያ የሐዘናችን መድረሻ እንዲህም ናት። ስለ አገር አባቶቻችን ያስተማሩን እውነት ይሄ ነው። ከታላላቆቻችን የሰማነው፣ ከፊተኞቻች ያወቅነው ጥበብ ይህ ነው። በነፍሶቻችን ላይ የአባቶቻችን የአደራ ቃል አለ። ይሄን የአደራ ቃል ይዘን ነው የምንኖረው።
አርበኝነት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለ፣ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደም ውስጥ የሚቀዳ የሉአላዊነት ድንበር ነው። የእያንዳንዳችን ትላንት፣ የእያንዳንዳችን ዛሬና ነገ በአርበኞቻችን ሞት የተገኘ ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እንደ ድርና ማግ ፈትለውና ሸምነው በትውልድ ልብ ውስጥ የቋጩ የዚህኛውም የዚያኛውም አለም ጀብደኛ ነፍሶች ናቸው። በእኚህ ነፍሶች ውስጥ መኖር ለአገርና ህዝብ የሚከፈል የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል። በነዚህ ነፍስ ውስጥ መኖር ራስን ለሌሎች ህልም ገምሶ እንደመስጠት እቆጥረዋለው። በአባቶቻችን ደጋግ ነፍሶች ዛሬ እኔና እናንተ ወልደን ከብደን እድሜ ቆጥረናል። ብርቱ ሕዝብ፣ ስልጡን አገር ተብለን በዓለም አደባባይ ተመስክሮልናል።
ነገ ለሚፈጠረው አዲስ ትውልድ ደግሞ እኔና እናንተ እናስፈልጋለን። በአባቶቻችን ሀቅ እንደኖርን ሁሉ በእኛም ሀቅ የሚኖር ትውልድ ይመጣልና ራሳችንን ለኃላፊነት ማዘጋጀት ይኖርብናል። አባቶቻችን በዚህ ልክ ባይኖሩ ኖሮ አሁን ላይ እኛ በዚህ ልክ አንገኝም ነበር። አባቶቻችን ለእኛ እንዳስፈለጉ ሁሉ እኛንም የሚፈልግ ትውልድ ይመጣልና አስፈላጊ ዜጋዎች ሆነን መቆም የዜግነት ግዴታችን ነው። በአባቶቻችን መኖር ኖረናል። በተስፋቸው ለምልመናል፣ በእውነታቸው ደምቀናል አሁን ሌሎችን ለማኖር የእኛ ተራ ነው።
ተነጋግሮ በመግባባት ለሌሎች የምናስፈልግበት፣ ለሌሎች የምትሆን ምቹ አገር ለመፍጠር የአርበኝነት ሥራ የምንሰራበት ሰዓት ላይ ነን። ዛሬ መልካም ነገር ለመስራት ከቀኖች ሁሉ ትክክለኛው ቀን ነው። በዚህ ቀን ላይ መልካም ስራ በመስራት በእኛ በኩል ለሚመጣው አዲስ ትውልድ ስንቅ ለመሆን መነሳት ይጠበቅብናል። የእኛ ዛሬ በአባቶቻችን የተፈጠረ ነው። የልጆቻችንም ነገ በእኛ መልካም ዛሬ የሚፈጠር ይሆናል። የሀሳባችን መልካም መሆን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን በዙሪያችን ላሉም በረከትና መልካምነትን ነውና ሁሉን ነገር ከሀሳብ እንጀምር። ህልምና ራዕያችን ለሌሎች እንዲጠቅምና እንዲበጅ አድርገን እናዘጋጀው።
አባቶቻችን የኢትዮጵያ የትላንት ብሩህ መልኮች ነበሩ። አርበኞቻችን ለእያንዳንዳችን ደማቅ ዛሬ የሞት ዋጋ የከፈሉ የመልካም ልቦች ባለቤት ነበሩ። ሁላችንም ለሁላችን እናስፈልጋለን። ሁላችንም አስፈላጊዎች ሆነን ነው ወደ ምድር የመጣነው። በአባቶቻችን የአርበኝነት ተጋድሎ ዛሬ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተፈጥረዋል። ነገ ደግሞ በእኔና በእናንተ የአርበኝነት ተጋድሎ የሚፈጠር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ይኖራል።
ከእኛ በኋላም ያለው ትውልድ እርስ በእርሱ የሚደጋገፍ ነው። ደምቀው የተጻፉ ብዙ ትላንትናዎች በእያንዳንዳችን ዛሬ ውስጥ አሉ። ለህይወታችን እጅግ አስፈላጊ ሆነው አጠገባችን የቆሙ ሰዎች ነበሩ። ለመኖራችን ብርታት ሆነው በትላንትና በዛሬአችን ውስጥ የበቀሉ ደጋግ ነፍሶች ስለመኖራቸው አልጠራጠርም። ይሄን እውነት ወደ አገርና ህዝብ ስናመጣው አርበኞቻችንን እናገኛቸዋለን። አርበኞቻችን የእኔና የእናተ የጋራ እውነት ናቸው።
በዓለም አደባባይ ብዙዎች አንገታቸውን ቀና ማድረግ ተስኗቸው አቀርቅረው በሚኖሩበት በዚህ ዘመን ቀና ብለን እንድንራመድ፤ ማነህ ስንባል ኢትዮጵያዊ ነን ብለን በኩራት እንድንናገር ያደረጉን እነሱ ናቸው። በጥቁርነት ውስጥ ዘለዓለማዊ ክብርን፣ ዘለዓለማዊ ነጻነትን ያጎናጸፉን በዛኛው ትውልድ ማህጸን ውስጥ የበቀሉ ዓርበኞቻችን ናቸው። ዛሬ በአገራችን ላይ ጀብድ ለመስራት የእኔና የእናንተ ተራ ነው። ዛሬ የእኔና የእናንተ የድል የተስፋ ቀን ነው። ታሪክ ከማውራት ወጥተን ታሪክ የምንሰራበት ዘመናችን ነው።
እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በብዙ ችግርና መከራ ውስጥ የምትገኝበት ሰዓት ላይ ናት። ከትላንት በባሰ የእኛን አንድነት የእኛን አብሮነት የምትፈልግበት የችግር ጊዜ ላይ ናት። ከውስጥም ከውጪም ጠላቶች ተነስተውባታል። አንድነቷን ህብረቷን ለመሸርሸር የተንኮል ሴራዎችን የሚያሴሩ ግለሰቦች ቡድኖች አገሮች ሳይቀሩ የተነሱበት ጊዜ ነው። እንደ አባቶቻችን ትውልድ የማይረሳውን የጀግንነት ተግባር ፈጽመን ለማለፍ ትክክለኛው ሰዓት ላይ እንገኛለን።
ከእኔነት ወጥተን ለአገራችን ምርጡን ለማድረግ በአንድነት የምንቆምበት የተጋድሎ ጊዜ ላይ ነን። አባቶቻችን በዓድዋ ጣሊያንን፣ በካራማራ ሶማሊያን፣ እንዲሁም በሌሎችም የጦር ግንባር ዘምተው በአርበኝነት በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ ዛሬ ላለችው ኢትዮጵያ ምሳሌ ሆነዋል።
እኛም ነገ ለምትፈጠረው አዲሷ አገርና አዲሱ ትውልድ የሚሆን አኩሪ ስራን የምንሰራበት ጊዜ ላይ ነን። እንደ አባቶቻችን የኢትዮጵያዊያን ደማቅ ቀለሞች ሆነን ስማችንን ከትውልድ አብራክ ውስጥ እንጽፍ ዘንድ ዛሬ የእኛ ቀን ነው። አገራችን በውስጥም በውጪም እዬዬ እያለች ነው። ብዙ እንባዎች፣ ብዙ ዋይታዎች የሚሰሙበት ሰሞን ላይ ነን።
የሕዝቦች በአንድነት መቆም ግድ የሚልበት የጭንቅ ሰዓት ላይ ነን። በፖለቲካው በኢኮኖሚው በማህበራዊው ህይወታችን ውስጥ አገራችን የእኛን አርበኝነት የምትፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። አሁን ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን ምርጡን የምንሰራበት ከሁሉ ምርጥ ወቅት ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያን እወዳለው የሚል ሁሉ ከወሬነት ባለፈ በተግባር የሚፈተንበት ጊዜ ነው።
እኔ የአገሬ ለቅሶ ይሰማኛል። እንድንረዳት በእናታዊ አሳዛኝ አይኖቿ ስታየኝ አያታለው። የአገሬ በአንድነት ተነሱ ድምጽ ይሰማኛል። የኢትዮጵያ ህመም የእያንዳንዳችን ህመም ነው። በመከራዋ ውስጥ መከራችን አለ። ዛሬውኑ እንዳባቶቻችን በአንድነት በመቆም የአገራችንን ችግር እልባት መስጠት ይኖርብናል። አብዛኞቹ ችግሮቻችን አንድነትን ህዝባዊነትን የሚሹ ናቸው። አብዛኞቹ መፍትሄዎች ደግሞ በእኔና በእናንተ እጅ ውስጥ ናቸው። እኔና እናንተ በአንድነት ከቆምን ችግሮቻችን ሁሉ እሳት እንዳየው ቅቤ ቀልጠው እንደሚጠፉ ጥርጥር የለኝም።
የእስካሁኑ ችግሮቻችን በአንድነት ማጣት በመለያየት የመጡ ናቸው። ባለመነጋገር፣ ባለመደማመጥ የተፈጠሩ ናቸው። መለያየታችን የፈጠራቸው ችግሮቻችን ናቸው ዛሬ ላይ በየቦታው መከራ ሆነው የሚያሰቃዩን። አርበኛ ለመባል የግድ ጦር ሜዳ ሄደን መዋጋት አይጠበቅብንም። አርበኛ ለመባል ጦርና ጎራዴ ወይም ደግሞ መሳሪያ መታጠቅ አይኖርብንም። በብዕራችን መልካም ነገር በመጻፍ አርበኛ መሆን እንችላለን። በተግባራችን አስፈላጊዎች በመሆን ታሪክ መስራት እንችላለን። በእያንዳንዱ አገራዊ ችግር ላይ በነቃ ተሳትፎ መፍትሄ በማምጣት የዚህኛው ትውልድ አርበኛ መሆን እንችላለን።
እንደ አገር ለሚነሱብን አፍሪካዊም ሆነ አለም አቀፍ ተቃውሞዎች በአንድነት በመቆም ጀብድ መስራት እንችላለን። በተሰማራንበት የስራ መስክ ላይ አገርና ሕዝብ የሚጠቅም አመርቂ ውጤት በማምጣት አርበኛ መሆን እንችላለን። ጥሩ ነገር በመስራት፣ መልካም ነገር በማሰብ በዙሪያችን ላሉ አስፈላጊዎች ሆነን በመቆም በዚህም አርበኛ መሆን ይቻላል። መልካም ሥራ ለመስራት ከተዘጋጀን ጀብድ ልንሰራባቸው የምንችልባቸው በርካታ አገራዊ ጉዳዮች አሉ። ችግሩ ግን ካበደው ጋር ማበድ፣ ድንጋይ ካነሳው ጋር ድንጋይ ማንሳታችን ነው።
አገራችን በአስተሳሰባችን ውስጥ ናት። ከቆሻሻ አስተሳሰብ ወጥተን ወደ ሚደነቅ ብርሀናዊ እውነት መምጣት ይኖርብናል። አብዛኞቻችን ታሪክ ከመስራት ይልቅ ታሪክ በማውራት የምንኖር ነን። ዛሬ ላይ ታላቅ ነገር ለመስራት ከመሞከር ይልቅ በአክሱምና ላሊበላ እየተደነቅን ስራ ፈተን የምንቀመጥ ብዙዎች ነን። ትልቅ ለመሆን ከመጣር ይልቅ ትልቅ ነበርን ብለን ያለፈን በማውራት ጊዜ የምናጠፋም ነን። ትልቅ ነገር ለመፍጠር ከተዘጋጀን ይቻለናል።
አባቶቻችን ባልዘመነና ባልሰለጠነ ዘመን ነው አለምን ጉድ ያስባለ ታሪክ የሰሩት። እኛም የዛሬዎቹ ትውልድ በብዙ ነገሩ ምቹና ስልጡን በሆነ ዘመን ላይ ነን፤ ለህዝባችንም ሆነ ለአገራችን ታሪክ ለመስራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ምቹ ዘመን ላይ ነን። የአባቶቻችንን ወኔ ለብሰን ላሉብን አገራዊ ችግሮች መፍትሄ በማምጣት፤ የሚያግባቡንና ችግሮቻችንን የሚያራግፉልን ከፍ ያሉ ሃሳቦችን በማመንጨት የዜግነታችንን እንድንወጣ በማሳሰብ ላብቃ። ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 22 /2014