አገሬን እንደ ተማሪ፤
ማነጻጸሪያው ይጥበቅም ይላላ አገሬን የማመሳስላት ከመደበኛ ተማሪ ጋር ነው። ተማሪ ይማራል፤ የተማረው ትምህርት ግቡን ስለመምታቱ ለማረጋገጥም በተርምና በሴሚስተር እየተፈተነ ዕውቀቱ ይረጋገጣል።
አልፎ አልፎም ተማሪው ከተማረው ትምህርት ውጭ የንባብ ጥረቱንና አርቆ ገማችነቱን ለማረጋገጥ ሲፈለግ በትምህርቱ ውስጥ ያልተሸፈኑ አንዳንድ ጠጠር ያሉ ጥያቄዎች ጣል ጣል ይደረጋሉ። ይህ አካሄድ በየትኛውም መምህር ዘንድ የሚተገበር የተለመደ ተግባር ነው። ዓላማው ተማሪውን ለመጥቀም እንጂ ለጉዳት ታስቦ አይደለም።
አገሬም እንዲሁ በዘመናት ውስጥ ስትፈተን የኖረችው በገመተችውና በተለማመደቻቸው ችግሮቿ ብቻ ሳይሆን ባልጠረጠረቻቸው ሰበቦችና መንስዔዎች ጭምር ነበር/ነውም። ለምሳሌ፡- በየዘመናቱ ተላምዳው አብራው የኖረችው ድርቅ “በየምንትስ ዓመታት” ወቅት ጠብቆ በቋሚነት እንደሚከሰት በመንግሥትና በባለሙያዎች እየተነገረንና በችግሩም እየተጠበስን መኖራችን እየታወቀ እነሆ ዛሬም ድረስ ዕንቆቅልሻችንን የሚፈታ “ታዳጊ ኃይል” አጥተን ረሃብና ቸነፈር መዝሙራችን ሆኗል።
እንኳን እኛ “ሰብዓውያን” የምንሰኝ ፍጡሮች ቀርተን አባይ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ አዋሽ፣ ገናሌ፣ ባሮ ወዘተ. እያልን በሽንገላ የምናንቆለጳጵሳቸው ወንዞቻችን አፍ ቢኖራቸው በረሃብተኛነት በምንታወቅበት እንቆቅልሻችን ሳይሳለቁብን የሚቀሩ አይመስለንም። በተለየ ሁኔታ ግን በአርምሞ እየታዘበን እብስ የሚለው የዋቢ ሸበሌ ወንዝና ከአገር ጫፍ እስከ ጫፍ በትዝብት እየገላመጠን የሚያልፈውና በአሸዋ ውስጥ ሰምጦ የሚያንቀላፋው የአዋሽ ወንዝ ተፋሰሶች ግራና ቀኛቸው ለዘመናት በድርቅ እየተንገበገቡ ስለሚያስተውሏቸው የልባችሁን ገልጻችሁ የምር ገስጹን ብንል “ሥራ ጠሎች” ብለው እንደሚንቁን ለመገመት አይከብድም።
የአገሬ ፈተናዋና ችግሯ ከታወቀ ለምን መልሱ ጠፋት? በየአሥር ዓመቱም ይሁን በየአሥራ አምስት ዓመቱ ዙሩን ሳያዛንፍ እየጠበቀ ድርቅ በኢትዮጵያ እንደሚከሰት ትንቢቱን ከሚነግሩን ይልቅ ለምን ፍቺውን ጨምረው አያሳውቁንም? “ሕልሙንም ፍቺውንም አሳውቁኝ” (ትንቢተ ዳንኤል ምዕ. 2)፤ በማለት ጠቢባኑን የሞገተው የባለቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነፆር ለካስ ልክ እንደኛው ግራ ቢገባው ኖሯል። አሥር ዓመት ወይንም አሥራ አምስት ዓመታት ትንቢቱን ከነገሩን ጀምሮ እያንጎላጀጁ ረሃቡንና ቸነፈሩን በጉጉት የሚጠብቁ መንግሥታዊ ተቋማትስ ለምን ለመፍትሔው ሠርተው አላሰሩም? እስከ መቼ ስንዴ ለምነን፣ እስከ መቼስ የድርቅ መርዶ ለማርዳት ዓለም አቀፍ ረጂዎችንና መገናኛ ብዙኃንን በኮንፍረንስ ስም እየሰበሰብን እዬዬ እያልን እናለቅሳለን?
“ሚሊዮኖች ተራቡ፣ ሚሊዮን እንስሳት አለቁ፣ የተፈጥሮ አራዊቶች ተሰደዱ፣ ይሄን ያህል ሰው በረሃብ ምክንያት ተፈናቀለ፣ ድርቁ ሲከፋም ይህንን ያህል ሰው ሞተ ወዘተ.” የሚለው የመከራ አበሳችን መቼ ነው ከላያችን ተንከባሎ የሚወድቀው? መደበኛ ተማሪ የተርምና የሴሚስተር ፈተናዎችን ሳያሰልስ እንደሚፈተን ሁሉ ምክንያቱ በግልጽ እየታወቀ አገሬ እስከ መቼ በድርቅና በረሃብ እየተፈተነችና ለእርዳታ እጆቿን እንደዘረጋች እንድትኖር እንፈርድባታለን? በመሪር ልቅሶ እያነባችስ ዘመኗን በእህህታ እንድትጨርስ ለምን በየንባት? መልስ ባናገኝም እንጠይቃለን። ባንደመጥም እንናገራለን።
አስተያየት ስንሰጥ ከማድመጥ ይልቅ፤ “ቢጮኹና ቢጽፉ ምን ያመጣሉ”፤ እያሉ እንደ ጅል በልባቸው ቢስቁብንም ኅሊናቸውን መሞገታችን አይቀርም። ስህተትን ከማረም ይልቅ በመከላከል ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ሹማምንቶቻችን ቢሰሙን ይበጃቸዋል፤ ካልሰሙም ውጤቱ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም። “ምከረው፣ ምከረው እምቢ ያለ እንደሆነ መከራ ይምከረው” የሚለው ብሂል ለአፍ የሚቀል አባባል ብቻ ሳይሆን ለእውነትነቱ ማረጋገጫ ሊቀርብለት የሚችል የጠቢባን ምክር ጭምር ነው – ከገባቸው።
የአገር ጠሎች አገር፤
አገር ጠል ባለ አገሮች በሚሸርቡት ሴራ ይህቺ መከረኛ አገር እስከ መቼ ቁም ስቅሏን እንዳየች ትኖራለች? የሃሳብ ልዩነቶችን በተረጋጋ ስሜት ተነጋግሮና ተማምኖ ከመተራረም ይልቅ በትንሽ በትልቁ “ሰይፍ ለመማዘዝስ” አዚም የጫነብን ምን የሚሉት ኃይል ነው? አገርን እያዋረዱ ለአገር ተቆርቋሪ መስሎ መታየት፣ አገርን ለማፈራረስ አውታሯን እያናጉ ስለ ሕዝብ ልዕልና መስበክ፤ እኮ ምን የሚሉት ክህደት ነው? እጅግ የሚያሳዝነው ነገር በአገር ላይ እየዶለቱና ክብሯንና ሕዝቧን ዝቅ አድርገው ማዋረዳቸው እየታወቀንና እየታወቃቸው ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት “በእያጎያዊ” ሴራ ራሳቸውን እንደ እስስት እየለዋወጡ የሚኖሩት የአገር ጠል ባለ አገሮች ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ አሳሳቢነቱ የገዘፈ ይመስላል።
እውነቱን አፍርጠን እንምከርበት የሚል ወኔ የሚኖረን ከሆነ ይህቺ መከራ ቀለቧ የሆነው አገር ዛሬም ድረስ እየተፈተነች ያለችው ከባዕዳን ይልቅ “ባለ አገር ነን” በሚሉና ከራሷ ማህጸን በበቀሉ ልጆቿ እንደሆነ በብዙ ማሳያዎች ማመላከት ይቻላል። የምንኮራበትንና የምንኩራራበትን የነበር ታሪኮቻችንን ድርሳናት ለጊዜው ገጻቸውን አጥፈን በማቆየት የዛሬውን ገመናችንን ወደ መፈተሹ ጠንከር ብንል እውነታው ፍንትው ብሎ ሊታየን ይችላል።
አገር ጠል ባለ አገሮች ሁልግዜም የሚሰባሰቡትና ግምባር የሚፈጥሩት የግል ጥቅም መኖሩን ሲያረጋግጡ ነው። በአንደበታቸው ጫፍ የሕዝብን ስም ቢያንጠለጥሉም በልባቸው ሲቀምሙ ውለው የሚያድሩት ግን የክፋት አሲድ ነስንሶ ለማለያየትና ለማናቆር ነው። የሚያጅባቸውን ሠራዊት የሚያሰክሩት፣ ሸንጓቸውን የሚያወፍሩት፣ የሴራ አሸክላቸውን ዘርግተው በአገር አንገት ሸምቀቆውን ለማጥበቅ የሚሞክሩት አገር ታንቃ የምትሞት እየመሰላቸው ነው። አገር ጠል ባለ አገሮች ራሳቸው ሞተው በድናቸው በአፈሯ ውስጥ ይሸሸግ ካልሆነ በስተቀር አገር ሞታ ንፍሮ እየተቃመ በሙሾ የምትቀበር ተሰባሪ ሸክላ እንዳልሆነች እንመሰክራለን።
የእንሽላሊት ባህርይ የተላበሱት እኒህን መሰል አገር ጠል ዜጎች ስለ ማንነታቸው የሚያስመሰክሩት በወረቀት መታወቂያቸው እንጂ ለሕዝብ የሚጠቅም ፍሬ በማዝመራቸው አይደለም።
የእንሽላሊትን ስም ካነሳን አይቀር ስለ ባህርይዋ ጥቂት ነገር መናገሩ ተገቢነት ይኖረዋል። እንሽላሊት መገኛዋ የትም ነው። ከቤተ መቅደስ እስከ ቤተ መንግሥት፣ ከገበሬው ማሳ እስከ ነጋዴው መደብር፣ ከተራ መኖሪያ ቤት እስከ “ባለጠጎች” መንደር፣ ከትምህርት ቤት እስከ ሠራዊት ካምፕ፣ ከሐኪም ቤት እስከ ፍርድ ቤት ወዘተ. ሽው እልም፣ ሽር ብትን እያለች የምትውለው በነፃነት ነው።
የአገር ጠሎች ውሎም እንዲሁ ነው። “ከዙፋን ቤት” እስከ ራስ ቤት፣ ከአደባባይ እስከ ጓዳ፣ ከቤተ መቅደስ እስከ “ቤተ-ፖለቲካ”፣ ከንግድ ዘርፉ እስከ ፍትሕ ሥርዓቱ እግራቸውንና መረባቸውን ዘርግተው በሕዝብ ስም እየማሉ አገርን ለማረድ ካራ ሲስሉ መዋላቸውን የምናስተውለው እለት በእለት ነው።
በመሸንገያ ቃላት መበልጸጋቸው፣ በልባቸው ጽላት ላይ ክፋት ቀርጸው የሕዝብን ስቃይና የአገርን መፈራረስ እየቃዡ መኖራቸው ልዩ ባህርያቸውና መታወቂያቸው ነው።
በሥልጣን ላይ የተቆናጠጡትም ሆኑ በሥልጣን ቅዠት የሚናውዙት በርካቶቹ የአገሬ ፖለቲከኞች፤ አዋዋላቸው እንደ እንሽላሊቷ በሁሉም ስፍራ ሥር ሰደው፤ በሴራ ግብራቸው ደግሞ እንደ ክፉ ኮብራ ለመናደፍ አድፍጠው የሚውሉት የተመቻቹ ሁኔታዎችን በመሰለል ነው። አገር ጠል ሆኖ ስለ አገር በጎነት ለመስበክ የሚሞክሩት በውስጣቸው የሞተው ኅሊናቸው እንዳያንሰራራ አፈር በማልበስ ጭምር መሆኑ ከገባን ሰነባብቷል።
እውነቱን እንመስክር ከተባለ አንዳንዶቹ በረቀቀና በተጠና ስልት፣ ጥቂቶች በየዋህነት እየተነዱ የሚፈጽሟቸውን የአገር ጠልነት ድርጊቶች ከትዝብት አልፈን ብንገላልጠው ብዙ ማለት ብቻ ሳይሆን ብዙ ማስረጃዎችንም ማቅረብ ይቻላል።
እስከ ዛሬ የኖርነው እነዚህ በአገር ላይ መሰሪ ቲያትር የሚከውኑትም ሆኑ የሚቆጣጠራቸው አካል ይሰሙናል ብለን በመገመትና “ልብ ያለው ልብ ያድርግ” በሚል ትዝብት እየገረመምናቸው ነበር። ይህን ማድረጋችን “አካፋን አካፋ” ለማለት ድፍረቱን አጥተን ሳይሆን መንግሥታዊ ሥርዓቱን በጫንቃው ላይ የተሸከመው ባለአደራ ፓርቲ ጆሮ ይሰጠናል ብለን ተስፋ በማድረግና ለጊዜ ጊዜ መስጠቱ የሚያዋጣ ስለመሰለን ነው።
አሁን ግን ብዙው መከራችን በዝቶ “የመኖር ወይንም ያለ መኖር የሞት ጥላ ስላጠላብን” ያመቅነውን ጉዳታችንን በይፋ በመግለጥ መንፈራገጡ ይበጅ መስሎናል። እንደ እውነቱ ከሆነ አገር ጠል ባለ አገሮችን የምንተቸውን ያህል አገር ወዳድ ተብዬ “ካብ አይገቡዎችም” ወደ ሕሊናቸው ተመልሰው ለእውነት እንዲቆሙ መሞገቱ ተገቢ ይመስለናል።
ብዙዎቻችን አገር አለን ብለን፣ የሕዝብ አደራ ግድ ብሎን “ከባእድ ምድር ተድላ ይልቅ የአገርን ጠረን” መርጠን ወደ ምድራችን ተመልስን ዋጋ እየከፈልን ያለነው የግፉዓንን እምባ ያበስን፣ በሰለጠንበት ትምህርት ያገዝን መስሎን ነበር። ነገሮች ሁሉ ወደ አልተፈለጉ አቅጣጫዎች ሲሄዱ እያስተዋልንም ተረጋግተን የቆምነው ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል የሚል ጽኑ ተስፋ በመሰነቅ ነበር።
ይህ ተስፋ እየበነነና እየተነነ አገር ጠሎች የጀግና ክብር ተሰጥቷቸው ሲታመኑ አገሬ ብለው ዋጋ እየከፈሉ ያሉት ሩቅ አላሚዎች ሲገፉ ማስተዋል ይቆጠቁጣል፤ ይመራል። ሲከፋም፤ “እረ ምረር ምረር ምረር እንደ ቅል፤ ስላልኮመጠጠ ስላልመረረ ነው ዱባ ‘ሚቀቀል” አሰኝቶ ወደ አልተፈለገ ውሳኔ ይመራል።
የአገራችን መከራዋ ለምን ሊበዛና ሊንዛዛ ቻለ? “ካልመራናችሁ” ብለው የወተወቱትና በዘመድም፣ በእውቂያም፣ በፖለቲካ ቤተሰባዊነትም “በትረ ሙሴውን” ከምርጫ ኮሮጆ ያፈሱት በርካቶች የፈተናችንን “ቀይ ባሕር” ከፍለው በድል እንደሚያሻግሩን በመሐላ ሳይቀር እንድናምናቸው ካስገደዱን በኋላ ይብስ ወደ ባሕሩ ውስጥ ሲዘፍቁን መመልከት ምን ይሉት አዚም ነው። በሕዝብ ስም ምለውና ተገዝተው ሕዝብ ማማረርና መናቅ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ማጉላላት፣ ለራስ ጓዳ ጥቅማ ጥቅሙ ላይ መራኮት፣ ለሕዝብ መብት ደንታ ማጣት የእነዚህ አገር ጠል “ባለ አገሮች” ክፉ በሽታ ነው።
ይህንን የተሸሸገ ባህርያቸውን የገለጠው የበቀደሙ የሕዝብ ውይይት የብሶት እሪታ ነው። እንደምን በመላው አገሪቱ ተመሳሳይ ድምጽ ሊሰማ ይችላል? እንደምንስ ተመካክሮ እንደገባ ጥቂት የሰው ቁጥር ሚሊዮኖች በተመሳሳይ ድምጸትና ቃላት እምባ በተቀላቀለበት ብሶት መከራቸውን ይዘረግፋሉ።
ገዢው ፓርቲ ቢገባው በውይይቶቹ ላይ የተዥጎደጎዱት የሲቃ ድምጾች ለወቅታዊ አቋሙ የውሃ ልኩ ማሳያ ቱምቢ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በወደፊት ዕድሉም ላይ ወሳኝና ጠቋሚ መልዕክቶች የተላለፉበት ጭምር ነበር።
ሌላው የአገር ጠልነት መገለጫ እየተንጸባረቀ የሚስተዋለው የንግዱን ዘርፍ በሞኖፖል በተቆጣጠሩ በአንዳንድ “ዘረፋ አምላኩ” በሆኑ “ባለ ሀብቶች” ላይ ጭምር ነው። ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያ “ባለ ሀብቶች” እንዴት ወደ ስኬት ማማ እንደተስፈነጠሩ ታሪካቸውን የሚነግሩን ከምንም ተነስተውና ከተራ ሥራ ተመንጭቀው እንደሆነ የሚመሰክሩት በንግግር ብቻ ሳይሆን መሐላም አክለው ነው።
በዕለት ሕይወታቸው ላይ የሚስተዋለው ዘረፋና ማድፋፋት የሚተገበረው ደግሞ “እንደ እናንተው ነበርኩ” በሚለው ምስኪን ሕዝብ ላይ መሆኑ ተቃርኖውን ያጎላዋል። በዚህም ጉዳይ ላይ የሕዝብ አክብሮት እንኳን ቢቀር ሕሊና እንዲከበር መረር ብለን እንጠይቃለን።
መቋጫና መደምደሚያ ሃሳባችን አንድና አንድ ነው። አገር ጠል ባለ አገሮች በወንጠፍት ይፈተሹ። ድምጻቸው ሁሌም የሚሰማ የሚመስላቸውና “ሀገር አፈራርሰው” እና ሕዝብ አስመርረው ለዘላለም የሚመኙ የፖለቲካው “ደብል ፌስ” የባህርይ ተገላባጭ ጃኬት ለባሾችም አርቀው በመመልከት ወደ ቀልብያቸው ቢመለሱ ይበጃቸዋል። የበቀደሙ የሕዝብ ስብሰባ “ለገዢዎቹ ጌቶቻችን” የትናንት ትዝታ ብቻ ሳይሆን የነገ የማንቂያ ደውል ሆኖ ሊቀሰቅሳቸውም ይገባል።
በፓርላማችን ወንበርተኞች አናት ላይ ድምጹን አጥፍቶ እንደተኛው ደወል ከበላይ ያለው ሕዝብም ዝምታን መርጦ በአርምሞ መቀመጡ ድምጽ አያሰማም ማለት አይደለም። የሕዝብ ድምጽ እንደ እግዜር ድምጽ “ዝግባውን ይሰነጥቃል”። የሚጠራጠር ካለ መልእክተኛውን መብረቅ ማስታወስ ይቻላል። የሕዝብ ጎርፍ ከተነደለ መገደቢያም ሆነ መከተሪያ ዘዴ አይኖረውም። “እድል አንዴ፤ ጥፋት ሁለቴ” ይላል የአገሬ ብሂለኛ። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 /2014