የትዕግስትን ከፍታ በ«መታገስ ዋጋ አለው» ቃኝቶ የትዕግስቱን ጣፋጭ ፍሬ የሚያጣጥመው ኢትዮጵያዊ፤ ትዕግስቱ እንደ ሞኝነት፣ ጊዜ መስጠቱ እንደ ዝንጋኤ ሲቆጠርበት «ትዕግስትም ልክ አለው» ይሉትን ብሂልን ፈጥሮ የትዕግስቱን ልክ ማለፍ፣ የመከፋቱን ጫፍ መውጣት በዝምታ እንደማያልፍ ያስተምራል።
ለእነዚህ ሁለት ብሂሎቹ «ለሁሉም ጊዜ አለው» ብሂሉ ላይ ተመስርቶ ሁሉንም በጊዜውና በቦታው አሳምሮ እየከወነ ዘመን ተሻግሯል፤ ታሪክ ሠርቶ፣ ወግ ባህሉን መስርቶ፣ ማህበራዊ ቁርኝቱን አጽንቶ በከፍታው ላይ ኖሯል።
ይሄንንም በማህበራዊ ጉድኝቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ጅረት ተግተልትለው ላለፉት የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓቶች ማቅኛነትም ተጠቅሞባቸዋል። ጥያቄዎቹን መዝነው፣ ንግግሮቹንም አድምጠው መልስ ሲሰጡት ሸልሞ ማንገስን፤ ጥያቄዎቹ ምላሽ፣ ንግግሮቹም አድማጭ የተነፈጉ መስሎ ሲሰማው አዋርዶ ማውረድን ተክኖበታል።
በዚህ ሂደትም ጥያቄ ጠይቆና የሚሰማውን ተናግሮ «… ቃሌን ሰማኝ፣ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ፤ … እንደ እጄ ንጽህና ይመልስልኛል» ብሎ ሲጠብቅ፤ ንግግሮቹ ያለ አድማጭ፣ ጥያቄዎችም ያለ ምላሽ የቀሩ መሆናቸውን ሲገነዘብ ለሁሉም የጊዜውን ፍርድ ሰጥቶ ሸኝቷል፤ አዳዲስ ባለፍርዶችን ተክቶም ለተራ ፍርድ ሰይሟል።
ለዚህ እንደ ማሳያ ሦስት ፈርጆችን እንጥቀስ፤ አንደኛው በንጉሣውያን ሥርዓት የሚገለጸው የአፄዎቹ አስተዳደር ነው። ይህ ወቅት ኢትዮጵያዊ (በሕዝብ የወል ስም ልጠቀመው) በባላባትና ጭሰኛ የዕዝ ሰንሰለት ውስጥ እንዲገባ የሆነበት ጊዜ ነበር።
በዚህም ጭሰኛውና ባላባቱ በሲሶ ልኬት ላይ ተመስርተው በኑሮ ጅረታቸው ይፈስሱ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አልሆንልህ ያለው እና የጭሰኝነት ቀንበሩ ጫንቃውን ያዛለው ሰፊው ሕዝብ፤ ጭሰኝነት በቃኝ፣ እኔም እንደ በአላባቱ የመሬት ባለቤት ልሁን ሲል መሞገት ጀመረ።
እናም ሰፊው ሕዝብ ከዛሬ ነገ፣ ከዘንድሮ ለቀጣይ ዓመት ጥያቄዬ መልስ ያገኛል፤ ጩኸቴም ይደመጣል በሚል ተስፋ መጠበቅ ጀመረ። ይሁን እንጂ በጪሰኛው ጉልበትና ላብ ላይ የተመሠረተው ባላባታዊ ሥርዓቱ የጭሰኛው ንግግር በጆሮው ሊገባ፤ ጥያቄውንም ሊመልስ አልቻለም።
ታግሶ መጠበቅ ዋጋ እንዳለው የተገነዘበው ሕዝብም፤ መታገሱ ዋጋ እንዳልተሰጠው ሲያውቅ የትዕግስቱ ልክ አለቀ። እናም የእንቢታው ጊዜ ደርሶ የባላባትነት ዘመን፤ የጭሰኝነት ጉዞ እንዲያበቃ ለማድረግ ተነሳ ጊዜው ነበርና የራሱን ጥያቄ በራሱ መለሰ። ጭሰኝነት ከባላባትነት ተቆራረጠ፤ የጌታና ሎሌ ጉዞ ተቋጨ፤ ሁሉም ባለርስት፣ ሁሉም ባለ ቤት ሆነ።
ወቅቱ አዲስ መንገድ፣ አዲስ ቅኝት ይዞ መጣ። ጭሰኝነትና ባላባትነት መቋጫ ሲያገኝ፤ ሶሻሊዝም ለመለመ። የሠራተኛው መደብ ቦታውን ተረከበ። በ«ኢትዮጵያ ትቅደም» ቅኝት ጉዞው የሰመረ መሰለ።
ይሁን እንጂ እያደር ቅኝቱ መቀየር፤ ኢትዮጵያን ማስቀደሙ መፈተን ጀመረ። መሬትን ለባለመሬቱ ያደረገው የሕዝብ እንቢታ፤ በማንነት ካባ ለመሬት ንጥቂያ ተጋበዘ። የማንነት ነፃ አውጪዎች ባነሱት ነፍጥ ሕዝቡ መታመስ ጀመረ። አገር አቅኚና የማንነት ነፃ አውጪዎች ሕዝብን ተከልለው መፋተግ፣ መዋጋት፣ ማጋደልና መገዳደል መለያቸው ሆነ።
አብዮተኞችና ብሔረተኞች የሚለው ጎራ አገርን ለከፋ ጦርነት፤ ሕዝብን ለእልቂት እና ለዴሞክራሲ ጥማት ዳረጉት። በጉሮ ወሸባዬ የተተከለው የደርጋዊ ሥርዓት የመሣሪያ ላንቃን ማዘጋትም ሆነ የሕዝቡን እንግልት ማስቆም የተሳነው መሰለ። በውስጣዊም በውጫዊም ጫናው አገርና ሕዝብ ተፈተኑ፤ መፈተናቸው ደግሞ ለጥያቄ እንዲነሱ፤ ለተቃውሞ እንዲበረቱ አደረገ።
ንግግራቸው በፀረ አብዮተኝነት፤ ጥያቄያቸው በአፈሙዝ ምላሽ ማግኘት ጀመረ። ይሄም ሕዝብ ሕልውናው በለጠበትና በቃኝ ብሎ ለብሔረተኞች በር ከፈተ። እናም አብዮታዊው ጉዞ ሲገታ፤ ብሔረተኛው ፌዴራሊዝም ተተከለ።
ብሔረተኛውን ፌዴራሊዝም የወለደው ሥርዓት በልማት፣ በዴሞክራሲና በሌላውም ስም ምሎ ለሕዝብ የሚሠራ መሆኑን ሲናገር፤ ሕዝብም ተቀበለው። መተባበርና አብሮት መስራት ጀመረ። ዓመት፣ ሁለት ዓመት፣ … አምስት ዓመት፣ አስር ዓመት፣ ሃያ ዓመት፣… ቀን ቀንን፣ ወር ወርን፣ ዓመት ዓመትን እየተካ የአብሮነት ጉዞው ቀጠለ። ሆኖም ጊዜው በረዘመና ሥርዓቱ በተደላደለ ቁጥር መሃላው ተዘነጋ፤ የሕዝብ ፍላጎቶች ቸል ተባሉ፤ ከሕዝብ ይልቅ ለእኔና ለቡድኔ የሚል አመራርና የፖለቲካ ስሪት ተተከለ።
ይህ ደግሞ ሕዝብ ቆም ብሎ እንዲያስብ፤ በራሱ ድጋፍ ራሱን እየጨቆነና እያፈነ መሆኑን እንዲገነዘብ፤ እየሆነ ስላለው እንዲናገር፤ እንዲሆን ስለሚፈልገው እንዲጠይቅ አደረገው። ንግግሮቹ ሰሚ፤ ጥያቄዎቹም ምላሽ ያገኙ እንደሁ በሚልም በትዕግስት ጠበቀ።
ሆኖም ንግግሩ ከአክራሪነት፣ ከጽንፈኝነት፣ ከትምክህተኝነት፣ ከጠባብነት፣ ወዘተ ፍረጃ የዘለለ ጆሮ ሰጥቶ ያደመጠው አልነበረም። ጥያቄዎቹም ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የኮማንድ ፖስት አፈና፤ እስርና እንግልት ዳረጉት እንጂ ጠብ የሚል ምላሽ አላስገኙለትም።
ይሄኔ ሕዝብ ቆም ብሎ ማሰብ ያዘ። በኢ_ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል መጎዳቱ፤ የፖለቲካ እና የማህበራዊ በደል ውስጥ መግባቱ፤ በማንነት ስም የተሰጠው ቦታ፣ የተከለለለት መሬት እርስ በእርሱ እንዲገፋፋና እንዲገዳደል የተሰመረለት መሆኑን ተረዳ። እናም መገፋፋቱን ትቶ መሳሳብ፤ መጠራጠሩን ትቶ መመካከር፤ መገዳደሉን ትቶ መተባበር ያዘ። የራሱን ዕድል በራሱ ሊወስንም ከፋፍሎ እንዳይተባበር፣ የሃሰት ትርክት ፈጥሮ እንዳይደማመጥ፣ ባደረገው ሥርዓት ላይ ሆ ብሎ ተነሳ።
በዚህም ታንኩንም ባንኩንም በእጁ ይዞ የማይናወጥ የመሰለው ሥርዓት ተነቅንቆ ተነቀለ፤ ሕዝብ በለውጥ ማዕበል ከፍ አለ።
የለውጡ ማዕበል ለውጥ ወልዶ፤ የኢህአዴጋዊው ሥርዓት ከእሳቤው ብልጽግና ተተካ። የመከፋፈል ጉዞው በሕብር ወዳጌጠ አንድነት፤ የመጠራጠር ስሪቱ ወደ መተማመን ውቅር፤ የመገፋፋት ኑረቱ ወደ መተባበር እንዲለወጥ ለማድረግ ሥራ ተጀመረ።
ይሁን እንጂ የኢህአዴጋዊ ለውጡ ባህሪው ሪፎርም እንጂ አብዮት ባለመሆኑ ሰርጎ ገብ ቅሬቶች እና የተገፉትም ከውጭ ሆነው ሂደቱን መነቅነቅ ጀመሩ። ለውጡ በእንቅፋት፤ ሕዝብም በፈተና እንዲታጀብም አበክረው ሰሩ።
እነዚህ የተገፉ የመሰላቸው ኃይሎች በውስጥም በውጭም ሆነው የፈጠሩት ቅንጅት እና ከቀደመው ተጠቃሚ የነበሩ አካላት ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በሚያደርጉላቸው እገዛ ታጅበው የሚፈጥሩት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግር ቀላል አልነበረም።
ኢኮኖሚው በአንድ ሰንሰለት የተያዘ እንደመሆኑ የኢኮኖሚው አሻጥር ገነገነ፤ የደህንነት መዋቅሩ በአንድ ኃይል ቁጥጥር ስር ስለነበር ይሄን ማላቀቁ ጦር እስከመማዘዝ ደርሶ ብዙ ዋጋ አስከፈለ፤ ማህበራዊ ትስሰሩ ቀድሞ እንዲላላ ተደርጎ ስለነበር ሕዝቦች ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ አደረገ።
እናም ሰላምና ፀጥታው ከፍቶ የደህንነት ስጋትን ወለደ፤ የኢኮኖሚ ሳቦታጁ ማረፊያ ያጣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ተከለ፤ ማህበራዊ ስሪቱም አለመተማመንና መገፋፋትን መገለጫው ያደረገ መሰለ። የእነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ ሕዝብ አብዝቶ እንዲጮህ፤ አብዝቶም መፍትሄ እንዲያገኙ እንዲጠይቅ አደረገው።
ሆኖም ጩኸቶቹም ሆኑ ጥያቄዎቹ ዛሬም ድረስ ከመድረክ ምላሽ የዘለለ ተጨባጭ ነገር ያሳዩት አይመስሉም። ይህ ደግሞ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተናግሮ ሰሚ የማጣትን፤ ጠይቆ ምላሽ የመነፈግን ስሜት የሚፈጥር ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው።
ሕዝብ ደግሞ መልስ አልባ ጥያቄዎች፤ አድማጭ አልባ ንግግሮች እንዲኖሩት አይፈልግም። በመሆኑም «ሳይቃጠል በቅጠል» ነውና የሕዝብ ንግግሮች ሊደመጡ፤ ጥያቄዎቹም ሊመለሱ ይገባል።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን መጋቢት 21 /2014