ሴት ወደ ማጀት፤ ወንድ ወደ ችሎት አባባል በብዙ ታታሪ ሴቶች አማካኝነት ድባቅ እንደተመታ እየኖርንበትና እያየነው በመሆኑ ነጋሪ አያሻንም። ችሎቱንም ሆነ ማጀቱ በእነርሱ ውጤታማነት ይመራል። ለዚህ ደግሞ ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ሥራቸው ጭምር እንዳገዛቸው ማንም ይረዳዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ብዙዎች ከአይችሉም አስተሳሰብ እንዳልወጡ እንመለከታለን።
ለዚህም ማሳያ ብናነሳ የኃላፊነት ቦታዎች በወንዶች እንጂ በሴቶች እንዳይሸፈኑ ብዙ ጥረት ይደረጋል። ነገር ግን ይህም ሆኖባቸው ያልተበገሩና ከወንዶች ተሽለው የተገኙ ሴቶች እጅግ በርካታ ናቸው ።
ብዙዎቹ ሴቶች በትምህርት መስኩ የበቁና የነቁ የቢሮ ሠራተኞች እንደነበሩ በአሁኑ የዐቢይ አስተዳደር ብቻ በኃላፊነት ቦታ የተቀመጡት ጥሩ ማሳያ ናቸው። እነርሱ እናትነታቸውን ከብቃታቸው ጋር አስተባብረው አጀብ የሚያሰኝ ሥራ ሠርተዋል፤ እየሠሩም ይገኛሉ። አገርን በማገልገሉም በኩል ጥሩ አሻራ አሳርፈዋል። ዛሬም ይህ ተግባራቸው በታማኝነት የሚቀጥል እንደሆነ በተለያየ መልኩ በማሳየት ላይ ናቸው። ነገር ግን ብዙ ሰው ውጤታማነታቸው የሚታይና የሚለካ ቢሆንም ከወንድ እኩል ናቸው ብሎ ሲያበረታታቸው አይስተዋልም።
የሴቶችን አቅም በብዙ መልኩ ማረጋገጥ እንደቻልን ብንመለከትም ወደ ፊት እንዲወጡ ሲደረግም ግን እምብዛም አይታይም። ለዚህ መንስኤው ደግሞ ሴት ወደ ማጀት ወንድ ወደ ችሎት የሚለው እድሜ ጠገብ አባባላችን ዛሬም ድረስ በውስጣችን መኖሩ ነው። በአገራችን ብሎም በዓለም ላይ የሴቶችን መብት የሚያስጠብቁ በርካታ ሕግጋት ቢኖሩም እነኝህ ሕግጋት የሚፈጥሯቸውን መብቶች ሴቶች እንዳይጠቀሙበት የሚደረጉበት ብዙ መልኮች አሉ። እናም ይህንን ከመፍታት አኳያ ብዙ ስልጠናዎችን የሚሰጡና የሚያማክሩ አንድ እንግዳ ለዛሬ ይዘን ለመቅረብ ወደናል።
እንግዳችን ቅድስት ጽጌ የምትባል ስትሆን፤ ሴት ወደ ማጀት ወንድ ወደ ችሎት የሚለውን አስተሳሰብ የሕግ አማካሪና ጠበቃ በመሆን ከአጨናገፉት መካከል አንዷ ነች። ከወረዳ እስከ ፌደራል ፍርድ ቤቶች ድረስም ሠርታለች። የብዙ እናቶችንና ወጣቶችን እንባ አብሳለች። በግሏ የማማከርና የጥብቅና ሙያው ላይ ሆና አስተሳሰቡ ዛሬም በሴቶች ላይ እንዳይደገም የተቻላትን ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ከወንድሞቿ ጋር በስፋት የልጅነት ጊዜዋን አሳልፋለች። እንደ ሴት ልጅ ጫና ሳይደረግባትም ነው የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችው። በዚህም ነፃና ግልጸኛ እንድትሆን አድርጓታል። የምትፈልገውን እያደረገችና መሆን የምታስበውን እየሆነች ለዛሬ የበቃችውም በዚህ ምክንያት ነው።
ሴት ልጅ ከምንም በላይ ነፃነት ያስፈልጋታል። ያን ጊዜ የሚደርስባት አይኖርም ብላ የምታምነው ቅድስት፤ የሴትነት ልዩ ስጦታ መታየት የሚጀምረው ይህን ጊዜ ነው። አስተዳደግ ጭቆና የበዛበት ከሆነ ለማደግም ሆነ ለመነሳት አዳጋች ነው። አቅም ቢኖራት እንኳን ተሸናፊ እንደሆነች ታስባለች። ስለሆነም ከቤት ወጥታ መሆን የምታስበውን መሆን አትችልም ትላለች። በቤተሰቧ ውስጥ ስትኖር ጫና ባይባልም ወንዱ እየተጫወተ አግዢኝ የምትባለው እርሷ ናት። እናም ሁሌም በአስተዳደጋችን ውስጥ ልዩነቶች አሉና እነዚያ ስለሚያድጉ ነው ዛሬም በእኩል እንደምንሠራ የማይታመነውም ብላናለች።
ለቅድስት ዛሬ ላይ መድረስ የእናቷ ሚና በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። በተለይም ከሴትነቷ ጋር ተያይዞ የማይመክሯት ነገር አልነበረም። የራሷ ገቢ እንዲኖራትና የባሏን እጅ እንዳትጠብቅ ሁልጊዜ ይነግሯታል።
በራስ የመተማመን አቅሟን አጎልብታ ያሻትን ትተገብራለች። የምትፈራው አካል የለምም። ሴቶችም በአስተዳደጋቸው እንኳን ባይሆንላቸው በኑሯቸው ይህንን ለማድረግ እንዲሞክሩ ትመክራለች። በተለይም ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ እነርሱ ያዩትን ስቃይ እንዳይደግሙት ብዙ መልፋት እንደሚገባቸውም ታሳስባለች።
በአስተዳደጓ ውስጥ አልችለውም የሚል ነገር አታውቅም። በመሞከር ውስጥ ማደግ፣ በመሞከር ውስጥ መብለጥ እንዳለ እየተማረችም ነው የኖረችው። ይህ ሲሆን ደግሞ ደጋግሞ መውደቅ እንዳለም ትረዳለች። ወድቃ እንደማትቀርም እንዲሁ። ስለዚህም ዛሬም መሞከር የሚያስደስታት ለዚህ ነው። የተሻለ ነገር ለማግኘት የማትቆፍረው ድንጋይ የለም። ይህ ደግሞ ከቤተሰብ እስከ ማኅበረሰብ ከዚያም አልፎ እስከ ትምህርት ቤት ተወዳጅና ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል።
በተለይም በትምህርት ቤት በኩል የደረጃ ተማሪ ከመሆኗም በላይ የማስተባበር ልምድ ያላትና ያሰበችውን የምትተገብር መሆኗ ሁሉም እንዲወዳት ያደረጋት ጉዳይ እንደሆነ ታስታውሳለች። ብዙዎች የሚሰሟትና ያለችው የሚፈጸምላት ልጅ እንደነበረችም አትረሳውም። ዛሬም ቢሆን ይህ ባህሪዋ ቀጥሏል። ሐቀኛና ለእውነት የምትቆም ነች። በዚህም ከባድ ፈተና ገጥሟት እንደነበር ትናገራለች።
ፈተናው ከሥራ ጭምር ያሳገዳት ነው። ከሥራ የለቀቀችበት አጋጣሚ መነሻውም ይኸው ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። የያዘችው የፍርድ ቤት «ኬዝ» (ጭብጥ) ባለስልጣናት ጭምር እጃቸውን ያስገቡበት ነበር።እናም የእርሷ አቋም ‹‹ማንም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው›› የሚል ነውና ሕጉንና ያለውን መረጃ መርምራ እውነቱን ፈረደች። ባለስልጣኑንም የምታስጠይቅበት ሁኔታ ፈጠረች። ይህ ያልተመቸው ኃላፊም ከሥራዋ እንድትታገድ አደረጋት። ነገር ግን በቀላሉ የማትበገርና ነጻነቷን የማታስነካ በመሆኗ ሕጉን ተከትላ እውነቱን አረጋገጠች። እንደውም እገዳው ምክር ቤት የሚያውቀው አልነበረምና እዚያ ድረስ በመሄድና በመክሰስ መብቷን አስከብራለች።
በቦታዋ ተመልሳ የተወሰነ ዓመት ከሠራች በኋላ ግን በዚያ መቀጠሉ ምቾት አልሰጣትም። ስለዚህም ሥራዋን ለቃ በግሏ ወደ መሥራቱ ገባች። የሕግ ትምህርትን የመረጠችበት ምክንያትም እንዲህ አይነት ከባድ ችግሮችን ለመጋፈጥ በመሆኑ በግል መሥራቱ የበለጠ ነጻነትን እንደሚያቀዳጅ ታውቃለች። በዚያ ላይም የማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲሁም የባህል ጫናው የሚፈትናቸውን ሴቶች በሕጉ ዘርፍ እንዴት ማገዝ ይቻላል የሚለው ስለሚያሳስባት የዛሬውን ጉዞዋን ጀመረች።
ቅድስት በሕግ ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ሠርታለች፤ አሁንም በቢዝነስ ሕግ ሁለተኛ ዲግሪዋን እየተማረች ትገኛለች። ቀጣይም የመማር እቅድ አላት። ምክንያቱም ከተፈጥሮ ከተሰጣት ብልሃት በተጨማሪ ሴትን ልጅ የሚያልቀው ትምህርት ነው ብላ ታምናለች። በእርግጥ ከአዲስ አበባ ወጥታ አለመማሯ በተለይም እስከ መጀመሪያ ዲግሪዋ ድረስ በጣም ያናድዳት ነበር። የአገሯን የተለየ ገጽታ ማየትም ያጓጓታል። ይሁን እንጂ ይህንን ፍላጎቷን በሥራ ላይ ባለችበት ጊዜ አሟልታዋለች።
መጀመሪያ ከአዲስ አበባ የወጣችው የሕግ ባለሙያዎች ቀድመው የሚወስዱትን ስልጠናን ለመከታተል ባህር ዳር በመሄድ ነው። ደስ የሚል ቆይታ እንደነበራትም ታስታውሳለች። በመቀጠል ሥራ መቀጠሩን የፈለገችው ወረዳ ላይ ሲሆን፤ ከክልሉ ሳትወጣ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ ከስምንት ዓመት በላይ ሠርታለች። ከዚያ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ተቀላቀለች።
በወረዳ ቆይታዋም የሚገርሙ አጋጣሚዎች እንደ ነበሯት ታነሳለች። አንደኛው ለሴት ልጅ የሚሰጠው ክብር አናሳ መሆንና የሥራ ዘርፍ ጭምር የተመረጠበት ሁኔታ መኖሩ ሲሆን፤ ‹‹ዳኛው አይመጣም እንዴ?›› የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳላት እንደነበረ ታወሳለች። ‹‹እኔ ነኝ›› ስትላቸው ደግሞ ሴት ከመቼ ጀምሮ ነው መፍረድ የጀመረችው እያሉ ይሟገቷት እንደ ነበርም አትረሳውም። ይሁን እንጂ ሙያውን መውደዷና ትግሉን ለመቋቋም እንደገባችበት ታውቃለችና ሁሉንም በማስረዳት ታልፈዋለች። ከጊዜ በኋላም አክብሮቱና ማመኑ እንደመጣላት ታስረዳለች።
እንግዳችን ሌላው የገጠማት ነገር ከአዲስ አበባ ወጥታ ባለማወቋ ውሃና መብራት አለመኖሩ ነው። በዚህም ከምግብ እስከ አካባቢ መልመድ ድረስ ያሉ ፈተናዎች በቀላሉ የሚለመዱ አልሆኑላትም ነበር። ሆኖም ችግሩንም፣ ፍቅሩንም ማየት ሕልሟ ነበርና ሳትደክም አልፈዋለች።
ሕጉ ሴት ስለሆነች ምንም የምትከለከለው ነገር እንደሌለ ቢያስቀምጥም ሴት ስለሆነች ብቻ እያላት የማይሰጣት ብዙ መብቶች እንዳሉም በሙያው ውስጥ ሆና አይታለች። እናም ይህንን አዋዶ ከመሄድ አንጻር ብዙ እንድትለፋም ሆናለች። እንጀራቸው ባይሆን እንኳን ሕግን ሴቶች ቢማሩና ቢኖሩት መልካም ነው። ምክንያቱም ሴቶች ሕግን በማወቃቸው ብቻ የራሳቸውን ጥቅም ከማስከበርም ባለፈ ለሌሎች መሟገት ያስችላቸዋል የሚል ጽኑ እምነት አላት። በዚህም የማደጋቸውን ከፍታም ይገነዘባሉ ትላለች።
ባለታሪካችን በሥራዋ ዛሬ ድረስ የምትጸጸትበትም ኬዝ ገጥሟታል። ይህም የባልና ሚስት ጉዳይ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ወደ ፍርድ ቤት መጥተው በሽምግልና እየታረቁ ይፈታሉ። አንድ ቀንም እንደተለመደው ሲመጡ በዚያ መልኩ እንዲታረቁ ላከቻቸው። አፋቱኝ እያለች ብትለምንም የሚሰማት አልነበረም። ይሁን እንጂ ለቀጣይ ቀጠሮ ግን የሆነው የሚያስደነግጥ ነበር። ባለቤቷ ሳይፋታም፣ ሳይታረቅም ገሏት ተገኘ። ቅጣቱን አግኝቶ ቢታሰርም የእርሷን ሕይወት መታደግ ባለመቻሏ ግን ዛሬ ድረስ ይቆጫታል። እናም ፍርድ በራሱ ሕመም ያለበት እንደሆነ ከእነዚህ አይነት ኬዞች መረዳት ይቻላል። ሆኖም ለእውነት ካደረግነው ግን ሁላችንም ነጻ ይሆናል ትላለች።
ቅድስት ሌላው ያነሳችው ነገር የሴት ልጅ ውበቷ አዕምሮዋ መሆኑን ነው። ሴትነት ከውበትም በላይ በአዕምሮ ማማር ነው። ነገር ግን ብዙዎች የሚያስቡት ሴት ልጅ ለመኖር ውበቷ ይበቃታል ብለው ነው። ይህ እጅግ የተሳሳተ ምልከታ ነው። ምክንያቱም ውጪያዊው ውበት ነገ ይጠፋል። የዚያን ጊዜ ባዶ መሆንና ጥገኝነት ይመጣል። እናም መጉላት ያለበት አዕምሮ እንጂ አካላዊ ቁንጅና አይደለም። በአዕምሮ መዋብ ሌሎችን መብለጥ እንደሆነ ሴቶች ማመንም ማሰብም አለባቸው። መሠረታዊ መርሐቸውም ሊያደርጉት ይገባል። ውስጣዊውና በአዕምሮ የበለጸገው ማንነት መክሰም የለበትም። ስለሆነም ሴቷ ይህንን ግቧም ኑሮዋም ልታደርገው ይገባል ስትል ትመክራለች።
ሴቶች ከሥራ አኳያ ብቻ ሳይሆን ከመሆንም አንጻር በብዙ ነገሮች ፈተና ይገጥማቸዋል። በጊዜ ሂደት ግን ያሸንፉታል የምትለው ቅድስት፤ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ከራስ የጀመረ ለውጥ ማምጣት ሲቻል ነው። እልህ አስጨራሽ ትግል ቢኖርበትም ለቀጣይ ድል እንደሚያበቃ አምኖ መጓዝም ያስፈልጋል። ለዚህም ቢሆን ከቤተሰብ፣ ከማኅበረሰብና ከባለቤቷ ጭምር የሚገጥማት ፈተና ቀላል አይሆንም። ነገር ግን ይህንን በትዕግስት ማለፍ ይኖርባታል የሚለው ሌላው መልዕክቷ ነው።
ሥራ ለሴቶች በየትኛውም በኩል ቀላል ነው። እድልና አጋጣሚን ብቻ ይፈልጋል እንጂ። እናም ይህንን እድል መጀመሪያ ወንዶች ሊፈጥሩት እንደሚገባ ታሳስባለች። በምክንያትነት የምታነሳውም ለወንዶች ያለው ሁኔታ ምቹ ነው። ወንዶች በብዙ ምቾት ውስጥ የኖሩና ያደጉ ናቸው። ዛሬም ብዙ እድሎች ይሰጧቸዋል። በዚያው ልክ ማኅበረሰቡ የፈረጀውን የሴት ሥራ ተብሎ የሚታሰበውን እንዲሠሩ አይፈቀድላቸውም። አልፈው ከተገኙም የሚሰድባቸው ብዙ ነው።
በዚህም ለማገዝ ይሸማቀቃሉ። ይህ ደግሞ ሴት ልጅ በቤትም በቢሮም ደክማ እንድትሠራ ያደርጋታል። በአንዳንድ መልኩ ውጤታማ የማትሆነውም ከዚህ የተነሳ ነው። ስለሆነም ወንዶች እናታቸውን፣ እህታቸውንና ሚስታቸውን የሚወዱ ከሆነ ሴቶችን በቻሉት ሁሉ ማገዝ እንዳለባቸው ታስገነዝባለች።
በአስተሳሰብ የላቀና ለሴት ልጅ ውግንና ያለው ወንድ ካለ ሚስትም ሆነች እህት የተፈለገው ቦታ ላይ ትደርሳለች። ምክንያቱም ለእርሷ መሻሻል ብዙ ነገሮች ያደርጋልና፤ ቤትም ጭምር መተጋገዞች ይለምዳሉና ነው። ሴት በብዙ ነገር እንዳትደክም መንገድ ይጠርጋል። በዚህም ቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ውጪውም ላይ ብዙ ነገሮች ይቀየራሉ። የመጀመሪያው ነገር ሴቷ ራሷንና ቤተሰቧን መለወጧ ሲሆን፤ ሌላው አገሯ ላይ የምታደርገው አበርክቶ ነው።
በስፋት የጎሉና አርኣያ የሆኑ ሴቶችን እንድናይ የሆነውም ይህ መሠረት ስላላቸውና አስተዳደጋቸው በብዙ መልኩ የተገነባ ስለሆነ ነው። ስለሆነም ሴቶችን በመደገፍ ከቤተሰብ ባለፈም ለአገር የተሻለ አበርክቶ ማስገኘት እንደሚቻል ሁሉም ሊገነዘብ የግድ ይላል።
ሴት ጋ የሚባክን ጊዜ የለም። ይህ ደግሞ ትጉህ ሠራተኝነቷን ከማሳየት ባለፈ መልካም ዕድሎችን እንድታገኝ ያስችላታል መልእክቷ ነው። እኛም መልዕክቷን ተግባራዊ እናድርገው በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 /2014