የአንድ አገር እድገት የሚወሰነው በኢኮኖሚና በተማረ የሰው ኃይል ብዛት ነው። ለዚህ ደግሞ ተቋማዊ የሆነ አሠራርና ክትትል ያስፈልገዋል። በአገራችንም ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ሲሠራ ቆይቷል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የትምህርት ዘመን ከ1900 ዓ.ም በፊት በአብዛኛው በሃይማኖት ተቋም (ለምሳሌ፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን) ጋር የተሳሰረ ሆኖ ቆይቷል።
በመሆኑም መደበኛ የሚባለው የትምህርት ሂደት ከሃይማኖት ጋር የሚካሄድ ነበር። ከ1900 ዓ.ም በኋላ ግን ጥቂት ሕፃናት የዘመናዊ ትምህርት ማግኘት ችለዋል። በዚህ ጊዜ የመጀመሪያው ከሃይማኖት ትምህርት የወጣ የትምህርት ሥርዓት ተስተውሏል።
ለዚህ ደግሞ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በዘመናዊው ትምህርት ቤት የመጀመሪያው ነበር። በ 1925 ዓ.ም 20 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቢከፈቱም የተማሪዎች ቁጥር ከስምንት ሺህ መብለጥ አልቻለም ነበር። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በትምህርት ዘርፍ በርካታ ትምህርት ቤቶች የተከፈቱበት በተቃራኒው ደግም በርካቶች ከትምህርት ገበታ በተለያዩ ምክንያቶች የተገለሉበት ዘመን ነበር።
በደርግ ዘመነ መንግሥትም የትምህርት ሥርዓቱ ከኃይለስላሴ ወቅት ከነበረው የቀጠለ ቢሆንም፤ የራሺያ ኮሚኒዝም የተቀላቀለበት ነበር። ይህም ሆኖ በአገሪቱ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በሚያስችል መልኩ ሲሠራ መቆየቱ ይነገራል። ለምሳሌ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ኑሮ በዘዴ፣ እርሻና እደ ጥበብ ነክ ጉዳዮች በሥርዓተ ትምህርት ተቀርፀው ይሰጡ ነበር። ከዚህም ባለፈ አንድ ተማሪ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ሲወጣ የቀለምም የሙያም እውቀት እንዲይዝ የሚያደርጉ ትምህርቶች ይሰጣሉ።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተምረው የሚወጡ ተማሪዎችም በግዴታ የተመደቡበት ቦታ ሄደው ይሠሩ ነበር። ይህ ሁኔታ ተማሪው ሰው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሕዝቡን እንዲያገለግል በማድረግ ለውጥ ማምጣት አስችሏል። የደርግ ዘመነ መንግሥት በሕዝባዊ ትግል ከወደቀ በኋላ አገሪቱን ማስተዳደር የጀመረው ኢሕአዴግም አዲስ የትምህርት ሥርዓት ቀርፆ ወደ ተግባር አስገብቷል።
በዚህም ቀደም ብለው የነበሩ ትምህርቶች እንዲቆሙ ተደረገ። የመማሪያ መጽሐፍትም ከክህሎት ይልቅ የመንግሥት ሥርዓቱን ያማከሉ ሆነው የተቃኙ በመሆናቸው የትምህርት ጥራት እንዲቀንስ አድርጓል። በወቅቱ የትምህርት ቤቶች ብዛት ላይ በመተኮሩ ጥራት ያለው የትምህርት ማምጣት እንዲዘነጋ አድርጎታል።
ከዚህም ባለፈ የመምህራን ትምህርት አሰጣጥ ትኩረት የተሰጠው ባለመሆኑ ብቁ ተማሪዎችን ማፍራት አልተቻለም።
የኢሕአዴግ መንግሥት በስልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እንዲሁም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በብዛት በመገንባትና በማዳረስ ረገድ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። ነገር ግን ጥራት ያለው ትምህርትና የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት አልተቻለም።
ለምን ቢባል የትምህርት ሥርዓቱ በፖለቲካ አስተሳሰብ በመቃኘቱ ነው። እዚህ ላይ የአንድ አገር ትምህርትም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች የሚወሰኑት አገሪቱ በምትተዳደርበት ፖለቲካ ነው። በኢትዮጵያ ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው።
የትምህርት ሥርዓቱ ትውልድ ማፍሪያ ሳይሆን ትውልድን መግደያ መሣሪያ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል እስከመባል ተደርሶ ነበር። በዚህ ረገድ በ1993 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠቃለያ 10ኛ ክፍል ላይ ይሁን ሲባል የነበረው ግርግር የሚታወቅ ነው።
የትምህርት ሥርዓቱም የሁለተኛ ደረጃ ማጠቃለያ 10ኛ ክፍል ሆኖ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ደግሞ መሰናዶ በሚል ሁለት ዓመት ተምረተው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲገቡ ተደረገ። ይሄ አሠራር ታድያ ውሎ ሲያድር ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት እንዳይኖር አድርጓል።
ለዚህ ማሳያዎችን እናስቀምጥ። የመጀመሪያው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠቃለያ 10ኛ ክፍል ላይ ወስደው ውጤት የማይመጣላቸው ተማሪዎች ወደ መምህራን ኮሌጅ እንዲገቡ ይደረጋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ እውቀት ያለው አስተማሪ እንዳይኖር በር ከፍቷል።
ከዚህም በዘለለ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ለመምህርነት የሚሰጡት ግምት አናሳ በመሆኑ በትምህርት ክፍል በሚመርጡበት ወቅት ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው እንዲገቡበት ይደረጋል። ይሄ ሁኔታ በፍላጎት የሚያስተምር መምህር እንዳይኖር አድርጓል።
የትምህርት ሥርዓቱ ከመሻሻል ይልቅ ቁልቁል እየወረደ መምጣቱ ሳያንስ በተከታታይ ዓመት የ12ኛ ክፍል መውጫ ፈተና መሰረቅ ኃላፊነት የሚወስድ አካል አጥቶ አሁን እንደ ፋሽን እንዲቆጠር አድርጎታል።
ይባስ ብሎ የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የሥነዜጋና ስነ ምግርባር ትምህርት ውጤት አለመያዝና የአስተራረም ስህተት የፈጠረውን ጫና ተመልክተናል። ሰሞኑንም ጉዳዩ ከአንድ ክልል አልፎ ሌሎች ክልል የነበሩ ተማሪዎችንም ቅሬታ እያስነሳ ይገኛል።
የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በአገር አቀፍ ወጥ ሆኖ እንደመሰጠቱ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። ታድያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሁን ባለበት አቋም የመጡትን ቅሬታዎች በአግባቡ ከመፈተሽ ይልቅ ያልተገባ ክርክር ይዟል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ከአዘገጃጀቱ ጀምሮ ፈተናው ተሰጥቶ እስኪታረም ድረስ ከፍተኛ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር ይፈልጋል። ፈተናው በአገሪቱ በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምክንያት በሁለት ዙር እንደመሰጠቱ እንዲሁም የሕግ ማስከበር ዘመቻው በሚካሄድበት አካባቢ የሚገኙ ተማሪዎች ያሉበት ሁኔታ ጉዳዩን የተለየ ያደርገዋል።
በአማራና በአፋር ክልል የሚገኙ ተፈታኝ ተማሪዎች በምን መልኩ መስተናገድ አለባቸው የሚለው ጉዳይ ቀድሞ ታስቦ መሠራት ነበረበት።
ሌላው የሚነሳው ነገር ለምን በተደጋጋሚ ፈተናዎች ይሰረቃሉ የሚለው ጉዳይ ነው። የ12ኛ ክፍል ፈተና አገር አቀፍ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ክትትል የሚደረግበት ነው። ፈተናውም ሲዘጋጅ ምስጢራዊነቱን ጠብቆ ሊሆን በተገባ ነበር። ነገር ግን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ፈተናዎች እየተሰረቁ በማኅበራዊ ሚድያ መልሶቻቸው ሲዘዋወሩ ማየት እየተለመደ ነው።
ይህ ሁኔታ ትምህርት ሚኒስቴር ተከታትሎ በጥናት ማስቆም ሲገባው የፈተናው መልሶች ወጥቶባቸዋል የሚባሉትን የትምህርት አይነቶች በመሰረዝ የተማሪዎችን ሕይወት ማመሳቀል እንደመፍትሔ ይዟል።
እዚህ ላይ መታየት ያለበት የፈተና መልስ የወጣባቸው ትምህርቶች መሰረዛቸው ሳይሆን የተሰረዙትን ትምህርቶች በራሳቸው ለፍተው ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ጉዳይ ነው። ፈተናን ሰርቆ ማውጣት የሚችል የከሰረ ሕሊና ያለው ሰው፣ የተማሪዎች መውደቅ የማያሳስበው መምህር እንዲሁም ይህ ሁኔታ የማያሳስበው የትምህርት አመራር መኖር የተማረ የሰው ኃይል እንዲሁም የትምህርት ጥራት እንዲቀንስ ማድረጉ ሊስተዋል ይገባል።
የተማሪዎችና የመምህራን ጉዳይ በክልል የትምህርት ቢሮዎች ትኩረት ተሰጥቶ የማይሠራ እስኪመስል ድረስ ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል። ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ወጥ የሆነ አሠራርና ትውልድ የሚቀርፅ ፖሊሲ ተዘጋጅቷል ቢባልም በተግባር የሚታየው ግን ተገላቢጦሹ ነው።
ለነዚህ ሁሉ መፍትሔ የሚሆነው ትምህርት ሚኒስቴር ያለበት አቋም ገምግሞ ፈጣን ማሻሻያ ማድረግ እንጂ፤ ለስህተቶች ሁሌም ያልተገባ ምክንያት እየደረደሩ መቀመጥ ነው ብዬ አላምንም።
አምኃየስ መርድ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 /2014