ኢትዮጵያን በሚመለከት የአሜሪካ ጥቂት የኮንግረስ አባላት ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ሕጎችን በማዘጋጀት ይፀድቅላቸው ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስመርተዋል።
በኒውጀርሲ ሴናተር ቶም ማሊኖውስኪ መሪነት ተረቆ የቀረበው ‹‹ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ››የተሰኘው ረቂቅ ሕግ፣በ25 ገጾችና በ12 ክፍሎች የቀረቡ ጠንካራ አንቀጾችን ይዟል።
ረቂቅ ሕጎቹ ተቀባይነት አግኝተው ተፈጻሚ የሚሆኑ ከሆነም በተለያዩ መስኮች ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል።
አንዳንድ የዘርፉ ምሑራን እንደሚሉት የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በሕጎች ላይ ያላካተቱት ነገር ቢኖር፣ “የመንግስትን ሥልጣን ለሕወሃትና ሸኔ አስረክቡ የሚለው ዓረፍተ ነገር ብቻ ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል። ‹‹የኢትዮጵያን ሕልውናና ነጻነት የሚዳፈር ብቻ ሳይሆን ማዕከላዊው መንግሥት እንዲዳከምና ኢትዮጵያ የሊቢያን መንገድ እንድትከተል ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ አደገኛ ሕግ ነውም››ይሉታል።
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ ረቂቅ ሰነዶች የኢትዮጵያን ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱ አደገኛ ሰነዶች ሲሉ ይገልጿቸዋል። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የአሜሪካ ማዕቀብ የሚጎዳው በድህነትና በግጭት የቆየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ነውም››ይላሉ።
ሕጉ በረቂቁ ኢትዮጵያን የሚያዳክምና በአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋትና ቀውስ እንዲፈጠር የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር በፋይናንሱ ዘርፍ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የብድር፣ ዕርዳታና መሰል ጥቅማ ጥቅሞች ማስቀረትን ያለመ መሆኑ ተመልክቷል። አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደኅንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆም እንዲሁም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎችና የገንዘብ ምንጮች (አይኤምኤፍና የዓለም ባንክን ጨምሮ) ገንዘብ እንዳታገኝ እስከ ማድረግ የሚደርስ እርምጃም ተካቶበታል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽኖች ጋር ያላትን ግንኙነት በማገድ ኢንቨስትመንቶችንና የገንዘብ ልውውጦችን የማስቆም አቅም አለው።ረቂቅ ሕጉ መሠረታዊ መብቶችንም ያግዳል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችና አጋሮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዳያደርጉም ሆነ ገንዘብ እንዳይልኩ ይከለክላል። የኢሚግሬሽን ገደቦችንም ያካተተው ይህ ረቂቅ ሕግ የቪዛ አመልካቾችና የወደፊት የዲቪ ማመልከቻዎች መሰረዝንም የሚያካትት ነው። ‹‹ይህ ሕግ ከጸደቀ የአገሪቱ ኢኮኖሚን በከፍተኛ መልኩ በማድቀቅ በእያንዳንዱ ዜጋ ኑሮ ላይ ከባድ ጫና በማድረስ እጅግ አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር ነው››ይላሉ አቶ ኤፍሬም።
ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን የውጪ የፋይናንስ ድጋፎችን እንደምትቀበል የሚገልጹት የምጣኔ ሃብት ምሑራንም፤በትምህርት፣ በጤና፣ በመንገድ ግንባታ ዙሪያ የመሠረተ ልማቶች ግንባታ ለማስቀጠል ብድር ያስፈልጋል።ይህ ረቂቅ አዋጅ ኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ግንባታዋን እንዳታስቀጥል እክል የሚፈጥር ከሆነ ተጎጂው መንግሥት ሳይሆን ተራው ዜጋ ነው›› ይላሉ። ሕጎቹን በሚመለከት አንዳንዶች፣ ሕጎቹ ኢትዮጵያ ላይ ሳይሆን ገዢው መንግሥት ላይ ጫና ማሳደርን ዓላማ ያደረጉ ናቸው በሚል ሙግት ሲገጥሙ ይስተዋላል።ይህን እሳቤ የሚደግፉት እንዳሉ ሁሉ በርካቶች ይቃወሙታል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ግርማ፣ እሳቤው ፍፁም ስህተት መሆኑን በማስረገጥ አምርረው ይቃወሙታል። አንድ መጽሐፍ በሽፋኑ ወይንም በርዕሱ ሳይሆን በይዘቱና ውስጡ ባለው ትሩፋት እንደሚመዘን ሁሉ፣ ይህን ሕግ ጠንቅቆ ለመረዳት ውጪውን ሳይሆን ውስጡን መፈተሽ የግድ ስለመሆኑ አጽእኖት ይሰጡታል።
‹‹እነዚህ ረቂቅ ሕጎች በውጭ ሽፋናቸው ለኢትዮጵያ ሰላም፣ልማትና መረጋጋት የሚያስቡ ይምሰሉ እንጂ ውስጣቸው ሲገለጥና ይዘታቸው ሲፈተሽ በጣም አደገኛ፣የኢትዮጵያን ሕልውና የሚፈታተኑ በእጅጉ የሚያዳክሙ ብሎም የሚጎዱ ናቸውም››ይላል።
እነዚህ ሕጎች ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሆን ተብለው የተቀመሩ ሴራዎች መሆናቸውን የሚያስገነዝቡት አቶ ወንድወሰን፣ ሕጎቹ እንዲፀድቁ እድል መስጠትም የሚጎዳው ፖለቲካውን፣መንግሥትን ወይም ባለስልጣንን ሳይሆን አገርና ሕዝብን ነው››ይላሉ።
ሌላው ቀርቶ ዲያስፖራው ሁሌም ለሚያስብና ለሚወዳቸው ቤተሰቦቹ ገንዘብ እንዳይልክና እንዳይረዳ ብሎም አገሩን እንዳያግዝ የሚያደርጉ መሆናቸውን የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፣ መንግሥትና በአመራር ላይ የሚገኝ ግለሰብን አዳክማለሁ በሚል አገርን ለጥፋት የመዳረግ ግዙፍ ስህተት መሆኑን መረዳት እንደሚያስፈልግም አፅእኖት ይሰጡታል።
አቶ ወንድወሰን፣መንግሥትን በሁለንተናዊ ጫና የማውረድ ፍላጎት በዚህ መልክ ፈፅሞ ስኬታማ እንደማይሆን ምርጫ ተካሂዶ ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው የመረጡትን መንግሥትም በዚህ መልክ የሚወድቅ እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ። ይህን እሳቤ የሚደግፉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኤፍሬም ማዴቦም፣አሜሪካ በተለያዩ አገራት ላይ ማዕቀብ ብትጥልም ስኬታማ ሆና እንደማታውቅ ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ላይ በተቀመረው ረቂቅ ሕግም አሜሪካ ልታሳካ የምትፈልገውን እንደማታገኝ እርግጥ መሆኑን ያሰምሩበታል። መንግሥታት በየጊዜው ቢቀያየሩም አገር ግን እንደማትቀየር እና በውጭ ጣልቃ ገብነትና ሴራ ደካማ መንግሥት ተፈጥሮ ጠንካራ አገር እንደማይኖር ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዝቡት አቶ ወንድወሰንም፣ ሕጎቹ እንዲፀድቁ መፍቀድ ሕዝብና አገር ላይ ከሚያስከትለው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንፃር በኅብረት መረባረብ የግድ እንደሆነም አጽእኖት ይሠጡታል።
በተለይ ዲያስፖራው ሕጎቹን አምርሮ መቃወም እንዳለበትና ኤጀንሲውም ዲያስፖራውን በማስተባበር ረገድ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።
በአሁን ወቅትም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ የአሸባሪው ቡድን ትሕነግ ደጋፊዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተቀመረው ረቂቅ ሕግ ከማስረቀቅ እስከ ማስጸደቅ ተግተው እየሠሩ ናቸው። በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም የኢትዮጵያ ወዳጆችም በሌላ በኩል ፊርማዎችን በማሰባሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ፣ ሕጉን የሚደግፉ የኮንግረሱን አባላት በማነጋገርና ተቃውሞዎችን በማሰማት ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ ከፍተኛ ተጋድሎና በማድረግ ላይ ተጠምደዋል።
ትላንትም በዋሽንግተን ዲሲ ታላቅ ሰልፍ ተካሂዷል። በሰልፉ ላይ ረቂቅ ሕጉ ለአሜሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም መሆኑን ጎልቶ ተስተጋብቷል።
በመላው አሜሪካ ከሚገኙ የኮሙዩኒቲ አደረጃጀት ኃላፊዎች፣ የታስክ ፎርስ፣ የሲቪክ ማኅበራት አመራሮችና ተወካዮች ውይይት ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም፣‹‹በአሜሪካ ኮንግረስ እና ሴኔት በኩል በረቂቅ ደረጃ የሚገኙት ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 በሚል የቀረቡ ረቂቅ ሕጎች ኢትዮጵያውያን በደም መስዋዕትነት ያስከበሩትን ሉዓላዊነት በእጅ አዙር ለመቀማት የተሸረቡ ሴራዎች ናቸውም›› ይላሉ።
ረቂቅ ሕጎቹ ከጸደቁ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖራት የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት በሌሎች ኃይሎች በጎ ፈቃድ እንዲንጠለጠልና ራሷን የማትከላከል ሽባ አገር እንድትሆን የሚያደርግ መሆኑን ያስገነዘቡት አቶ ደመቀ፣ ከዚህም ባሻገር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ወገናችን ጨምሮ ዲያስፖራውን ከእናት አገሩ እና ዘመዱ ጋር የሚያቆራርጡ እጅግ አሳሪ እና ታይቶ የማይታወቅ የሉዓላዊነት መቀሚያ ረቂቅ ሕጎች ናቸውም ነው ያሉት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲም፣ የረቂቅ ሕጎቹ ይዘት ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የሚጎዳና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላገናዘበና አገሪቱ ለሰላም የዘረጋችውን እጅ ከግንዛቤ ያላስገባ››ሲሉ ይተቹታል።
ረቂቅ ሕጉ በይዘት ደረጃ ሲታይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ቀድሞውኑ በኢትዮጵያ መንግሥት የተመለሱ ስለመሆናቸውንም ያስገነዝባሉ።
ሰነዱ በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ አንጻር የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን የተመለከተ ምርመራ እንዲካሄድ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት እንዲኖርና አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ፤ ሶስቱም እንኳር ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ችግር እንደሌለበትና ጥያቄዎቹ እንደተመለሱ ነው ያብራሩት።
‹‹ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት ጦርነት መሆኑ እየታወቀ በአሜሪካ በኩል የአሸባሪን ወገን ደግፎ እንደዚህ ዓይነት ረቂቆችን ማስኬድ ስህተት ነው››ያሉት አምባሳደር ዲና፤የረቂቅ ሕጉ መጽደቅ በአገር አቀፍ ደረጃ ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያደናቅፍ መሆኑንም ሳያመላካቱ አላለፉም።
ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶክተር) በጉዳዩ ላይ ከፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ረቂቅ ሕጉ ኮሚሽኑ ከመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ጋር በጣምራ የጀመረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ነው ያመለከቱት።
‹‹የተፈጠረ ችግር ቢኖር ጉዳዩን በሚመለከታቸው የአገሪቱ ተቋማት መታየት ሲገባው በኢትዮጵያ ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርገው ጥረት ሌላ ቀውስን የሚያመጣ ነው››ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አሁን በኮንግረስ አባላት የቀረበው ረቂቅ ሕግ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን የዓለም አቀፍ ሕጎች መርሕን ያልተከተለ የጣልቃ ገብነት ጫናና የሰብዓዊ መብት ሕጎችን የሚጥስ ነው ሲሉም ገልጸውታል።
እነቶም ማሊኖውስኪ ያረቀቁት ይህ ሕግ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ዝግጁነት ችላ ያለ ከመሆኑም በላይ በአሜሪካና በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ግንኙነት መካከል ሰፊ ስንጥቃትን የሚፈጥርና ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ከግምት ያላስገባም መሆኑም ይገልጻል። የጦርና የደኅንነት ትብብር ማዕቀብ መጣልም ሌላው ሕጉ ለአሜሪካ መንግሥት ከሚሰጣቸው ሥልጣኖች አንዱ ነው።
ረቂቅ ሕጉ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ያላገናዘበና ኢፍትሐዊነት የተስተዋለበት መሆኑንም የሚጠቁሙት አምባሳደር ዲና፣ የሁለቱን አገራት የቆየ ግንኙነት የሚጎዳና የአካባቢውንም ሰላምና ደህንነት ችግር ውስጥ የሚጥል እንደሆነም ነው ያስገነዘቡት።
አስተያየት ሰጪዎች የረቂቅ ሕጎቹ ኢትዮጵያን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የሚጎዱ በመሆናቸው ተቀባይነት እንዳያገኙ በእጅጉ መቃወም እንደሚያስፈልግ አፅእኖት ሰጥተውታል።
ይህን የማድረግ ጊዜው ደግሞ ነገ ሳይሆን ዛሬ መሆን አለበት የሚለውም የጋራ ሃሳባቸው ሆኗል። ሕጎቹ ‹‹ኢትዮጵያን ለማድቀቅ የተቀመሩ በመሆናቸው አምርረን እንድንቃወም ያደርጉናል።
ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረ አደገኛ ጥቃት ካላሰባሰበን፣ ሌላ ምን ሊያሰባስበን አይችልም›› የሚሉት አቶ ወንድወሰን፣በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ተቃውሟቸውን እንዲያጠናክሩም አስገንዝበዋል።
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል አገሪቱ ገጥሟት የነበረውን ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጫና ለመቋቋም ዲያስፖራው ወገናችን ቁርና ፀሐይ ሳይገታው ላሳየው እውነተኛ አገር ወዳድነት ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም፣እነዚህ ረቂቅ ሕጎችም እንዳይጸድቁ ከምንጊዜውም በላይ በተቀናጀ በአንድነት ዘመቻ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስምረውበታል።
መንግሥት እየወሰዳቸው የሚገኙ እርምጃዎች አገርን ያስቀደሙና ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ታሳቢ በማድረግ የሚወሰኑ መሆናቸውን ጠቁመው፣በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ መቼም ቢሆን እንደማይደራደር ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዲጠናከር ሁሌም ዝግጁ መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ሉዓላዊነቷን የሚጋፉ የእጅ አዙር ጥምዘዛዎችን ግን እንደማትቀበል ነው ያረጋገጡት። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲም፣ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።
ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ መቃወም ያለባት ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ጋር ቢዝነስ እየሠሩ ያሉና ለመሥራት በሂደት ላይ ያሉ የአሜሪካ ካምፓኒዎች ጭምር መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ሕጎችን በመቃወም ረገድ መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በተለያየ መድረክ እየተወያየ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ከሴናተሮችና ከኮንግረስ ሰዎች ጋርም ውይይቶች አሉ።
በኢትዮጵያ ላለው የአሜሪካ ኤምባሲም የሕጉ ጠቃሚ አለመሆንና ስለጉዳቱ በየጊዜው እየተገለጸላቸው ነው ብለዋል። የዲያስፖራዎችና ኢትዮጵያውያን ጥረት እንዳለ ሆኖ የመንግሥት ጥረቶች የማያቋርጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የሁለቱን አገር ግንኙነት ለማሻሻል በአሜሪካም በኩል ፍላጎት መኖሩን ያነሱት አምባሳደሩ፤ ረቂቅ ሕጎችን በተመለከተ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ጋር የተወያዩ ሲሆን ረቂቅ ሕጎች በአሜሪካ አስተዳደር በኩል በአሁኑ ሰዓት የሚፈለጉ እንዳልሆን ማወቅ መቻሉንም ነው የጠቆሙት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ብልሃት የተሞላበት ዲፕሎማሲ መከተል እንዳለበት ያስገነዘቡት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ኤፍሬም ማዴቦም በበኩላቸው፣ ‹‹የምንፈልገው የእድገት ደረጃ እስከንደርስ ዓለምአቀፍ ግንኙነታችንና የዲፕሎማሲ ሥራችንን በእልህ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በእውቀት ላይ የተመረኮዘ መሆን መቻል አለበት›› ብለዋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 /2014