‹‹ፀሃይ መማር ትወዳለች›› በሚለው የቴሌቪዥን የሕፃናት ፕሮግራማቸው ይታወቃሉ።የማሕረሰብ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችንም ይሰራሉ።ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን የወሰዱ የሕፃናትና ታዳጊዎች ፊልሞች አዘጋጅም ናቸው።የልጆችን የትምህርት ዘርፍ በማጎልበት የሃያ ዓመት ልምድም አላቸው።
ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ የሕፃናት መጻሕፍትንም አሳትመዋል- የ “ዊዝኪድስ ዎርክሾፕ ሶሻል ኢንተርፕርይዝ” ድርጅት መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ።
ድርጅታቸው (ዊዝኪድስ ዎርክሾፕሶሻል ኢንተርፕርይዝ) ትምህርታዊ የሆኑ ሚዲያዎችን በማዘጋጀትና የሚዲያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የልጆችና ታዳጊዎችን ሕይወት በትምህርት የመቀየር ዓላማን ይዞ በመነሳት ከዛሬ አስራሰባት ዓመታት በፊት ተቋቁሟል።በእነዚህ ዓመታትም ልጆችና ታዳጊዎች በውስጣቸው ያለውን እምቅ ችሎታ የሚያወጡበት መንገድ እንዲመቻች ፈጠራን ባማከለ መልኩ ሲሰራ ቆይቷል።
ይህንኑ ተደራሽ ለማድረግም ሚዲያውንና ቴክኖሎጂውን ይጠቀማል። በተለይ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ አማካኝነት ሥራዎቹን ለበርካታ ልጆችና ታዳጊዎች ተደራሽ በማድረጉ በብዙዎች እንዲታወቅ አድርጎታል።ለዚህም በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ ሳይቆራረጥ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ የቆየውና አሁንም እየታየ ያለው ‹‹ፀሐይ መማር ትወዳላች›› የሚለው የልጆች ፕሮግራም ተጠቃሽ ነው።
በ‹‹ፀሃይ መማር ትወዳለች›› የቴሌቪዥን ፕሮግራም እድሜያቸው ከሶስት እስከ አስር ዓመት የሚደርሱ ልጆችን የአእምሮ እድገት ያማከለና በሰባት ቋንቋዎች የተዘጋጀ ፕሮግራም ይቀርባል፡ ይህም ልጆች ስብእናን፣ የንባብ ክህሎትን፣ ሥነ ምግባርን፣ ጤናንና የተለያዩ ክሂሎቶችን እንዲያዳብሩ በእጅጉ ረድቷቸዋል።
ከዚህ ባለፈ “ዊዘኪድስ” የልጆችን የተለያዩ የእድገትና የእድሜ ደረጃዎችን፣ የቋንቋና የተለያዩ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ በሳይንስና በጥናት የተደገፉ ትምህርቶችን ለልጆችና ታዳጊዎች እያደረሰ ይገኛል።በቅርቡ ደግሞ ወላጆች በኢትርኔት አማካኝነት በልጆቻቸው ስብእና ግንባታ ዙሪያ የተለያዩ ትምህርቶችን የሚቀስሙበትን መንገድ አመቻችቷል። ድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሩክታዊት ‹‹የልጆች እድገት ሲታሰብ ከፅንሰት ጀምሮ ያለውን ሂደት የሚያጠቃልል በመሆኑ የማሳደግ ሥራውም ከዚህ ይጀምራል›› ይላሉ።
በተለይ ደግሞ ከፅንስ ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመት ያለው የልጆች እድሜ ከስብእና ግንባታና አእምሮ እድገት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ወሳኝ ጊዜ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ልጆች ሙሉ ስብእና እንዲኖራቸውና እድገታ ቸውም የተሟላ እንዲሆን ብሎም ሙሉ ችሎታቸውን እንዲጠቀሙ ታዲያ ገና ከፅንስ ጀምሮ እርዳታውና ክትትሉ እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ።
የዚህ እድገት ወሳኞቹና ትልቁን አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ደግሞ ወላጆች፣ አሳዳጊዎችና ብዙ ጊዜያቸውን ከልጆች ጋር የሚያጠፉ ሰዎች ናቸው ይላሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ቀደም ባለው ሁኔታ አብዛኛዎቹ ወላጆች ልጆችን የሚቀርጹት ከፈጣሪያቸው በሚያገኙት ፀጋ፣ ከቤተ ክርስቲያንና ከመስጂድ በሚያገኙት ትምህርት ነበር።ሆኖም በአሁኑ ጊዜ የአኗኗር ዘይቤውና ሕይወት እየተቀየረ በመምጣቱና ዓለም ወደ አነስተኛ መንደር እየተለወጠች በመሄዷ ከዚህ ጋር በሚሄዱ ክሂሎቶች ወላጆች ራሳቸውን ማብቃት ይኖርባቸዋል።
ይህንኑ ለመደገፍም ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በተለይ ደግሞ ከአእምሮ ልሂቃኖች፣ ከሥነ ልቦና ባለሙያዎች፣ ከመምህራን … ጋር በመሆን ለወላጆች በጥናት ላይ የተመረኮዙ እውቀቶችን ዊዝኪድስ ይሰጣል።
‹‹ፀሐይ ለቤተሰብ›› የተሰኘውና ወደ ኮርስ የተቀየረው የቴሌቪዥን ፕሮግራምም ወላጆች በተለያዩ ባለሙያዎችና በተለያዩ ርእሰጉዳዮች ላይ የልጆቻቸውን በራስ መተማመንና የስሜት ክሂሎት ለማሳደግ የሚያስችሏቸውን ብልሃቶች ያገኙበታል።
የወላጅነት ትምህርት ፕሮግራሙ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገና ማንበብና መፃፍ የማይችሉ ወላጆችን ጨምሮ ማንኛውም አሳዳጊዎች በስልካቸው አማካኝነት በድርጅቱ ድረ-ገፅ ውስጥ ገብተው አጫጭር የቪዲዮ ኮርሶችን ለመከታተል የሚያስችላቸው ነው።ወላጆቹ ወይም አሳዳጊዎቹ እያንዳንዱን ኮርስ ከወሰዱ በኋላም ምን ያህል አውቀዋል የሚለውን ለመመዘን የሚያስችል አሰራርም በዚሁ ድረ-ገፅ ላይ ተዘርግቷል፡፡
ይህም ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ የተወሰኑ ኮርሶችን ተከታትለው ከልጃቸው ጋር እንዲሆኑና ራሳቸውም እንዲማሩ የሚያስችለውን ዕድል ይፈጥ ራል።የልጆች ስብእና እድገት የአካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ማህበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና መንፈሳዊ እድገት ውጤት በመሆኑና ይህ እድገት ደግሞ በተለያዩ ክሂሎቶች መደገፍ ስለሚኖርበት ፕሮግራሙ ወላጆች ይህን ክሂል እንዲያገኙም ያስችላቸዋል።
በዋናነት ደግሞ ልጆች በተለያዩ የእድገት ደረጃዎች ምን አይነት ስሜቶችን እንደሚያሳዩ፣ እንዴትስ እነሱን መርዳት እንደሚቻል፣ ምን አይነት ሥነ ልቦና እንዳላቸውና ይህንንም እንዴት ማበልፀግ እንደሚቻል፣ ምን አይነት አካላዊ እድገት እንደሚያመጡና ከነዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ መረጃዎችን ወላጆች ከሕፃናት ሀኪሞች፣ ከሥነ ልቦና ባለሙያዎችና ከአእምሮ ሀኪሞች ሚያገኙበት ነው። በዚህ የክሂሎት ትምህርት ሂደትም ወላጆች የሚሞክሯቸውና ወዲያው የሚተገብሯቸው ሥራዎችና ዘዴዎች ይኖራሉ።
የተለየ ማቴሪያል ሳይገዙ እንዴት ልጆቻቸውን በማንነታቸው፣ በአስተዳደጋቸውና በሁለንተናዊ እድገታቸው ማበልፀግ እንደሚችሉ መንገድ ድረገፁ ያሳያል፡፡ እንደ ወይዘሮ ብሩክታዊት ገለፃ ወላጆች የወላጅነት ትምህርት ፕሮግራሙን ለመከታተል በቅድሚያ http://www.t4f.et በተሰኘው የድ ርጅቱ ድረ-ገፅ ውስጥ ገብተው ይመዘገባሉ።
በመቀጠልም የመረጡትን የልጆች ሥብእና ለመገንባት የሚያስችላቸውን ነፃ የክሂሎት ኮርሶችን ይከታተላሉ።ከ200 ብር ጀምሮ በመክፈል መከታተል የሚፈልጓቸው የሕይወት ክሂሎት ኮርሶችም በድረ-ገፁ ላይ ይገኛሉ፡፡ በድረገፁ ላይ ለወላጆች የሚሰጡት አብዛኛዎቹ ኮርሶች በታዳጊዎች ስብዕና ግንባታ ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ በሥነ ልቦናና ስሜታዊ እድገታቸው ላይ የሚያውጠነጥኑ ናቸው።
ይሁንና በሂደት አካላዊ አድገታቸውን ያማከለ፣ አመጋገብን የሚመለከቱ፣ የሰውነት አጠባበቅን የሚዳስሱና በሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ኮርሶችም በድረ-ገፆቹ እንዲጫኑ ይደረጋል። በተደረገው ምዘና በጣም አስፈላጊ ሆነው የተገኙት ኮርሶች ግን የሥነ ልቦና፣ ስሜታዊና አጠቃላይ የስብእና እድገት ላይ ያተኮረ ነው።
ከኮርሶቹ ባሻገር ሳይንሳዊና በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሁፎችም በድረ-ገጹ እንዲሰፍሩ ተደርጓል።በተመሳሳይ የቴሌቪዥን ፕሮግራምም በድረ-ገጹ ላይ የሚገኙ በመሆኑ ወላጆች በርካታ መረጃዎችን ያገኙበታል፤ ግንዛቤዎ ችንም ይጨብጡበታል።በየጊዜውም ኮርሶች ይጨመ ሩበታል። እስካሁን ድረስ ወላጆች በድረገቱ አማካኝነት የሕይወት ክሂሎት ትምህርት እንዲያገኙ በድርጅቱ በኩል በስፋት ማስታወቂያ ባይሰራም ኮርሶቹ ግን እየተጫኑ ነው።
ድረገጹ በይፋ ሥራ በመጀመሩም በርካታ ወላጆች ከወዲሁ ድረ ገጹን እየተቀላቀሉ ነው።‹‹Tsehay for Family›› በሚለው የድርጅቱ የፌስቡክ ገጽ ላይ ያለውን “ሊንክ” በመጫንም ወላጆች በቀላሉ መመዝገብ ይችላሉ።በዚሁ የፌስቡክ ገጽ ላይም አጫጭር መልእክቶች ይላካሉ።በ7ሺህ 700 የአጭር ጽሁፍ መልእክት አገልግሎትም ይሰጣል።በዚህም ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ ነው።በበርካታ ሰዎችም ዘንድ ልጆቻቸውን በመጠበቅ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ መንገዱን የመፈልግ አዝማሚያም ይታያል።ይሁንና ሰው በዋናነት የተቸገረው መንገዱን እንዴት ማግኘት እንዳለበት ስለሆነ መፍትሄው በዚሁ በኩል ይገኛል። በቤተሰብ ውስጥ በአግባቡ ያልተያዘ ልጅ ከቤተሰብ አልፎ በአካባቢ ብሎም በአገር ላይ ትልቅ መቃወስ እንደሚያስከትል የሚታወቅ ነው።ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ ወላጅ አገርን መጥቀም ማለት ጠንካራ ቤተሰብ መፍጠር ማለት እንደሆነ እየተረዳ መጥቷል።
ይህ መፍትሄ በዊዝኪድስ ዎርክሾፕ ሶሻል ኢንተርፕርይዝ ድርጅት ሲቀርብ ደግሞ ክሂሎቱን አዳብሮ ልጆቹን በመልካም ሥብእና ለማሳደግ ፍላጎት አሳይቷል።በመሆኑ በርካቶችም የዚህ ድረገጽ ቤተሰብ እየሆኑ ይገኛሉ። ይህም በርካታ ወላጆች ንቃት እንዳላቸውና ልጆቻቸውን በእውቀት መደገፍና የተሻለ ነገር ማድረግ እንደሚፈልጉ ያሳያል።ልጆች ከተጸነሱበት ጊዜ አንስቶ አስኪያድጉ ድረስ አስፈላጊውን ምላሽ በተገቢውና በእውቀት በተደገፈ መልኩ ሲሰጣቸው ደግሞ ሙሉ እምቅ ችሎታቸውን ለመጠቀም ይችላሉ።
ይህም በቀጣይ በሰዎች የብቃት ደረጃ ላይ መሻሻል ስለሚያመጣ፤ የሰው ካፒታልም ስለሚፈጠር በአገር ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።ይህን የሰው ካፒታል አቅም ለማሳደግ ታዲያ ሁሉም ከቤቱ መነሳት ይጠበቅበታል፡፡ ወይዘሮ ብሩክታዊት እንደሚሉት በነዚህ ኮርሶች አማካኝነት ወላጆች በየቀኑ በቤታቸው የሚተገብሯቸውን ክሂሎት ያገኛሉ።ከዚህ በፊት ልጆች የሚያድጉበትን የዘልማድ መንገድ በመተው በእውቀት፣ በሳይንስና በተለያዩ ዘዴዎች ለማሳደግ ያስችላቸዋል።
ይህም የልጆችን የተሻለ ብቃት ለማውጣት ይረዳል።የወላጆች ሚናም ልጆች ያላቸውን እምቅ ችሎታ እንዲያወጡ መርዳት ነው።ለዚህ ደግሞ ዊዝኪድስ የጀመረው መንገድ እንደመልካም አጋጣሚ ይቆጠራል። በቀጣይም ዊዝኪድስ ዎርክሾፕ ሶሻል ኢንተርፕርይዝ ድርጅት በልጆች ሥብእና ግንባታና ሌሎችም የታዳጊዎች እውቀት ጭመራ ላይ ያተኮሩ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን የመስራት እቅድ አለው።በተለይ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ሙሉ ሥራዎቹን ዲጂታላይዝ የማድረግ ውጥንም ይዟል።
ከአስር እስከ አስራ ስምንት ዓመት ያሉ ታዳጊዎች የሚጠቀሙበትና ‹‹የጥበብ ልጆች›› የተሰኘ፣ ራሱን የቻለ ድረገጽ በማዘጋጀት ታዳጊዎቹ በሰውነታቸው እድገት፣ በአካባቢያቸው ሁኔታና በተለያዩ ስሜቶች የሚመጡ ጫናዎችን ተቋቁመው ጠንካራ ስብእናቸውን የሚያዳብሩበት፣ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን የሚሰሩበት፣ የአመራር ብቃት የሚያዳብሩበት፣ የሥነ ተዋልዶ ጤናን በሚመለከት የተሻለ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ትምህርታዊ ፕሮግራምም ያዘጋጃል።
በአሁኑ ሰአት ፕሮግራሙ ከኢትዮጵያ ባለፈ በአምስት የተለያዩ የአፍሪካ ቋንቋዎች እየተዘጋጀ ይገኛል።ይህም ልጆች በኢትርኔት አማካኝነት ድምበር አልባ ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። የልጆች እድገትና ማንነት ወላጆች ከሚያደርጉትና እና እነርሱ ከሚሆኑት ይጀምራል።
ወላጆችም የመጀመሪያው የልጆቻቸው መምህራን ናቸው።በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሕይወትና በሥራ ጉዳዮች ተጠምደው በቤት ውስጥ የሚያሳልፏቸው ጊዜያቶች እያነሱ መጥተዋል።ይሁንና ወላጆች ያላቸውን ጊዜ የተሻለ ማድረግ ይችላሉ።ይህንንም በተለያዩ ዘዴዎችና በድረገጽ በተደገፈ መልኩ ዊዝኪድስ መረጃዎችን ለወላጆች እያቀረበ ይገኛል።ወላጆችም በዚህ ረገድ ራሳቸውን በክሂሎት ያበቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ልጅ ማሳደግ ትልቅ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ከመሆኑ አኳያ ምግብ መስጠት፣ ትምህርት ቤት መላክና እቃዎችን መግዛት ብቻ በቂ ባለመሆኑ የልጆችን ማንነት፣ ሥብእና፣ ስሜትና ሥነልቦናን ከመገንባት አኳያ ትልቁ ሃላፊነት የወላጆች ነው።ይህ ተግባር ደግሞ ለትምህርት ቤቶች ብቻ የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ ወላጆች በዚህ ረገድ ራሳቸውን ማስተማር ይጠበቅባቸዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 /2014