በመካከሉ የመለያየት ግድግዳን ያቆመ ማሕበረሰብ እጣ ፈንታው ምን ይመስላችኋል? ያለፉት ታሪኮቻችን ሰላምን በማምጣት ረገድ ምን አይነት መልክ ነበራቸው? እንደ አገር እኚህን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ ይኖርብናል። ሆኖም እንደ አገር በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉን።
አሁን ላይ ችግር እየፈጠሩብን ያሉት እነዛ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ናቸው። ሁሉም ጥያቄ መልስ አለው፤ መልስ እንዳይኖረው ሆኖ የተፈጠረ ጥያቄ የለም። ለጥያቄዎቻችን መልስ ለማግኘት ግን መነጋገርና መወያየት ያስፈልጋል።
እኛ አገር አብዛኞቹ ጥያቄዎች የሚጠየቁት በስሜት ነው፣ የሚመለሱትም በስሜት ነው። በስሜት የተጠየቁ ጥያቄዎች፣ በስሜት የተመለሱ መልሶች በሕዝቦች መካከል የጠብ ግድግዳ ከመፍጠር ባለፈ የሚፈይዱት የለም። መጀመሪያ ስንጠይቅ ጥያቄአችን አገርና ሕዝብ የሚጠቅሙ እንደሆኑ ልብ ልንል ይገባል።
ስንመልስም አገርና ትውልድን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል። ግን ይሄን አይነት የተግባቦት ባህል ስለሌለን ሁሌም በጥያቄዎቻችን ነውጥ እንደፈጠርን ነው።
ሁሌም በመልሶቻችን ችግር እንዳመጣን ነው። በመካከሉ የመለያየት ግድግዳን ያቆመ ማሕበረሰብ ለለውጥ የሚሆን ምንም አቅም አያገኝም። ጥያቄዎቹን ከራሱ ፍላጎትና ዓላማ አንጻር ብቻ የሚጠይቅ ዜጋና ቡድን ራሱን እንጂ ብዙሃኑን ሕዝብ ሊጠቅም የቆመ አይደለም። ስለዚህ ከጥያቄዎቻችን በፊት እናስብ። ከጥያቄዎቻችን በፊት የጥያቄዎቻችንን ዓላማ እንመዝን።
የሰው ልጅ የሥልጣኔ እርምጃ አእምሮው ውስጥ ባለ የማድረግ አቅም የተዋቀረ ነው። አንድ ማሕበረሰብ የአእምሮውን ሃይል ተጠቅሞ ችግሮቹን ማስተካከል ካልቻለ ኋላ ቀር ነው ሊባል ይችላል። የእውቀት ሃይል ሕይወትን ቀላልና ምቹ ማድረግ ነው።
ሥልጣኔ ደግሞ በዚህ የእውቀት ሃይል ውስጥ የሚፈስ የብዙ ማሰብ፣ የብዙ ክህሎት፣ የብዙ ምክክር ስብጥር ነው። ነገር ግን ከእኛ የማሰብ አቅም በላይ ችግሮቻችን ከበረቱ፣ በመነጋገር ሰላምን ማምጣት ካልቻልን እውቀት የለንም ወይም ደግሞ እውቀታችንን በትክክል እየተጠቀምንው አይደለም ማለት ነው።
ይህ ደግሞ ልንመልሳቸው የሚገቡ በርካታ የቤት ስራዎች እንዳሉን አመላካች ነው። የእኛ አገር አሁናዊ ገጽታው ይሄን እውነት የተጋራ ነው፤ ምክንያቱም ችግሮቻችን እየበለጡን ነው፤ ለሰላም የሚሆን አቅም እያጣን ነው፤ ለብዙ ነገር በራችንን ስንከፍት ለውይይት ግን አሻፈረኝ የምንል ነን።
ታዲያ ሥልጣኔያችን የቱ ጋ ነው? ቀደምትነታችንስ ምኑ ጋ ነው? በዚህ ረገድ ራሳችንን ማየት ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ ያለፉት ሃምሳ ዓመታት በቂና ከበቂ በላይ አስተማሪዎቻችን ናቸው። መማር ብንችል የሚያስተምሩን በርካታ የመከራ ታሪኮች ነበሩን፤ ግን እየተማርንባቸው አልመጣንም።
እናም መለወጥ አለብን፤ በውይይት ጥንታዊነታችንን እንመልስ፤ ባጣነው ሰላም ምትክ ሥልጣኔን እንጀምር። ችግሮቻችን ከእኛ በላይ ሳይሆን እኛ ከችግሮቻችን በላይ ሆነን ለትውልዱ መድህን እንሁነው።
ዝም ብለን እኮ ፊተኞች አልሆንም። ቀዳሚነት እኮ ዝም ብሎ አይገኝም። ከሰው ልጅ መጀመሪያነትን፣ ከፍጥረት ብኩርናን ያገኘንው እኮ ጥንት ዓለም ባንቀላፈችበት ዘመን በመንቃታችን ነው። አለም ግራ በተጋባችበት ጊዜ ለችግሮቻችን መላ ስለዘየድን ነው።
አለም ህግና ስርዐት ሳይኖራት እኛ በህግና በሥርዓት ስለተተዳደርን ነው። ዛሬ ያ ጥበባችን የት ሄደ? ዛሬ ያ የአባቶቻችን የምክክርና የውይይት ልማድ የት ገባ? እኛ ነን ወይስ ፖለቲካው ተጠያቂ፤ ማን ነው ለዚች ውጥንቅጧ ለወጣ አገር ሃላፊነት የሚወስድ? እንቃ! የአባቶቻችንን ጥበብ እናስብ። እኛ ከተዘጋጀን፣ በራችንን ለውይይት ክፍት ካደረግን መስማማት ያቅተናል ብዬ አላስብም።
ለአገራችን ሰላም በማምጣት፣ ለትውልዱ እርቅን በማስቀመጥ የተበላሸ ታሪካችንን እናድስ። በሃምሳ ዓመታችን የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ የተበላሹና የተወለጋገዱ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሽኩቻዎቻችንን ወደ ተግባቦት በመቀየር ለራሳችን ውለታ እንዋልለት።
አንድ አገርና ሕዝብ ችግሮቹን በውይይትና በመነጋገር የማይፈታ ከሆነ ገና ሥልጣኔ ላይ እንዳልደረሰ የሚያሳይ ነው። ምንም ያክል የበረታና ወደ ፊት የቀደመ ትውልድ ቢሆንም በችግሮቹ ላይ የበላይ የሆነ የሰላም ሃይል ከሌለው ኋላ ቀር ነው የሚባለው። ዛሬ ላይ ከማንም ፊት ተፈጥረን ኋላ የቀረነው ሃይላችንን በማይጠቅመን ነገር ላይ ስላዋልነው ነው። የጥላቻ ሃይል አደገኛ ነው። የመለያየት መንፈስ ክፉ ነው።
በዚህ ነውረኛ ሃይል ውስጥ ለዘመናት ተጉዘናል። የሰው ልጅ ስለመለያየት የሚያስብ ከሆነ በውስጡ የፍቅር ሃይል መሞት ይጀምራል። ላለመስማማት የሚነጋገር ከሆነ የሰላምን ስፍራ አይደረስበትም። በውስጣችን የጥላቻን ዘር ስንዘራ የፍቅርን ዋርካ ነቅለን እንጥላለን።
ፍቅር የሌለው አካልና ነፍስ ደግሞ እንስሳዊ ባህሪን የተላበሰ ነው፤ ከሥርዓት በታች ነው። የነዚህ ሁሉ ፍጻሜ ደግሞ ሰላም አልባ አገርና ሕዝብ መፍጠር ነው። እናም ሞታችንን በፍቅር መግደል ይኖርብናል። ሰላማችንን በውይይት መመለስ ደግሞ ለነገ የማንለው የጋራ ጉዳያችን ነው። አእምሮ በአፍራሽ ሃሳቦች ሲጠቃ የመስራት፣ የመለወጥ፣ የመነጋገር ባህሉን እያጣ መገፋፋትን ልምድ እያደረገ ነው የሚሄደው።
ሰውነት እውነትን ሲሸሽ የመጥፎ ነገር ባሪያ ነው የሚሆነው። ይሄ እውነት ደግሞ ከጥንት እስከዛሬ በእኛ አገር ላይ ነበር። ምንም እንኳን ለውጭ ጠላቶቻችን የማይበገር የአንድነት ክንድ ቢኖረንም እርስ በርስ ግን በብዙ ነገር ላይ ሆድና ጀርባ ሆነን ሰንብተናል። የተራመድንባቸው አያሌ የታሪክ ዳናዎች በጦርነትና፣ በመለያየት እኩይ ሰንበር ያወጡ ነበሩ። አሁን ሌላ ማንነትን መላበስ አለብን።
በዚህማ በዚያም የሚነሱትን የሃሳብ ተቃርኖ ለጦርነት ሳይሆን ለልማት፣ ለመለያየት ሳይሆን ለአንድነት ልንጠቀምባቸው ይገባል። ለውይይት የተቀባ፣ ለምክክር የሰለጠነ አእምሮ ያስፈልገናል። ልዩነቶችን ተቀብሎ የሚያስታርቅ፣ አስታርቆም ለአገር እሴት የሚጨምር ሕዝብና መንግሥት ያሻናል። መክሮና አስታርቆ፣ አዋዶና አስተቃቅፎ አንድነትን የሚያመጣ ሥርዓት ይናፍቀናል። ይሄ እንዲሆን ደግሞ አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ይሆናል።
መንግሥት የታየውን ማየት አለብን። በዚህ የመነቃቃት ዘመን ላይ ወደ ኋላ ሊያስቀሩን ከሚችሉ ማናቸውም ነገሮች መታገስ አይኖርብንም። ብሄራዊ ምክክሩ ለአገራችን ያስፈልጋታል። ለአገራችን ብቻ አይደለም፤ ለእኔም ለእናተም ያስፈልገናል። ላለፈው፣ ላለውና ለሚመጣው ትውልድም ያስፈልገዋል።
ብዙዎቻችን ባለፈ ታሪክ ተገፋፍተን እናውቃለን፤ ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም ሲል ይቅርታን በማስተማር ያስተቃቅፈናል ብዬ አምናለው። አሁን ባለን ታሪክ ተቀያይመን የቆምን አለን፤ ይሄንንም በማስማማት ብሄራዊ ምክክሩ የላቀ ዋጋ አለው። ብሄራዊ ምክክሩ የማይገባበት የማሕበረሰብ ክፍል የለም። ያለፉ ችሮቻችንን ከመፈተሽ ጀምሮ ለሚመጣውም ዋስትና የሚሆን ነው። በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማሕበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ሁሉ ሚና ያለው ምክክር ነው፣ ለአገራችን በብዙ መልኩ ያስፈልጋታል። መንግሥት ጀምሮታል እኛ ዜጎች ማስቀጠል አለብን።
እንደ እኔ ሃሳብ ይሄ የምክክር መድረክ ከዛሬ ብዙ ዓመት በፊት ተጀምሮ ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ ኪሳራ ባልደረሰብን ነበር። እኛ ጀምሮ ማቆም ልማዳችን ነው፤ እስከዛሬ ብዙ ነገሮችን ጀምረን አቁመን እናውቃለን፤ ከእንግዲህ ግን በኢትዮጵያ ስም ተጀምሮ የሚቆም ነገር መኖር የለበትም። የዚህን አገራዊ የምክክር ፍሬ ሳንበላ መቆም የለብንም።
ይልቁንም በችግሮቻችን ላይ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት በሰላም ጥላ ስር ማረፍ አለብን እላለሁ። ሰላም እንሻለን፤ ምክንያቱም የመከራን ጥጉን አይተነዋል። በዚህ አገራዊ ምክክር የጦርነት ጉዟችንን የሚያበቃበት፣ በመነጋገር የምናተርፍበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ምድር የሰላም ጸሀይ ፈንጥቃ የምናይበት እንደሚሆን ብዙዎቻችን ተስፋ አለን።
ተስፋዎቻችን ብርሃን እንዲፈነጥቁ ልዩነታችንን ወደ ጎን ብለን በሚያግባቡን የአንድነት ሃሳቦች ላይ መወያየት ይኖርብናል። የመንግሥትን ምከረ ሃሳብ በመቀበል ሰላሟ የበዛ አገር መፍጠር ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። በስይጥንና መሰልጠን የለም፤ በሰላም እጦት አገር እየታመሰች፣ ባለመግባባት ህዝብ እየተገፋፋ ወደ ፊት መራመድ ዘበት ነው። ልንደርስበት ላሰብንው የስኬት ጉዞ አንድነት ያስፈልገናል።
ተወያይቶ መግባባት ግድ ይለናል። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ የምንፈጥረው አንዳች አገራዊ በረከት የለም። በመሆኑም ወደ ነገ ለመሄድ የዛሬ ጎዳናዎቻችንን እንጥረግ፤ ወደ ከፍታ ለመውጣት ባለመስማማት የተራመድንባቸውን እነዛን የመለያየት ትናንትናዎች በይቅርታ እንመለስባቸው። እንደኛ አገር ፖለቲከኛ ስለ ሰላም የተናገረ የለም። እንደእኛ አገር አዝማሪ ስለ ሰላም ያዘመረ የለም።
እንደእኛ አገር ዘፋኝ ስለ ሰላም የዘፈነ የለም፤ ሁሉም ግን ሰላምን ማምጣት አልቻሉም። ምክንያቱም በልዩነት ውስጥ ተግባብቶ አንድ መሆንን ሃብታችን ስላላደረግን። እንደእኛ አገር የሃይማኖት አባት ስለ ሰላም የሰበከ የለም። እንደእኛ አገር አክቲቪስት ስለ ሰላም የደሰኮረ የለም፤ ሁሉም ግን ሰላምን ለማምጣት የከፈሉት ዋጋ ኢምንት ነው።
ሰላም ስፍራው ውይይት ውስጥ ነው። ሰላም ስፍራው በመተው ውስጥ ነው። ዓለም ላይ ከትናንት እስከ ዛሬ ጦርነት ያልተካሄደባቸውን ጊዜአቶች ቢቆጠሩ እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ዓለም ከትናንት እስከዛሬ በብዙ ችግርና ጦርነት ውስጥ ናት።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች፣ እነዚህ ሁሉ ጦርነቶች ባለመግባባት የተፈጠሩ መሆናቸው ደግሞ የሰው ልጅ ምን ነካው የሚያስብልን ጥያቄ ያስነሳሉ። ዛሬ ላይ በሰላምም ሆነ በኢኮኖሚ ራሳቸውን ከፊት ያቆሙ አገራት ለውይይት በራቸውን የከፈቱ ናቸው። ብዙዎቻችን ላለመስማማት ዋጋ የምንከፍል ነን። ሰው እንዴት ላለመስማማት ዋጋ ይከፍላል? ዋጋ መክፈል ያለብን ለመስማማት ነው።
ለመስማማት ዋጋ መክፈል የአስተዋይ መንግሥት፣ የአስተዋይ ማሕበረሰብ መገለጫ ነው። በመሸነፍ ውስጥ ያለውን ማሸነፍ የሚያውቁት ጥቂት ልባሞች ብቻ ናቸው። ብዙዎቻችን ይሄን እውነት አልተገነዘብነውም። ከእንግዲህ ላለመስማማት ዋጋ መክፈል አይኖርብንም፤ ከእንግዲህ ለማሸነፍ ብቻ መወያየት አይኖርብንም፤ በአሸናፊ ሃሳብ መረታትንም ልምድ ማድረግ ይኖርብናል።
ምክንያቱም የብሄራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ በመግባባት ሰላም ማምጣት ስለሆነ ነው። ሰላም ልዩነትን በማጥበብ የሚመጣ ነው። ሰላም በመግባባት እንዲመጣ ሆኖ የተፈጠረ ነው። በየትኛውም የዓለም ታሪክ ሰላምን በጦርነት ያመጣ አገርና ሕዝብ የለም። ወደ ፊትም አይኖርም። ሰላም በጦርነት ይመጣል ብለው የሚያስቡ እነሱ ደካማዎች ናቸው።
እንደዚህ አይነት አስተሳሰቦች የሚፈጠሩት ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ባልዘመነና ባልሰለጠነ አእምሮ በኩል ነው። እኛ ብቻ ነን በጦርነት ሰላምን ለማምጣት ስንሞክር የኖርነው። እኛ ብቻ ነን በመለያየት ውስጥ አገር ለመገንባት ስንጥር የነበረው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ይሄን እውነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ የታሪክ ድርሳናት ናቸው። እነዚህ ዘመናት እንድንማርባቸው የተሰጡን ይመስለኛል። ብንማርባቸው እንደ እኛ የሚያተርፍ ማንም አይኖርም። ምክንያቱም ለዘመናት ስንከስርባቸው ኖረናልና ነው። ልብ ካለንና አይናችንን ገልጠን ማየት ከቻልን ዛሬ ላይ የሰላምን ዋጋ ሊያስተምሩን የሚችሉ በእኛው አገር የተከሰቱ አያሌ የመከራ ትዕይንቶች በዙሪያችን አሉ።
እንማርባቸው፤ እንለወጥባቸው። የሰላም ስፍራው መነጋገር ብቻ ነውና በውይይት ማሸነፍን እንልመድ። ለዚህም ለዘመናት በመካከላችን የገነባናቸውን የጠብ ግድግዳዎች ማፍረስ፤ ሞታችንን በፍቅር ገድለን ማሸነፍ ግድ ይለናል። ይሄን በማድረግም ወደ ከፍታ በአንድነት የምንሄድባቸውን የሰላም ድልድዮች መገንባት ይጠበቅብናል። በዚህ የምክክር እድል ተጠቅመን ለራሳችንም ሆነ ለትውልዱ የሰላም አዋጅ እናውጅ እያልኩ ላብቃ። ቸር ሰንብቱ!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 /2014