የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም ከፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር በአዋጅ ቁጥር 1162/11 እና መመሪያ ቁጥር 3/2011 መሠረት ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሒዱና የሠነድ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ተገልጾላቸዋል። ሆኖም ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን አጠናቀው ባለማቅረባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ እና ለቦርዱ እንዲያስገቡ በማለት ቦርዱ ጠቅላላ ጉባኤ ያላካሄዱ እና የሰነድ ማሻሻያ ያላደረጉ አገራዊም ሆነ ክልላዊ ፓርቲዎች ጉባኤ አድርገው ሰነዳቸውን እንዲያሻሽሉ ማሳሰቢያ ከሰጣቸው ፓርቲዎች መካከል አንዱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ነው።
ፓርቲው የተላለፈውን ማሳሰቢያ ተከትሎ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሔደ ሲሆን፤ በፓርቲው ውስጥ ለውጦች እንደነበሩ ተገልጿል። የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ በሚመለከት እና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይ የሠላም እና ደህንነት ጉዳይን እና ኢኮኖሚው ላይ ያላቸውን አቋም እንዲሁም ፓርቲው እየሠራ ያለውን ሥራ በሚመለከት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በቀድሞ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አሁኑ አዲስ በተዋቀረው ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ደግሞ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጋሻው መርሻን አነጋግረን እንዲህ አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- እርግጥ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክልላዊም ሆኑ አገራዊ ፓርቲዎች እስከ መጋቢት 9 ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ ብሏል። ከምርጫ ቦርድ ማሳሳቢያ ሌላ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መጋቢት 11 ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሔደበት ተጨማሪ ምክንያት አለው? ወይስ የምርጫ ቦርድን ትዕዛዝ ብቻ ተከትሎ ነው? ጥያቄያችንን ከዚህ እንጀምር ?
አቶ ጋሻው፡- ትክክል ነው። ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች አስገዳጅ ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ነበር። እስከ መጋቢት 9 ጉባኤው መካሔድ ነበረበት ቢልም እኛ ግን ቀደም ብለን ለመጋቢት 11 እያመቻቸን እንደነበር የገለፅን በመሆኑ አስገዳጅ ቢሆንም በመጋቢት 11 እንድናካሂድ ተፈቅዶልን አካሂደናል። ምርጫ ቦርድ እንዲሻሻሉ ያላቸውን ደንቦች በማሻሻል ጉባኤያችንን አጠናቀናል።
አዲስ ዘመን፡- ከ11 ወር በኋላ በድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ ታካሂዳላችሁ የሚል መረጃ አለ። ለምን አሁን ማጠቃለል አልተቻለም? የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የምርጫ ዘመን የሚጠቃለለው በዛ ጊዜ ስለሆነ ነው? ወይስ የተለየ ሌላ ምክንያት አላችሁ?
አቶ ጋሻው፡- በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የፓርቲው ደንብ እያንዳንዱ የምክር ቤት አባል የሚቆየው ለሶስት ዓመት ነው ይላል። ከየካቲት 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት 2015 ዓ.ም ድረስ መቆየት አለበት። ለዚህ ደግሞ የሚቀረው 11 ወር ብቻ ነው። ከዛ በኋላ የእዚህኛው ብሔራዊ ምክር ቤት የሥራ ዘመን ስለሚያልቅ እንደአዲስ ብሔራዊ ምክር ቤት መዋቀር ስላለበት በዛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ የምናደርግ ይሆናል።
የአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤ ግን ምርጫ ቦርድ ሁሉም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ በአስገዳጅነት በማስቀመጡ ብቻ የተካሔደ ነው። ምርጫ ቦርድ ባለው መሠረት ቢያንስ 500 የፓርቲ አባላት በተገኙበት መካሔድ አለበት ማለቱን ተከትሎ አንዳንዶቹ ቀን ከተጨመረላቸው ውጪ ሁሉም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ አድርገዋል። ሌሎችም አሁንም ድረስ እያካሔዱ ነው። እንደሌሎቹ ሁሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲም ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጓል። በፓርቲው ደንብ እና ሥነሥርዓት መሠረትም ከ 11 ወር በኋላ ጉባኤውን ያካሒዳል። በዛ ጊዜ የአመራር ለውጥ መደረግ ስላለበት በዛ ጊዜ የምናደርገው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የአሁኑን ጠቅላላ ጉባኤ ሲያካሒድ በምን በምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ተወያየ? የድርጅቱን ቁመናስ እንዴት ቃኛችሁት?
አቶ ጋሻው፡- እንዳልኩት ጉባኤው አስገዳጅ የምርጫ ቦርድ ጉባኤ ስለሆነ እርሱን ተከትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወነ ስለሆነ ሰፊ ግምገማ ማድረግ የሚያስችል አይደለም። ለመሰብሰብ ያህል የተካሄደ ብቻ ነው። አንዳንድ ማስተካከል ያለብንን የደንብ እና የሥርዓት ጉዳዮችን ማስተካከል ስለነበረብን አስተካክለናል። ከዛ ውጪ በጥልቀት ያየናቸው ነገሮች የሉም።
ነገር ግን ለሁለት ዓመት ፓርቲው የመጣበትን አፈፃፀም ገምግመናል። እንዲሁም ከመንግሥት ጋር አብሮ መሥራት እና አለመስራት በሚለው ጉዳይ ላይ አጀንዳዎች ተነስተው እርሱንም በጥልቀት ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ለማየት ተሞክሯል። እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫን በሚመለከት ምን መደረግ አለበት? የምንሄደው ወዴት ነው? በሚለው ላይም መነጋገር ችለናል። የምርጫ ቦርድ ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል ያላቸው የደንብ አንቀፆች ተነስተው እነርሱ ላይ ውይይት ተደርጎ ፀድቀዋል። ጉባኤው የአንድ ቀን ጉባኤ ስለነበረ ያነሳነው እነዚህን ጉዳዮች ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ፓርቲዎች የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ን ጨምሮ ከምርጫው በኋላ ተቀዛቅዘዋል አይሰሩም ይባላል። እናንተ በትክክል እየሠራን ነው ትላላችሁ? በተለይ ከወቅቱ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር እየሠራችሁ ነው?
አቶ ጋሻው፡- ምርጫ ላይ ፓርቲዎች ስለሚሠሩ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታው ሞቅታ ውስጥ ስለሚገባ ሰዎች ሁሉ ትኩረት ሲሰጡ የፓርቲዎች እንቅስቃሴም ሕይወት ያገኛል። አጠቃላይ ፓርቲዎች ምን እየሠሩ እና ምን እያሉ ነው የሚባለው እና ጆሮ የሚሠጠው በዛ ጊዜ ነው። ምርጫ ካለፈ በኋላ ግን ሕዝቡ ወደ ሌላ ሥራ ስለሚዞር የፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የማየት ሁኔታው ዝቅ ይላል። አንደኛው ምክንያት ይሔ ነው።
ሌላው ደግሞ የምረጡኝ ቅስቀሳ ስለሚኖር ቅስቀሳውም በአደባባይ በየመድረኩ እና በየቴሌቪዥን ጣቢያው ስለሚካሔድ፤ ፓርቲዎቹም በዛ ጊዜ በአጠቃላይ ስትራቴጂያቸውን ስለሚያስተዋውቁ፤ እነዚህ ደግሞ ሞቅታ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ልክ እግር ኳስ ውድድር ሲኖር ወሬው ሁሉ ስለእግር ኳስ እንደሚሆነው ሁሉ ምርጫ ሲኖር ወሬው ሁሉ ስለፓርቲዎች ይሆናል። የዋንጫ የእግር ኳስ ጫወታ ካለቀ በኋላም ጫወታ ይኖራል። ነገር ግን ወሬው የመታየታቸው መጠንም ሆነ የሰዎች አጠቃላይ ትኩረት እንደዋንጫው ጊዜ አይሆንም። የፓርቲዎች ጉዳይም ተመሳሳይ ነው። ፓርቲዎቹ ከምርጫው በኋላም ሥራቸውን ይቀጥላሉ፤ ቡድን እያደራጁ ያሰለጥናሉ ይሠለጥናሉ። ሌሎች ሥራዎችንም ይሠራሉ። ነገር ግን ሰዎች ትኩረት ላይሰጡ ይችላል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ምርጫ ካለፈ በኋላ የአባላት ሥልጠና ላይ የአባላት ጥራት ላይ ተሻጋሪ በሆኑ ሥራዎችን እና አጠቃላይ ስትራቴጂክ የሆኑ ሥራዎች ላይ ሲሠራ ነበር። ፓርቲዎችም በተመሳሳይ መልኩ ይሠራሉ። ሰዎች ይህ ሲሰራ ላያዳምጡ እና ላያውቁ ይችላሉ። ነገር ግን እየሠራን ነው። ወደ ፊትም እንሠራለን። በእኔ እምነት ከምርጫ በኋላ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተቀዛቀዘ ፓርቲ ነው ብዬ አልገምትም።
አዲስ ዘመን፡-ከወቅቱ ተለዋዋጭ የፖለቲካ አንፃር ስል ሰላም እና ደህንነት ላይ ምን አላችሁ?
አቶ ጋሻው፡- በአጠቃላይ አገሪቱ በፖለቲካ ችግር ውስጥ ናት። በኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት አለ። ሰዎች ይፈናቀላሉ። በአደባባይ በጅምላም ሆነ በግል ሰዎች ይገደላሉ። ይሔ አገራችን የገባችበት ችግር ነው። ይህንን ችግር የተወሰኑ አደረጃጀቶች እና የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ የሚፈቱት ችግር አይደለም። ይህንን መፍታት የሁላችንም ሃላፊነት ነው። ችግሩን ያመጣነው ሁላችንም ነን፤ የመፍትሔው አካልም መሆን ያለብን ሁላችንም ነን የሚል እምነት አለኝ።
ሁላችንም ሕዝባችን በችግር ውስጥ መሆኑን መካድ የለብንም። መውጣት፣ መግባት እና ተንቀሳቅሶ መሥራት አይቻልም። በጣም ትንንሽ የተደራጁ ቡድኖች በየሠፈሩ ሕዝባችን ላይ መከራ እየደገሱ እና እያደረሱ ነው። እነዚህ ችግሮች በሁላችንም ትብብር መቀረፍ እንዳለባቸው አፅዕኖት ሰጥቼ እናገራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ልክ ንዎት! እዚህ ላይ የሁላችንም ሚና መኖር አለበት። ነገር ግን ለችግሩ መቃለል መንግሥት የአንበሳ ድርሻ አለው። ወረድ ሲል እናንተ ፓርቲዎችም ሚናችሁ ከሌላው ማሕበረሰብ የግድ ከፍ ያለ ነው። እዚህ ላይ ምን ትላላችሁ?
አቶ ጋሻው፡- እውነት ነው። እኛ አጀንዳ በተፈጠረ ቁጥር መግለጫ እንድንሰጥ ይጠበቃል። እዚህ አገር በየቀኑ የተለያየ አደጋ ይፈጠራል፤ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥማሉ። ለእነርሱ ሁሉ መግለጫ ተሰጥቶ እና ጥያቄ ቀርቦ የሚዘለቅ አይደለም። ምክንያቱም በየቀኑ ችግር ያጋጥማል። በየቀኑ ማሕበራዊ ሚዲያውን አጠቃላይ ሚዲያውን የሚቆጣጠር ነገር ያጋጥማል። ስለዚህ ሁሉም ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እና ጥያቄ ቀርቦ ተወያይቶ መግለጫ መሥጠት የሚቻል አይደለም። በተቻለ መጠን በተመረጡ እና ጉልህ በሆኑ መግለጫ ብንሰጥባቸው ሊቀየሩ በሚችሉ ነገሮች ላይ መግለጫ እንሰጣለን።
ነገር ግን በእያንዳንዱ ላይ መግለጫ እንስጥ ካልን የፓርቲ ፖለቲካን ትተን አክቲቪስት ሆንን ማለት ነው። ይሔ የአክቲቪስት ሥራ ነው። እኛ የፓርቲ ፖለቲካ ነን። ግልፅ ግብ እና ታክቲካል አካሔድ አለን። ስለዚህ በዚህ ጊዜ እዚህ ቦታ ላይ እንደርሳለን ብለን መሥራት የሚገባንን ነገር እንሠራለን። ለእያንዳንዱ ነገር እንናገር እንሳተፍ ካልን እና ያንንም ካደረግን ግን ሥራችን የአክቲቪስት ይሆናል። ነገር ግን ያንን ሚና መወጣት ያለባቸው አካላት ሊኖሩ ይችላሉ። ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ይህንን ሚና ሊጫወት ይችላል።
ነገር ግን ከፓርቲያችን በተጨማሪ እንደግለሰብ ሃሳብ የምንሰነዝርባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በፓርቲ ደረጃ ደግሞ ስትራቴጂክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ታክቲካል በሆነ መንገድ ትኩረት ሰጥተን እንንቀሳቀሳለን። በእኔ እምነት አሁን እየታየ ያለው ችግር መንስኤው መንግሥት ብቻ አይደለም። መንግሥት የሚገባውን ያህል እየሠራ አይደለም ? አዎ ትክክል ነው እየሠራ አይደለም። ከዚህ በላይ ማድረግ ነበረበት? አዎ ነበረበት። ነገር ግን ደግሞ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ችግር መፍታት ያለበት በመንግሥት ብቻ ነው ተብሎ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም። በጠቅላላ እያንዳንዳችን ከኛ ምን ይጠበቃል ብለን ሁላችንም መሥራት የሚገባንን መሥራት አለብን። ዝም ብለን ለመንግሥት ከተውነውና በመንግሥት ብቻ ካሳበብን ማሕበረሰቡ ጋር ሲመጣ ቆይቶ እያንዳንዳችን እኔም ሆነ አንቺ ጋር መምጣቱ አይቀርም። ሁላችንም የችግሩ መፍትሔ ለመሆን መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ።
መንግሥት አንዳንዴ ግዴለሽ በሚሆንበት ጊዜ መመለስ፣ አቅጣጫ ማሳየት እና ማስጨነቅ ሲያስፈልግም ማስጨነቅ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። እንጂ በሆነ ባልሆነው እየሔዱ ‹‹ና ግጠመኝ›› ማለት ይህች አገር ካለችበት ሁኔታ አንፃር የሚበጅ አይደለም። ስለዚህ የችግሩ የመፍትሔ አካል መሆን አለብን ብዬ አምናለሁ። ችግር ለመፍታት ተብሎ የበለጠ ችግር መፍጠር አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- ትክክል ነዎት! በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት አይገባም። ነገር ግን አሁን በጉባኤያችሁ ላይ የወቅቱን የሠላም እና ደህንነት ጉዳይ አይታችሁታል። ተወያይታችሁበታል ? ስለኢኮኖሚውስ ምን እያላችሁ ነው? ሕዝቡ ከእናንተ ብዙ እንድትሉ ይጠብቃል። በተለይ የኑሮ ውድነቱን በሚመለከት ፓርቲያችሁ ምን ይላል?
አቶ ጋሻው፡- ልክ ነው የኑሮ ውድነቱ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ነው። ድህነቱም እየተስፋፋ ነው። አሁን ብዙ ሰው በአስቸጋሪ የኑሮ ቅርቃር ውስጥ ይገኛል። በጣም ፈጣን ማስተካከያ ካልተደረገበት አገር የሚያፈርስ ጉዳይ ነው። ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ ፈጣን እርምጃ እና ማስተካከያ ይፈልጋል። በመንግሥትም ሆነ በንግዱ ማሕበረሰብ በኩል ማስተካከያ መኖር አለበት ሲባል፤ ያሉ አሻጥሮች መቆም አለባቸው፤ አንዳንድ ሸቀጦችን የሚይዙ ካልተስተካከሉ አደጋው የከፋ ይሆናል።
በዋናነት ትልቅ የሆነ የምሁራን ውይይት እና ክርክር ያስፈልጋል። የአገራችን ኢኮኖሚ ወዴት መሔድ አለበት? የሚለው ላይ ብዙ ማሰብ እና መወያየት ይስፈልጋል። ምክንያቱም ይህች አገር በጣም ትልቅ ናት። ከ10 ያላነሰ ሕዝብ የሚኖርባት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ይህች አገር ብትበተን ምናልባትም ሕዝቡ ዓለምን የሚያጥለቀልቅ ይሆናል። የፀጥታ ሁኔታው አለመረጋጋት ላይ የኑሮ ውድነቱ ተጨምሮበት አገሪቷን ወደ ከፋ ሁኔታ እንዳያደርሳት መንግሥት ግዴታውን መወጣት አለበት። የንግዱ ማሕበረሰብም መሥራት መቻል አለበት። እንዲሁም ሁላችንም ታትረን የምንሠራ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የሠላም እና ደህንነት ጉዳዩ ላይም ሆነ ኢኮኖሚው ላይ እያጋጠመ ያለውን ችግር በሚመለከት ማለትም የኑሮ ውድነቱ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ሚናውን የሚወጣው እንዴት ነው?
አቶ ጋሻው፡- ከሚመለከታቸው አካላት ውስጥ እኛ አንዱ ነን እንጂ ብቸኛዎቹ አይደለንም። ይሔ በአገር ውስጥ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታን የሚመለከት ነው። በእኛ በኩል የሚጠበቅብንን ሁሉ የምናደርግ ይሆናል። አባላቶቻችን ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ማሕበረሰብ ለምሳሌ የፀጥታ ጉዳይ ላይ ግጭት እንዳይፈጠር የሚሠራ ማሕበረሰብ እንዲኖር ጥረት እናደርጋለን። ግጭት ሲኖርም ለማስታረቅ የምንሠራ ይሆናል። አባሎቻችን ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቡም በሥነምግባር የሚመራ እንዲሆን ፓርቲያችን የሚሠራ ይሆናል። ታታሪ የሆነ ማሕበረሰብ መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ። ከአንድ ፓርቲ የሚጠበቀውን በሙሉ እንሠራለን። የበቃ እና የነቃ ታታሪ ማሕበረሰብ የመፍጠር ራዕይ እንዳለን አስቀምጠናል። በዛው መልኩ የምንሠራ ይሆናል። እርሱን ለማሳካት የምንችለውን ሁሉ የምንሠራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ
አቶ ጋሻው ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ.ም