ቀድሞ በየሱቁ ደጃፍ ፀሐይ እየመታውና አቧራ እየለበሰ ስናይ ለጤናችን ነበር የምንሰጋው። ምክንያቱም ለምግብነት የሚውል ነገር ሁሉ በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበት የጤና ባለሙያዎች አበክረው በማስጠንቀቅ ምክር ቢሰጡም፤ ምክሩን ከቁብ ቆጥሮት በተግባር የሚያውለው ቁጥሩ የበዛ አይደለም።
ሻጩም ሸማቹም በዕለት እንቅስቃሴ ላይ ነው የተጠመደው። ጥንቃቄ በጎደለው አያያዝ በየሸቀጣሸቀጡና አልፎ አልፎም በአንዳንድ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ከጠረፍ አካባቢ እየመጡ በየአስፓልቱ ዳር ቀኑን ሙሉ ፀሐይ ላይ ለሽያጭ ቀርበው ይስተዋሉ የነበሩ የምግብ ዘይቶች አሁን ላይ ስለጤና ስጋትነታቸውን ልናነሳቸው ቀርቶ ለአይናችን እንኳን ብርቅ ሆነውብናል።
‹‹የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል›› እንዲሉ፣ በመንገድ ስንሄድ እንኳን የሸቀጣሸቀጥ ሱቆቹ ከደረደሩት ዕቃ መሃል ከርቀት አንጋጠን የምናየውና የምንፈልገው ከመደርደሪያቸው ላይ ዘይት መኖሩን ነው። አነስተኛ ሸቀጣሸቀጥ መሸጫዎች በአብዛኛው ባለአንድ ሊትር ዘይት ከመደርደሪያቸው አያጡም ነበር።
ቅድመ ዋጋ መናርና የአቅርቦት ችግር ሸማቹ የምርቱን አይነት፣ ምርቱ የውጭና የአገር ውስጥ ስለመሆኑ፣ በሊትርም ባለ አንድ፣ ባለሁለት፣ባለሶስትና ባለአምስት አማርጦ ነበር የሚጠይቀውና የሚሸምተው። ዋጋውም እንዲሁ የተለያየ በመሆኑ በምርጫው ነበር የሚገዛው።
ከጎረቤት አገራት ቅርበት ያላቸውና ምርቱን በቀላሉ የሚያገኙ እንደ ጅጅጋ፣ አፋር ያሉ ክልሎች ዘመድ ያላቸው ወይንም የሚመላለስ ሰው የሚያውቁ በቅናሽ ዋጋ በማስመጣት አማራጮችን የሚጠቀሙም የሕብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው ይታወቃል።
አሁን ግን ዘይት ከመደርደሪያ የጠፋው በመኻል ከተሞች ብቻ ሳይሆን በርካሽ ይገኝባቸዋል በሚባሉ የዳር አካባቢዎችም ጭምር ነው። አንድ ወዳጄ እንዳጫወተኝ፤ በሥራ አጋጣሚ ወደነዚህ ዳር አካባቢዎች የመውጣት እድሉን ሲያገኝ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን አስቤዛውን ለመሸፈን የሚያስችለውን የምግብ ዘይት ለመግዛት ነበር ያቀደው።
በስፍራው ሲገኝ ግን የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ከሚሸጠው ዋጋ በላይ ሆኖ ነበር ያገኘው። አምስት ሊትር ዘይት አንድ ሺ አምስት መቶ ብር ሲሉት ለማመን መቸገሩን ነበር ያጫወተኝ። እዚህም በየመኖሪያ አካባቢያችን የዋጋ ጥናት ማድረጋችን አልቀረም።
አነስተኛ የዋጋ ቅናሽ የሚጠበቀው በመሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማሕበራት (ሸማቾች) በኩል የሚቀርበው በመሆኑ ስናልፍና ስናገድም ጥያቄያችን ዘይት ነው። ሸማቾች ቀደም ሲል የስኳርና የዱቄት አቅርቦት ነበር ጥያቄ የሚበዛባቸው። የዱቄት ዋጋ ነጋዴዎች ከሚያቀርቡት ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ ዱቄት ለመግዛት ወደነርሱ የሚሄድ የለም። ረጃጅም ሰልፍ ይስተናገድበት የነበረው የስኳር አቀርቦትም ረገብ በማለቱ እንደከዚህ ቀደሙ ሰልፍ አናይም።
እዚህ ላይ ግን የስኳርና የዱቄት አቅርቦት የተጠቃሚ ፍላጎት እርካታ አስገኝቶ ነው የሚል መደምደሚያ ለመስጠት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። አሁን ባለተራ የሆነው የምግብ ዘይት አቅርቦት መሆኑን ለመግለጽ እንጂ። እኔ በምኖርበት ጀሞ አካባቢ የምግብ ዘይት ዋጋ መናር እጅግ አነጋጋሪ ከመሆኑ በፊት ነው በሸማች የሕብረት ሥራ ማሕበራት አቅርቦቱ የተቋረጠው።
ምክንያት መጠየቅ ቢቻልም መለስ ስለማይገኝ መኖሩን ብቻ መጠየቅ ነው የሚሻለው። የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ ስድስት መቶ ብርና ከዚያ በላይ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በአካባቢው ሸማቾች ማሕበራት እየቀረበ አይደለም። አሁን ደግሞ አንድ ሺህና ከዚያ በላይ ዋጋ ሲጠየቅ አሁንም ሸማቹ ተስፋ ሳይቆርጥ ወደነዚህ የሸማች ማሕበራት ነው የሄደው።
እኔም በአንዱ ቀን መንግሥት በአስቸኳይ ከውጭ እንደሚያስገባና በአገር ውስጥ አምራቾችም አቅርቦቱ እንደሚኖር ማሳወቁን በማስታወስ ጥያቄዬን አቀረብኩ። ከነበሩት ሰራተኞች የተሰጠኝ ምላሽ እነርሱም እንደማንኛውም ሰው መስማታቸውን ነው። ነገሩን በቀልድ ከማለፍ ውጭ አማራጭ አልነበረኝም። ይልቁንም ዘይት ለመጥፋት ሲቃረብ ባለአንድ ሊትሮዎቹ ነበሩ ቀድመው የጠፉት።
በተገኘሁበት የሸማቾች ማሕበር ሱቅ ውስጥ በ170 ብር ሂሳብ አንድ ሊትር ይዘው ነበር። ባለው ዋጋ አምስት ሊትር ብገዛ አንድ ጊዜ አምስት ሊትር ከምገዛው የማተርፈውን ማስላቱን ተያያዝኩት። ‹‹ችግር በቅቤ ያስበላል›› ይባል የለ። ሰዎች ከችግር ተነስተው አይደል መፍትሄ የሚፈልጉት፤ እኔም በስሌት ለማትረፍ ጥረት አደረኩ።
የዘይት ዋጋ መናርና የአቅርቦት ማነስ አጀንዳ ሆኖ ከሕዝብ እስከ መንግሥት ባነጋገረበት ወቅት፤ ነጋዴው የነገውን ትርፍ ታሳቢ አድርጎ በክምችት የያዛቸውን ከየመጋዘኑ ማውጣቱን፣ 12 ነጥብ 5 ሊትር በአስቸኳይ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባና ከዚህ ውስጥም 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊትር መግባቱን፣ ቀሪው 7 ነጥብ 7ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ፣ ለሶስት ወራትም በየወሩ 50 ሚሊዮን ሊትር አገር ውስጥ እንደሚያስገባ እንዲሁም የአገር ውስጥ አምራች ድርጅቶችም በተለይም ፌብላ የሚባለው የግል የዘይት አምራች ድርጅት ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ የፓልም ዘይት እያቀረበ መሆኑ ተናግሯል።
እንዲህ ያለው የሚያረጋጊያ መረጃ ደግሞ በተግባር ካልታየ የመንግሥትን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ መክተቱ የማይቀር ነው። ይህን ስል ግን ‹‹ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል›› የሚባለው አይነት እንዳይሆን በመስጋት ነው። የምግብ ዘይት አቅርቦቱ እንደሚስተካከልና በዋጋ በኩልም ተስፋ የሚሰጥ መረጃዎች የቀረቡት ከመጋቢት ወር መግቢያ ጀምሮ ነው።
ቢያንስ እንኳን ሰሞነኛውን ችግር በተወሰነ ደረጃም መፍታት ነበረበት። ሆኖም ችግሮች ከመፈታታቸው ይልቅ እንዲለመዱ ነው የሆነው። የቻለው አሁንም ገዝቶ እየተጠቀመ ነው። አቅመ ደካማ የሆነው የሕብረተሰብ ክፍልስ? አንዳንዶች እንደሚሉትና በየማሕበራዊ ድረ ገጹ ተሰራጭቶ እንዳስተዋልነው ዘይትም እንደ ነዳጅ (ቤንዚን) የተለያየ መጠን ባላቸው ጀሪካኖች ተጠራቅሞ የጥቂቶች ሲሳይ እየሆነ ይሆን? እንዲህ ያለው ፌዝና ቧልት መቀጠል የለበትም። መንግሥት የችግሩን ቁልፍ መፈተሽ ይኖርበታል።
አቅርቦት ለማሻሻል ጥረት እያደረገ ባለበት ማግሥት ለጊዜውም ቢሆን ችግሮች አለመፈታታቸው እንደ አንድ የመንግሥት አገልጋይ ጉዳዩ ሊያሳስብ ይገባል። አነስተኛ ገቢ ያለውን ሕብረተሰብ ያገለግላሉ ተብለው መንግሥት የመስሪያ ቦታ ሰጥቷቸው አግልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋሙ ሸማች የሕብረት ሥራ ማሕበራት ፍትሀዊ በሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ የተቋቋሙበትን ዓላማ ካላሳኩ ለምን በቸልታ ይታለፋሉ? አብዛኞቹ ሸማች ማሕበራት በአገልግሎት አሰጣጣቸው ቅሬታ የሚቀርብባቸው ናቸው።
ከነጋዴው ጋር የሚመሳጠሩ ስለመኖራቸውም ሀሜት ይሰማል። በተለይ ከፍተኛ የሕዝብ ፍሰት ባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሸማች የሕብረት ሥራ ማሕበራት ሊፈተሹ ይገባል። እነርሱን በማደራጀትና በመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው አካል ምን እየሰራ ነው? በተለይ እንዲህ መሰረታዊ በሆኑ አቅርቦቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው የመንግሥትን ጥረት ካላገዙ የመኖራቸው ጥቅም ምን ላይ ነው? ሕዝቡ መንግሥት ቃል የገባው የምግብ ዘይት አቅርቦትና የዋጋ ማረጋጋት እርምጃ የት ደረሰ? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ስለማይቀር ይሄ እያንዳንዱን አስፈጻሚ አካል ሊያሳስበው ይገባል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 /2014