እናርጅና እናውጋ
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ የሚገኝ ወረዳ ነው፡፡ ከዞኑ ዋና ከተማ ደብረማርቆስ 115 ኪሎ ሜትር፤ ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር ደግሞ በ198 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
እናርጅና እናውጋ ለምን ተባለ?
የአጼ ልብነ ድንግል ሁለት ሴት ልጆች ናርጂ እና ናውጋ የሚባሉ አካባቢዎችን ይገዙ ነበር፡፡ ናርጂ እና ናውጋን ጠዛ የሚባል ወንዝ ለሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ ሁለቱ ሴቶች ሲገዙ ቆይተው «ከዚህ በኋላ እኛ ይበቃናል፤ ልጆቻችን ያስተዳድሩ፤ እኛ እያረጀን ነው›› በማለት አርጅተን ማውጋት (ማውራት) ነው ያለብን ለማለት እናርጅና እናውጋ አሉት ይባላል፡፡
መርጡለማርያም
በምሥራቅ ጎጃም ውስጥ የሚገኝ ወረዳ ነው፡፡ ከዞኑ ዋና ከተማ ደብረማርቆስ 189 ኪሎ ሜትር እና ከአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር በ184 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡
መርጡለ ማርያም ለምን ተባለ?
መርጡለ ማለት በግዕዝ አዳራሽ ማለት ነው፤ ማርያም ያው የማርያም ስም ነው፡፡ መርጡለ ማርያም ማለት «የማርያም አዳራሽ » ማለት ነው፡፡ ይህ ስም ብዙ ጊዜ መርጦ ለማርያም ተብሎ ይጠራል፡፡ አንድ ቃል ስለሆነ በመሃል ክፍተት መኖር አልነበረበትም፡፡ ትርጉሙ ልብ እንዲባል ነው ክፍተት ያደረግንበት፡፡ በትክክል ሲጻፍ መርጡለማርያም ነው መሆን ያለበት፡፡ ክፍተት ኖረም አልኖረም ግን ቃሉ መርጦ ለማርያም ሳይሆን መርጡለ ማርያም ነው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011