አገራቸውን ከመውደድም ባለፈ ዝቅ ብለው፣ ምቾታቸውን ሁሉ ትተው ላገራቸውና ሕዝባቸው ከሠሩ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል ይጠቀሳሉ። የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መስራችና ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ በመምህርነትና በአማካሪነት፤ እንዲሁም በመሪ ተመራማሪነት ከአገራቸውም አልፈው ለመላው ዓለም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉ ናቸው። በተለይም አገራቸው በምርምሩ ዘርፍ የተሻለ ድጋፍና አቅም ይኖራት ዘንድ ብዙ የለፉ መሆናቸውን የእስከ ዛሬው የሕይወት ጉዟቸውና ተግባሮቻቸው ያረጋግጣሉ።
በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችና በቴክኖሎጂው፣ እንዲሁም በሳይንሱ መስክም አገራቸው ስለምትጠቀምበት ሁኔታ በቻሉት ልክ የሠሩ ናቸው። ለዚህም በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል። እናም ይህ የሕይወት ተሞክሯቸው ብዙዎችን የሚያስተምር በመሆኑ ዳክተር ኃይሉ ዳዲን ለዛሬው ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል። ተማሩባቸው” ስንልም ጋበዝናችኋል።
እንስሳት ወዳዱ ልጅ
ተወልደው ያደጉት በአርሲ ክፍለ አገር ሱዴ ወረዳ ቡርቂቱ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው። የቤተሰባቸው ዋና መተዳደሪያ ግብርና ሲሆን፤ ይህም እርሳቸውን ከእንስሳት ጋር እንዲቆራኙ አድርጓቸዋል። እርሻው እንዳለ ሆኖ ከብት ማርባት ላይ መሰማራታቸው እንስሳት ወዳድ አድርጓቸዋል። ከሁሉም በላይ ግን የእንስሳት ፍቅራቸውን የጨመረው የአንተ ናቸው ተብሎ ተለይቶ የሚሰጧቸው ከብቶች መኖራቸው እንደሆነ አይረሱትም።
በሌላ በኩል ቤተሰብ ራሳቸውን እንዲችሉም ማገዛቸው ከእንስሳት ጋር ያላቸውን ቅርርብ አጠንክሮላቸዋል። ምክንያቱም እንስሳቱን የሚጠብቁትና የሚንከባከቡት በዓመት አንድ ጊዜ ሸጠው የትምህርት ወጪያቸውን ለመሸፈን ነው። ስለዚህም ትርፋማ ለመሆን የቻሉትን ሁሉ ያደርጉላቸዋል። ይህ የሥራ ሁኔታቸው ሌላም እድል ሰጥቷቸዋል። ሥራን ከግብርናው ጋር አስተሳስረው ይወዱ ዘንድ አስችሏቸዋል።
እንግዳችን ልጅነታቸውን ሲያስታውሱ መጀመሪያ ትዝታቸው የሚሆነው ከእንስሳት ጋር የተሳሰረው ክፍል ሲሆን፤ በልጅነት ዶሮዎችን ማርባትና ሽጠው ለትምህርት ወጪያቸው ማድረጋችውን ያስታውሱታል። በዚህም ቤተሰቡን በተለያየ ነገር እያገዙ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በተጨማሪም በክረምት የአዝመራ ወቅት አረም ማረሙም ሌላው ሥራቸው ነበር። ከሁሉም በላይ ግን እናታቸውን በጣም ስለሚቀርቧቸውና ስለሚወዷቸው ማንኛውንም ሥራ ሳይመርጡ፣ የወንድ፣ የሴት ሳይሉ የሚያግዟቸው ነገር እጅጉን ያስደስታቸዋል። ከወንዝ ውሃ በመቅዳት፣ እንጨት በመፍለጥና ልብስ በማጠብ ሲያገለግሏቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደነበር ያነሳሉ።
ዳክተር ኃይሉ፤ በባህሪያቸው ተጨዋች፣ የጀመሩትን ከግብ ማድረስ የሚወዱና በማካፈል የሚደሰቱ ሰው ናቸው። ማድመጥና ማንበብም ልዩ መለያቸው ነበር። የልጅነት ህልማቸው ተመራማሪና ሳይንቲስት መሆን ነው። ይህንንም እንዳሳኩት ያምናሉ። ከሰዎች ጋር ሲኖሩም ተመሳስሎ ሳይሆን እውነት እውነቱን አስረድተው ተማምነው ነው። ጥፋት ካለም ከመወሰን ወደ ኋላ አይሉም። ለዚህ ደግሞ አስተዳደጋቸው መሰረት ጥሎላቸዋል።
ከጨዋታ ሁሉ ኳስ በአጥቂነት ቦታ ላይ ሆነው መጫወት የሚያስደስታቸው ሲሆን፤ ወግም በጣም ይወዳሉ። ከትልልቅ ሰዎች በተለይም እናትና አባት እግር ስር ቁጭ ብሎ ታሪክ መስማትና ከጓደኞቻቸው ጋር ቡና እየጠጡ መጫወትና ቁም ነገር ማውጋት ቀዳሚ ምርጫቸው ነው። ለዚህ ግን መሰረታቸው እናታቸው መሆናቸውን ያስረዳሉ። እርሳቸው ከትምህርት ቤት ሲገቡ ተረት ይነግሯቸዋል። ያንንም አዳብረውት ዛሬም ድረስ ይደሰቱበት ዘንድ ቅርስ አድርገውታል። ሌላው “አልችለውም” የሚሉት ሥራ አለመኖሩ ሲሆን፤ በመሞከር ያምናሉና ዛሬም ድረስ ይጠቀሙበታል።
የልጅነት ጊዜ መቼም የሚረሳ አይደለም። ዛሬ ድረስ እየኖርኩት ያለሁት ሕይወት ነው የሚሉት ባለታሪካችን፤ አሁን እየሰሩት ካለው ይልቅ በልጅነታቸው ያደረጉት ነገር እንደሚታወሳቸው ያስረዳሉ። በዚህም “ልጅነቴ ሕይወቴ ነው” የሚል እምነት አላቸው።
ከቡላላ እስከ ኮሪያ
ቤተሰቦቻቸው ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸውና በልጆቻቸው ተስፋ የሚያደርጉ ሲሆኑ፤ እነርሱ ባይማሩም በትምህርት መለወጥ እንደሚቻል አምነው የሚፈልጉትን ያደርጉላቸዋል። ትምህርት ቤት እንዲገቡም የፈቀዱላቸው ይህ ምልከታቸው የሰፋ በመሆኑ ነው። በእርግጥ አባታቸው በወቅቱ ከትምህርት ይልቅ በግብርናው ሃብት ማፍራት ላይ ትኩረት ነበራቸው። ይህም ከትምህርቱ ይልቅ ንብረት ማስተዳደሩ ይበልጣል ብለው ያስባሉ። በተለይ የመጨረሻ ልጅ በመሆናቸው ሀብት ንብረቱን ማን ይወርሰዋል፤ ማንስ ያስተዳድረዋል ብለው ያምናሉ። ቤተሰብ ይበተናል ብለውም ይሰጋሉ። ይሁን እንጂ አንድም ቀን እንዳይማሩ ገድበዋቸው አያውቁም።
እናታቸው ደግሞ በተቃራኒው ናቸው። ከሀብት በላይ ትምህርት ያስፈልጋል የሚል አቋም አላቸው። በመሆኑም እንዲማሩ ይገፋፏቸዋል። እንደውም ትምህርት ቤት ያስመዘገቧቸው ጭምር እርሳቸው ናቸው። ለመማራቸው ትልቁን ሚና ተጫውተዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት በዚያው በትውልድ አካባቢያቸው መሆኑ ደግሞ ብዙ ነገሮችን የተሻለ አድርጎላቸዋል። ትምህርት ቤቱ “ቡላላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” የሚባል ሲሆን፤ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማሩበት ነው። ከዚያ ወደ ሮቤ ከተማ ሄደው “ዲደኣ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ገቡ። ከሰባተኛ እስከ 12ኛ ክፍልም ትምህርታቸውን ተከታተሉ። በእርግጥ ይህ ትምህርት ቤት ከትውልድ ቀያቸው የሁለት ሰዓት መንገድ ተጉዘው የሚገኝ ነው። በዚህም ስንቅ ተሸክሞ ጭምር መጓዝን ይጠይቃል። መራብ መጠማትም አለበት።
ከሁሉም በላይ ራስ የማስተዳደሩ ኃላፊነት በስፋት የሚታይበት ቦታ ነው። ብዙ አዲስ ነገርን የሚያዩበት ከተማም ነው። ስለዚህም በአልባሌ ነገር ከመታለል ራስን ቆጥቦ የተሻለ ነገርን ለማግኘት ቁርጠኛ መሆን ግድ ነው። በዚያ ላይ ሦስት ሆነው ተከራይተው ሲኖሩም ተቻችሎ መኖርም ያስፈልጋል። እናም ይህንን ሁሉ አድርገው ትምህርታቸውን በሚገባ መከታተል ችለዋል። ጊዜው ከባድና የተመረጠ ብቻ የሚገባበት ቢሆንም እርሳቸውም ለወቅቱ የሚመጥኑ ተማሪ በመሆን የ12ኛ ክፍል ውጤታቸውን ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ አድርገውታል። እንዲያውም ከአካባቢያቸው ከነበሩ ጥቂት ተማሪዎች ሁለቱ በሚያልፉበት ጊዜ እርሳቸው አንደኛው ነበሩ።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ለመማር አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ያቀኑት ባለታሪካችን፤ በእንስሳት ሳይንስ የትምህርት መስክ ተመርቀዋል። ከዚያ ወዲህ ከትምህርት ጋር ዳግመኛ የተገናኙት ከአራት ዓመት ከስድስት ወር የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ነው። በተመሳሳይ የትምህርት መስክ ማለትም በእንስሳት ሳይንስና ጄኔቲክስ ላይ ጥናታቸውን አድርገው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከደቡብ አፍሪካ የስቴሌንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ማግኘት ችለዋል።
አሁንም ከአራት ዓመታትን የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጀመሩ። ከቶኪዮ ግብርና ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ሞሎኪውላር ጄኔቲክስ ተመርቀዋል። ከዚያ በኋላ ያሉት የአቅም ግንባታዎች በማስተማርና በምርምር የካበቱ ናቸው።
እውቀት የመራው ሥራ
ከሥራ ጋር የተዋወቁት በግል መስሪያ ቤት በኮንትራት ተቀጥረው ሲሆን፤ መስሪያ ቤቱ ኢንተርናሽናል ላይቭስቶክ ሪሰርች ኢንስሲቲዩት (ILRI) ይባላል። በመረጃ ሰብሳቢነትና ማጠናቀር ባለሙያነት ያገለገሉበት ነው። ስድስት ወር ያህልም ሠርተውበታል። ይህ መስሪያ ቤት የ2070 ብር ደሞዝተኛ አድርጓቸዋል። ሆኖም ከዚያ ይልቅ ክልላቸውን ማገልገል ህልማቸውም ፍላጎታቸውም ነበርና የደለበ ደሞዛቸውን ትተው በዝቅተኛ ደሞዝ ማለትም በስድስት መቶ ብር ተቀጥረው ኦሮሚያ ክልልን ተቀላቀሉ። የአዳሚ ቱሉ ግብርና ምርምር ማዕከል ሰራተኛም ሆኑ።
በምርምር ዘርፉ ምርምርን በመምራትና በመመራመር ብዙ እንደሰሩ ያምናሉ። ለምሳሌ፡- በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ፣ በደቡብ ኮሪያ መንግስትና በኢትዮጵያ መንግስት የሚደገፉ የምርምርና ልማት ፕሮጀክቶችን በመምራት፣ አገራዊ የእንስሳት ዝሪያ ማሻሻያ ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀትና በመምራት አገልግለዋል።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ጨርሰው ሲመጡም የአዳሚ ቱሉ ምርምር ማዕከሉ ዋና ኃላፊ ሆነው ተመድበዋል። አራት ዓመት ተኩል በቦታው ላይም እንዲያሳልፉ ሆነዋል። ይህ ደግሞ ኃላፊነታቸውን የተወጡበትና በዚያው ልክ ከባድ ፈተና ያሳለፉበት ጊዜም እንደነበር ያስታውሳሉ።
የተማሩት የዘመኑን ሳይንስ በመሆኑ ለኢትዮጵያ እንደሚጠቅም ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሆኖም አገራቸው ላይ ግን ያሰቡትን ምርምር ለመስራትና አገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችላቸው ሁኔታ አልነበረም። በዚህም ጊዜ ሳይፈጁ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ደቡብ ኮሪያ አቀኑ። ፖስት ዶክ ሳይንቲስት ሆነውም በደቡብ ኮሪያ ዩኒቨርሲቲ ያገለገሉ ሲሆን፤ ተወዳድረው የዩኒቨርሲቲ መምህርነትን በማለፋቸው የባዮ ቴክኖሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ሆነውም ለአራት ዓመታት በደቡብ ኮሪያ ሠርተዋል። ወደ አገራቸው መመለስንና በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ማገልገልን አሰቡ። አጋጣሚዎቹ በተለያየ ጊዜ የሆኑ ናቸው። የመጀመሪያው የቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ዳክተር ካሱ ኢላላን ያገኙበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ከወይዘሮ ደሚቱ ጋር የተገናኙበት አጋጣሚ ነው።
ሁሌም የአገራቸው ጉዳይ ከአዕምሯቸው አይጠፋምና እነርሱን ሲያገኙዋቸው ደግሞ ይበልጥ አገራቸውን የማገልገሉ ጉጉታቸው ጨመረ። ምክንያቱም እነርሱ የመጡበትን ሀሳብ ባዮ ቴክኖሎጂን ኢትዮጵያ ውስጥ መመስረት ተፈልጎ መሆኑን አወቁ። ከእርሳቸው ጋር የተገናኙትም ከኮሪያ ዩኒቨርሲቲ እና የምርምር ተቋማት ልምድ ለመውሰድ በመጡበት ወቅት በደቡብ በኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ዳክተር ዲባባ አብደታ እንግዶቹን የደቡብ በኮሪያ ተቋማት እንዲያስጎበኟቸው በመጠየቃቸው ጥሩ የትውውቅ አጋጣሚ ፈጠረላቸው። እናም “እኔ ያለኝን ለምን አልሰጥም?” እንዲሉ አድርጓቸዋል። አገራቸው ላይ መሥራት ከፈለጉ ሁሉን ነገር እንደሚያመቻቹላቸው ገለጹላቸው፤ ይህም ወደ አገራቸው እንዲመጡና ባዮ ቴክኖሎጂ ላይ እንዲሰሩ ገፋፍቷቸዋል።
ጥያቄውን ወደ ጎን ሳይሉ ወዲያው ወደ አገራቸው የተመለሱት ዳክተር ኃይሉ፤ ዩኒቨርሲቲው በጣም ይፈልጋቸው ነበርና የመልቀቂያ ደብዳቤ ሲያስገቡ ቦታው ካልተመቻቸው ዳግም እንደሚቀበሏቸው ተነግሯቸው ነው የመጡት። ይሁን እንጂ አገርን ማገልገል በሚመቸውም በማይመቸውም ነው ብለው ያምናሉና አልተመለሱም። ይልቁንም በአልተመቻቸበት ሁኔታ ላይ ሆነው ብዙ ነገሮችን ወደ መስራቱ ገቡ እንጂ። የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂን እንዲያቋቁሙ ከተመረጡት
መካከል አንዱ በመሆናቸው የተቻላቸውን ሁሉ ያደረጉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዛሬ ላይ እንዲደርስ አድርገዋል። በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉም አሁን ስድስተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል።
በኢንስቲትዩቱ በርካታ ተግባራትን የከወኑ ሲሆን፤ በዋናነት ከፈጸሙኋቸው ተግባራት መካከል ለመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች የሥራና ኢንስቲትዩታዊ መዋቅር ማዘጋጀት፤ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ፖሊሲና እስትራቴጂ መቅረጽና ማስፀደቅ፤ የመስሪያ ቤቱን የፋይናንስና አስተዳደር ደንብና መመሪያ ማዘጋጀት፤ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትንና ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር ንድፈ ሀሳቦችን መተግበር ይገኙበታል። በተለይም በጤና፤ በግብርና፤ በኢንዱስትሪ፤ በአካባቢ ባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ እንዲሁም በባዮ ኢንፎርማቲክስና ጄኖሚክስ ዘርፍ ብዙ ውጤታማ የምርምርና ልማት ተግባራትን እንዳከናወኑ ይጠቀሳሉ።
የእንስሳት ባዮ ቴክኖሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዳክተር ኃይሉ ዳዲ፤ በመሪ ተመራማሪነት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ከፍተኛ ተቋማት ውስጥ የሠሩም ናቸው። እንዲሁም ከ50 በላይ የምርምር ስራዎችን በማበርከት ይታወቃሉ። በተጨማሪ ከምርምር ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተርነት እስከ ምክትል ዋና ዳይሬክተርነት በኃላፊነት ቦታዎች ላይም አገልግለዋል። ውጤታማ አስተዳዳሪ እንደነበሩም ሥራዎቻቸው ይመሰክራሉ።
ከአስተዳደራዊ አስተዋጽኦ በተዛማጅነትም በኮንኩክ ዩኒቨርሲቲ፣ ሴኦል፣ ደቡብ ኮሪያ በእንስሳት ባዮ ቴክኖሎጂ ረዳት ፕሮፌሰርነት የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስተማር፤ እንዲሁም ተማሪዎችን የምርምር ሥራዎቻቸውን በተመለከተ በማማከር አገልግለዋል። እንዲሁም የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የምርምር ሥራን በመፈተን አገልግለዋል፤ አሁንም እያገለገሉ ይገኛሉ።
እስከ ዋና ተመራማሪነት በዘለቁባቸው ሂደቶች የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን የሰሩት ዳክተር ኃይሉ፤ በኮሪያ ቹንግ ቡክ ዩኒቨርሲቲ በዋና ተመራማሪነት የምርምር ሥራዎችን ሠርተዋል። ለምሳሌ የጂን ሞለኪዩላር መዋቅርን ማጥናት፣ የጂን ጂኖታይፕንግ ዘዴ ማልማት፣ እና የእንስሳት ዝሪያ ዘረመል ትንተና ከሰሯቸው የምርምር ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ቀደም ሲል በአገራቸው ሳሉ ማለትም በ2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂካል እና ኬሚካል ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ተባባሪ ዲንም በመሆን ሠርተዋል። አሁንም ቢሆን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂካል እና ኬሚካል ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ፤ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ያስተምራሉ። እንዲሁም በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተዛማጅ የምርምር ሥራዎችን ከተማሪዎቻቸው ጋር እየሰሩ ይገኛሉ። ከኩባ፤ ኮሪያ፤ ቻይና፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ደቡብ ኮሪያ ካሉ የምርምር ማዕከላትና ከፍተኛ ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የምርምር ሥራ በጋራ መስራት የቻሉና ያስቻሉም ናቸው።
የአገር አበርክቶ
እንግዳችን ከ25 ዓመት በላይ በመምህርነትና ተመራማሪነት ልምድ አላቸው። በተሳካ ሁኔታ የተለያዩ የምርምር ንድፈ ሀሳቦችን በመጻፍ፤ ለውድድር በማቅረብና የተሻለ ሆነው ለተገኙት ንድፈ ሃሳቦቹ መተግበሪያ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ላይ የተካኑ ናቸው። ለዚህም ማሳያው ከኮሪያ መንግስት ለምርምር የሚውል የገንዘብ ድጋፍ፤ በተመሳሳይ ከጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲም እንዲሁ ለቢሮ ግንባታ፤ ለቢሮ መገልገያዎች እና መጓጓዣ ለአጭርና ለረዥም ጊዜ ስልጠናዎች ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ ያስገኙ ናቸው።
ከኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን ብዙ ሥራ ለመስራት ትብብር የሚፈጥሩ ናቸው። ለዚህም እንደማሳያነት የሚጠቀሰው ከኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር የሚሰሯቸው ተግባራት ሲሆኑ፤ የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ አግኝተው ምርምሩ እንዲሰራ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ።
እንግዳችን የካበተ የመምህርነት፤ የተመራማሪነት እንዲሁም አስተዳደራዊ እውቀትና ክሂሎትን ያዳበሩና ያካበቱ የእንስሳት ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ በመሆናቸውም በተለያየ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት በእንስሳት ሳይንስ ዙሪያ ባሉ የሙያ ማህበራት አባል በመሆን ሙያዊ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞም “እያንዳንዱ የምርምርና ልማት ፕሮጀክት ወደ አገር በዕርዳታ ስም ሲመጣ መመርመርና ጠቀሜታው መታየት አለበት።” የሚል ሙያዊና በልምድ የዳበረ አስተያየት አላቸው።
“በልቶና ጠጥቶ የጠገበ አገር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እያመጣ ከእኛ ጋር መሥራት ይፈልግ ይሆናል። እኛ ግን መራጮች መሆን አለብን። ምክንያቱም እንደ አገር የሚያሳስበን የእንጀራና ዳቦ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ምርጫችን ከዚህ ጋር የተመጣጠነ መሆን አለበት። ይህንን ከማድረግ አንጻርም እንደ አገር በባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተሰራ ይገኛል” ያሉትም ሌላው አስተያየታቸው ነው። “የፕሮጀክት ቅበላው ግለሰባዊ ጥቅም ሊሆን አይገባም። እታችኛው ድረስ ወርዶ አገርን በሚጠቅም መልኩ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ሁሉም በዚህ ኃላፊነት መሥራትም ይኖርበታልም” ባይ ናቸው ዳክተር ኃይሉ።
‹‹ኢትዮጵያ የእድገት ማማ ላይ ለመድረስ ካሰበች የእንስሳት ዘርፉን መሰረት ማድረግ ይኖርባታል።›› የሚሉት እንግዳችን፤ ሁሉም ቦታ ላይ ሰብል አይበቅልም። እንደውም አንድ ሶስተኛው የሚሆነው የአገራችን ክፍል ቆላማ አይነት ባህሪን የሚላበስ ነው። እናም ይህንን ቦታ ለእንስሳት ማርባት ብትጠቀምበት ኖሮ ከበለጸጉት አገራት ተርታ የማንመደብበት ሁኔታ አይኖርም ነበር። እነ አሜሪካ በሥጋ ንግድ ሀያላን ሆነዋል። እኛ ደግሞ ከዚህ የምንበልጥበት ብዙ አማራጭ አለን። አንዱን ብቻ ብናነሳ አንድ የቦረና የስጋ በሬ በውጭው ዓለም እስከ አስር ሺህ ዶላር ይሸጣል። እኛ ግን እንስሳቱ፣ መሬቱ፣ ገበያው እያለን እስከ ዛሬ በአግባቡ አልተጠቀምንም። በቀጥታ አርብተን ለዓለም ማስረከብ ብንችል ከመኪና አምራች ኩባንያዎች የማይተናነስ ገቢ እናገኛለን። ሆኖም በእጅ ያለ ወርቅ ሆኖብን ልናደርገው ፈቃደኛ አይደለንም። እናም ልብ እንበለው ሲሉ ያስገነዝባሉ።
የቦረና ከብት ላይ ከዚህ በፊት የማሻሻል ስራ ተጀምሮ ሰርተውበት ያውቃሉ፤ የሚተገብረው ጠፋ እንጂ። አሁንም ቢሆን ለተግባራዊነቱ እየሰሩ እንዳሉ ነግረውናል። አንዳንድ ክልሉ ላይ ያሉ አሰራሮችና የአመራሮች መቀያየር ሁኔታውን ቢያጓትተውም ቀና ሰዎችና የሚተባበሩ አካላት ከተገኙ ሥራው የተፈለገው ላይ ይደርሳልም ብለውናል።
እንግዳችን አገራቸውን የሚያገለግሉት በትልልቅ ኃላፊነቶች ላይ ብቻ አይደለም። ከማህበረሰቡ ጋር የሚያቀላቅላቸውን ሥራም በመከወን ነው። ለአብነት በሚኖሩበት አካባቢ በአገር ሽማግሌነትና በእድር ዳኝነት ጭምር ያገለግላሉ። ልማቱ ላይም ቢሆን በስፋት ይሳተፋሉ። አልፎ ተርፎ ከቀበሌና ወረዳዎች ጋርም በመተባበር ያቅማቸውን ያበረክታሉ። በሚፈለጉበት ሁሉ ሰዓታቸውን ሳይሰስቱ ምሽት ጭምር ጊዜ በመስጠት ያገለግላሉ።
ሽልማቶች
ስኬቶች ዝም ብለው እንደማይመጡ የሚያነሱት ባለታሪካችን፤ ቀደም ሲል የነበራቸው የውጭ አገር የሥራ ልምድና ውሳኔ ሰጪነታቸው እንዲሁም ቀደም ሲል የሠሯቸው አስተዳደራዊ ተግባራት ለስኬታቸው መሰረት እንደሆኑ ይናገራሉ። በዚህም ባካበቷቸው ዕውቀትና ክሂሎት አንቱታን ያበረከቱ ሽልማቶችን አግኝተዋል። በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ተቋማት አማካኝነት ላበረከቷቸው አስተዋፅኦዎች የተለያዩ እውቅና እና ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፣ በ2016 ዓ.ም ለምርጥ አገራዊ ምርምር ከብሔራዊ የምርምር ገንዘብ ድጋፍ ውድድር የምስክር ወረቀት ያገኙት ተጠቃሽ ነው።
ሌላው ሽልማታቸው በ2013 ዓ.ም ያገኙት ሲሆን፣ በኢትዮጵያና በኮሪያ መካከል የዲፕሎማቲክ ግንኙነት 50ኛ ዓመት ላይ ምርጥ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሰዎች የእውቅና ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በኮሪያ ሴኦል ከተማ ላይ በተበረከተበት ወቅት እርሳቸው አንዱ ነበሩ። እንዲሁም በ2011 ዓ.ም የተሟላ የከብት ዝርያ ልማትና ጥበቃ ስትራቴጂ በማዘጋጀታቸው ከኢትዮጵያ መንግስት የወርቅ ማዴሊያ ሽልማት ተቀብለዋል:: በስተመጨረሻ የምናነሳው ሽልማት በ2007 ዓ.ም ምርጥ የምርምር የወረቀት የገንዘብ ሽልማት ከጃፓን የእንስሳት ሳይንስ ማኅበር ያገኙት ሲሆን፤ ይህም ዓመታዊ ስብሰባ ሲካሄድ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ምክንያት ያገኙት ነው።
የሕይወት ፍልስፍና
ለሚሰሩት ሥራ መታመን ተገቢ መሆኑን ከማመን ባለፈ፤ እንደ ዜጋ ለአገር የሚጠበቅብኝን ማድረግ አለብኝ ብለው የሚያምኑ ናቸው። ሌላው “እዚህ ምድር ላይ እንዲሁ አልተፈጠርኩም፣ የተፈጠርኩት ለአላማ ነው” የሚል ፅኑ እምነት አላቸው። እንደ መርህም ይከተሉታል። በዚህ መርህ መሰረትም የግል ሕይወትን፣ የቤተሰብንና የሕዝብን ብልፅግና ማሳካት ይቻላል ባይ ናቸው። በዚህም ዘወትር በቅንነት መስራትና ለውጤት መትጋት ያስፈልጋል ይላሉ።
መልእክት
ቴክኖሎጂ በሌላ ቴክኖሎጂ ይተካል፤ የተሻለ ሊመጣም ይችላል፤ አዲሱ ለአሮጌው መሰረት ይጥላል። የቴክኖሎጂ ዕድገት ፍጥነቱ ከምናስበው በላይ ነው ማለት ይቻላል። አሮጌውን ሳንረዳ በፊት አዲሱ የሚመጣበት፣ ወከባ እና ውድድር ዘመን ውስጥ ከገባን ቆይተናል። ይህ ግን ለእኛ ቅድሚያ ሊሆን አይችልም። እንደኛ ያሉ ታዳጊ አገሮች የሚያስፈልጋቸው ምግብና የአገር ደህንነት ጉዳዮች ናቸው። እናም ጉዳዮቹ ጊዜ የሚሰጣቸው አይደሉምና ጠንክረን መስራት ያለብን እነዚህ ላይ ነው።
የምርምር ሥራዎቻችን በጤና፣ በግብርና እና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ማመንጨት ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል። ዘመኑ በጣም ውድድር የበዛበት በመሆኑና የሚወጡት ቴክኖሎጂዎች ጥራትና ብዛት ከፍተኛ በመሆኑ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ብዙ ጥራት ያለው ምርምር መሥራት የግድ ነው የሚሉት ዶክተር ኃይሉ፤ ዛሬ በዓለማችን ስጋ በላብራቶሪ መመረት ችሏል። በጄኔቲክ ኢንጂነሪንግ ፍጡራንን ወደ እምንፈልገው መቀየርም ተችሏል። ስለዚህ ብዙ ጊዜ የለንምና መማርና ምርምር መሥራት የውዴታ ግዴታችን መሆን አለበት። ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ ማውጣትም ያስፈልጋል። ለምሳሌ:- የህክምና፣ የግብርና፣ የመከላከያ … ቴክኖሎጂዎች ዋነኞቹ ናቸውና ያንን አስቦ መስራት እንደሚገባ ይመክራሉ።
እኛ በተፈጥሮ የታደልን ወሳኝ ሕዝቦች ነን የሚሉት ዶክተር ኃይሉ፤ ነገር ግን መንገስ የምንፈልገው በሚታየው እንጂ በአለን ሀብት አይደለም። ይህ ደግሞ ራሳቸውን በምግብ ያልቻሉ አስብሎናል። አንዲት አገር ኃያል የምትሆነው በምግብ ራሷን ስትችልና ከሰላምና ጸጥታ አንፃር ራሷን ስትከላከል ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ እኛ ተፈጥሮ ያገዘውን በምግብ ራስን የመቻል ኃይላችንን መጠቀም ይገባናል። ያለንን ማየትም ያስፈልገናል ሲሉ መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ።
እውነት ሁሌም አሸናፊ ናት። የአገራችን ፖለቲካም በዚህ መልኩ አይቀጥልም። ምክንያቱም ማህበረሰቡ አገሩን ይወዳል፤ እውነትንም ይዞ የሚጓዝ ነው። እናም ያንን ተስፋ አድርገን ዛሬን መንቀሳቀስ አለብን። ትልቁ ችግር የተማረው ማህበረሰብ ጋ በመሆኑ እነርሱን ማሳፈር ላይ ሊሰራ ይገባል። ለዚህ ደግሞ አንድነት ወሳኝ ጉዳይ ነው። የማህበረሰቡን ትስስርና እምነት አይደለም ይህንን ጊዜያዊ ነገር የቆየን ቁርሾ ይፈታል። ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ በዚህ ላይ መረባረብ ይገባዋል የሚለውም ሌላው መልእክታቸው ነው።
ተማርኩ የሚለው አካል የሕዝብን እጣ ፋንታ ለጥቅሙ ከማዋል ሊቆጠብ ያስፈልጋል። በቀን ሆዱ ዘላለም ለማይኖርባት ምድር ሕዝብን ማስለቀስ አይገ ባውም። በእያንዳንዱ ተግባሩ ማህበረሰቡን ማሰብ አለበት። አገሩንም ማስቀደም ይገባዋል። ይህንን ሳይተገብር ከቀረ ግን ማህበረሰቡ እርግፍ አድርጎ እንደሚ ተወው ማወቅ አለበት። ያን ጊዜ መነሻም መኖሪያም አይኖረውም። ስለዚህም ከአሁኑ ማሰብ ይኖርበታልም ሲሉ ይመክራሉ።
እንደ አገር ሕዝቡ ምንም አይነት ቅራኔ ውስጥ አይደለም የሚል እምነት አለኝ የሚሉት ዶክተር ኃይሉ፤ ሁለት ቡድኖች ተነስተው ሲፋለሙ እያስተዋወቅን መቀጠላችን ነገሮች እንዲካረሩ አድርገናቸዋል። ደጋፊ አለን የሚሉ ጨቋኞችም አፍርተናል። ማቅራራትና መጥፎ ተግባራቸውን መከወኑን የተያያዙትም ለዚህ ነው። እናም ይህንን ተግባራችንን አሁን ማቆም ይገባናል። ቡድኖቹን መደገፍ ፈጽሞ የለብንም። ከዚያ ይልቅ የንጹሀን ደም እንዲመለስ ከመንግስትና ከሕግ አካላት ጋር መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ። ግጭት ውስጥ የሚከተን ድህነቱ በመሆኑም ተባበርን በመስራት ነገሮችን መፍታት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ አስቦና አሰላስሎ የሚሠራ እንዳለ ሁሉ ሳያስቡ በስሚ ስሚና በስሜታዊነት የሚንቀሳቀሱ አካላት ብዙ ናቸው። ይህ ደግሞ ነገሮችን በብዙ መልኩ አደበላልቋል። ራስን ጭምር አለማመንንና ማጥፋትን አምጥቷል። በተጨማሪም በህብረተሰብ መካከል መቃቃርን ፈጥሯል። ውድመትና ቀጣዩን ትውልድ ቂም እንዲያረግዝም የማድረጉ ተግባር እየታየ ነው። ስለሆነም እንደዜጋ ሁሉም ከስሜታዊነት ራስን ወደ ማየት መምጣት አለበት። አገራችን ቢሊዬኖችን ሊያስተናግድ የሚችል ሀብትና አቅም ያላት ናትና መጋጨቱ ይብቃን የሚለው የመጨረሻ ሀሳባቸው ነው። እኛም ምክራቸው ይተግበር በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መጋቢት 18 ቀን 2014 ዓ.ም