ብዙዎች ወደ ምድር መምጣታቸው በምክንያት እና በዓላማ እንደሆነ ያምናሉ። የመጡበትን ዓላማ ለማሳካትና የመኖራቸውን ምክንያት በተግባር ለማሳየት ከላይ ታች ይላሉ ይወጣሉ፤ ይወርዳሉ።
እንዲህ አይነት ሰዎች ታድያ ለብዙዎች መትረፍ የሚችሉ ከመሆናቸው ባለፈ በበጎ ሥራቸው ሁሌም መታወስ የሚችሉበትን መልካም ሥራ በመሥራት የማይሞት ስማቸውን ተክለው ያልፋሉ። ‹‹የዛሬው እንግዳችንም ወደ ምድር የመጣሁት በምክንያት ነው፤ ፈጣሪ እኔን ሲፈጥረኝ ዓላማ አለው ስለዚህ ዓላማውን ላሳካ የግድ ነው›› ይላሉ።
በተለይም የኢትዮጵያን የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ለመለወጥ ራዕይ ሰንቀው ይንቀሳቀሳሉ። በትምህርት አጥብቀው የሚያምኑ በመሆናቸው ሰዎች በተማሩት ትምህርት ለውጥ ማምጣትና መቀየር ካልቻሉ የተሳሳተ ነገር አለ ብለው የሚያምኑ ብቻ አይደሉም የተሳሳተውን አስተካክለው ለማለፍ የሚተጉ እንጂ፤ እኚህ ሰው የጠብታ አምቡላንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክብረት አበበ ናቸው።
በሕይወታቸው ሙሉ ለተፈጠሩለት ዓላማ መኖር የሚያስደስታቸው አቶ ክብረት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ጃንሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልደው አድገዋል። ወላጅ አባታቸው የኮርያ ዘማች የነበሩ ሲሆን ከእርሳቸው በርካታ መልካም የሆኑ ነገሮችን ተምሬያለሁም ይላሉ።
የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው በጂማ ዩኒቨርሲቲ የነርሲንግ ትምህርታቸውን በዲፕሎማ ተከታትለዋል። በተማሩት የነርሲንግ ትምህርት በቀድሞው አጠራር በባሌ ክፍለ አገር ጊኒር በተባለ ቦታ ለአምስት ዓመታት አገልግለው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። ለትምህርት ትልቅ ቦታ ያላቸው አቶ ክብረት፤ በጊኒር ቆይታቸው ከጊኒር ተማሪዎች ጋር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው 3.8 አምጥተው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በማታው ክፍለ ጊዜ የአንስቴዥያ ትምህርታቸውን በመከታተል የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
በዚህ ወቅት ቀን ቀን በሙያቸው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያገለግሉም ነበር። ለአንስቴዢያ ካላቸው ፍቅር የተነሳ በርካታ አጫጭር ኮርሶችን ወስደዋል። በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ የሊደርሺፕ ትምህርት ቢካተት መልካም ነው የሚሉት አቶ ክብረት፤ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ የክፍል አለቃን በመምረጥ ተማሪዎች የአመራርነት ብቃት ማዳበር ያለባቸው መሆኑን ሲገልጹ፤ እርሳቸው በአውሮፓ የተከታተሉት የሊደርሺፕ ትምህርት በሕይወታቸው ትልቅ ለውጥ ማምጣት የቻለ መሆኑን በማስታወስ ነው። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በአንስቴዥያ ሙያ በሚያገለግሉበት ወቅት ለሙያው በነበራቸው ጥልቅ ፍቅር በርካታ መጽሐፍቶችን በማንበብ በዘርፉ ያላቸውን ዕውቀት አዳብረዋል።
በንባብ፣ በዕውቀትና በልምድ የዳበረ ሞያቸውንም ለብዙዎች ለማድረስ ብሎም የተፈጠሩበትን ዓላማ ለማሳካት ጠብታ አምቡላንስን በ2001 ዓ.ም አቋቋሙ። ጠብታ አምቡላንስ ከመቋቋሙ አስቀድሞ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በአንስቴዥያ ህክምና 17 ዓመታት አገልግለዋል። የአንስቴዥያ ህክምና አገልግሎት ሕመም ማስታገስን ጨምሮ በጽኑ የታመሙ ህሙማንን መከታተል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ክብረት፤ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሚሰሩበት ወቅት ያስተዋሏቸው በርካታ ክፍተቶች በግላቸው ጠብታ አንቡላንስን እንዲያቋቁሙ አድርጓቸዋል።
ለአብነትም አደጋ ከተከሰተበት ቦታ እስከ ሆስፒታል ሰፊ ክፍተት እንዳለ ሲያነሱ አደጋ የደረሰበት ሰው ወደ ህክምና ቦታ ይሄዳል። ነገር ግን ዓለም ላይ ያለው ሂደት አደጋ ሲደርስ ሞያተኛው አደጋው የደረሰበት ቦታ ላይ ይደርሳል። በአገሪቱ ያለው ይህ አሰራር ሙሉ ለሙሉ ተቃራኒ በመሆኑ ወደ ዘርፉ ለመግባት አስገድዷቸዋል።
በዓለም ላይ ያለው የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ታሪክ ምን ይመስላል የሚለውን ለመመለስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ መጽሐፍቶችን አገላብጠዋል። ያገላበጧቸው መጽሐፍቶች ሁሉ ታድያ በአደጋ ጊዜ ለሚደርሱ ጥሪዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የግድ መሆኑን አስተምሯቸዋል።
በድንገተኛ ህክምና ውስጥ ዋናው ጉዳይ ሰዎች እንደሚያስቡት አምቡላንሱና ሞያተኞቹ ሳይሆኑ የጥሪ ሲስተሙ ነው የሚሉት አቶ ክብረት፤ አደጋው በደረሰበት ቦታ ሁሉ ፈጣን ምላሽለመስጠት የድንገተኛ ህክምና በስፋት መሰራት ያለበት ዘርፍ እንደሆነም ይናገራሉ
። ‹‹ሰዎች ራዕይ ከሌላቸው እንደማገዶ ይማገዳሉ›› የሚሉት አቶ ክብረት፤ የወታደር ልጅ ከመሆናቸው ባለፈ ከእህትና ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ሲያድጉ በርካታ ያልተሟላላቸው ነገሮች የነበሩ እንደሆነ ያስታውሳሉ። ይሁንና በልጅነታቸው ያጡትን ሁሉ ለማግኘት ደግሞ በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል። ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ ምሽትን ጨምረው ቅዳሜና እሁድ ስድስት ሆስፒታሎች ውስጥ ተዘዋውረው ሲሰሩ ነበር።
ባላቸው ትርፍ ጊዜ ሁሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በሚወዱት ሙያ በማገልገላቸው ሕይወታቸውን መለወጥ እንደቻሉና ቤት መኪና የመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮችን አሟልተዋል። ከዚህ በኋላ ሁሉም ተሟላልኝ በቃኝ ያላሉት አቶ ክብረት ለሌሎች መትረፍ ያለባቸው መሆኑን በማመን ዕይታቸውን አስፍተዋል። በመሆኑም በዘርፉ ያካበቱትን ጥልቅ ዕውቀት ተግባራዊ በማድረግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የግል የድንገተኛ ህክምና ለማቋቋም ባሰቡበት ቅጽበት ምቹ ሁኔታ ተፈጠረልኝ ይላሉ።
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሚሰሩበት ወቅት የልብ ችግር ያለበት አንድ የውጭ ዜጋ ወደ እንግሊዝ አገር ሲሄድ አብረው የመሄድ ዕድል አጋጠማቸው። በወቅቱ ለዘርፉ ያላቸውን ፍላጎትና ትጋት በቅርበት የሚያውቁ የሥራ ባልደረቦቻቸው ይህን ሀሳብ ሲያቀርቡላቸው በደስታ ተቀብለው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እንግሊዝ አገር በመጓዝ በውጭው ዓለም ያለውን የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት የማየት እድል አጋጠማቸው።
‹‹ጥቂት የማይባሉ ጓደኞቼ ባጋጠመኝ የውጭ ጉዞ ምክንያት በዛው እንደምቀር ቢገምቱም እኔ ፈጣሪ መሻቴን ተመልክቶ ያሳየኝን ድንቅ ነገር በአገሬ ላይ የመተግበር ዕቅድ ይዤ ወደ አገሬ ተመልሻለሁ›› የሚሉት አቶ ክብረት፤ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የመጀመሪያ ሥራቸው መልቀቂያ ማስገባት ነበር።
ሥራቸውን ለቀው በውስጣቸው ያለውንና በውጭው ዓለም የተመለከቱትን የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ለመክፈት ወጥተዋል ወርደዋል። ሂደቱ እጅግ ፈታኝና ተስፋ አስቆራጭ የነበረ ቢሆንም አበዳሪ በማጣታቸው መኖሪያ ቤታቸውን እንዲሁም መኪናቸውን በመሸጥ በ350 ሺ ብር ጠብታ አምቡላንስን አቋቁመዋል። በወቅቱ በነበረው ውጣ ውረድ ከነቤተሰባቸው ረሃብ ላይ ሊወድቁ ይችሉ የነበረ ቢሆንም በግላቸው በተለያዩ ቦታዎች እየሰሩ የቤተሰባቸውን ሕይወት ማስቀጠል ችለዋል። ፈቃድ ለማግኘት ስድስት ወራትን አስጠብቋቸዋል። ከዚህ በኋላም የስልክ ጥሪ እየተቀበሉና አምቡላንስ እየነዱ ላለፉት አሥራ ሶስት ዓመታት ፈታኝ የሚባሉ ወቅቶችን በማሳለፍ ከሚተርፉበት ወደማይተረፍበት በማድረግ ቢዝነስ ሞዴል ሰርተው ጠብታ አምቡላንስ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረስ እንዲችል አድርገዋል።
ነገር ግን ጠብታ አምቡላንስ የሚገባውን ያህል አላደገም ይላሉ። የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሥራውን በሁለት ሚኒባሶች የጀመረው ጠብታ አምቡላንስ በአሁኑ ወቅት 20 አምቡላንሶች የደረሰ ሲሆን አምስት አሮጌ አምቡላንሶችን ሸጦ በ15 አምቡላንሶች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ዋናው ነገር ሲስተም መዘርጋት ነው የአምቡላንሶች ቁጥር መብዛት አይደለም የሚሉት አቶ ክብረት፤ በአንድ አምቡላንስ በርካታ ጥያቄዎችን መመለስ የሚቻል እንደሆነም አጫውተውናል።
ጠብታ አምቡላንስ ከሚሰጠው የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት በተጨማሪ ጠብታ ፓራሜዲክ ኮሌጅ ከፍቶ የኢመርጀንሲ ሜዲካል ቴክኒሻን ትምህርትን በዲፕሎማ ደረጃ እየሰጠ ይገኛል። በመጀመሪያው ዙር 20 ተማሪዎች ተምረው ትምህርቱን አጠናቅቀው የተመረቁ 16 ተማሪዎች ሥራውን የተቀላቀሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ 60 ተማሪዎችን እያስተማረ የሚገኝ ነው።
በቀጣይ ዓለም በደረሰበት ደረጃ ልክ አገልግሎቱን ለመስጠት አሜሪካን አገር ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የፋይናንስ ጥያቄውን በኖርዌይ በኩል ለመፈጸም በዝግጅት ላይ የሚገኝ ሲሆን በዚህ መሰረት የመግቢያ ፈተናውን ያለፈ ማንኛውም ሰው በነጻ መማር የሚችል ይሆናል።
‹‹እኔ አገሬን የምወድ አንድ ተራ ዜጋ ነኝ›› የሚሉት አቶ ክብረት፤ ምኞትና ፍላጎታቸው በሚችሉት ሁሉ አገርን መጥቀም ሲሆን ሥራ በመፍጠር በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ በተለይም ወጣቶች ምክንያታዊ እንዲሆኑና ለአገርና ለራሳቸው ሀሳብ እንጂ ለሌሎች ሀሳብ እንዳይሞቱና ተስፋ እንዲኖራቸው፤ ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ይተጋሉ። ይህን መሰል አበርክቷቸውንም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተግባራዊ ያደርጋሉ።
በግላቸው በሚደርሳቸው ጥሪዎች ሁሉ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑት አቶ ክብረት፤ መደበኛ ሥራቸው የሆነውን የጠብታ አምቡላንስ ድርጅት ውስጥም የሚሰሩ ሲሆን ድርጅቱ በዋናነት ከተፈጠረበት የ24 ሰዓት የአምቡላንስ አገልግሎት በተጨማሪ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ መስጫ ኪቶችን ያመርታሉ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በርካታ ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን ለአብነትም ከጤና ጥበቃ 20 አምቡላንሶችን እንዲሁም ከአለርት ሆስፒታል ሁለት አምቡላንሶችን ወደ ትክክለኛ አምቡላንስ የመቀየር ሥራ ሰርተዋል።
አጫጭር ስልጠናዎችን ጨምሮ ትምህርት የሚሰጡበት ኮሌጅም ሶስተኛው የሥራ ዘርፋቸው ነው። አቶ ክብረት፤ ‹‹ሥራ ፈጣሪ አልቃሻ አይደለም›› በማለት በቀጣይም የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት እቅድ ያላቸው መሆኑን ሲገልጹ፤ ሥራ የሚሰሩት ገንዘብን አስበው እንዳልሆነና የተፈጠርኩበት ዓላማ ነው ብለው እንደሆነ ያስረዳሉ።
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተቃጣውን የቦንብ አደጋ ጨምሮ በከተማዋ በተፈጠሩ የተለያዩ አደጋዎች ላይ ከክፍያ ውጭ ቀድመው መድረሳቸውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ የጠብታ አምቡላንስ ህልም ይህ ብቻ ሳይሆን ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ በመድረስ በቂ፣ ምቹና አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት እንደሆነም ይናገራሉ። አገልግሎቱን በስፋት ተደራሽ ለማድረግም በቅርቡ እናት ባንክ አራት ኪሎ ሺ ሰማንያ አካባቢ መሬት ገዝቶላቸዋል።
በመሆኑም ኤሊኮፕተር ማቆም የሚችል ባለ ስምንት ወለል ህንጻ ለመሥራት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። የግንባታ ሥራው በአንድ ዓመት ውስጥ የሚያልቅ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ክብረት ተጨማሪ ቦታዎች የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ሲገልጹ አራት ኪሎ ሆኖ መላው አዲስ አበባን ተደራሽ ማድረግ የማይቻል ነው ይላሉ።
የሥራ ዕድልን በተመለከተም ለ67 ቋሚና ለ27 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለው ጠብታ አምቡላንስ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣትም የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት ችሏል። በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት አድቫንስ አምቡላንስ የነበረው ጠብታ አምቡላንስ ብቻ በመሆኑ አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ፌንትሌተር ያለው አምቡላንስ ለሶስት ወራት ያለምንም ክፍያ በድምሩ ለአንድ ዓመት ለጤና ጥበቃ ሰጥተዋል። በተጨማሪም በተለያየ የኑሮ ውጥንቅጥ ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰበ ክፍሎችም እንዲሁ አቅማቸው በፈቀደላቸው መጠን በየጊዜው ድጋፍ ያደርጋሉ።
‹‹እያንዳንዱ ሰው የሚለካው ለሌሎች ለመኖር ባለው ጥልቅ አስተሳሰብ ውስጥ ነው›› ብለው የሚያምኑት አቶ ክብረት የቀጣይ ዕቅዳቸው በመላው አገሪቱ አገልግሎታቸውን ተደራሽ ማድረግ አንዱ ሲሆን፤ የአፍሪካን የድንገተኛ ህክምና ስልጠና ሀብ በማቋቋም ከመላ አፍሪካ መጥተው ስልጠናውን እንዲያገኙ ማድረግ ደግሞ ሁለተኛው ዕቅዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
በሶስተኛ ደረጃ ያስቀመጡት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲሆን ከውጭ አገር የሚገቡ የህክምና ቁሳቁሶችን በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሪን ከማዳን ባለፈ ፈጣን ምላሽ መስጠት፣ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትን ማስተናገድ የሚያስችል ትራሆማ ሆስፒታል ማቋቋም እና ኤር አምቡላንስ አገልግሎት ሲስተም መዘርጋትም ሌላው ህልማቸው ነው።
ታድያ ይህን ሥራ የሚሰሩት በተራ ነጋዴ አስተሳሰብ ትርፍን በማጋበስ ሳይሆን ሳያተርፉም ሳይከስሩም እንደሆነ ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014