ወይዘሮዋ ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ሲመክሩ ከርመዋል። ያሰቡትን ለመፈጸም፣ የልባቸውን ለማድረስ ጊዜ የበቃቸው አይመስልም። እሳቸው ልጆቹን ባገኙ ጊዜ ሚስጥራቸው ይበዛል፣ ጨዋታቸው ይለያል። ሁለቱ ጎረምሶች ከእናታቸው ሲውሉ የሚያወሩትን ያውቃሉ።
ሁሌም ሲገናኙ የእናትና ልጆቹ ወግ በአንድ ጉዳይ ያተኩራል። ወይዘሮዋ ከወለዷቸው ስምንት ልጆች መሀል ሁለቱን መምረጣቸው በምክንያት ነው። ሁለቱ ጎረምሶች የእናታቸውን ሀሳብ ይቀበላሉ። ትዕዛዝ ይፈጽማሉ፣ የሚሉትን ሰምተው ያሉትን ያደርጋሉ። ሁለቱ ልጆች ከእናታቸው መምከራቸውን ወደውታል። በተነሳው ሀሳብ፣ በተያዘው ዕቅድ ፈቃዳቸውን ከሰጡ ቆይተዋል። ሁለቱ ልጆች ለትምህርት እምብዛም ናቸው።
እኩዮቻቸው ቀለም ሲቆጥሩ፣ ፊደል ሲለዩ ቸል ሲሉ ቆይተዋል። ዕድሜያቸው ከፍ ሲል ግን ፍላጎታቸው ጨመረ። ገንዘብ በመያዝ ጥቅም ማግኘት ፈለጉ። እናት ይህን ሲረዱ የልጆቹን ምኞት ሊሞሉ የሀሳባቸውን ሊያሳኩ ሞከሩ። አባት ከገንዘብ ይልቅ ዕውቀት ይበልጣል፣ ትምህርት ይልቃል ሲሉ ሞገቱ። ልጆቹ የአባወራው ምክር አልጣማቸውም።
ሀሳባቸውን አጣጣሉ። ገንዘብ እንደሚሻል፣ ጥቅም እንደሚበልጥ ገለጹ። እናት የእነሱን ሀሳብ ደግፈው መቆማቸው ያስደሰታቸው ጎረምሶች በየቀኑ ከእሳቸው መማከር ጀመሩ። ገንዘብ እንዲያገኙ፣ ከጥቅም እንዲጋሩ የሚያስችል መላ ፈለጉ። አባት የትምህርቱ ጉዳይ እንደማይሆን ሲገባቸው በስራ እንዲያሳልፉ አስገነዘቡ።
ልጆች አልሰሙም። ሀሳብ ምክራቸውን አልተቀበሉም። ከጊዜያት በኋላ… ጋሞጎፋ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ። የሸሌ ቀበሌና አካባቢው በልምላሜው ይታወቃል። ስፍራው በብዛት የሚያፈራው የሙዝ በረከት ለበርካቶች የእንጀራ ማግኛ ሆኖ ዓመታትን ዘልቋል። አቶ ንጋቱ ቡታ መልካም ገበሬ ናቸው። እሳቸውን ጨምሮ መላውን ቤተሰብ የሚያስተዳድሩት በእርሻ ስራ ነው። ንጋቱን የሚያውቋቸው ሁሉ ስለጥንካሬያቸው ይመሰክራሉ።
በየጊዜው ከለምለሙ መሬት፣ ውለው በሚከፍሉት የጉልበት ዋጋ የላባቸውን አያጡም። አቶ ንጋቱ በሚውሉበት እርሻ የሚያገኙት የሙዝ ምርት ህልውናቸው ሆኖ ቆይቷል። ምርቱ በየዓመቱ በእጥፍ እያተረፈ ካሰቡት ያደርሳቸዋል። ሰውዬው ባለቤታቸውንና ስምንት ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩት ከአትክልት እርሻውና ከሙዙ በረከት ነው። አባወራው ሁለቱን ልጆች ማስተማሩ አልሆነላቸውም። ወጣቶቹ የመማር ፍላጎት የላቸውም።
አባት ግን ተስፋ አልቆረጡም። አማራጭ ያሉትን ሌላ መተዳደሪያ አበረከቱ። ለሁለቱ ጎረምሶች ባጃጅ ገዝተው ሰጡ። የአባት ስጦታ ከእጃቸው የደረሰው ወንድማማቾች ባጃጁን ይዘው ለስራ ተሰማሩ።
ውለው እያረፈዱ፣ አርፍደውም እያመሹ ገንዘብ መቁጠር፣ ራስን መርዳት አወቁ። ለጥቂት ጊዚያት በስራው የቆዩት ወንድማማቾች እንደጅማሬው አልዘለቁም። በባጃጁ ስራ ውጤታማ አልሆኑም። ከትርፉ ኪሳራቸው፣ ከቁምነገሩ ግዴለሽነታቸው አየለ።
ይህን የተረዱት አባት በሆነው ሁሉ አዘኑ። እነሱን ለመለወጥ፣ ራሳቸውን ለማሻሻል ያደረጉት ሙከራ መና መቅረቱ ገባቸው።
አዲስ ሀሳብ…
ሁለቱ ልጆች ለወደፊቱ ይበጀናል በሚሉት ሌላ ሀሳብ ተወጠሩ። አዲሱን ዕቅድ ለአባታቸው ከማሳወቃቸው በፊት ከወላጅ እናታቸው ጋር መምከር እንዳለባቸው አሰቡ። እናት ሀሳባቸውን ከተረዱ በኋላ ልጆቹ በሚሉት ሁሉ ተስማሙ። በአባታቸው እጅ ከሚገኘው የአትክልት መሬት ያስፈልገናል የሚሉትን ለክተው መውሰድ እንዳለባቸው አመኑበት። የእናትና ልጆቹ ሀሳብ በየቀኑ በምክር ዳበረ።
በተገናኙ ቁጥር ጨዋታቸው የመሬቱ ጉዳይ ብቻ ሆነ። ይዞታውን ከፍለው መውሰድ እንዳለባቸው ከወሰኑ ወዲህ ልጆቹ ከእናታቸው ተወዳጁ። ሀሳቡን በጋራ አንስተው ለመጠየቅ ወጠኑ። አሁን እናትና ልጆቹ የውስጣቸው ፍላጎት በአንድ ታስሯል። የወደፊት ህልማቸውን እያለሙ፣ ማድረግ የሚገባቸውን ያስባሉ።
የአትክልት መሬቱን ሲረከቡ ስለሚያለሙት እርሻ፣ ስለሚያፍሱት ምርት ያቅዳሉ። ምኞታቸው ማየል ሲጀምር ሀሳባቸውን ለሚመለከተው መልካምሥራ አፈወርቅ ሰው ማቅረብ እንዳለባቸው ወሰኑ። ጥቂት ቆይቶ ታታሪው አባወራ የልጆቹና የሚስታቸው ጥያቄ በግልጽ ደረሳቸው።
ዓመታት ከለፉበት የእርሻ ማሳ፣ ላብና ጉልበት ከከፈሉበት ለም መሬት ቆርሰው ሊሰጡ እንደሚገባ ተነገራቸው። አባወራው በተጣለባቸው ግዴታ፣ በተላለፈባቸው ውሳኔ አልተስማሙም።
ከዚህ ቀደም ለልጆቹ የከፈሉትን ዋጋ ፣ ለማስተማር የደከሙበትን ጊዜ አስታውሰው ፍላጎታቸው ተገቢ አለመሆኑን አስረዱ። እናትና ልጁ በአባወራው ምላሽ ብሽቀት ያዛቸው። አባት ከአትክልቱ መሬት ከለማው እርሻ ከፍለው ያለመስጠታቸውን ከክፋት ቆጥረው ቂም ያዙባቸው። በአባወራው፣ በሚስታቸውና በልጆቹ መካከል ኩርፊያና ቅያሜ ነገሰ። ልጆች ከእናታቸው ጋር ሆነው አባታቸውን በክፉ ዓይኖች አስተዋሉ።
ቤተሰቡ መሀል የገባው ቅያሜ አልተፈታም። ልጆቹ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አባታቸውን ከመሞገት፣ ከመጨቅጨቅ አልቦዘኑም። እናት የልጆቹን ሀሳብ ደግፈው እንደቆሙ ነው። ባል ከሚያርሱት መሬት ፍራፍሬ ከሚታፈስበት እርሻ ከፍለው ያለመስጠታቸው ሚስትን ያናድድ፣ ያብከነክን ይዟል።
ታታሪው አባወራ ከወትሮው የተለየ ነገር የላቸውም። የሚስትና ልጆቻቸውን ኩርፊያና ጭቅጭቅ ችለው ከእርሻ ውለው ይገባሉ። ቤት ሲደርሱ የቀድሞው አቀባበል አይቆያቸውም። እማወራቸው በኩርፊያ፣ ሁለቱ ልጆች በግልምጫ ያነሷቸዋል። ሁሉን እንደባህሪው የሚችሉት አባት መሽቶ ሲነጋ ከእርሻቸው፣ ይገኛሉ።
ከማሳው ደርሰው ሲደክሙ ይውላሉ። ሰሞኑን አቶ ንጋቱ ከሰፊው እርሻቸው መሀል አልተገኙም። እንደወትሮው ማልደው የሚደርሱበት የፍራፍሬ ማሳ ብቻውን እያረፈደ ነው። የታታሪውን አርሶ አደር ትጋት የሚያውቁ አንዳንዶች በቦታው ባለመታየታቸው ይነጋገሩ ይዘዋል። ሰውዬው ያለአንዳች ምክንያት እንደማይቀሩ የገመቱ የቅርብ ሰዎች ሁኔታው ቢያሳስባቸው ደህንነታቸውን ተጠራጥረዋል።
ከፖሊስ ጣቢያው…
ድንገት ከፖሊስ ጣቢያው የደረሱት ሶስት ሰዎች ከዕለቱ ተረኛ ፖሊስ ፊት ቀርበዋል። ፖሊሱ እንዲቀመጡ ወንበር ሰጥቶ የሚሉትን ለመስማት ተዘጋጀ። ሶስቱ ሰዎች የአቶ ንጋቱ ባለቤትና ሁለቱ ልጆቻቸው ናቸው።
ፖሊሱ ሰዎቹ ከነገሩት ሀሳብ ተነስቶ ጥያቄዎችን መሰንዘር ይዟል። ሶስቱም ለሚጠየቁት ሁሉ በእርጋታ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል። ወይዘሮዋ ፊታቸው ላይ ጭንቀት ይነበባል። ባለቤታቸው አቶ ንጋቱ ከቤት ወጥተው ሳይመለሱ መቅረታቸው አሳስቧቸዋል። ይህንኑ ጉዳይ ለፖሊሱ እያስረዱ እየተናገሩ ነው።
ፖሊሱ ከወይዘሮዋ ጥቂት መረጃዎችን ወስዶ ወደ ሁለቱ ጎረምሶች ፊቱን አዞረ። ወንድማማቾቹ ገጽታ ላይ የእናታቸው አይነት ስሜት ይነበባል። ሁለቱም ለተጠየቁት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሰጡ። አባታቸው ለስራ ወጥተው አለመመለሳቸውንና ይህ ጉዳይ የመላው ቤተሰብ ስጋት እንደሆነ ተናገሩ።
ፖሊሱ የሰውዬውን የስራ ባህርይ፣ የቅርብ ሰዎቻቸውን ማንነትና ሌሎች ጥያቄዎችን አክሎ ማብራሪያ ጠየቀ። ተጠያቂዎቹ የሚያውቁትንና የሚጠራጠሩትን ተናግረው ሕግ አባታቸውን እንዲፈልግላቸው ተማጸኑ። ወይዘሮዋ የስምንት ልጆቻቸው አባት እንደዋዛ ከቤት ወጥቶ መቅረት አሳዝኗቸዋል።
ይህን ስሜትም ለፖሊሱ መሸሸግ አልቻሉም። እየተጨነቁ፣ እየተረበሹ፣ ተማጽኖ አቀረቡ። ከጠፉ ሳምንት ሆኗቸዋል የተባሉትን አባወራ ቤተሰቦች ያቀረቡትን ተማጽኖ ይዞ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ሰነደ። ስለግለሰቡ ያገኘውን መጠነኛ መረጃ በዋቢነት ሰንቆም ቤታቸው ይገኝበታል ወደተባለው መንደር ለመንቀሳቀስ ዝግጅቱን አጠናቀቀ።
ፖሊስ በቆላ ሸሌ ቀበሌ …
ፖሊስ ከአንድ ቀን በፊት በንዑስ ፖሊስ ጣቢያው ቀርበው የአባወራውን መጥፋት ወዳመለከቱት ቤተሰቦች መገኛ መገስገስ ጀምሯል። የቆላ ሸሌ ቀበሌ በርካታ ነዋሪዎች በጋራ የሚኖሩበት አካባቢ ነው። በዚህ መንደር የአቶ ንጋቱ ድንገት መሰወር አሳሳቢ ሆኖ ከርሟል።
ታታሪው ገበሬ ጠዋት ማታ በሚመላለሱበት የ‹‹ገለዳ›› መንገድ ሳይታዩ መክረማቸው መንደሩን ሲያነጋግር ቆይቷል። የአቶ ንጋቱ ባለቤትና ሁለት ልጆቻቸው አባወራው ድንገት ከቤት ወጥተው ያለመመለሳቸውን ለነዋሪው ተናግረዋል።
ይህን ወሬ ተከትሎ ስጋት የወደቀበት ሰፈርተኛ አባወራው ይሄዱበታል ያለውን ቦታ ሲገምትና ሲያፈላልጋቸው ከርሟል። ከዛሬ ነገ ይመጣሉ የተባሉት ሰው ድምጻቸው ሳይሰማ፣ መድረሻቸው ሳይታወቅ ቀናትን አስቆጠሩ። ፖሊስ ከስፍራው ደርሶ መረጃዎችን ማሰባሰቡን ቀጠለ። የአቶ ንጋቱን ማንነት የሚያውቁ በርካቶች ከፖሊሶች ጎን ቆመው እገዛቸውን አሳዩ።
ፖሊስ ለሚጠይቀው ጉዳይ እየተባበሩ፣ ለሚጠራጠሩት ጥቆማ እየሰጡ ትብብራቸውን ገለጹ። የተደራጀው የምርመራ ቡድን የአካባቢውን ህብረተሰብ ደጀን አድርጎ አባወራውን ለማግኘት የፍለጋ መረቡን ዘረጋ። ቤተሰቦቻቸውን እየጠየቀ፣ ስለእሳቸው የሚያውቁትን እንዲያስረዱት እየመረመረ ስለጠፉት አባወራ ፍንጭ ለመያዝ አሰሳውን ቀጠለ።
የአባወራው ቤተዘመዶችም የሰውዬው ድንገት መጥፋት ቢያሳስባቸው ለፖሊስ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። ፖሊስ ቀድሞ የያዘውን መረጃ አጠናክሮ ተጨማሪ ሀሳብ ለማግኘት ትግሉን ይዟል። ፖሊስ መንደሩ በሹክሹክታ የሚወራውን ሀሜት ቢጤ በዋዛ ማለፍ አልፈለገም።
‹‹ሽው..›› የሚለውን ወሬ በወጉ ለማጥራት ከሰዎች መሀል ተገኝቷል። ከመንደሩ ሰዎች አብዛኞቹ የጥርጣሬ አቅጣጫቸውን አንድ አድርገዋል። የአባወራው መጥፋትና መገኘት ከሶስት ሰዎች እጅ እንደማያልፍ በእርግጠኝነት እየተናገሩ ነው። የተጠናከረው የምርመራ ቡድን የሚወራውን ወሬ ‹‹ሀሜት›› ነው፣ ብሎ ማለፍ አልቻለም።
ከየአቅጣጫው የሰማውን መረጃ አሰባስቦ እማወራዋና ሁለት ልጆቻቸው ዘንድ ቀረበ። ከጠፉ ዘጠነኛ ቀን ያስቆጠሩት አባወራ አሁንም መገኛቸው አልታወቀም። ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ የቅርብ ሰዎች ስለእሳቸው ያዩት የሰሙት ጉዳይ የለም። ፖሊስ ይህን ቋጠሮ ለመፍታት እስከመጨረሻው ይጓዛል። የአቶ ንጋቱ ባለቤት ከመርማሪው ፖሊስ ፊት ቀርበው በድጋሚ ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠየቁ። ሴትዬዋ ከቀድሞ የተለየ ሀሳብ አልሰነዘሩም።
ሁለቱ ጎረምሶች ዳግም ለጥያቄ ቀርበው እውነታውን ተናገሩ ተባሉ። እነሱም ከወላጅ እናታቸው የተለየ ሀሳብ አልነበራቸውም። ፖሊስ በሶስቱ ሰዎች ምላሽ አልተማመነም። የምርመራ ቡድኑ አባላት በቂ ማስረጃዎችን ከያዙ በኋላ የአባወራውን ግቢ በተለየ እይታ ማሰስ ጀመሩ።
የሚያጠራጥሩ ቦታዎችን እየፈተሹ፣ ጉድባ ጉድጓዱን ቃኙ፣ ከለላና አጥሩን ጥሰውም ፍለጋቸውን ቀጠሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪና የአባወራው ቤተሰቦች በዙሪያቸው ይከተላሉ። በድንገት… የወንጀል ምርመራ ቡድኑ አባላት ግቢውን ዳር እስከዳር ከበው አሰሳቸውን ቀጥለዋል። የሁሉም ዓይኖች በጥንቃቄ ይቃኛሉ።
የሁሉም እግሮች መረጃ ለማግኘት፤ ከእውነቱ ለመድረስ ይፈጥናሉ። ፖሊሶቹ በድንገት ከዋናው መኖሪያ ቤት ጀርባ የተዘጋ ቤት ስለመኖሩ አወቁ። ይህን ተከትሎ ተፈላጊው ሰው በዚህ ቤት ሊኖሩ ይችላል የሚል ግምት ተያዘ። ከጀርባው ቤት በር ላይ የታየው አንድ ምልክት ለምርመራው የሚረዳ አዲስ ፍንጭ ሆኖ ተገኘ። የቡድን አባላቱ አሮጌውን የእንጨት በር ተጠግተው በአግባቡ ቃኙት። በሩ ላይ በግልጽ የሚስተዋል የደም ነጠብጣብ ቁልጭ ብሎ ታያቸው።
በፖሊሶቹ የሚመራው ቡድን ያገኘውን ማስረጃ በመረጃነት መዝግቦ ሶስቱን እናት ልጅ በቁጥጥር ስር አዋላቸው። አሁንም የምርመራ ቡድኑ በጥንቃቄ አሰሳውን ቀጠለ። በግቢው ውስጥ አዲስ የመጸዳጃ ጉድጓድ ስለመቆፈሩ የደረሰበት ጥቂት ቆይቶ ነበር። ቡድኑ ጊዜ አላጣፋም። በእጁ የገባውን አካፋና ዶማ ተጥቅሞ የመጸዳጃ ቤቱን ጉድጓድ መቆፈር ጀመረ። ከጥቂት ቁፋሮ በኋላ ስፍራው በርከት ባለጭድ መሞላቱ ታወቀ።
ቁፋሮው አልተቋረጠም። ጭዱን ተከትሎ ፍራሽ መሰል ጨርቅ ብቅ ሲል ታየ። ሁሉም ተመልካች በድንጋጤና በተለየ ትኩረት የሚሆነውን ጠበቀ። የቆፋሪዎቹ አካፋና ዶማ ጥቂት ዘልቆ ቁፋሮውን ቀጠለ። እጅና እግሩ በገመድ የተጠፈረ፣ መላ ሰውነቱ በቡትቶ ጨርቅ የተጠቀለለ በድን አካል በድንገት ተከሰተ።
በግቢው ድንጋጤ የወረሰው ጨኸትና፣ እሪታ ተከተለ። ከቀናት በፊት…ሚያዝያ 7 ቀን 2006 ዓ.ም በሀብት ይገባናል ምኞት በቁጭት ሲብሰለሰሉ የቆዩት እናትና ልጆች፤ የሀሳባቸው መቋጫ መድረሱን አውቀዋል።
ይህ ምሽት ልባቸው የሚሞላበት ያሰቡት ሁሉ የሚሳካበት ይሆናል። እናት በጉዳዩ ከልጆቻቸው ከመከሩ ቆይተዋል። ልጆቹም ይህን እንደሚፈጽሙ አረጋግጠዋል። አሁን አባወራው ንጋቱ በተለመደው ሰዓት ከቤታቸው ደርሰዋል። የታቀደ፣ የተደገሰላቸውን አላወቁም። የሚሆነውን አልጠረጠሩም። ምሽቱ ለእሳቸው እንደሌላው ቀን ነበር። ሚስት የባላቸውን፣ ልጆቹም የአባታቸውን መድረሰ አረጋግጠዋል። ሰውዬው ቤት ከገቡ ለመኝታ እምብዛም አይቆዩም። ይህን አሳምረው የሚያውቁት እናትና ልጆቹ የአባወራውን በዕንቅልፍ መሸነፍ እየጠበቁ ነው። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ሆኗል። ሶስቱ ሰዎች ወደአባወራው መኝታ ተጠጉ፤ ሰውዬው ቢጎትቷቸው አይሰሙም። በከባድ ዕንቅልፍ ተሸንፈዋል።
የትዳር አጋራቸውና ሁለቱ የአብራካቸው ክፋዮች መጥረቢያና ዱላቸውን አነሱ። ዕንቅልፍ በጣላቸው ሰው አካል ላይም አሳረፉ፤ ሰውዬው ለመጮህና ለማምለጥ ዕድል አላገኙም። በከባድ ሲቃ ተውጠው መንፈራገጥ መንፈራፈር ያዙ። ቤተሰቦቻቸው አልሳሱላቸውም። እየደጋገሙ የጭካኔ ምታቸውን አበረቱ።
ይህ ሲሆን ከነሱ በቀር ያየ፣ የሰማ አልተገኘም። መርማሪው ሳጂን ከበደ ካሳ ሶስቱ ሰዎች ቀጥሎ ያደረጉትን እንዲያስረዱት ጠየቃቸው። የአባወራውን አስከሬን ከቤት አውለውና አሳድረው በግቢው በቆፈሩት አዲስ የመጸዳጃ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ ጠፍረው እንደቀበሩት ተናገሩ።
መርማሪው የተጠርጣሪዎቹን ሙሉ ቃል ከመዝገቡ አሰፈረ። የወንጀል አፈጻጸሙ የክስ ሂደት ይቀጥል ዘንድም የምርመራ መዝገቡን ለዓቃቤ ህግ አስተላለፈ።
ውሳኔ…
ኅዳር 5 ቀን 2007 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሶስቱን ተከሳሾች የክስ መዝገብ ሲመረምር ቆይቶ ለመጨረሻ ውሳኔ በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በወንጀሉ ባላቸው ተሳትፎ ልክ ድርጊታቸውን መዝኖ ይገባቸዋል ያለውን የፍርድ ውሳኔ አስተላለፈ። በዚህም መሰረት በአንደኛው ተከሳሽ ልጅ ላይ የሞት ፍርድ፣ እንዲሁም አባወራውን በጭካኔ በገደሉ ቀሪዎቹ እናትና ልጆች ላይ የዕድሜ ልክ የእስር ቅጣትን በይኗል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014