• ተፈናቃዮች ባሉበት ይቆጠራሉ
• ‹‹ሲ ኤስ ፕሮ›› የተባለ ሶፍትዌር ሥራ ላይ ይውላል
አዲስ አበባ፡- መጋቢት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚጀመረው አራተኛው ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጄንሲው ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፤ አራተኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለማካሄድ አስፈላጊውን መሳሪያና የሰው ኃይል ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት አበራሽ ታሪኩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ተፈናቃዮች ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ቆጠራው እስከሚጀመርበት ጊዜ ድረስ ወደመጡበት አካባቢ መመለስ ያልቻሉት ዜጎች ግን ባሉበት ቦታ ይቆጠራሉ፡፡
በቆጠራው ወቅትም ተፈናቃዮቹ የመጡበትን ብሄር ጨምሮ ማኛውንም መረጃ በአግባቡ መግለጽ እንዳለባቸው የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ ለቆጣሪዎችም አስፈላጊው ሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ የመጡበት አካባቢና ተፈናቅለው ያሉበት አካባቢም በመረጃው እንደሚካተት ጠቅሰው ጉዳዩን የሚከታተል አካል መኖሩንም አብራርተዋል፡፡ እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ በሕዝብና ቤት ቆጠራው ብሄር፣ ጾታ፣ ሃይማኖትና የማህበራዊ አኗኗር ሁኔታዎችም ይመዘገባሉ፡፡
በብሄር አሞላል ላይ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል የብሄር ኮድ አልተሰጠም፡፡ ለዚህም የብሄር ስብጥርን መረጃ አስፈላጊነት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እንደሚሰጥና በተለያየ አጋጣሚ ትክክለኛ ብሄራቸው ይሄ ነው ማለት ለማይችሉትም ‹‹ሌሎች›› የሚል ኮድ ተዘጋጅቷል፡፡ በሌላ በኩል የአንድ ቤተሰብ አባላት ሆነው የተለያየ ሃይማኖት የሚከተሉ ስለሚኖሩ እያንዳንዱን ተቆጣሪ ሃይማኖት እንደሚጠየቁም ወይዘሪት አበራሽ ተናረዋል፡ ፡
ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ግን በወላጆቻቸው ሃይማኖት የሚሞላ እንደሆነ ጠቁመዋል። በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ የሶፍትዌር ልማት እና ዳታ ቅብብሎሽ ቡድን መሪ አቶ ታቢት አህመድ እንደገለጹት፤ አራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከዚህ በፊት ከተደረጉት ሦስት ቆጠራዎች በተለየ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ነው፡፡ ለዚህም በአሜሪካ የቆጠራ ቢሮ የተዘጋጀውና ቀደም ሲል የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ የተለያዩ ጥናቶችን አድርጎበት ውጤታማ የሆነው ‹‹ሲ ኤስ ፕሮ›› የተሰኘ ሶፍትዌር ሥራ ላይ ይውላል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011
በዋለልኝ አየለ