አገር ተብሎ በወል ስም ሲጠራ ብዙ ሀሳቦች ወደ አእምሯችን እንደሚመጡ እሙን ነው። ለምሳሌ ያህል “አገር ማለት ሰው ነው ሰው ማለት አገር ነው” ከሚለው አባባል አንስቶ እስከ “ወንዙ፣ ተራራው፣ አየሩና ሸንተረሩ” በሚሉ የተለያዩ መገለጫዎች እንሞላለን።
ይህ እንዳለ ሆኖ እኔ በግሌ “አገር የሚመሰረተው በሰው አማካኝነት ነው ወይስ በተፈጥሮ ከተቸረን መልከአ ምድር ብቻ? ወይስ ሌላ የማይታወቅ መስፈርት ይኖረው ይሆን?” በማለት ለመጠየቅ እወዳለሁ።
ሃሳቡን በዚህ መልኩ ለማስቀመጥ የፈለኩት ያለምክንያት አይደለም። ጆሴ ኦርቴጋ የተባለ ፖርቹጋላዊ ፀሐፊ ይህንኑ ጉዳይ አንስቶ የራሱን አተያይ በዚህ መልኩ ያስቀምጣል “የአገር ዋርካ የሚቆመው በጋራ አብሮነት ነው፤” የሚል። እኔም ይሄንን እጋራለሁ “ኢትዮጵያዊነትም የጋራ አብሮነት ውጤት” የሚል አመለካከትም አለኝ። እንደ እኔ ሃሳብ ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ነው።
ዜግነት ደግሞ በአንድ የተወሰነ አገር ውስጥ የጋራ አብሮነትን የሚያሳይ ስርአት ነው። በዚህ እሳቤ ከሄድን የምንረዳው አንድ ነገር ቢኖር እኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ መሰረት፣ የጋራ ጉዳይ፣ የጋራ ባህል፣ ለወደፊትም የጋራ እድል ያለን ሕዝቦች መሆናችንን ነው።
የተሰባሰብነውም በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ነው። ይህ ማለት ዛሬ እና ትናንት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ነገና ለወደፊትም አብሮ ለመኖር የጋራ ስምምነት ያለን ሕዝቦች የሚያመላክት ነው።
በዚህ ሃሳብ ከተስማማን ዘንዳ “ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገን አብሮ ለመሆን ህልማችን አሊያም ወደ ግባችን ጋር የሚያደርሰን ምን ሰርተናል?” ስል እጠይቃለሁ። በአንድ ያሰባሰበን ዋልታና ማገር ውርጩንና ውሽንፍሩን ከመከለል ባሻገር አብሮነታችን እንዲጠነክርና እንዲጎላ የሚያስችል መሰረት እንዲኖረው አድርገን ይሆን ያነፅነው? ይህ እንዲሆን የጋራ ስርአት የጋራ መሰረታችንን የቱ ጋር ጀምረናል? እስከ የትስ ነው የምንሄደው? የሚለውን ሀሳብ አሁን መጠየቅ ግድ የሚለን ይመስለኛል። እንኳን “ኢትዮጵያዊ” የሚል ስም ይዞ በጋራ የሚኖረው ሕዝብ ይቅርና ጎረቤት አገሮቻችን እንደ ኤርትራ፤ ሶማሌ በቋንቋም በባህልም በእጅጉ ይመስሉናል።
ኧረ እንዲያው ሁሉንም እንተወውና “ሰው” የሚለው እሳቤ ብቻውን ያስተሳስረናል። ሰው አንድ የሚያደርገው በርካታ ነገሮችን በማዳበር ነገ የሚሻገር አገር ለመስራት መጣር ይገባዋል።
አሁን አሁን ግን “ለምን ትናንሽ ሀሳቦችን እያነሳን ልንቆራቆዝ ተነሳን” የሚል ሀሳብም ወደልቤ እየተመላለሰ ቤተኛ ከሆነኝ ሰነባብቷል። ለመሆኑ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለፀቦቻችን መነሻ የምናደርጋት የጋራ ቤታችን የአሁኗ ኢትዮጵያ እንዴት ተመሰረተች? እንደኔ እንደ እኔ ኢትዮጵያ የቆመችው በአፄ ምኒልክ ዘመን ነው።
አሁን ላይ ላለው የአንድነት ክፍፍልና የእርስ በእርስ መጠላለፍ መሰረት የሆነውም ያንን የኢትዮጵያ አመሰራረት የምንረዳበት መንገድ ለየቅል መሆኑ ነው ብዬ አስባለሁ። ግማሹ “በቅኝ ግዛት (ወረራ) አይነት የተፈጠረች ነች” ሲል፤ ከፊሉ ደግሞ “ቀድሞ የነበረችውና ኋላ ላይ በታሪክ አጋጣሚ የተበታተነች ኢትዮጵያን መልሶ አንድነቷን ማስጠበቅ ነው” ይላል።
ይህ ሁሉ ግን የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች፣ ወደ ምስራቅ አፍሪካ መስፋፋት ሲጀምሩ ኢትዮጵያን የመከፋፈል የተጠቀሙት ሴራ ላይ የተንጠለጠለ ነው። ምክንያቱም ምንም እንኳን አጼ ምኒልክ የሰሩት አገርን አንድ የማድረግ ተግባር ሴራቸው ያከሸፈ ቢሆንም፤ ሰሜኑን ከደቡብ ለመነጠል ብርቱ ሥራ ሰርተው ነበር።
እንደ እኔ እይታ ያኔ አፄ ምኒልክ፤ በሉዓላዊነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከት፣ ሁሉም በጋራ መቆም አለባቸው ከሚል መነሻ ነው አንድነት መፍጠሩን ምርጫቸው ያደረጉት። በዚህ መሃል ግጭት፣ በግጭት መሃል ሞት ይኖራል፤ ይሄ የታሪካችን አንድ ክስተት ነው።
ዛሬ አንድ ሆኖ የሚታየው አብዛኛው አገር፣ አሁን ላይ የያዘው ቅርፅ በእንዲህ አይነት ክስተቶች አልፎ የመጣ ነው። መልካም መሰረትን ለመጣል ሲነሱ ሁሉም ሰው ነቃፊ ባይሆንም ደጋፊ ይሆናል ማለት ግን አይቻልም።
የአንድነት ጉዞው ያስቆጣቸው ያኮረፉም ሆነ ለዛሬዋ አገር መቆም መሰረት ናት ብለው የሚያምኑቱ ዳር እስከዳር ተነቃንቀው ጣሊያንን በዓድዋ ተራሮች ላይ ተዋድቆ ስለመከተው ኢትዮጵያዊነት ግን ቅሬታ ያላቸው አይመስለኝም። ለዚህም ምስክሩ ታላቁ የጥቁሮች ድል ዓድዋ ነው።
ከላይ የተመለከትነው አይነት በአንድ ተሰባስቦ አገር የማጽናት ውጤት የታየው በዓድዋ ጦርነት ላይ ነው። በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በግልፅ ለአንዲት የጋራ ሉዓላዊ አገር ተዋድቀዋል። ስለዚህ ዓድዋ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ ነው። ዓድዋ ላይ የምናየው ኢትዮጵያዊነትን ነው።
የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በጋራ የሉዓላዊነት አደጋን የቀለበሱበትና አብሮነታቸውን ያጠናከሩበት፣ ወደፊትም በነፃነት ለመኖር የተስማሙበትና ሁሉም ለወደፊት አብሮነታቸው አሻራቸውን ያሳረፉበት ነው ዓድዋ።
ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት የጋራ አብሮነት ውጤት ነው። ለዚህ ነው ለኢትዮጵያዊነት በአንድነት መትመም፤ ለነፍስ ሳይሳሱ ለሞት መሽቀዳደም ምሳሌው ዓድዋ የሆነው። ኢትዮጵያዊነት ማለት በአብሮነት የሚቀጥል፣ የወደፊት ነፃነትን አስከብሮ የሚያኖር፣ በጋራ ለማደግ የመስማማት ውጤት ጭምር ነው።
በዚህ መንፈስ ነው ነፃነታችንን አስከብረን ዛሬ ላይ የደረስነው። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ቅኝ ግዛት ውስጥ የወደቁበት ሚስጥሩ፣ ይሄን አብሮነት ማጣታቸው ነው። ስለዚህ ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማለት በወደፊት አብሮነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው።
በኢትዮጵያዊነት ነው ቅኝ ሊገዙን ለፈለጉት ያልተበገርነውና እራሳችንን አስከብረን የኖርነው። ይሄ የመተሳሰራችን የህብረታችን ውጤት ነው። እኔ እንደማምነው በመካከላችን በአፍ እየተቀባበሉ ከሚሰብኩን ጥላቻ በላይ ምድር ላይ በመኖር ሂደት ውስጥ ያልጠፋ የአብሮነት ስሜትን ይታየኛል።
ሁሉም ፈጣሪን የሚያምን ፈሪያ እግዚአብሔር ያለው ሕዝብ ይዘን ልባችን በሞላው ክፋት እንደዥዋዥዌ “አንዴ እዚህ አንዴ ደግሞ እዚያ” ባንላተም የተሻለ ይሆናል። በቅንነት ስህተትም ልማትም መልካም ነው።
ከጀርባው ተንኮል የሌለው አካሄድ “ነገ” ተሰርታ ልናያት ለምንሻት አገራችን መሰራት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ዛሬ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ትግሬ እያልን እርስ በእርስ የምንከራከረው፣ የጋራ ጉዳይ፣ የጋራ አገር ስላለን ነው።
ክርክሩ ራሱ የተመሰረተው በጋራ ጉዳያችን ላይ ነው። አሁን ማተኮር ያለብን “ለወደፊት በጋራ ልዩነቶቻችንን አቻችለን እንዴት እንኑር” በሚለው ጉዳይ ላይ ነው።
“በምን መንገድ ነው ከትንሽ ስንጥቃት ተነስቶ ትልቅ ገደል የሆነብንን የልዩነቶቻችንን ክፍተት የምንሞላው? እንዴትስ ነው አንድ የሚያደርጉንን ነገሮች አጉልተን ከጥላቻና ከመጠፋፋት ሀሳብ የላቀ አብሮነት የሚያመጣልንን በረከት የምንቋደሰው?” በማለት እራሳችንን ጠይቀን እየከረረ የመጣውን ልዩነታችንን ማስታረቅ እንችላለን የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ።
ሌላውና ዋናው ነገር “አገር ማለት የጋራ አብሮነት ውጤት ነው” ካልን “እገሌን የትኛውን ቁስሉን ስነካው ነው የበለጠ የሚያመው?” እያልን እሳት ከምንጭር ይልቅ “እንዴት ነው በጋራ የወደፊቷን አገራችንን ገንብተን ለልጅ ልጆቻችን የተረፈች የሰላም ደሴት የምናደርጋት?” የሚል ሀሳብ በሁላችንም ልብ ይፀነስ ዘንድ እየተመኘሁ ሃሳቤን በዚሁ ልቋጭ። ሰላም!
ብስለት
አዲስ ዘመን መጋቢት 17 /2014