መሬቱን ሰንጥቆ በመውጣት ያለማንም ከልካይ መንገዱን ይዞ እንደወራጅ ውሃ ይፈሳል።ማረፊያውም በአካባቢው በሚገኝ መቸላ ወንዝ ነው። ውሃ እና ዘይት ሲቀላቀል የሚኖረውን አይነት መልክ በወንዙ ውስጥ ምልክት ሆኖ ይታያል። ይህን ያየው የአካባቢው ነዋሪም እንግዳ የሆነውን ነገር በአቅራቢያው ለሚገኘው የመንግሥት ተቋም በማሳወቅና ውሎ አድሮም ሀብቱ ስለሚሰጠው ጥቅምና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ሲገነዘብ በመንግሥት ትኩረት አግኝቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ጥያቄ በማቅረብና ሀሳብ በመስጠት ብዙ ደክሟል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲም የሀብቱን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የመጀመሪያ ጥናት አካሂዷል።ዩኒቨርሲቲው የሀብት መጠኑን ለማወቅና ሌሎች መረጃዎች ለመሰብሰብ ሁለተኛ ዙር ጥናት ለማካሄድ ቢያቅድም የበጀት እጥረት ገጥሞት ሊቀጥል አልቻለም። እንዲህ የአካባቢ ማህበረሰብ ጥያቄ ያነሳበት፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲም ጥናት በማካሄድ ጥረት ያደረገበት፣ ዶማና አካፋ ይዞ ጥልቅ ጉድጓድ መቆፈር ሳያስፈልግ፣ ብዙ ድካም ሳይጠይቅ መሬት ሰንጥቆ ከምድር ውስጥ የተገኘው ሀብት ለኃይል የሚውል ነዳጅ ነው።
ሀብቱ የሚገኘው ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ ለገሂዳና ወረኢሉ በሚባሉ ወረዳዎች ድንበር ላይ መቸላ በተባለ ወንዝ አቅራቢያ ነው። በአካባቢው እንዲህ ያለ ምልክት መታየቱና ነዳጅ ፍለጋ የሚካሄድባቸው እንደ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን፣ ሰሜን አፋር፣ ኦሞ ወንዝ፣ ደቡብ ክልል አካባቢዎች ተደምረው ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ነዳጅ አምራች ከሚባሉ አገራት ጎራ የምትቀላቀልበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ትልቅ ተስፋ አሳድሮ ነበር። በፎቶግራፍ ጭምር ተደግፎ እየቀረበ ብዙ የተባለለት ይህ ሀብት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ፣ ጥቅም ላይ ውሎ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖረው በጥናት ጭምር ይደረግ የነበረው ጥረት ስለመቀጠሉ፣እንደሚከተለው ቃኝተናል። ዋቢ ያደረግነውም በደቡብ ወሎ ዞን በኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሥር የሚገኘውን የማዕድን ዘርፍና በጥናትና ምርምር የተሳተፈውን ወሎ ዩኒቨርሲቲ ነው።
በዞኑ በለገሂዳና ወረኢሉ ወረዳዎች ድንበር መቸላ ወንዝ አቅራቢያ ተገኘ ስለተባለው የነዳጅ ሀብት በመምሪያው የማዕድን ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ጀማል እድሪስ እንዳስረዱት፤ በእነርሱ ተቋም ነዳጁ በአካባቢው የተገኘበትን ወይንም የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ በመረጃ ማስደገፍ ባይቻልም በአካባቢው በስፋት መነገር የጀመረው ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ነው።
ሀብቱን ቀድሞ ያየውም የአካባቢው ማህበረሰብ ሲሆን፣ መረጃውም የተገኘው ከአካባቢው ማህበረሰብ ነው። ነዳጁ የፈሰሰበትን እርጥበት ያለውን አፈር ወይንም ጭቃ ወስዶ በማንደድ ለሚፈልገው አገልግሎት በማዋል ኃይል የሚሰጥ መሆኑንም የአካባቢው ማህበረሰብ በራሱ አረጋግጧል። የነዳጅ ሀብቱ ወደ መንግሥት መዋቅር ውስጥ የገባው በዚህ ሂደት ነው።
የአካባቢው ማህበረሰብ የሰጠውን መረጃ መነሻ በማድረግ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከገባ በኋላ ምን ተግባራቶች ተከናወኑ? አቶ ጀማል በሰጡት ማብራሪያ፤ ሀብቱ በጥናት ተረጋግጦ ከተለየ በኋላ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላይ እንዲውል ከማዕድን ዘርፍ ጋር በተያያዘ መድረኮች ሲኖሩ ጉዳዩ የአካባቢውን ማህበረሰብ ጨምሮ በወረዳና በዞን ይነሳል። የፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴርም ሀብቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ተንቀሳቅሷል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሳልኮም ፔትሮሊየም ለተባለ ኩባንያ 2005 ዓ.ም ላይ ፈቃድ ሰጥቶ ኩባንያው በአካባቢው ላይ እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ኩባንያው ሥራውን ከዳር አላደረሰውም።
ኩባንያው ሪፖርት ሲያቀርብ የነበረው ፈቃድ ለሰጠው አካል በመሆኑ ማዕድን ዘርፉን የሚመራው የዞኑ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የተደራጀ መረጃ የለውም። በአገሪቱ የማዕድን ልማት አዋጅ መሠረት በኢንደስትሪና ነዳጅ ማዕድናት ልማት ላይ የሚሰማሩ ወደ ማምረት ሥራ ከመግባታቸው በፊት ቅድመ ልማት ጥናት ያካሂዳሉ። ቅድመ ልማት ጥናቱ ሀብቱ መኖሩን፣ አዋጭነቱንና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን የሚያካትት ሲሆን፣ የጥናት ሥራው እስኪጠናቀቅም ጊዜ ይወስዳል። ሳልኮም ፔትሮሊየም ኩባንያም በቆይታው ከጥናት ያለፈ ሥራ እንዳልሰራ መገመት ይቻላል። የቅድመ ጥናት ሥራ በቂ በጀት ይዞ መስራት ስለሚጠይቅ የገንዘብ እጥረት ገጥሞት ሥራውን ጥሎ እንደወጣ ቅድመ ሁኔታዎቹ ያሳያሉ።
ጅምር ሥራው ለውጤት ባይበቃም። የተጀመረው ሥራና ጥረት መቋረጥ የለበትም።በተለይም ሀብቱ የሚገኝበት አካባቢ ሌሎች የማዕድን ሀብቶችን እንደሚያስተዳድረው ሁሉ ትኩረት ሊሰጠውና ነገሩን እንደዋዛ ሊያየው ስለማይገባ አሁን ስላለው ነባራዊ ሁኔታና ቀጣይ ሥራዎች ምን መልክ ይኖራቸዋል ስንል ላነሳነው ጥያቄ አቶ ጀማል ‹‹ሳልኮም ኩባንያ አቋርጦ ከወጣ በኋላ ጥያቄ ያቀረቡ ሌሎች ድርጅቶች አልተገኙም። ይሁን እንጂ የአካባቢው ማህበረሰብ ሀብቱ ጥቅም ላይ አንዲውል ግፊት ከማድረግ አልተቆጠበም።የለገሂዳ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትም በተንቀሳቃሽና በፎቶ ምስል በማስደገፍ ሀብቱን በማስተዋወቅ ትኩረት እንዲያገኝ፣ እንዲሁም ባለሀብት ለመሳብ ጥረት እያደረገ ነው። ዘርፉን የሚያስተዳድረው ክፍል አመራርም ለፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር በማሳሰብ ጥረቱ አልተቋረጠም። የቆየ ቢሆንም እኔና የወረዳው አስተዳዳሪ ማዕድን ሚኒስቴር ባመቻቸው መድረክ ላይ ተገኝተን ጉዳዩ ተነስቶ ከአካባቢው የሚቀርበው ጥያቄ ተገቢ እንደሆነና ድርጅቶችን ወደ ሥራው እንዲገቡ የማድረግ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ቃል ተገብቶ ነበር።ይሁን እንጂ ወደተግባር የተለወጠ ነገር የለም። ጥያቄ ማቅረብም ሆነ የማስተዋወቁ ሥራ አሁንም አልተቋረጠም›› በማለት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስረድተዋል።
አቶ ጀማል እንደገለጹት አካባቢውን ከልሎ ጥበቃ ለማድረግ ስፋት ስላለው ጥረት አልተደረገም። እስካሁንም በአካባቢው ላይ ደረሰ የተባለ ጉዳት ባለመኖሩና ለዘረፋም ይጋለጣል የሚል ስጋት ባለመፈጠሩ ልዩ ትኩረት ለማድረግ መነሳሳት አልተፈጠረም።በዙሪያው የግብርና ሥራ ይከናወናል። አንዳንድ ጥርጣሬዎች ቢኖሩ እንኳን የአካባቢው ማህበረሰብ ነቅቶ የሚጠብቅ በመሆኑ ችግሩን መቆጣጠር ይቻላል። ነዳጁ በተገኘበት አቅራቢያ ትምህርትቤትም ይገኛል። በአንዳንዶች በሚሰጠው መላ ምትና ግምት ትምህርትቤቱ በሚገኝበት ስፍራ ጭምር ነዳጅ በስሩ ይኖራል። በአካባቢው ነዳጅ መገኘቱ ከተሰማ አመታት ተቆጥሯል። መጠኑ እየጨመረ ነው ወይንስ ባለበት ነው የሚለውን ክትትል ያደርጉ እንደሆነም አቶ ጀማል ለቀረበላቸው ጥያቄ የተለየ ፍሰት አለመኖሩ መረጃው እንደሌላቸው ነው ምላሽ የሰጡት።
‹‹ሀብት ላይ ሆነን የምንራብ ሰዎች እኛ ኢትዮጵያውያን ነን›› የሚሉት አቶ ጀማል፤ ሀብቱን ወደ ጥቅም መለወጥ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ። ‹‹አካባቢያቸው ላይ የተገኘው የነዳጅ ሀብት በራሱ ጊዜ ወጥቶ የተገኘ ሀብት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የነዳጅ ሀብት የኦጋዴን፣ የአባይ፣ የጋምቤላ፣ የመቀሌና መተማ ተብሎ ተከፋፍሎ ነው የተቀመጠው።ከእነዚህ ውስጥ ወደ መሬት በተጋለጠ ሁኔታ የወጣው በአባይ ክፍል የሚገኘው በለገሂዳና ወረኢሉ ወረዳዎች ድንበር ላይ የተገኘው ነዳጅ ነው። ነዳጅ በአሁኑ ጊዜ በዓለምአቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ መሠረታዊ በሆነበት ሁኔታ በቀላሉ የተገኘውን ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ወደኋላ መባል የሌለበት ጉዳይ ሆኖ ወደ ሥራ ማስገባቱ ላይ መጓተቶች ይስተዋላሉ።ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በገጠማት ጦርነትና በዓለም ላይ በተከሰተው በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያቶች እንደ አገር ሥራዎች መስተጓጎላቸውና አካባቢያችንም በጦርነቱ ምክንያት ለተወሰኑ ጊዜያቶች እንቅስቃሴዎች አልነበሩም። እነዚህ ተደማምረው የነበረውን ክፍተት አባብሰውታል። በክልልና በፌዴራል ደረጃ የጥናት ሥራ እንዲጠናከርና ትኩረት እንዲሰጥ ትረታችን ይቀጥላል›› ሲሉ አስረድተዋል። አሁን ላይ አካባቢው በመረጋጋቱ የማዕድን ዘርፍ ላይ መሰማራት የሚፈልግ የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ኩባንያ ወደ አካባቢያቸው እንዲሄድ ጥሪ አቅርበዋል።
የመጀመሪያውን ጥናት ያደረገው የወሎ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ግኝትና ቀጣይ ሥራ በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብኩላቸው በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል በኢንጂነሪንግ ጂኦሎጂ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርትክፍል ኃላፊ ዶክተር ደሳለኝ ገዛኸኝ እንዳስረዱት፤ ከሶስት አመት በፊት (2011 ዓ.ም) ነው የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስፍራው በመሄድ የጥናት ሥራውን ያከናወነው። የጥናት ቡድኑም በስፍራው ተገኝቶ ያረጋገጠው ከመሬት ውስጥ የሚፈስ ነዳጅ መኖሩን ነው። የመንደድ ባህሪ ማሳየቱም ነዳጅ ስለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫም ስለነበር በዚህ መንገድም ተፈትሾ ተረጋግጧል። የጥናት ቡድኑ ናሙና ይዞ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመመለስ በቤተሙከራ ቤት ውስጥ በተከናወነው የምርምር ሥራ ከፍተኛ የሆነ (98 በመቶ) የነዳጅ ድፍድፍ መኖሩ ነው የተረጋገጠው። ጣሊያን ኢትዮጵያን በኃይል በወረረበት ወቅት የቀበረው ነው የሚል አባባል አለ። በጥናት የተረጋገጠው ግን ትክክለኛው የነዳጅ ድፍድፍ ከመሬት ውስጥ መኖሩን ነው። ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የምርምር ውጤቱ በጥናት ቡድኑ ቀርቧል። ጥናታዊ ውጤቱም በጥናትና ምርምር የህትመት ውጤት (ጆርናል) ላይ እንዲወጣ ተደርጓል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ጥናት ሥራ በዚህ መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጣይ ሥራ የሀብት መጠኑን ማጥናት ነበር። ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር ደግሞ በቂ የሆነ በጀት ያስፈልጋል። ጥያቄውም ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ቀረበ። ግን ምላሽ አልተሰጠም። በወቅቱ በማዕድን ሚኒስቴር የሚመለከተውን አካል በማነጋገር የተደረገውም ጥረት ሁለተኛው የጥናት ሥራ እንዲቀጥል የሚያስችል አልነበረም። አስፈላጊ መረጃም ሆነ ድጋፍ ማግኘት አልተቻለም። በመሆኑም የጥናት ሥራው በዚህ ተገድቦ ቀርቷል። ቀጣይ የጥናት ሥራው በቂ በጀትና ለሥራው የሚያግዝ መሳሪያ ያስፈልጋል። የጥናት ቡድኑ መንግሥት በውጭ ኩባንያ የማስጠናት ፍላጎትም ካለው የመጀመሪያውን ጥናት ያካሄደው ቡድን አጋዥ ሆኖ ሊሰራ እንደሚችል ተጨማሪ ሀሳብ ጭምር በአማራጭ አቅርቧል። የነዳጁ መጠን ስለመጨመሩም ሆነ በአካባቢ ሥነምህዳር ላይ ሊያሳድር ስለሚችለው ተጽዕኖ በጥናት ቡድኑ በኩል ዳግም ለማየት የተሞከረ ነገር ይኖር እንደሆን ዶክተር ደሳለኝ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤የአካባቢው ማህበረሰብም ለብርሃን እየተጠቀመበት እንደሆነ እንደማንኛውም ሰው መረጃውን ከመስማት ውጭ በእነርሱ በኩል የተለየ ሥራ አልተሰራም።
አሁን ባለው ዓለምአቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ያሻቅብ እንደሆን እንጂ ይቀንሳል የሚል ግምት የለም። ነዳጅ ደግሞ ከእለት እንቅስቃሴ ጀምሮ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ እጅግ ይፈለጋል። በአሁኑ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ኢኮኖሚያዋ ላይ ጫና እየተፈጠረባት ላለው ኢትዮጵያ ደግሞ የነዳጅ ዋጋ መጨመር አዳጋች ይሆናል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ምድር የሰጣትን ሀብት ወደ ጥቅም መለወጥ ላይ ነገ ዛሬ የሚባል መሆን የለበትም። ጥረቶች ቢኖሩም መቆራረጦች በማጋጠማቸው ለውጤት አልበቃም። ከሰሞኑ ደግሞ አንድ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ከማዕድን ሚኒስቴር ተሰምቷል። በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ቤዚን (ተፋሰስ) ላይ በቻይና ኩባንያ ሲካሄድ የነበረው የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ከግብ ሳይደርስ አመታት መቆጠሩ ይታወሳል።ማዕድን ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሚገኘውን ይህን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ስምምነቱ ከኔዘርላንድስ ስዌል እና አሶሼት ኢንክ ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ሲሆን፣ ኩባንያው በሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ 3 ሺህ 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ የተሰሩ የፍለጋ እና የጥናት ውጤቶችን መነሻ በማድረግ በአካባቢው ያለውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት መጠን የማሳወቅና ኢኮኖሚያዊ ግምገማን የሚያሳይ ጥናት እንደሚካሄድ ነው ዘገባዎቹ የሚያመለክቱት። በስምምነት ስነስርአቱ ላይ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን የኩባንያው ተወካዮች እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸውም ተመልክቷል። ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በኢትዮጵያ በእያንዳንዱ አፈር ሥር የሚገኝ ሀብትን ወደ ውጤታማነት ለመቀየር ያለውን ሀብት ለማወቅ፣ አውቆ ለመቀመጥ ሳይሆን በሀብቱ ለመበልጸግ፣ በተለይም በኦጋዴን ቤዚን አካባቢ የሚገኘውን ሀብት ቴክኖሎጂን በመጠቀም አልምቶ ለአገራዊ ጥቅም ለማዋል በተደረገው ጥረት የወጣውን ጨረታ አሸናፊ ለሆነ ድርጅት መስጠት መቻሉን መናገራቸውም ተገልጿል። ኩባንያው በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባና የጥናት ሥራውም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ማሳወቁ ታውቋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓ.ም