ድጋፍና ክትትል የሚያስፈልገው የክልሉ ማዕድን ልማት

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ወርቅና የድንጋይ ከሰል ጨምሮ በተለያዩ ማዕድናት የበለጸገ ነው፡፡ በክልሉ ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት እና የከበሩ ማዕድናት ይገኛሉ። በተለይ በዳውሮ እና በኮንታ አካባቢዎች ወርቅና የድንጋይ ከሰል በስፋት ይገኛል።

ቀደም ሲል የተካሄዱ ጥናቶችም በክልሉ ከ36 ዓይነት በላይ ማዕድናት እንዳሉ ማመላከታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በክልሉ ሌሎች ማዕድናት እንዳሉ ጠቋሚ አመላካቾች መኖራቸውንም የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በርካታ አምራቾችም በዘርፉ ተሰማርተው እየሠሩ ናቸው፡፡ በዳውሮና በኮንታ አካባቢዎች እንዲሁ የድንጋይ ከሰል ከፍተኛ ክምችት ያለ መሆኑን ተከትሎ የድንጋይ ከሰል በከፍተኛ ደረጃ ማጠብ የሚችል ፋብሪካ ተገንብቶ በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረማርያም ሰጠኝ እንደሚሉት፤ ክልሉ የበርካታ ማዕድናት ባለቤት ነው፡፡ ለውጭ ገበያ በሚቀርቡና የውጭ ምንዛሬ ወጪን በሚያስቀሩ እንደ ወርቅ እና ድንጋይ ከሰል ባሉት ላይም ክልሉ አተኩሮ ይሠራል፡፡

ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ ውጤታማ አፈጻጸም ለማምጣት አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ያመለክታሉ፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በተለይ ወርቅ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉትም፤ በበጀት ዓመቱ 300 ኪሎ ግራም ወርቅ እንዲሁም በስድስት ወራት 150 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት ታቅዷል፡፡ ከዚህም በስድስት ወራት 75 ነጥብ 525 ኪሎ ግራም ወርቅ ተመርቷል። በድንጋይ ከሰልም እንዲሁ በስድስት ወራቱ 100ሺ ቶን ለማምረት ታቅዶ፤ 50ሺ ቶን የድንጋይ ከሰል ተመርቷል፡፡

የወርቅም ሆነ የድንጋይ ከሰል ምርት የእቅዱን 50 በመቶ ያህል ነው መፈጸም የተቻለው፡፡ ወርቅ የታቀደውን ያህል መፈጸም ላልተቻለበትና ለምርቱ መቀነስ ዋንኛ ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ ሕገ ወጥነት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በወርቅ ሕገ ወጥ ግብይት ላይ የተሠማሩ አካላት በተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ወርቅ ወደ አጎራባች ክልል በማውጣት በጋምቤላ ክልል ዲሞ አካባቢ በመውሰድ እንደሚሸጡ ያመላክታሉ፡፡

የድንጋይ ከሰል አምራቾች በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች የተነሳ በሙሉ አቅማቸው ማምረት አለመቻላቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የነዳጅ አቅርቦት አለመኖር ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም አምራቾች ነዳጅ በሚፈልጉት ልክና መጠን እንደማያገኙ ገልጸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ሙሉ ጊዜያቸውን በድንጋይ ከሰል እጥበት ሥራ ላይ ማዋል አለመቻላቸውን አመልክተዋል። ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ የዘርፉ አካላትም የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል አለመደረጉ ሌላው ክፍተት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፉ ከመሬት ኪራይ፣ ከሮያሊቲ፣ ከፍቃድ እና ከመሳሰሉት አገልግሎቶች ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። በስድስት ወራት 20 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሰው፣ 35 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

የገቢው አፈጻጸም ከእቅድ በላይ ለመሆኑ ዋነኛው ምክንያት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሆኑንም ጠቅሰው፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አስታውቀዋል፡፡ ይህም በአፈጻጸሙ ላይ ለውጦች እንዲታዩ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ በክልሉ በርካታ አምራቾች ፍቃድ አውጥተው በማዕድን ልማት ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በስድስት ወራቱ 12 ባሕላዊ እና 58 ልዩ አነስተኛ አምራቾች በማዕድን ዘርፉ ተሰማርተው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ባለፉት ስድስት ወራት 12 ልዩ አነስተኛና ሁለት ባሕላዊ አምራቾች ምንም ዓይነት ወርቅ አላቀረቡም፡፡

በበጀት ዓመቱ በሐምሌ ወር በጣም ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩ 32 አምራቾች ፍቃድ መሰረዙንም ጠቅሰው፣ በቀጣይ አሳማኝ ምክንያት በሌላቸው አምራቾች ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ አስገንዝበዋል። ቀደም ሲል ባሕላዊ አምራቾች በርካታ እንደነበሩ አስታውሰው፣ በቅርቡም በባሕላዊ መንገድ ወርቅ ለማምረት እየተደራጁ ያሉ አምራቾች ልማቱን ሲቀላቀሉ ቁጥራቸው ሊጨምር እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

ከልዩ አነስተኛ አምራቾች መካከል አብዛኞቹ ሥራ እንዳልጀመሩ ጠቅሰው፣ የዚህ ዋናው ምክንያት የማሽነሪ አቅርቦት አለመኖር ወይም በ70 ለ30 አብሯቸው የሚሠሩ ባለሀብቶች ባለማግኘታቸው መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አሳማኝ ምክንያት የሚያቀርቡት አምራቾች ምክንያታቸው በደንብ ሊታይና ሊመረመርላቸው እንደሚችል ጠቁመው፤ ከእነዚህ ውጭ ባሉት ላይ ግን ርምጃ መውሰድ የግድ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በድንጋይ ከሰል ማምረት ላይ ፍቃድ የወሰዱ ከ20 በላይ ቢሆኑም፣ ወደ ማምረት ሥራው የገቡት በዳውሮ እና በኮንታ ዞኖች በእያንዳንዳቸው አራት በአጠቃላይ ስምንት አምራቾች ብቻ ናቸው፡፡ በቅርቡ በምርመራ ሥራ ላይ የቆዩ ወደ ምርት እንዲገቡ የተደረገበት ሁኔታ ስላለ በቀጣይ ወራት ምርቱ ይጨምራል ተብሎ ይገመታል። በተለይ በቅርቡ የተመረቀው የኢቲ ማይንግ ፋብሪካ ምርት ወደ ሥራ መግባት በቀሪዎቹ ወራት የምርቱ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የማዕድን ዘርፉ ብዙ የሥራ እድል የሚፈጥር እንደመሆኑ በሥራ እድል ፈጠራ ረገድ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ሰባት ሺ ለሚሆኑ ሥራ አጦች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በግማሽ ዓመቱ ደግሞ ለ3,500 ያህል ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም ግን አነስተኛ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ለዚህም በተለይ ደግሞ በታችኛው መዋቅር ያሉ የኮንስትራክሽን ማዕድናትን (አሸዋ፣ ድንጋይ እና የመሳሰሉትን) ለማምረት ተደራጅተው በሚሠሩ አካላት በኩል ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይ ድጋፍና ክትትል በማድረግ በኩል በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ ይህ ሲሆን ዘርፉ ከሚፈለገው በላይ የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ያመለክታሉ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደጠቆሙት፤ በክልሉ በማዕድናት አለኝታ ቦታ ልየታ ላይ ጥናት ተደርጎ የመለየት ሥራ አልተሠራም፡፡ ክልሉ በ2014 ኅዳር ወር አካባቢ በአዲስ መልኩ የተቋቋመ እንደመሆኑ ቀደም ሲልም እንዲሁ የማዕድን አቅም ክምችቱ መጠን ጥናት አልተካሄደበትም፡፡

ማዕድናቱ በተለመደው መልኩ በባሕላዊ መንገዶች እየተመረቱ ወይም ባለሀብቶቹ በራሳቸው ጥናት እያደረጉ ወደ ሥራ የሚገቡበት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስትቲዩት ጋር የተወሰኑ ጥናቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፣ በጥናቶቹ ውጤት ላይ በመመሥራት ማዕድናቱ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በርካታ የተለያዩ ማዕድናት ስለመኖራቸው ጠቋሚ አመላካቾች አሉ፡፡ በተለይ ምዕራብ ኦሞ ዞን ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶች ከ36 በላይ ማዕድናት እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በማዕድናት ዙሪያ ጥናቶችን በማካሄድ ለመለየት ይሠራል፡፡

በክልሉ ብዙ ቦታዎች ላይ የድንጋይ ከሰል፣ የወርቅም ሆነ ሌሎች ማዕድናት ዓይነቶች ክምችት አለ፡፡ በቤንች፣ በጉራፈርዳ፣ ሸኮ ዞን በየኪ ወረዳ፣ የከበሩ ማዕድናት እንዳሉ ጠቋሚ አመላካቾች ታይተዋል፡፡ እነዚህን በመለየት ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ የድንጋይ ከሰል አምራቾች ምርታቸውን ለኢቲ ማይንግ የሚያቀርቡበት ሁኔታ መመቻቸቱን አመልክተው፣ የድንጋይ ከሰል ጥሬውን ሲሸጡ ወዲያውኑ ገንዘብ አይሰጣቸውም፤ ክፍያ በወቅቱ ካለመከፈሉ ጋር ተያይዞ ችግሮች እየፈጠረባቸው ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ አምራቾቹ ለነዳጅ፣ ትራንስፖርትና ለመሳሰሉት ክፍያ ወዲያውኑ እንዲፈጸምላቸው ቢፈልጉም ቶሎ ስለማይሰጣቸው ይቸገራሉ ያሉት አቶ ገብረማርያም፣ ይህን ችግር ለመፍታት ቢሠራም ሙሉ በሙሉ አልተፈታላቸውም ይላሉ፡፡ በቀጣይም ከሚመለከተው አካል ጋር እንዲወያዩ በማድረግ ችግሩ የሚፈታበትን ሁኔታ ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በድንጋይ ከሰል አምራቾችና በኢቲ ማይንግ መካከል የገበያ ትስስር መፈጠሩን ጠቅሰው፣ በዳውሮ አካባቢ የድንጋይ ከሰል የሚያመርቱት አራት አምራቾች ለኢቲ ማይኒንግ እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል፡፡ ኮንታ ዞን ላይ ያሉት ደግሞ ወደ ሌላ ቦታ ወሰደው እንደሚሸጡ ተናግረው፣ እነርሱንም ከፋብሪካው ጋር ለማስተሳሰር እየተሠራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ በክልሉ እየተመረተ ያለው የድንጋይ ከሰል የጥራት ደረጃ ይለያያል። የድንጋይ ከሰሉ የካሎሪ መጠን 6ሺ፣ 2ሺ እና ከዚያ በታች ሊሆን ይችላል፡፡ ኢቲ ማይኒንግ ፋብሪካ እነዚህን የተለያየ የካሎሪ መጠን ያላቸውን የድንጋይ ከሰሎች ወስዶ አጥቦ 5ሺ800 ያህል ካሎሪ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል በማምረት ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያቀርባል፡፡

ከማዕድን ዘርፉ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኛው በወርቅ ላይ እየተፈጸመ ያለው ሕገ ወጥነት መስፋፋት አንዱ ነው የሚሉት አቶ ገብረማርያም፣ ለዚህም ወርቅ የሚታጠብበት ሳይት ድረስ በመሄድ የሚደረገውን የድጋፍና ክትትል አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በወርቅ ማምረት ላይ የተሰማሩ ልዩ አነስተኛና ባሕላዊ የወርቅ አምራቾች ወጪያቸውን በማስላት ከዚያ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ወርቅ ወደ ባንክ እንዲያመጡ ለማድረግ ከአምራቾች ጋር መግባባት ላይ ለመድረስ መሠራት እንዳለበትም ይጠቁማሉ፡፡ ዘርፉን በሚገባ ለመከታተልና ለመደገፍ ከሰው ኃይል ጋር ተያይዞ ውስንነት እንዳለም ጠቁመው፣ ሌላው ተግዳሮት የበጀት እጥረት መሆኑንም አስታውቀዋል። በችግሮች ውስጥ በመሆን በተቻለ መጠን ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡

የድንጋይ ከሰል አምራቾች በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ እንዳልሆነም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረው፣ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የሚያስችሉ የድጋፍና ቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ ፍቃድ ወስደው ወደ ሥራ ላልገቡት የአንድ ወር ጊዜ ያህል ማስጠንቀቂያ በመስጠት በዚህ ጊዜ ውስጥ ሥራ ያልጀመሩት ፍቃድ ተሰርዞ መሬቱ ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ፍቃድ የወሰዱትንም ፍቃድ የማጥራት ሥራ በመሥራት ምርታማነት እንዲጨምር እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ አዳዲስ ፍቃድ የወሰዱት ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግም አመላክተዋል፡፡ ሕገወ ጦችንም ለመከላከልና ለመቆጣጠርም ከቀበሌ አመራር አንስቶ ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ መሥራት የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You