– 435 ቤቶች ያሏቸው ስምንት ሕንፃዎች ለመገንባት1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተመድቧል
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ28 ዓመታት በኋላ አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምንት ከአራት ተቋራጮች ጋር ተፈራረመ፡፡
ያረጁ የቁጠባ ቤቶችንና ቪላዎችን በማፍረስ እስከ ሃያ ወለል የሚደርሱ ሕንፃዎችን ለመገንባት ማቀዱንም አመልክቷል፡፡ በኮርፖሬሽኑ የቤት ልማት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ ዘካሪያስ ሰብስቤ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ቤቶቹ የሚገነቡት በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች መሐል አካቢዎች ሲሆን በተለይም በአዲስ አበባ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚገነቡት ቤቶች በአምስት ሳይቶች ተለይተዋል፡፡
ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ 435 ቤቶች ያሏቸው ስምንት ሕንፃዎች በ1 ነጥብ 9 ሄክታር መሬት ላይ ይገነባሉ፡፡ ለዚህም 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 60 በመቶ የሚሆነው በተቋሙ ቀሪው ደግሞ በባንክ ብድር ይሸፈናል፡፡ «የተያዘው በጀት ዓመት ሳይጠናቀቅ ሁለተኛውን ምዕራፍ ግንባታ ለመጀመርና በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አቅደናል» ያሉት አቶ ዘካሪያስ ይህም ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ውጪ ባሉት ዘጠኙም ክፍለ ከተሞች ላይ 11 ሳይቶች መለየታቸውንና 3 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡
ለዚህም 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ ያሉትን ያረጁ የቁጠባ ቤቶችንና ቪላ ቤቶችን በማፍረስ በምትካቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ለመገንባት ማቀዱን አመልክተዋል፡፡ «በአሁኑ ወቅት 28 ሄክታር ላይ ያረፉት እነዚሁ ቤቶችን በአዳዲስ ሕንፃዎች ለመተካት የሚያስችል ጥናት ለማጥናት ዝግጅት ያጠናቀቅን ሲሆን ጥናቱን በዋናነት ከኔዘርላንድስ መንግሥት ጋር በመተባበር እየሠራን ነው» ብለዋል፡፡ ጥናቱ ከሦስት እስከ አራት ዓመታት ይፈጃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት አቶ ዘካሪያስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማማከር ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ዘካሪያስ ማብራሪያ በመልሶ ማልማት ከሚፈርሱት ቤቶች ውስጥ 22 አካባቢ እንዲሁም ገርጂ በተለምዶ ነጫጮች ቤት የሚባሉ ቤቶች ናቸው፡፡ ቤቶቹን መልሶ መገንባት ያስፈለገውም ከአካባቢውና ወቅቱ ከሚፈልገው ዘመናዊ የከተማ ማስተር ፕላን ጋር አጣጥሞ ለመሄድ ሲባል ነው፡፡ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ 43 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ አንጋፋ ተቋም ቢሆንም የዕድሜውን ያህል ያላደገና ለዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደነበሩበት አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ውዝፍ ሥራዎች መስመር ለማስያዝ በ2011 በጀት ዓመት የሪፎርም ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በተለየ ሁኔታ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች መካከል አንደኛው የቤቶች ግንባታ ሲሆን ላለፉት 28 ዓመታት ከቤት ልማት ርቆ የነበረውን ተቋም ዳግም ወደ ልማት ለመመለስ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ ዣንጥራር አባይ በበኩ ላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ ሌላ የገቢ ምንጭ የሌለውና ከመንግሥት ባጀት የማይ መደብለት ነው። በቅርቡም ፍትሐዊ የቤት ኪራይ ተመን ማሻሸያ ማድረጉ ገቢውን ለማሳደግና በሁለት እግሩ እንዲቆም የሚረዳው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
«በአንድ በኩል የቤት ጥያቄውን ለመመለስ ቤት መገንባት፤ በሌላ በኩል የቤት ግንባታ ለማከናወን የፋይናስ ችግር ፈታኝ ሆኖበታል። በመሆኑም ሁለቱንም እያጣጣሙ መሄድ ይጠይቃል» ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ መረጃ እንደሚያመለክተው ተቋሙ በአሁኑ ወቅት 18ሺ 153 ቤቶችን የሚያስተዳደር ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተከናወነው የመልሶ ማልማት ሥራ ብቻ 1 ሺ 400 ቤቶቹን አጥቷል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 7/2011
በማህሌት አብዱል