አንድ አገር እንደ አገር እንዲቀጥል ከሚያስፈልጉ ነገሮች መካከል ሰላም ግንባር ቀደሙን ሚና ይጫወታል። ሰላም ካለ ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ መብላት ተምሮ መለወጥ እና ያሰቡትን ሁሉ ማሳካት ብዙ ከባድ አይሆንም። ነገር ግን ሰላም በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከተናጋ ይህ ሁሉ ነገር እንዳልነበር ከመሆኑም በላይ አገርም ህልውናዋን ጠብቃ ልትቀጥል የምትችልበት ሁኔታ በጣም ጠባብ ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያም እየታየና እየተሰማ ያለው ነገር እጅግ አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ የኖረ የቀደመ የመተሳሰብ፣ አብሮ የመኖርና የመደማመጥ ባህላችንን ያጠፋ፤ እንደ አገርና ህዝብ ወደኋላ እየጎተተን ያለ ስለመሆኑም እየታየ ነው። ከዚህ ችግር እንድንወጣ “በአንድ ልብ አሳቢ ባንድ ቃል ተናጋሪ” ልንሆን እንደሚገባም ብዙዎች እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
እኛም በርካታ አመታትን በመምህርነት ካሳለፉ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የአገር ፍቅር ስሜት እንዲኖራቸው ትውልድን የሚያንጹ ስራዎችን በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ከሚሰሩና በፓን አፍሪካኒዝም ሙቭመንት ላይ አገራቸውን ወክለው የተለያዩ ተግባራትን ከሚፈጽሙት፤ መምህር አካሉ አብርሃም ጋር ቆይታን አድርገናል። መልካም ቆይታ፡፡
አዲስ ዘመን፦ በሰላም ሚኒስቴር ውስጥ ሰርተዋል፤ በዛ ላይ ሚናዎት ምን ነበር? አሁን ደግሞ እንደ አገር የምክክር ኮሚሽን ተብሎ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነውና ይህንን እንዴት ይገልጹታል?
መምህር አካሉ፦ አገር አቀፍ የምክክር መድረኩ መከናወን የጀመረው ዛሬ ሳይሆን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ነው። በወቅቱ የሰላም ሚኒስትር የነበሩት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ከሁሉም ክልሎች ከመጡ አካላት ጋር ትልልቅ ውይይቶች ሲደረጉ ነበር። በዚህ ላይም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኛ እንደመሆኔ አጀንዳ ከመቅረጽ ጀምሮ የተለያዩ ሰነዶችንም በማዘጋጀት ተሳትፌያለሁ። በነበሩ ውይይቶችም የህዝቡን አንድነት መተሳሰብ አብሮ ለመሆን ያለውን ፍላጎት ታዝቤያለሁ። በመሆኑም ወሳኝ የምክክር ጊዜያት አልፈዋል ማለት ይቻላል።
አሁን ደግሞ እየታሰበ ያለው አገራዊ የምክክር መድረክ እንደ አገር ብዙ የታሰበበት፣ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ጸድቆ ብዙ ታምኖበት የቀረበ፣ ብዙ ተስፋም የተጣለበት ነው። ከዓመት በፊትም በሰላም ሚኒስቴር በኩል ሲሞከር የነበረው እጅግ ጥሩ ነበር። ጥሩ ከመሆኑም በላይ አሁን ለመጣው አገር አቀፍ የምክክር ኮሚሽን መደላደልን ፈጥሯል። በመሆኑም ሰላም ሚኒስቴርም ስራው ሌላ አካል ዋናው ለዚህች አገር የሚያስፈልጋት አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ነው።
በመሆኑም በዚህ ኮሚሽንም አማካይነት የሚያጨቃጭቁን እንደ አገርና ህዝብ አንድ ሆነን እንዳንቀጥል እንቅፋት የሆኑን ነገሮች ላይ መመካከሩ በጣም ጠቀሜታ አለው። ለምሳሌ የጸባችን መነሻ እየሆኑ ካስቸገሩ ነገሮች መካከል አንዱ ሰንደቅ አላማ ነው፤ ይህንን ጉዳይ ህዝቡ ምን ይላል? ውስጡ ምንድን ነው ያለው? የሚለውን መነጋገር እስከ ወረዳ ድረስ ወርዶ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረግና ከዛ የሚፈልገውን ማወቅ፣ በዛ መሰረትም ወደ መፍትሔና ምላሽ መምጣት ነው የሚሻለው።
ሌላው የማያግባባን አንቀጽ 39ም ቢሆን መወያየት ይገባል፡፡ ክልሎችን ማዋቀር ሌላው ራስ ምታታችን ነው፡፡ አሁን 11 ክልሎች አሉን፡፡ ከዚህ በላይ እንጨምር ብንል የምናገኘው ጥቅምና የምናጣው ነገር ምንድን ነው? ለአገርስ የቱ ይበጃል? የሚለውንም ማስቀመጥ ይገባል። በመሆኑም ህዝብ ያመነበትንና የተቀበለውን ወደተግባር እየቀየሩ ያላመነበትን ደግሞ ወደጎን እየተው ወደሰላማዊ አደረጃጀታችን መግባት ያስፈልጋል።
እንግዲህ እንደ አገር ወደዚህ አገራዊ የምክክር ሂደት በቅን ልቦናችን ገብተናል፡፡ ገና ከመገባቱም በርካታ ፈተናዎች እየመጡ ነው። ነገር ግን ለችግሮቹ ሳይንበረከኩ አዋጩ ነገር ብሔራዊ ምክክር መሆኑን በመረዳት ተመካክሮ ችግርን መፍታት ትልቅነት ነው። በነገራችን ላይ አንድ ችግር በሰፈር በጎረቤት ሲከሰት ትልልቅ የሚባሉ ሰዎች ቁጭ ብለው ተመካክረው መፍትሔ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ያልተጠቀምንበት ነገር ግን አብሮን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህላችን ነው። አሁን በገዳ ስርዓት ስንት ችግር ነው ዛፍ ስር ቁጭ ተብሎ በሚደረግ ንግግርና ምክክር እልባት የሚያገኘው፤ እኛ ስለማናይ ስለማናውቅ ነው እንጂ በየቀኑ ምን ያህል ለሆኑ ጉዳዮች ነው እልባት የሚሰጠው፤ ሰዎች ነፍስ ተጠፋፍተው እንኳን በዚህ መንገድ ችግራቸው ላይ ውይይት በማድረግ ታርቀው እየኖሩ ነው።
በሲዳማም በተመሳሳይ “አፊኔ” የሚባል የእርቅ (የውይይት) መንገድ አለ፤ ሰዎች ነፍስ ተጠፋፍተው እንኳን አስከሬን ቁጭ አድርገው ገዳዩ ላይ በመወያያት እዛው ውሳኔ ይሰጣሉ፤ ያስታርቃሉ፤ የተበዳይ ቤተሰቦች የሚካሱበትን ሁኔታ እዛው ያመቻቻሉ። በመሆኑም በየባህላችንና ሀይማኖታችን የተሰጠም የውይይት የእርቅ ሂደት አለ፤ ብዙ ችግሮችን የሚፈታ፣ ነገር ግን ያልተጠቀምንበት ሀብት ነው። ይህንን የተሰጠንን ነገር ላለመጠቀማችን ትልቁ ምክንያት ደግሞ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ነን ባዮች የሚፈጥሩብን ጫና ነው። በእነሱ ምክንያትም አሁን ላለንበት ትርምስ ተዳርገናል።
እነዚህን ፖለቲከኞችም ሆነ አክቲቪስቶችን ወደጎን ትተን የራሳችንን መንገድ ከተከተልንና እሴቶቻችንን ከተጠቀምን ምክክሩ ትልቅ አቅም ይፈጥርልናል ብዬ አስባለሁ። ተንኮለኛ መበጥበጥ አመሉ የሆነ አካል ከምክክሩም በኋላ ቢሆን ላይጠፋ ይችላል፤ ነገር ግን በእነሱ ሃሳብ የሚነዳ አካል ባይኖር በተለይም ወጣቱ ማስተዋልን ቢላበስ ውጤቱ ያማረ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ፦ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ በርካታ ሀይማኖቶች የሚመለኩባት አገር ናት፤ የምክክር ኮሚሽኑ ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አገር ካጋጠማት የህልውና አደጋ ወደ አንድነት እንድትመጣ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
መምህር አካሉ፦ አዎ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መናኸርያ የሆነች አገር ናት፤ በርካታ ሀይማኖቶችም ይመለኩባታል፤ ይህንን እንደ እድልና መልካም አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ የምክክር ኮሚሽኑም ቢሆን ይህንን አጋጣሚ ከመጠቀም ባሻገር የሰውን የልብ ትርታ ረጋ ብሎ ማድመጥ ይጠበቅበታል። ሁሉም ክልል የሚያነሳው የራሱ የሆነ የተከማቸ ችግር አለበት።
ይህንን ሰከን ብሎ ሃሳቡን አምጥቶ አወያይቶ መፍታት ይጠይቃል። ይህ ሲደረግ እንግዲህ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ላይሆን ይችላል፤ ፈተናዎች ይኖራሉ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ይኖራሉ፤ በተለይም አውሮፓውያን የእኛ ሰላም መሆን ለእነሱ ህመም በመሆኑ እየከፈሉ በራሳችን ዜጋ ሊያስረብሹን ይችላሉ፤ በመሆኑም ረገብ ብሎ በቅን ልቡና አስተሳሰብ የሚመጣውን ሀሳብ ለውይይት ማቅረብና ፍርዱን ወይም ይበጀኛል የሚለውን ህዝቡ እንዲያስቀምጥ ማድረግ ያስፈልጋል።
በመሆኑም ትልቅ አቅም ህዝቡ ጋር በመሆኑ ህዝቡ ይበጀኛል የሚለውን እንዲያስቀምጥ ማድረግ ይገባል። ይህ ደግሞ አንድነታችንን ያመጣል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ ሁሌም ኢትዮጵያዊነትን ያቀነቅናሉ፤ እንዲሁም ፓን አፍሪካኒዝምን ያቀነቅናሉ፤ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስትም ፓን አፍሪካኒዝምን መልሶ ለማምጣት ከአፍሪካ መሪዎች ጋር እያደረገ ያለውን ሂደት እንዴት ይገልጹታል?
መምህር አካሉ፦ ፓን አፍሪካኒዝም እንደ ሃሳብ ትልቅ ነው። ትልቁ አላማውም አፍሪካን አንድ ማድረግ ነው። አፍሪካን ከአህጉርነት ወደ አንድ አገር ወስዶ ትልቅ አህጉር የማድረግ መንፈስ ነው። አሁን እንደ አህጉር የምንግባባው በእንግሊዘኛ ነው። ነገር ግን “ስዋሂሊ” የሚባለው ቋንቋ የራሳችን አፍሪካውያን ነው። አሁን ደግሞ በአፍሪካ ህብረት የራሳችን መሆኑ ተረጋግጧል፤ ከዚህ አንጻርም አብዛኛው አፍሪካውያን የሚግባቡበት በመሆኑም እርሱን ማሳደግና እርስ በእርሳችን እንድንግባባበት ማድረግ፤ አፍሪካን እያቆራረጠ የሚያያይዝ የባቡር መንገድ እንዲኖር ማስቻል፤ እንዲሁም የራሳችን አየር መንገድ፣ የደህንነት ቢሮና ሌሎቹም እንዲኖሩ ዛሬ ሳይሆን ቀደም ብሎ የታሰበበት ጉዳይ ነበር። አሁንም ማስቀጠል ይገባል።
በሌላ በኩልም እኛ እንደ አፍሪካ በፓን አፍሪካ ተሰባስበን እነሱ እንደሚሉት ዲቨሎፕመንት ባንክ ብለው እንደሚያቋቁሙት እኛም “ዲቨሎፕመንት ባንክ ኦፍ አፍሪካ” በማለት ብናቋቁም የሚቸግረንን ነገር ከዛ እየተበደርን መልሰን ለዛው እየከፈልን ብንሰራ እድገቱ በጣም ከፍ ይላል። ይህ ግን ምዕራባውያኑን ስለማያስደስታቸው ይህንን ያሉ የአፍሪካ መሪዎች እጣ ፈንታቸው መጥፋት ሆኗል፤ ግን ደግሞ እነሱ ይህንን ያደርጋሉ ብሎ ከጉዟችን መገታት ሳይሆን ጠንክረን ወደፊት መሄዱ ነው ብዙ ርቀት የሚያራምደን።
የአንድነትና አብሮ የመቆም ሀሳብ ያቀነቀኑ ከ20 በላይ የአፍሪካ መሪዎች ተገድለዋል፤ የመፈንቅለ መንግስትም እንዲካሄድባቸው ሆኗል፤ አሁን ደግሞ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉትም መሪዎች ላይ አስፈሪ ነገሮች ይስተዋላሉ፤ እንቅስቃሴያችን ሁሉ ለአውሮፓውያኑ ስጋት ነው። ለምሳሌ አሁን በቅርቡ ኢትዮጵያ “በቃ “ ብላ ተነሳች ይህ አነሳሷ ደግሞ ሁሉን ያንቀሳቀሰ ሆነ። በዚህ ደግሞ አሜሪካንን ጨምሮ ብዙ የአውሮፓ አገራት ደስተኛ አልነበሩም፤ እንደውም ስጋት ውስጥ ገብተው ነበር።
ስለዚህ ፓን አፍሪካኒዝም አሁን ብቻ ሳይሆን በእነ አጼ ሚኒሊክና በሌሎቹም ነገስታት ዘመን የተጀመረ ነው። ነጮቹን አይሆንም ባልናቸው ቁጥር የሚሰማቸው ይኸው ፓን አፍሪካኒዝም በመሆኑ አሁንም ወደፊትም አንድነታችንን አይፈልጉትም፤ እኛ ግን መጠበቅ ትልቁ ስራችን ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን ፦ አዎ አሁን ያነሱት የበቃ ንቅናቄ አሜሪካ በተለይም ከሕወሓት ጋር የገባንበትን ጦርነት ምክንያት አድርጋ ጫናዎችን ስታበዛብን ሃሳብ ያስቀየርንበት ዘመቻ ነው፤ ይሁን እንጂ አሜሪካን አሁንም በ HR6600 ሌላ አጀንዳ ከፍታብናለች፤ በዚህ ላይ የእርስዎ ሃሳብ ምንድን ነው?
መምህር አካሉ፦ ይህ እንግዲህ ማዕቀብ መጣላቸው የተለመደ ነው።እነሱ ማዕቀብ ሲጥሉብንም ሆነ ሊጥሉብን ሲያስቡ ራሳችንን ማዘጋጀት ያለብን ደግሞ እኛ ነን። በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ራሳችንን በተለያዩ ነገሮች ማነጽ መቻል አለብን። ለምሳሌ HR6600 ያመጡበት ዋናው ምከንያት እኛ አንሸነፍ ስላልናቸው መምቻ መንገድ አድርገው ነው። የእኛ እምቢ ማለት ለሌሎቹ ጥቁር ህዝቦች የሚያስተምረውን ነገር ስለፈሩት ነው። በፈረንሳይ በአሜሪካን ያለው ጥቁር ሁሉ እንዴ ማለት ጀመረ፤ ይህ ደግም ለእነሱ ትልቅ አደጋ ነው የሚፈጥረው። በመሆኑም እንደዚህ አይነት ነገሮችን እየፈጠሩ እኛ ላይ ጫና ማሳደር ግዴታቸው ነው፤ አፍሪካን በመኮርኮም ጥቁሮችን የማሳነሻ መንገድ ነው።
አንድ ኢትዮጵያ ናት ከዛሬ 126 ዓመት በፊት ጀምሮ ጣሊያንን በማሸነፍ እነሱን አልቀበልም ማለት የጀመረችው። ይህ ደግሞ ለእነሱ ትልቅ ወድቀት ሆኖ ዘላለም ሲያሸብራቸው ይኖራል። በዚህና ሌሎች ምክንያቶች እነሱም የእኛን ቀና ማለት አይፈልጉም እኛ ግን በተቻለ መጠን ራሳችንን በኢኮኖሚ አጠንክረን እምቢ ባይነታችንን አስጠብቀን መዝለቅ አለብን። HR6600 ሆነ ሌሎች የሚያደርጓቸው ነገሮች በሙሉ በአገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ የሚኖረው ጫና ከፍ ያለ በመሆኑም እነሱ በምክንያት እንደሚደጋገፉ ሁሉ እኛም ራሳችንን አጠንክረን የሚመጣውን ለመቀበል ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል።
በነገራችን ላይ አውሮፓውያን የሚኖሩት በእኛ ሀብት ነው፤ ከአፍሪካ በተጋዘ የተፈጥሮ ሀብት። ዛሬ ኑውክሌር እያሉ አለምን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ የሚጠቀሙበት ሁሉ ከአፍሪካ የሄደ ሀብት የተሰራ ነው። እነሱ ግን በጣም ብልጥና ነጋአቸው የሚያስፈራቸው በመሆኑ ወርቅ እንዲሁም ሌሎች የከበሩ ማዕድናትን በሙሉ ሰብስበው ለብዙ ዓመት እንዲበቃቸው አድርገው አከማችተዋል። በመሆኑ እነዚህን ነገሮቻቸው እንዳይጎሉባቸው በማለት ሃያሏን አገር አሜሪካንን ይደግፋሉ። አሜሪካንም ከእነሱ ጋር የምትጣመረው የጥቁርን ህዝብ በሀይሏ ለማሸማቀቅ ነው። በመሆኑም ይህንን ዝናዋን ላለማጣትም ትጥራለች።
አዲስ ዘመን፦አሁን ላይ እንደ አገር የገባንበት ችግር አለ በዚህ የተነሳ ደግሞ ብዙዎች ለጉዳትና ለችግር ተጋልጠዋል፤ እንደው ከዚህ ችግር ልንወጣ የምንችለው በምን መንገድ ነው ይላሉ?
መምህር አካሉ፦ አዎ ከችግራችን መውጪያ ትልቁ መንገዳችን በተቻለ መጠን ሰከን ብሎ ተረጋግቶ ነገሮችን በጥሞና ማየትና መደማመጥ ይመስለኛል። በተለይም ልንጀምር ያሰብነው አገራዊ የምክክር መድረክ ብዙ ነገሮችን ሊፈታ ይችላል ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን በየአካባቢው ያለው አስተሳሰብ ቅን መሆን ቢችል ፌደራል መንግስቱ ጋርም ያለው ተነሳሽነት ጥሩ ሆኖ ቢቀጥል እንደ አገር ከመፈራረስ ድነን አብሮነታችን ይቀጥላል፤ አገራችንም ወደፊት ትራመዳለች የሚል እምነት አለኝ።
እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ የመኖር የቆየ ባህል ያለን ልዩ የሆንን ህዝቦች ነን፤ አሁን የተፈጠረብንም ጦርነት በፖለቲከኞች ያለመግባባት ምክንያት የተፈጠረ እንጂ ህዝብ ተጣልቶ አይደለም፤ በመሆኑም አሁንም በሚሰሩ ስራዎች በሚፈጠሩ ንግግሮችና ውይይቶች እነዚህ ነገሮች ተቀርፈው ህዝብም እንደ ህዝብ አብሮ የሚኖርበት አገርን እንደቀድሞ አንድ የምትሆንበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ግምት አለኝ።
በተለይም ከዚህ በኋላ በአሸባሪው ሕወሓትም ሆነ በመንግስት በኩል የተጀመረውን የውይይት መድረክ ማጠናከር እንጂ እንደገና ጦር ሰብቆ ለውጊያ መዘጋጀት ዜጎቻችንን ያሳጣን ይሆናል እንጂ የሚጠቅመው ነገር የለም፤ በእስከ አሁኑም ምንም ያተረፍነው ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፦ የጀመርነው የምክክር መድረክ ፍሬያማ እንዲሆን ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
መምህር አካሉ፦ አዎ ይህ ውይይት ለእኛ ወሳኝ መሆኑን መረዳት ሊሰመርበት የሚገባ ነው። ይህንን ከተረዳን በኋላ ደግሞ ለውይይቱ ቅን መሆን ያስፈልጋል። ህዝብ ቅን ሆኖ የሚሆነውን ነገር በትኩረት መከታተል አለበት። ወጣቶችም ለራሳቸው ጥቅም ባደሩ፤ ነገ ሀሳባቸው ሲሞላላቸው ዞር ብለው በማያዯቸው ስግብግቦች ሃሳብ መነዳት የለባቸውም። ዞር ብሎ በማየት ምን ላገኝ ምን ላጣ እችላለሁ የሚለውን ማስተዋል ይገባል። የሀይማኖት አባቶች ልጆቻቸውን በመምከር በማነጽ በኩል ትልቅ ሀላፊነት አለባቸው፤ መንግስትም ቅን አስተሳሰቡን ይዞ መሬት ላይ ያለውን ነገር ባገናዘበ መልኩ ነገሮችን ማየትና መረዳት ይኖርበታል። መድረኩን ፈጠርኩ ለማለት ብቻ ሳይሆን የሚሳካበትንም ምቹ ሁኔታ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። የዚህ መድረክ ወሳኙ አካል ህዝብ ነው፤ ህዝብ ደግሞ በማይሆን ነገር መገፋት የለበትም።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
መምህር አካሉ፦ እኔም አመሰግናለሁ
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም