አይንና ፈገግታዋ ፍቅር ይተፋል። ደስ ትለኛለች። ቁንጅናዋ ብዙ ሰው የሚስማማበት አይነት ነው። እወዳታለሁ። የምንተዋወቀው ተማሪ እያለን ነው። ቆንጆ እንደሆነች እየተነገራት ያደገች ልጅ ናት። በቁንጅናዋም ሆነ በተፈላጊነቷ በምንም ሁኔታ ጥርጣሬ ገብቷት አያውቅም። ተቀማጥላ ያደገች ናት። አለባበሷ ቀለል ያለ ነው። ብዙዎች ይወዷታል። ሳቂታ መሆኗ ይሆን ቁንጅናዋ ከእርሷ ጋር ለመሆን የሚያስገድድ መግንጢሳዊ ሃይል አላብሷታል።
እንለያያለን ብለን አስበን አናውቅም። ነፍሳችን ይናበባል። ሳናወራ እንግባባለን። አብረን ስንሆን ሰአቱ ይፈጥንብኛል። ላገኘሁት ሰው ሁሉ ስለእርሷ አወራለሁ። ቶሎ ቶሎ ትናፍቀኛለች። ከተቀጣጠርን፣ አጭር ቀሚስ የለበሰች ጉብል ከሩቅ ስመለከት እሷ ትመስለኛለች። ከሰከንዱ እኩል ሰዓቴ ላይ እሽከረከራለሁ። አስሬ ቀና ደፋ እላለሁ። ካረፈደችም ገና ነው ብዬ ራሴን አፅናናለሁ። መቆየቷ አያበሳጨኝም። ረጋ ብዬ እንቀዠቀዣለሁ።
እለቱ ማክሰኞ ነው። መሃል ፒያሳ ላይ አንድ የምንወደው ካፌ አለ። እንደተቀመጥን አስታጋጇ መጥታ ‹‹ምን ልታዘዝ› አለች። እኔ ነጣ ያለ ማክያቶ አልኩ። እሷ ቡና አለች። ከሶስት ቀናት በኋላ ስለተገናኘን በስስት እየተመለከትኳት የባጥ የቆጡን እቀበጣጥርላታለሁ። እርሷም እንደናፈቀች ታስታውቃለች።
እጄን በእጇ ይዛ ዝም ብላ ታዳምጠኛለች። መብራት ባለመኖሩ ትኩስ ነገር ማግኘት አልቻልንም። ትእዛዝ ቀየርን። ለሁለታችንም ለስላሳ መጠጥ አዘዘች። ምርጫዬን ስለምታውቅ አልተቃወምኳትም። ጨዋታችንን ቀጠልን። በጨዋታችን መሃል መብራት መጣ። መብራቱን ተከትሎም ከተቀመጥንበት በላይ ከተሰቀለ አንድ ስፒከር ሙዚቃ መሰማት ጀመረ። ግርግር አትወድም። የምንሰማው ሙዚቃ ደግሞ ግርግር ነው። ተረበሸች። ተጨነቀች። ሃሳቧ ተበታተነ። የታዘዘውን መጠጥ አልጨረስነውም። እኔ እንዳውም አልተጎነጨሁትም። ‹‹እባክህ እንውጣ›› አለችኝ። ጥያቄዋ የተማፅኖ ነው። አልተከራከርኩም። በፍጥነት ሂሳብ አልኩኝ። የቸርቸር ጎዳናን ይዘን ቁልቁል ወደ ብሄራዊ አቀናን። የማናወራው የለም።
በጨዋታችን መሃል ቅድም ለምን ተረበሽ? ስል ጠየኳት።
‹‹ሙዚቃው ሙዚቃው ነዋ›› አለች።
ሙዚቃው ምን አልኳት።
‹‹ሙዚቃው በጣም በጣም ይረብሻል፣ ያበሳጫል፣ ጩሀት ብቻ እኮ ነው ፣አልሰማኸውም›› አለችኝ።
እውነቷን ነው ሙዚቃው ረብሻ ነበር። መልእክቱ ምን እንደሆነ እንኳን አይታወቅም። የሚለው አይሰማም። ግጥምና ዜማው ተመሳሳይ ነው። ድግግሞሽ ይበዛዋል። የሙዚቃ ስሜቴን ስለተጋራችኝ ደስ እያለኝ ይበልጥ አቀፍኳት። የተወሰነ ጊዜ አሳልፈን ወደ ቤት ሸኘዋት። ስመለስ እሷን ብቻ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ማሰላሰል ጀምርኩ።
እኔም ሆንኩ በርካቶች እንደሚስማሙበት፣ በአንድ አገር ወይም አካባቢ ያለ ኅብረተሰብ ማንነቱን፣ ቋንቋውንና አኗኗሩን የሚገልጽባቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉ ቢታመንም የሙዚቃን ያህል ሰፊ ዕድልን የሚፈጥር አይገኝም።
የተለያዩ የሙዚቃ ጠቢባንም «የአንድን አገር የስልጣኔ ደረጃ ለማወቅ ብትሻ፤ ሙዚቃውን ማዳመጥ በቂ ነው» ይላሉ። በእርግጥም ሙዚቃ የሰው ልጆች አኗኗርን እንደ መስተዋት መመልከቻ ሆኖ ያገለግላል። ሰዎች በሙዚቃ በሥነ ቃላቸው አማካይነት ደስታና ሐዘናቸውን፣ ድጋፍና ነቀፌታቸውን፣ ማግኘት ማጣታቸውን፣ ውድቀት ስኬታቸውን ወዘተ ይገልፃሉ።
ሙዚቃ ጥበባዊ ክህሎትን የሚጠይቅ ዕውቀት ነው። ፈጠራ ነው። ከሁሉም በላይ አዕምሮአዊ ሳይንስ ነው፤ ድምፅ አሳክቶና አቀናብሮ የታቀደውን ሃሳብ በሰሚው መንፈስና ስሜት፣ እንዲሁም በሰሚው አእምሮ ላይ ትርጉም እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ይሕን ለማድረግ ደግሞ ዘዴና እውቀቱን ከችሎታ ጋር ጠንቅቆ መረዳትን ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ ህዝብም አንድነቱም ባህሉም ውበቱም ፍቅሩና ጠቡም ሲገለፅ የቆየው በሙዚቃ ጥበብ ነው። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥም ገናና ሥምና ክብር የነበራቸው አርቲስቶች ተፈጥረዋል። በተለይም የክብር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ፣ ማሕሙድ አህመድ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ቴድሮስ ታደሰ፤ ሂሩት በቀለ፣ ብዙነሽ በቀለና ሌሎችም በምትሃታዊ ችሎታቸው ለአመታት ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ጥም አርክተዋል።
እነዚህ ከዋክብት ለሥም፣ ለዝናና ለገንዘብ ሳይሆን ለሙያ ፍቅር ለጥበብ ልዕልና ብለው ጥሪት ሳይቋጥሩ ለቆሙለት ጥበብ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። ዛሬም ድረስ የዘለቁና ምርጥ የተባሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ሠርተዋል።
በተለይም ከሶስት አስርት አመታት አስቀድሞ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሁለንተናዊ መልክ እጅጉን የተለየ ነበር። ቀደም ሲል አንድ ሙዚቃ ተሠርቶ ህዝብ ዘንድ ከመቅረቡ አስቀድሞ ግጥሙ፤ ዜማውና ድምፃዊው መግባባታቸው በጥልቀት ይፈተሻል። ይገመገማል።
ዛሬስ? ዛሬማ ሙዚቃ በትንሽ ድካምና በብዙ ድፍረት ብዙ ገንዘብ የሚዛቅበት ሆናል። የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይነሳ የተኛ መስሏል። ቀስቅሱኝ ቢልም የሚቀሰቅሰው አጥቷል። ነቄና አራዶች የሚባሉ ጥቂቶች ቁጥጥር ስር ወድቋል። ዜማና ግጥሙ ተጣልተዋል። ዛሬ ላይ ገንዘብ ካለህ ወዳጄ በቃ ሌላ ቢቀር ዘፈን ታወጣለህ እየተባለ ነው። ጩኸትና አደንቋሪ ስልት የተላበሱና «ብመጣም ባልመጣም በሩን ዝጊው በጣም›› አይነት የሙዚቃ ስራዎች ተበራክተዋል።
አሁን ላይ አለም አቀፉ የሙዚቃው ኢንዱስትሪ እጅግ በጣም ፈጣን እድገት የሚታይበት፣ተለዋዋጭና ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የኢትዮጵያን ሙዚቃ በአንፃሩ እንዲህ ነው ብሎ ለመግለፅም በማያስደፍር ቁመና ላይ ተቀምጧል።
በየቀኑ የሚመረቱ ሙዚቃዎች በአብዛኛው ግጥማቸው ያልተገጣጠመ፣ በመሳሪያ ድምፅ ጩኸትና ኳኳታ ብቻ የተሸፋፈኑ ሆነዋል። በብዙ መልኩ ከንግድና ከትርፍ ጋር የተያያዙና ጠለቅ ብለው የማይመራመሩ ጊዜያዊ ጭፈራ የሚሹ አድማጭ ተመልካቾችን ስሜት የማይገዙ ሆነዋል።
ዛሬ ላይ ጥበባዊ ይዘታቸው እዚ ግባ የማይባሉ ግጥምና ዜማቸው ሙሉ በሙሉ ከምዕራባዊያን የተኮረጁ የብልጣብልጥ ሙዚቃዎች እየተደመጡ ናቸው። መደማመጥንና መጠባበቅ በማይስተዋልበት መልኩ ከዚህም ከዛም ተዳቅለው የሚቀርቡ ዘፈኖች ተወዳጅ እየሆኑ ሙዚቀኛም እያስባሉ ናቸው። አሁን ላይ የልብ ልብ ነጠላ ዜማ የጥበበኞቻችን ምርጫ ሆኗል። በነጠላ ዜማ አገር መዞር ተለምዷል።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሙዚቃ መገለጫው ምንድ ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ጠፍቷል። የሌሎች አገራት የሙዚቃ ስልትን በቀላሉ መረዳት ብንችልም የአገራችን የሙዚቃ ስልት ከየት እንደሚመደብ ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ብዙም መድከም ሳያስፈልግ ጥበቡ ከአገር አልፎ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ምን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ችሏል የሚለውን መመለስ በቂ ይመስለኛል። በየጊዜው የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተወዳዳሪ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል። ይሕ ዜና ከተነገረን ወር እንኳን ሳይደፍን ተሳተፍንበት በተባለው ውድድር መዝለቅ ሳንችል መቅረቱን እንሰማለን።
ሙዚቀኞቻችንም እያደር በጥራት እያነሱ መጥተዋል። ሁሉንም ሙዚቃዎቻችንም ማለታችን አይደለም። እርግጥ ነው ዛሬ ላይ ጥሩ ጥሩ ድምፃውያን፣ የዜማ ደራሲዎችና ገጣሚዎች፣ የሙዚቃ አቀናባሪዎች እንዳሉ አይካድም። ይሑንና አብዛኞቹ ሙዚቀኞቻችን በጥበብ ስራዎቻቸው አዲስ ነገር የመፍጠር አቅም አጥተዋል።
የቆዩ ስልቶችም በአዲስ መልክ ማቀናበርና የሰው ዘፈን እየዘፈኑ መክበር ልምድ አድርገውታል። ስለ ዜማ፣ ግጥምና ጭብጥ ሳይሆን በተለይ ክሊፑ ላይ ስንት ልብሶችን እንደሚለውጡ፤ የት ቦታ የሙዚቃውን ክሊፕ ቢሰሩ የአድማጭ ተመልካቹን ቀልብ መውሰድ እንደሚችሉ የሚጨነቁ መስለዋል።
ይሕ በመሆኑም አብዛኞቹ ለህዝብ ከተለቀቁ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአድማጭ ተመልካችን ቀልብ የሚስቡና ከተሰሙ በኋላም ከአእምሮ የማይጠፉ ሙዚቃዎችን መስራት ከብዷቸዋል። በእርግጥ የማህበረሰቡ የሙዚቃ ምርጫ በየጊዜ ይለዋወጣል። ዛሬ ተወዳጅ የሆነ ሙዚቃ ወዲያው ሊሰለች ይችላል። ይሑንና አንዳንዶቹ አምና የሰሩትን ዘንድሮ መድገም ተስኗቸው፣ በአጭር ጊዜ ሰማይ ተሰቅለው በዚሁ ፍጥነት በመሬት ሲወርዱም እየተመለከትን ነው።
በእርግጥ ሙዚቃ ተወዳጅ መሆንና አለመሆኑን የሚወስነው አድማጭ ተመልካች ሚዛን ነው። ማንኛውም አድማጭ ተመልካችም ሙዚቃ የሚመርጥበት የግል መስፈርት አለው። ሙዚቃው ስለሚያስጨፍርና አርቲስቱ ታዋቂ ስለሆነ ብቻ የሚያዳምጡ የሚመለከቱ መኖራቸው አይካድም።
አብዛኛው አድማጭ የተመልካችም የዚህ እሳቤ ሰለባ ይመስለኛል። አድማጭ ተመልካቹ የረባ መልዕክት ያነገቡ ጠንካራ ሙዚቃዎችን ፈልጎ አፈላልጎ በማጣቱ በተለይ በምስለ መስኮት በሚተላለፉ ሙዚቃዎች ከመሳብ ይልቅ ሙዚቃው በቀረበበት መንገድ በተዋናዮቹ ተክለ ቁመና እና ልብስ እንዲሁም የአኗኗር ከፍታ መደነቅ ጀምሯል።
ስለሙዚቃችን ስናወሣ፣ ክሊፖቻቸው መነሣታቸው አይቀሬ ነው፤ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉና ከባህር ማዶ እንደተወረሱ የሚያሳብቁ የሙዚቃ ክሊፖች፤ ቅጥ አምባሩ በጠፋ አለባበስና በከፊል እርቃንነትና በፀረ ባህል የታጀቡ ሆነዋል።
የሙዚቃ ክሊፖቹ በማህበረሰቡ በተለይ በታዳጊዎች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ግልፅ ተፅዕኖ ማሳደራቸው እየታየ ነው። ክሊፖቹ በአብዛኛው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የሚወክሉ አይደሉም። የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ኑሮና የአኗኗር ዘይቤ አያስመለክቱም።
እጅግ ቅንጡ በሆኑ ሆቴሎች፣ መኖሪያ ቤቶችና መዝናኛ ቦታዎች ያሸበረቁ ናቸው። ተዋናዮቹም ለራቁት የቀረበ አለባበስ ብቻ የተባሉ ይመስላል። ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ዝናን ለመጎናፀፍ ከመራወጥና ዝነኛ ለመሆን ከመዳዳት ይልቅ ድርጊታቸው ተመልካች ዘንድ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅእኖ ለአፍታም ቆም ብለው ማሰብ ተስኗቸዋል።
እዚህ ላይ ቆም ብለን ልናስብ የሚገባን “የቀድሞው ወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን ለምን እስከዛሬ አልቀጠለም? ችግሩስ ምንድን ነው፣ የማንስ ነው» የሚለው ነው። የኢትዮጵያ ሙዚቃ የቁልቁለት ጉዞ መንስኤው በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
ከሁሉ በላይ ለጥበብ ክብር ማጣት ደረቱን ነፍቶ የሚታገል መታጣቱ ነው። ኢንዱስትሪው ይመለከተናል የሚሉ ሁሉ አይተው እንዳላዩ፤ ሰምተው እንዳልሰሙ የመሆናቸው ድምር ውጤት ነው። በዘርፉ እጅግ ትልልቅ ስምና ዝና ያላቸው ሙዚቀኞች በሙዚቃ ምክንያት ያገኙትን ገንዘብ የሚያፈሱት በሌላ የንግድ መስመር ውስጥ መሆኑ በራሱ ትልቅ ችግር ነው።
ይሑንና ይህ ታሪክ መቀየር ያለበት ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ መሰራት ያለባቸው የቤት ስራዎች አሉ። ከሁሉ በላይ ሙዚቃ የማሳተሙ ዕድገት ከገበያ ይልቅ ወደ ጥራት ተኮርነት መለወጥ አለበት። ለዚህ ደግሞ ለገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለጥበብ መገዛት የግድ ይላል። ስምና ገንዝብ ለማግኘት ከሙያው ማዕቀፍ፣ ከስነ ምግባር መውጣት ስህተት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ገንዘብ ብቻ ይኑርህ ሌላ ቢቀር ዘፈን ታወጣለህ! የሚለው ቀልድም ጊዜው ሊያልፍበት የግድ ይላል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም