ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት በተለየ ሁኔታ ሉአላዊነቷን አክብራና አስከብራ የኖረች አገር ስለመሆኗ ተደጋግሞ ይነሳል። ይህ እውነት የማይዋጥላቻው ቢኖሩም እንኳን እውነታውን መቀየር ግን የህልም እንጀራ እንደሚሆን ደግሞ የገባቸው ይመስላል። ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን አስከብራ የኖረች አገር ናት ሲባል ግን እንዲሁ በቀላሉ የመጣ ወይም ደግሞ ነጮቹም ሆኑ ሌላው ፈቅዶና ወዶ የቸራት አይደለም። ይልቁንም ሰደድ እሳት ክንደ ብርቱ በሆኑት ልጆቿ መስዋዕትነት በብዙ ትግልና እልህ አስጨራሽ ሂደት የተገኘ የዘመናት አንጸባራቂ ድል እንጂ።
ዛሬም ሉአላዊነቷን በጦር መሳሪያም ባይሆን በተለያዩ መንገዶች ለመዳፈር የሚገዳደሯት ዳር ዳር የሚሏት አልጠፉም። ኸረ እንደውም ብዙ ናቸው። የራሳችን ጥቅም ተነካ እኛ እንደምንፈልገው አይነት ታዛዥ መንግስትና ህዝብ ማግኘት አልቻልንም፤ ይህ ደግሞ ተልዕኳችንን ለማስፈፀም አገርን ለመበዝበዝ አልተመቸንም ያሉ የውጭና የአገር ውስጥ ጠላቶች አብረው ሉአላዊነቷን ለመንጠቅ ላይ ታች ሲሉ እያስተዋልን ነው።
“ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል” እንደሚባለው፤ ሕወሓትና ጀሌዎቻቸው የለኮሱት እሳት እራሳቸውን ሲለበልባቸው የአድኑኝ ተማጽኗቸውን ያዋጡናል ወዳሏቸው ሁሉ ከመሰንዘር ተቆጥበው አያውቁም። አሁንም በህዝብ ስም መነገድ የማይታክተው ይህ ቡድን ዛሬም ህዝቤ ተጎዳ። ተጨፈጨፈ። ተራበ፣ ተጠማ ከማለቱም በላይ እንደ አሜሪካን ላሉ ፍርደ ገመድል አገራት አቤቱታ እያቀረበ በአገር ላይ ጫና እንዲፈጠር ሌት ተቀን እየጣረ ነው።
ዛሬም እንደ አሜሪካን ያሉ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራትም የአሸባሪው ሕወሓት የ”ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል” ይሉት ማንቋረር በማድመጥ፤ ነገሩን ከስሩ ሳይረዱ ወይም ደግሞ እያወቁም እንዳላወቁ በመምሰል እንዲሁም የራሳቸውን ጥቅም ብቻ አሻግሮ በማየት አገራችንን በማዕቀብ ሊያንኮታኩቱ ተነስተዋል። ይህ እንግዲህ ዘመን አመጣሽ ቅኝ ግዛት መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ለቅኝ ገዢዎቹ እምቢኝ አልገዛም ከማለት ሌላ እንዴት እድርጎ አሳፍሮ እቅዳቸውን ሁሉ አክሽፎ እንደሚልካቸው ያውቅበታል። በዚህ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ጥርጥር ውስጥ የሚገባ አይመስለኝም። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያላከበረና የአገርን ጥቅም የሚጎዳ ነው የተባለለት ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን የእጅ አዙር ቅኝ ተገዢ ለማድረግ የተወጠነ ውጥን መሆኑ ቁልጭ ብሎ እየታየ ነው። በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ)፣ ያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን (ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት ተደርጎበት አሁን ለምልዓተ ኮንግረሱ ቀርቦ በእጅ ብልጫ እስኪያጸድቁት እየተጠበቀ ነው። ከጸደቀ በኋላስ የሚለው ደግሞ የብዙዎቻችን ጥያቄ ይመስለኛል፤ አዎ ከጸደቀ በኋላማ በጉልበት ማንበርከክ ያቃታቸውን ህዝብ መድሃኒት። ምግብ፣ እርዳታ አሳጥተው እጅ እንዲሰጥ ለእነሱ አቤት ወዴት እንዲል ማድረግ የመጨረሻ ግቡ ነው፡፡
“ኤችአር 6600። ረቂቅ ሕግ በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ፣ በሕግ አካሄድና የንግግር ይዘቶችን መገደብ ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፤ በኢኮኖሚው መስክ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳታደርግና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ብድርና እርዳታ እንዳይሰጡ ጫና እንደሚያሳድርም ይነገራል፤ እንግዲህ ይታያችሁ ይህ ውጥን አገራችን ለማደግ የአፍሪካ አገራት ተምሳሌት ሆና ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ቁልቁል ለማስኬድ ገቢያችንን አሳድጎ ኑሯችንን ይለውጣል ብለን ሌት ተቀን እንደ አይናችን ብሌን የምንከባከበውን ግድባችን ስራ እንዲስተጓጎል በማድረግ ሁሌም የእነሱ ጥገኛ ሁሌም ስንዴ ተረጂ ሁሌም ስደተኛና የእነሱ ቤት ሰራተኛ ለማድረግ ያለመ ነው።
በሌላ በኩልም አገር የሚያስፈልጋትን መደበኛ የጦር መሳሪያዎች ከነመለዋወጫቸው እንዳትገዛ ክልከላ ማድረግና መሳሪያውን የሚሸጡ አገራትና ባለስልጣናት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግም ይህ ረቂቅ ህግ መፅደቁ ይጠቅማቸዋል።
ረቂቅ ሕጉ መነሻው በኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ቢሆንም ለእኔ ግን ከዛም በላይ ሆኖብኛል። በትክክል በጦርነቱ ወቅት አላግባብ የጠፋ ነገር ካለ የተጣሰ የሰብዓዊ መብት ከታየ አጥፊውን ለይቶ መምታት ወይም ተጠያቂ ማድረግ እየተቻለ እንደ አገርና ህዝብ ሁላችሁም በጅምላ ትወቀጣላችሁ አገራችሁን ወደከፋ ችግር ውስጥ እንከታታለን ብሎ መነሳት ሉአላዊነትን መጣስ መዳፈር ንቀት ካልሆነ በቀር ሌላ ትርጓሜ ሊኖረው አይችልም።
በእውነት በጦርነቱ ላይ የተጣሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ ከሆነ የረቂቅ ህጉ መነሻ ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከሌሎች አገራት የምታገኛቸው እርዳታዎችና ድጋፎች ማቆምስ በርካቶችን ወደከፋ ድህነት አዘቀት ማስገባት አይደለም። ይህስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊሆን አይችልም። ወይስ እኛ ስናደርገው ሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ እነሱ ሲያደርጉት ደግሞ ሌላ ትርጓሜ ይይዛል። አልገባኝም።
ረቂቅ ሕጉ “በኢትዮጵያ ሰላም፣ ዴሞክራሲና መረጋጋት ማምጣት” የሚል ስያሜ ያለው ቢሆንም በውስጡ የያዛቸው ሐሳቦች በተቃራኒው ኢትዮጵያን የሚጎዱ ናቸው። የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት ከተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው በኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደር ዓላማ ያለው ብቻ ነው። ሕጉ ከጸደቀ ለ10 ዓመት የሚያገለግል በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ቀጣዮቹን ጊዜያት ምን ሊያስመስላቸው እንደሚችሉ መገመትም ቀላል ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር ነው፤ በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በአገር ውስጥም በውጪም ያሉ ሊቃወሙት እምቢኝ አሻፈረኝ ሊሉ የሚገባቸው ጊዜና ቦታ ላይ ነን።
ረቂቅ ሕጉ የአሜሪካ መንግሥት ፍላጎት ሳይሆን የተወሰኑ በሕወሓት ፍቅር ያበዱ የኮንግረስ አባላት የወጠኑት በዚህ መልክም ኢትዮጵያን ለመጉዳት ያዘጋጁት እቅድ መሆኑን መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ረቂቅ ሕጉ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ተወያይቶበት ሙሉ ኮንግረሱ እንዲወያይበት መመራቱን እየተነገረ ነው። ረቂቅ ሕጉን ለማፅደቅ በአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት ባሉ የሕግ ሂደቶች ውስጥ እንዲወድቅ ወይም ደካማ እንዲሆን ማድረግ እንደሚቻል ደግሞ ግልጽ ነው፤ ግን ደግሞ የተቀናጀ ሥራ ያስፈልጋል።
የዳያስፖራ አባላት ረቂቅ ሕጉን በሚገባ ተረድተው በየአካባቢያቸው ላሉ ተመራጮች ማስረዳት፣ ደብዳቤ መጻፍና በስልክ ማነጋገር ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ አኳያ በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የዳያስፖራ ተቋማት ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ ጥረት ማድረግ ከምን ጊዜውም በላይ ለአገር የሚያውሉት ትልቅ ውለታ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል። ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዱ የአሜሪካ ባለስልጣናትን እ.አ.አ በ2022 የግማሽ ዓመት ምርጫ በድምጹ መቅጣት እንደሚገባውም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
በመንግሥት በኩል በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማስረዳት በተለይም የሰብዓዊ ድጋፍን አስመልክቶ ያሉ እውነታዎችን አጉልቶ በማውጣት ለአሜሪካ መንግሥት ማብራሪያ መስጠት ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆን ደግሞ ረቂቅ ሕጉ የመጽደቅ እድሉ አናሳ ይሆናል። በሌላ በኩልም መንግሥት ሰላምን ለማምጣት እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶችና እየገጠሙት ያሉ ችግሮችን አስመልክቶ ገለጻ ማድረግ ሊያስብበት በቶሎም ሊሰራው የሚገባ ትልቅ ጉዳይ ይመስለኛል።
የኢትዮ-አሜሪካውያን የእድገት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት፣ አሜሪካን ኢትዮጵያንስ ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ፣ የ“በቃ” ወይም #NoMore ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴና ሌሎች የሲቪክ ተቋማት የ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ዘመቻ ያደርጉ ዘንድ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቅ ነው። ይህንን ማድረግ ከላይ እንዳልኩትም ከዚህ ቀደም ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የአገራቸውን ሉአላዊነት እንዳስጠበቁት ውድ ልጆቿ ሁሉ የአገር ባለውለታ መሆን ነው፡፡ አበቃሁ፡፡
በዕምነት
አዲስ ዘመን መጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም