ኢትዮጵያ እና የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም። ሀገሪቱ በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ህብረት የሰላም ተልዕኮ በበርካታ ሀገራት ተሳትፋለች። ቀደም ባለው ጊዜ በኮሪያ እና በኮንጎ፤ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሩዋንዳ፤ በቡርንዲ፤ በላይቤሪያ፤ በሶማሊያ እና በሱዳን የሰላም አስከባሪ ኃይል አሰማርታለች። በዚህም ከሀገሪቱ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ እውቅናዎችን አግኝታለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋዊ ድረ ገጽ ላይ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሀገሪቱ በተለያዩ ሀገራት ሠራዊት በመሰማራት ላደረገችው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እውቅና ተሰጥቷታል። ኢትዮጵያ የሕይወት መስዋዕትነትን ጭምር በመክፈል በተለያዩ ሀገራት ውጤታማ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ማከናወኗን፤ ሰላም የሰፈነባት ዓለም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ከፍተኛ ሚና መጫወቷን በአድናቆት ይገልጻል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተሰማራበት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ፤ ወታደራዊ ዲስፕሊንና ሙያዊ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሚሰማራ እና በተሰማራበት ሁሉ ውጤት የሚያስመዘግብ ልበ ሙሉ ሠራዊት ነው።
ሠራዊቱ ጀግንነት መለያው፤ ድል ማድረግ አርማው ነው። በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሁሌም ደማቅ ገድል የሚፈጽም ነው። ይህንንም በተሰማራበት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር ሁሉ አረጋግጧል፤ በርካታ ዕውቅናዎችንም አግኝቷል።
ከዚህ በተጻራሪ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የሰላም ተልዕኮን ዕውቅና ለመንሳት የሚደረጉ ጥረቶች ጤነኝነት የጎደላቸው፤ ከተራ ስም ማጥፋት ተለይተው የሚታዩ አይደሉም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶማሊያ መንግሥት በኩል የሚሰማው ወቀሳ ከዚህ የተለየ አይደለም።
በሶማሊያ የተሰማራው የሰላም ተልዕኮ ጊዜ መጠናቀቅን ተከትሎ አዲስ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሀገሪቱ ለማሰማራት እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት፤ ከሶማሊያ መንግሥት በኩል የሚሰማው ያልተገባ የስም ማጥፋት ዘመቻ ኢትዮጵያን ያገለለ የሰላም አስከባሪ ለማሰማራት ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ጉዳዩ ዓለም አቀፍ የመነጋገሪያ ጉዳይ ከሆነም ውሎ አድሯል።
በሶማሊያ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ምን ያህል ውጤት ያመጣል? የጎረቤቶቻችን ሰላም ማስከበር ያልቻሉ፤ ከሰላም ማስከበር ይልቅ የራሳቸውን አጀንዳ ይዘው ወደ አካባቢው ለመምጣት የሚፈልጉ እንደ ግብጽ ያሉ ሀገራት አካባቢውን ለተጨማሪ ግጭት ከማድረግ ባለፈ የሚኖራቸው ጠቀሜታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውም የብዙዎች ጥያቄ እየሆነ ነው።
በተለይም ለ17 ዓመታት ያህል ሰላሟን ጠብቆ አንጻራዊ ሰላም እንድታገኝ አስተዋጽኦ ላበረከተ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ መንግሥት በኩል እየተሰጠ ያለው ትርጉም የለሽ ስም የማጥፋት ዘመቻ ብዙዎችን ያነጋገረ ሆኗል።
ሶማሊያ ከምሥረታዋ ጀምሮ፤ ግጭትና ሁከት አጥቷት የማያውቅ ሀገር ነች። ይህም ሁኔታ ለአሸባሪዎችና ለጽንፈኛ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም ባሻገር አካባቢው በግጭትና በአለመረጋጋት እንዲታወቅ አድርጎታል። በእነዚህ የመከራ ዓመታት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከሶማሊያ ሕዝብ ጎን ተለይቶ አያውቅም።
ኢትዮጵያ ‘AMISOM’ አሁን ደግሞ ‘ATMIS’ እየተባለ በሚጠራው የአፍረካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ለሶማሊያ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ተልዕኮም አብዛኛውን የሶማሊያ መሬት በመሸፈንና ከጥቃት በመከላከል የሶማሊያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፤ የሶማሊያ መንግሥትም ተረጋግቶ መንግሥታዊ ሥራዎችን እንዲሰራ ብዙ የሕይወት መስዋዕትነት ከፍላለች።
በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት፤ 60 በመቶ የሚሆነውን የሶማሊያ ክፍል የሚጠብቀውና ከአልሻባብ ጥቃት የሚከላከለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው።
የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ በዓለም ያልተረጋጋ ከሚባሉትና ለሽብርተኞች መፈልፈያነት ምቹ ሥፍራዎች ናቸው ተብለው ከሚታወቁት አካባቢዎች አንዱ ነው። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ለሽብርተኝነት ተጋላጭ ሆናለች። የተለያዩ የሽብር ጥቃቶችን በመከላከል እና በመቀልበስ ሂደትም ሰፊ ሥራዎችን ስትሰራ ቆይታለች። በዚህም አኩሪ ተግባሯ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከበሬታን ተጎናጽፋለች።
እንደሚታወቀው፤ ሶማሊያን ሲመራ የቆየው የዚያድ ባሬ መንግሥት ከወደቀ በኋላ ሀገሪቱ ለረጅም ዘመን ያህል መንግሥት አልባ ሆና መቆየቷ ሶማሊያ የሽብርተኞች መናኸሪያ እንድትሆን አድርጓታል። ይህንንም ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት የማይሹ ኃይሎችን ወደ ሀገሪቱ ሰርጎ በመግባት ሀገሪቱን የደም ምድር ለማድረግ ብዙ ሞክረዋል። አሁንም ሙከራቸውን አላቆሙም። ይህም ሆኖ ግን እስካሁን ድረስ ከሙከራ የዘለለ ይህ ነው የሚባል ጥቃትን ለመፈጸም አልቻሉም።
በውስጥ የሰላም መደፍረስ አለ ከሚል የተሳሳተ ግምት አጋጣሚውን ለጥፋት ተልዕኮ ለመጠቀም ከሁለት ዓመት በፊት የአልሻባብ ኃይል በሱማሌ ክልል በኩል ሾልኮ በመግባትና ከሽብርተኛው ኦነግ ሸኔ ጋር በመግጠም ሀገሪቱን የሽብር ማዕከል ለማድረግ ሙከራ ቢያደርግም በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቅንጅት ቡድኑ አሳፋሪ ሽንፈትን ተከናንቦ ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር በሙሉ ተደምስሶ መመለሱ የሚታወስ ነው።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከተገደሉት የአልሻባብ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የአሜሪካ መንግሥት መገኛውን ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እከፍላለሁ ብሎ ማስታወቂያ ያስነገረለት ፉአድ መሐመድ ካህላፍን ጨምሮ ሁለት የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም ከ200 በላይ የሚሆኑት የቡድኑ አባላት ከመገደላቸውም በላይ ቡድኑ ይዟቸው የመጣቸው 13 ተሽከርካሪዎቹ ወድመውበታል፤ ትጥቅና ስንቁም ተማርኮበታል።
አልሻባብ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ዋናው የደም መፋሰስና የሞት ምንጭ ነው። ቡድኑ ከአልቃኢዳ ጋር ባለው ህብረትም ለቀጣናው ብቻም ሳይሆን ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ዋና ሥጋት ከሚባሉ ሽብር ቡድኖች አንዱ ነው። ሆኖም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይህንን የሽብር ቡድን በገባበት እየገባ የሽብር ውጥኑን ሲያመክን ቆይቷል። መፈናፈኛም አሳጥቶታል።
ሽብር እና ሁከት የሚበዛበትን እና ያለመረጋጋት የሚንዣብበትን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናን መታደግ የሚችለው የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ያሳተፈ የሰላም አስከባሪ ማዋቀር ሲቻል ነው። ይህ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እምነት ጭምር ነው። ሠራዊቱ በሶማሊያ ለ17 ዓመታት በመቆየቱ የሽብር ቡድኑን መግቢያና መውጫውን ከማወቁም ባሻገር የአሸባሪዎችን መፈልፈያ በአግባቡ የሚረዳ እና በገቡበት ገብቶም መምታት የሚችል ነው።
ከመጪው ጥር ጀምሮ የሰላም ማስከበር ኃይል ሆነው ይሰለፋሉ የተባሉት ግብጽ እና መሰል ሀገሮች በየትኛውም የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያን ያህል ስኬታማ አይደሉም። አካባቢውን በአግባቡ የማይረዱ፤ የጀግንነት ሰብዕና ያልተላበሱ እና በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውጤታማ ልምድ የሌላቸው ናቸው። እነዚህን ሀገራት በአካባቢው ለማሰማራት መወሰን አካባቢውን የሽብርተኞች መፈንጫ ከማድረግ የዘለለ ውጤት አይኖረውም።
የጉዳዩን አሳሳቢነት አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በቀጣይ የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱ ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ሆኗል።
የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዚሁ አዲስ ሽግግር እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ቀጣናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል። ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ ርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም ሲል የሁኔታውን አሳሳቢነት ያብራራል።
በአጠቃላይ ሶማሊያ የመረጠችው መንገድ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ብዙ መዘዝ ይዞ የሚመጣ ነው። በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሕዝብ የከፈለችውን መስዋዕትነት ከንቱ የሚያስቀርና ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት የተከፈለውንም የሕይወት ዋጋ ትርጉም የሚያሳጣ ነው።
በሌላም በኩል በኢትዮጵያ ሠራዊት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ተመናምነው የነበሩት የአልሻባብና የአልቃኢዳ ኃይሎች እንደገና እንዲያንሰራሩና አካባቢውን የሽብር ማዕከል እንዲሆን በር የሚከፍት ነው። ይህ ደግሞ ስጋቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ ጭምር ነው።
ከሁሉ የከፋው ስጋት ደግሞ በግብጽ አማካኝነት በስፋት ወደ ሶማሊያ እየገባ ያለው የጦር መሳሪያ አልሻባብ እጅ የመግባት እድሉ ሰፊ መሆኑ ፤ ይህም አልሸባብን በጦር መሳሪያ ከማስታጠቅ የማይተናነስ፤ በቀጣናው የከፋ ጥፋት ሊፈጥር የሚችል ነው።
የሶማሊያ መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን ተጨባጭ እውነታ ጊዜ ወስዶ ሊያየው ይገባል። በተለይም ለውዝግቡ መነሻ ተደርጎ የሚወሰደውን የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የሶማሊያ ሕዝብም ሆነ የቀጣናው ሀገራት በአግባቡ ሊረዱት ይገባል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ወደብና የባሕር በር ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑንና የጎረቤት ሀገራትም ኢትዮጵያን እንዲተባበሯት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም በግልጽ የተቀበለ ሀገር የለም። ለጥያቄው ምላሽ የሰጠችው የሶማሌ ላንድ ነች። ይህ ደግሞ በድርድር እና ሰጥቶ በመቀበል የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን ከሥነ ልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ሕዝቡ እንዲጋለጥ አድርጓል። የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ዝቅ ከማድረጉም ባሻገር በብዙ መልኩ ተጎጂ እንድትሆን አድርጓታል። ለበርካታ መሠረተ ልማቶችና ለድህነት መቀነሻ ልማቶች ይውል የነበረውን ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ለወደብ ብቻ በማዋል በድህነት ውስጥ እንድትማቅቅ አድርጓታል።
በአሁኑ ወቅት 120 ሚሊዮን ሕዝብ በ2050 አካባቢ ደግሞ በዕጥፍ የሚያድግ ሕዝብ ተይዞ “ስለቀይ ባህር እና ስለ ወደብ አታንሳ፤ ዝም ብለህ ተቀመጥ” የሚል አፋኝ አመለካከት ሊኖር አይገባም።
ሶማሊያ በሺዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የባሕር በር አላት። ይህ ሁሉ ለሶማሊያ ወደብ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል አይደለም። ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች የወደብ አማራጭ መሆን ትችላለች። በብዙ መልኩ የአማራጮች ተጠቃሚ መሆን ትችላለች ።
ዘይላ ሶማሊያ እንደ ሀገር ከመፈጠሯ በፊት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የባሕር በር ነው። ከዛግዌ መንግሥት ጀምሮ ኢትዮጵያ በወደቡ ስትጠቀም ኖራለች። ለኢትዮጵያ ቅርበት አለው። ከሞቃዲሾ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን የሚርቅ ስለሆነ ሶማሊያ ልትጠቀምበት አትችልም። መነጋገር ከተቻለ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የዘይላን ወደብ ኢትዮጵያ ብትጠቀምበትና ሶማሊያም በምትኩ ጥቅም ብታገኝ ሁለቱም ሀገራት አሸናፊ መሆን ይችላሉ።
የኢትዮጵያን ፍላጎት አፍኖ አሸናፊ መሆን አይቻልም። የሶማሊያ መንግሥት ለሶማሊያዊያን በርካታ ውለታ የዋለችውን ኢትዮጵያን በየሥፍራው እየዞሩ ስም ማጥፋትና በኢትዮጵያ ላይ ሀገራት የተሳሳተ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ሊያቆም ይገባል። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆኑ ሀገራት በሰላም አስከባሪ ስም መጋበዝ ደግሞ እሳቱ ለሁሉም የሚተርፍ መሆኑንም ቀድሞ መረዳት ተገቢ ነው።
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም