ከወርቅ ለተገኘው የውጭ ምንዛሬ እድገት ማሻሻያው ዋናውን ድርሻ ይይዛል

አዲስ አበባ፡– በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በወርቅ ማዕድን ለተመዘገበው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እድገት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዋናውን ድርሻ እንደሚይዝ የማዕድን ሚኒስትር ገለጹ።

ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከወርቅ ንግድ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እድገት የተመዘገበበት ሆኗል። ለዚህ ደግሞ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዋናውን ድርሻ ይወስዳል። የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ እንደሌሎች ዘርፎች ሁሉ በማአድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ምርትና ሽያጭ ለይ በተጨባጭ የሚታይ ውጤት ለማስመዝገብ አስችሏል።

መንግሥት የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የማእድን ምክር ቤት በማደራጀት በየወሩ የድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሆነም ጠቁመው፤ የፖሊሲ ማሻሻያው እንደተጠበቀ ሆኖ ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ ለሚያስገቡ ተጨማሪ ማትጊያ መደረጉም ለተገኘው ውጤት እገዛ አድርጓል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ማትጊያው ወርቅ አምራቾች ለብሄራዊ ባንክ ባቀረቡት የወርቅ መጠን ላይ ተመስርቶ የሚሰጡ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን የያዘ በመመሪያ የተደገፈ ነው።

መመሪያው አምራቹ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ ተንቀሳቅሶ ወርቁን ከሚሸጥበት የተሻለ ገቢ የሚያስገኝለት መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም በኮንትሮባንድ ይወጣ የነበረውን ወርቅ በብሄራዊ ባንክ በኩል እንዲያልፍ አስችሏል። ቀደም ሲል በጥቁር ገበያ በኩል ይንቀሳቀስ የነበረው እና በብሄራዊ ባንክ በኩል ያለው የውጭ ምንዛሬ ተመን ልዩነት የሚያጠብ ሆኗል ነው ያሉት።

በኮንትሮባንድ የሚወጣውን በማስቀረት በሀገሪቱ ያለውን ወርቅ በአግባቡ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የሚያስችል ሥርዓት መዘረጋቱን ጠቁመው፤ ይህም እንደ ሀገር ይባክን የነበረውን የወርቅ ምርት ለመታደግ ብሎም ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ያገኙት የነበረውን ያልተገባ ጥቅም በማስቀረት ሀገር እንድትጠቀም ያደርጋል። በሕግ አግባብ ብቻ የሚንቀሳቀሱትንም የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግም እንደሆነ አብራርተዋል።

ይህ አበረታች ውጤት በሌሎች ማዕድናትም ላይ እንዲደገም የማምረትም ሆነ የግብይት ሥርዓቱን ለማሻሻል ከክልሎችና ከኢንቨስተሮች ጋር ለመሥራት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኘ አመልክተው፤ አጠቃላይ የማዕድን ዘርፉ ላይ እየተገኘ ያለውን ለውጥ ለማስፋፋትና ለማስቀጠል እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በኣለም ላይ በከፍተኛ ዋጋ ወርቅ ከሚገዛባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። ወርቅ በዓለም ገበያ ላይ የሚሸጥ አስተማማኝ የዓለም መገበያያ ገንዘብ ሲሆን በየወቅቱ እየጨመረ የሚሄድ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፤ በዓለም ላይ ያለው የገበያ ሁኔታ ተለዋዋጭና ተገማች በማይሆንባቸው ጊዜያት ሀገራት ያንን ወርቅ ወደመያዝ ያዘነብላሉ። አሁንም በዓለም ተገማች የማይሆኑ ሁኔታዎች ስላሉ ሀገራት ወርቅን ወደመያዝ እየተሸጋገሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተገማች ኢኮኖሚ እንዲኖር እንደሚያስችል አመልክተው፤ ይህም በዘርፉ ለመሳተፍ ወደ ሀገር ለሚገቡ አልሚዎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ የተገኘውን ውጤት ዘላቂ ለማድረግ ይረዳል ብለዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ህዳር 20/2017 ዓ.ም

Recommended For You