የሃላባ ስታድየም ግንባታ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የሃላባ ዞን በእግር ኳስ ስፖርት የታዳጊ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በየደረጃው በተለየ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል። ይህን የዞኑን እንቅስቃሴውን ይበልጥ የሚያነቃቃና በአካባቢው የሚታየውን የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ችግር የሚቀርፍ ዘመናዊ ስታድየም እየተገነባም ይገኛል።

የፊፋ እና የካፍን የስታድየም መመዘኛ መስፈርቶች በሚያሟላ ሁኔታ እየተገነባ የሚገኘው የሃላባ ስታድየም መሠረት ድንጋይ ሰኔ 2016 ዓም ተጥሎ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ወደ ሥራ ተገብቷል። የስታድየሙ ግንባታ ሂደት በሶስት ምዕራፎች እንዲጠናቀቅ ታስቦ ሥራው የተጀመረ ሲሆን አሁን ላይ ሜዳውን የመደልደልና ለሰው ሠራሽ ሳር ንጣፍ ዝግጁ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወነ ይገኛል። የሰው ሠራሽ ሳሩ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ በመጠናቀቁም ንጣፉ በአጭር ጊዜ ተሠርቶ እንደሚጠናቀቅም የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምርያ አስታውቋል። አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችል ደረጃን እንዲያሟላ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ተወስዶ በልዩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑም ተጠቅሷል።

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምርያ ኃላፊ አቶ ታገል ጌታቸው፣ የስታድየሙ እግር ኳስ መጫወቻ ሜዳን ሰው ሠራሽ ሳር ለማልበስ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል። እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ በመጀመርያ ዙር ውል ተገብቶ እየተሠራ የሚገኘው የመጫወቻ ሜዳውና የመሮጫ መሙ (ትራክ) ሲሆን፤ ይህንን ጨምሮ የውሃ ማፋሰሻ ግንባታ ሥራዎች እየተጠናቀቀ ነው። የስታድየሙ ግንባታ ሥራ መጀመርያ በሶስት ምዕራፎች (የሳር፣ የትሪቡን እና መም) ይሠራል ተብሎ ቢታሰብም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በአንድ ዙር እንዲሠራ በተወሰነው መሠረት የመጫወቻ ሜዳውና የመሮጫ መም ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፣ የተመልካች መቀመጫና የክቡር ትሪቡን ዲዛይን ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ተሠርቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ዲዛይኑ ጸድቆ በቅርቡ ጨረታ ወጥቶ ወደ ሥራ የሚገባም ይሆናል። የሰው ሠራሽ ሳር ንጣፉ በ15 ቀናት ለማጠናቀቅና የመሮጫ መሙን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስም እየተሠራ ነው። ለግንባታው አስፈላጊው ግብዓት የቀረበ በመሆኑ የመደልደል ሥራ ተከናውኖ የሜዳው ግንባታ 80 ከመቶ በላይ መድረስ ችሏል። የስቴድየሙ ግንባታ የፊፋን እና ካፍን ደረጃ በሚያሟላ ሁኔታ እንዲገነባ ውል ተገብቶ ሥራው የተጀመረ በመሆኑ ተቋራጩ በዚያ መሠረት እየሠራ ነው። የሜዳውና መሙ ግንባታ በስድት ወር እንዲጠናቀቅ እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም የዋጋ ማሻሻዎች ሥራው እንዲጓተት ማድረጉን እና የትሪቡኑን ግንባታውም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ኃላፊው አስረድተዋል።

የግንባታውን ሥራ እያከናወነ የሚገኘው በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያለው ታን ኢንጂነሪንግ የተባለ ድርጅት ሲሆን፣ ቀደም ሲል የድሬዳዋን ስታድየም እድሳት መሥራቱ ተገልጿል። በአማካሪነት ደግሞ የሃላባ ዞን ኮንስትራክሽን መምርያ እንዲሁም ከ 8 በላይ የሚሆኑ መሃንዲሶች በሜዳውና ሌሎች ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ እግር ኳስና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል ሙያዊ እገዛዎችን እንዲያደርጉ ተጠይቀው ለመሳተፍ ፍቃደኛ መሆናቸውም ተገልጿል።

የካፍና የፊፋን መስፈርት ለማሟላት የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ነገሮች ምንድናቸው የሚሉት ጉዳዮች ተለይተው መያዛቸውን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ከምስራቅ አፍሪካ የሱዳንን እንደተመለከቱና መስፈርቱን መሠረት በማድረግ እየተሠራ እንደሆነም ይገልጻሉ። ሜዳው በፊፋ ደረጃ በየጊዜው እየተሻሻለ እውቅና የሚያገኝና ይህንንም ተቋራጩ ዕውቅና አሰጥቶ የሚያስረክብ ይሆናል።

የስቴድየሙ ግንባታ ከውሃ ዋና ውጪ የተለያዩ ውድድሮችን ማስተናገድ በሚችልበት ሁኔታ ማለትም አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቮሊቦል እና ሌሎች የቤት ውስጥ ውድድሮች መሠረተ ልማቶችን ያካትታል። በአጠቃላይ ስቴድየሙ የመለማመጃ ሜዳዎች፣ የክብር እንግዳ ማረፊያዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ክፍል፣ የልብስ መቀየሪያ ክፍል በማካተት እስከ 15 ሺ ሰዎችን የመያዝ አቅም እንደሚኖረው ታውቋል።

የስታድየሙ ግንባታ ሲጀመር 500 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ከዚህም በላይ ሊፈጅ እንደሚችል አቶ ታገል ይገልጻሉ። የገንዘብ ምንጩ ከመንግሥትና ሕዝብ መሆኑን እና ሕዝቡ የሚሠራው ፕሮጀክት አስፈላጊ መሆኑን አምኖበት የሀብት አሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አክለዋል። በተጨማሪም ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ምክክር እየተደረገ ሀብት የማሰባሰብ ሥራው በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የስታድየሙ መገንባት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የሜዳ ችግር በመቅረፍ የተለያዩ ሀገራዊ ውድድሮችን ወደ ክልሉ ማምጣት እንደሚቻል የሚናገሩት አቶ ታገል፣ በአካባቢው የሚገኙት ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች እንዲነቃቁ፣ ተተኪና ውጤታማ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደሚያስችል ያስረዳሉ። ዞኑ የእግር ኳስ አቅም ያለው ሲሆን፣ በፕሮጀክት ታቅፈው የሚሠሩ ታዳጊዎች፣ በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ 2 ክለቦች፣ በከፍተኛ ሊግ አንድ ክለብ እና በተለያዩ ደረጃዎች ታዳጊ ፕሮጀክቶች የሚወዳደሩበት ነው።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You