አደራን በየቤቱ የሚያደርሰው ወጣት

ወጣት አስናቀ ጥበቡ ይባላል። በአካባቢው ያለውን ክፍተትን በማጥናት ከጓደኛው ጋር በመሆን በመሠረተው ተቋም ለብዙዎች አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር በስሩ ለሚገኙ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። እ.አ.አ 2014 የተመሠረተው (Angles Ethiopian Gift De­livery) ውስጥ አስናቀ ሥራ አስኪያጅ ነው። ኤንጅልስ ኢትዮጵያ በዋናነት የሚሠራው ሥራም ሰዎች በጊዜ መጣበብ እና በቦታ ርቀት ምክንያት ለወዳጆቻቸው መስጠት ያልቻሉትን ስጦታ በወኪል ስጦታውን ማድረስ ነው። ‹‹በእኛ ውክልና ውስጥ ፍላጎቶን እናደርሳለን›› ተቋሙ ራሱን የሚገልጽበት ርዕስ ነው።

ሰዎች በቀደመው ጊዜ አንድ እቃ በሰዎች መልካም ፍቃድ አማካኝት እግረ መንገዳቸውን እንዲያደርሱላቸው ያደርጋሉ፤ ምላሹም ምስጋና እና ወዳጅነት ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህ ሃሳብ ወደ ሥራ እድል መቀየሩ ሊያስገርም ይችላል። ‹‹ያለንበት ጊዜ ብዙ አገልግሎቶችን ለማግኘት ቀላል ያደረገበት ጊዜ ነው። ነገር ግን በዛው ልክ ደግሞ በተለመደው እና ነባር በሆነው የማህበራዊ ግንኙነቶቻችን ላይ የራሱን የሆነ ተጽዕኖ አሳድሯል። ኤንጅልስ ጊፍት ያንን ክፍተት ለመሙላት የተቋቋመ ነው። ››

ሰዎች የሚፈልጉት ማንኛውንም እቃ ለመሸመት ሲፈልጉ እቃው ወደሚገኝበት የገበያ ማዕከል ላይ በመሄድ የሚፈልጉትን እቃ ይገዛሉ። አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ ሰዎች የሚፈልጓቸውን እቃዎች በቤታቸው ሆነው ደውለው በማዘዝ አልያም ቴክኖሎጂው በፈጠረው እና ነጋዴዎቹ በራሳቸው ማህበራዊ ገጾች ላይ የሚሸጧቸውን እቃዎች በማስቀመጥ እቃውን መግዛት ለሚፈልጉ ደንበኞቻቸው አስቀድመው ክፍያ በመቀበል ያሉበት ድረስ ይዘውላቸው ይሄዳሉ።

ይህ ሲሆን ገዢው ቦታው ድረስ በመሄድ የሚታጠፋውን ጊዜ የሚቀንስ ሲሆን ለሻጩ ደግሞ ለሚሸጠው እቃ ከሚጠይቀው ክፍያ ባሻገር እንደሚኖረው አሠራር ቦታው ድረስ በመውሰዳቸው ተጨማሪ ገቢን ያገኛሉ። እቃዎችን ከባለቤቱ ተቀብሎ ከሚመለከተው ሰው ማድረስ አሁን ላይ ራሱን የቻለ ሥራ ሆኗል። ሰዎች በሚኖሩበት ከተማ ውስጥም ሆነው እቃዎችን፣ ሰነዶችን ይህንን ሥራ በሚሰሩ ሰዎች አማካኝነት ይልካሉ። በአብዛኛውም የሞተር ሳይክል ትራንስፖርት ለዚህ ሥራ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።

ወጣት አስናቀ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በኢኮኖሚክስ ሲሆን አንድን የንግድ ሥራ ለመጀመር በአካባቢያችን ያለን ክፍተት ማየት ለሥራ ፈጠራ ጥሩ የሃሳብ መነሻ መሆኑ ያገዘው ይመስላል። ‹‹አንድን እቃ ለሚፈለገው ሰው ማድረስ እና ስጦታን ለሚሰጠው ሰው ማድረስ ይለያያል። ስጦታውን መስጠት የፈለገው ሰው በአካል ቢኖር ለተቀባዩ ሊፈጥረው የሚችለውን ስሜት በሚፈጥር መልኩ አቀራረብ ሊኖረው ይገባል። ›› ይህም ሰዎች ባልጠበቁበት ሰዓት ደስታ የመፍጠር ያክል ይዘት ይኖረዋል።

በመሆኑም ሰዎች ባላቸው የጊዜ መጣበብ፣ ከቦታ ርቀት እና በሀገር ውስጥ ካለመኖር የተነሳ ስጦታዎችን በእነዚህ አማካኝነት ይልካሉ። ‹‹ ሰዎች በተለያየ አጋጣሚ ልዩ ለሚሉት ቀን በአካል መገኘት ባይችሉ ከወዳጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ማስታወስ በሚፈልጓቸው ቀናት ላይ ስጦታ በመላክ መልካም ምኞታቸውን መግለጽ፣ ቀኑን ማስታወስ ሲፈልጉ እነሱን ወክለን ስሜታቸውን ሊገልጽ በሚችል መልኩ ስጦታቸውን በቀኑ እና በሰዓቱ እናደርሳለን። ›› ይላል ወጣት አስናቀ።

ስጦታዎች ለልደት፣ ለጋብቻ በዓል፣ ለምርቃት እና ለተለያዩ በዓላት በማስመልከት ሰዎች ስጦታቸውን በዚህ ውክልና ያደርሳሉ። ሥራውን በጀመረበት ወቅት በአብዛኛው ከሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊ ደንበኞችን በስፋት እንዳሉት የሚያስታውሰው ወጣት አስናቀ በአሁኑ ወቅትም በሀገር ውስጥ ያለው አቀባበል ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሷል።

‹‹የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አብረን ስለምንሰራ በሀገር ውስጥ ካሉ ኤምባሲዎች ጋር የመሥራት እድሉ ነበረን። በኋላ ግን የነበሩ የተለያዩ ግንኙነቶች በመቀዛቀዛቸው በሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት በድጋሚ በማጥናት አስፈላጊ እንደሆነ ሌሎች ደንበኞችን ወደማፍራት ገብተናል።›› ሲሉ ኮቪድ ፈጥሮት የነበረውን ችግር የተሻገረበትን መንገድ ይገልጻል።

የሥራው ባህሪ በብዛት ከደንበኞች ጋር በአካል ከመሆን ይልቅ በማህበራዊ ገጽ ላይ በሚደረጉ የሃሳብ ልውውጦች እንደሚያልቅ የሚገልጸው አስናቀ አብዛኛው የክፍያ መንገድ ጊዜው የፈጠራቸው የኦንላይን የክፍያ መንገዶች አማካኝነት ይፈጸማል። ‹‹ከደንበኞቻችን ጋር በአካል የምንገናኝበት አጋጣሚ ጠባብ ነው። የሚፈልጉትን የስጦታ ዓይነት እና ጥቅል ከነገሩን በኋላ ለክፍያ እንዲመች አሁን ላይ የሚገኙ የተለያዩ የባንክ አማራጮችን በመጠቀም ለደንበኞች ምቹ ለማድረግ እንጥራለን። ›› ሲል አሠራራቸውን ያብራራል።

የስጦታ ትንሽ የለውም የሚባለው የሀገራችን ብሂል እንዳለ ሆኖ ስጦታን በውክልና ለወዳጅ እንዲደርስ ማድረግ ክፍያው ምን ያህል ነው በሚል ወጣት አስናቀ የክፍያ ተመጣጣኝነቱን ጠይቀነዋል። ‹‹በአብዛኛው ተደራሽ የምናደርጋቸው ደንበኞቻችን መካከለኛ ገቢ ላይ ያሉ የምንላቸውን ነው። ከምንታዘዘው የስጦታ ዓይነት ባሻገር ስጦታውን ለማድረስ የምናወጣውን የትራንስፖርት ክፍያ አማካኝ የምንለውን አድራሻ በመለየት ተመጣጣኝ ክፍያ እንጠይቃለን። ከዚያም ደግሞ ከአገልግሎት ክፍያ በተጨማሪ በክፍያ ሥርጭቱ ላይ የሚጠቃለል ይሆናል። ›› በማለት ተደራሽ ለማድረግ ያሰቧቸውን የማህበረሰብ ክፍል እና ክፍያ አብራርቷል።

አንድ ደንበኛ ስጦታ ለመላክ ኤንጅልስ ቢፈልግ ስጦታው እንዲላክ ከሚፈልግበት አንድ ቀን አስቀድሞ የስጦታ ዓይነት ጥቅሎች ተመርጠው የሚጠናቀቁ ሲሆን የክፍያ ሁኔታውም በዚህ መልኩ ይከናወናል።

አስናቀ በሥራ አጋጣሚ ላይ የሚገጥሙ በርካታ ገጠመኞች መኖራቸውን ያስረዳል። ሰዎች ስጦታዎችን ለሰው ለመስጠት የመረጡትን ልዩ ቀን እንደ ምክንያት ይጠቀማሉ፤ ታዲያ የታዘዘው ስጦታው በተባለው ቦታ ልክ በቀኑ እና በሰዓቱ ሊደርስ ይገባል። አስናቀ ከዚህ ጋር ተያይዞ ያለውን ገጠመኝ እንዲህ አጋርቶናል። ‹‹አንዳንድ ትእዛዞቻችን የተቆረጠ ሰዓት የተቀመጠላቸው ይሆኑና የሚኖረውን የመንገድ መጨናነቅ መገመት አንችልም እና ቅርብ ነው ብለን የምናስባቸው አድራሻዎች ራሱ መድረስ የማንችልበት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። በዚህ ምክንያት ብዙ ገጠመኞች አሉን። ›› ሲሉ በዚህ ረገድ በርካታ ገጠመኞች መኖራቸውን ያስረዳል። ሆኖም ማንኛውንም የታዘዙ ስጦታዎች ከታዘዙበት አንድ ሰዓት ቀድመው ወደ ቦታው የመንቀሳቀስ ሥራቸውን እንደሚጀምሩ ያስረዳል።

‹‹አንዳንድ ጊዜ የምንጠቀማቸው የኦንላይን የክፍያ ሥርዓቶች የመዘግየት ሲስተም ያለመሥራት ነገር ይኖራል። በዚህ ወቅት እንደ አማራጭ የምንወስደው ብቸኛው ነገር እምነት ነው። ›› በማለት አገልግሎቱን በመስጠት እና ደንበኞችን ባለመግፋት ከአገልግሎት በኋላ ክፍያ ይጠይቃሉ በዚህም ክፍያውን ያልፈጸሙ እምነት/ታማኝነት ያጎደሉ ደንበኞች አልመኖራቸውን አስናቀ ያስታውሳል።

ኤንጅልስ ኢትዮጵያ ከተመሠረተ ከ10 ዓመት በላይ አስቆጥሯል። አስናቀ ከዚህ በኋላ ኤንጅልስ ኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ ሌሎች ጋር እንዲደርስ የማድረግ እቅዶች አሉት። ከሚሠራቸው ሥራዎች ባሻገር የተለያዩ የስጦታ ጥቅሎችን በራሱ በማዘጋጀት ለደንበኞች ማቅረብ ይፈልጋል።

ሥራውን በተጀመረበት ወቅት ከጓደኛው ጋር በመሆን ባዘጋጁት ይፋዊ ድህረ ገጽ ትእዛዞችን በመቀበል፣ ማስታወቂያዎችን በመሥራት ጀምረውታል። ‹‹አብዛኛው ሥራችን የታዘዘውን ስጦታ ማድረስ ሲሆን ይህንን ሥራ የሚያከናውኑልን ቋሚ እና ትእዛዝ ቁጥራችን በሚበዛበት ወቅት የምናሰማራቸው ሠራተኞች አሉን። ›› ይህም የሚሆነው የበዓላት ወቅት ላይ የሚኖረው የትእዛዝ ፍላጎት የሚጨምር መሆኑን አስናቀ ይገልጻል።

ከጓደኛው ጋር በመሆን የጀመረው የሰዎችን ስሜት እና ፍላጎት ተከትሎ ሰዎች የጎደሉበትን ቦታ መሙላት ሥራ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ሰዎች ተቀባይነት ማግኘቱን የሚገልጸው ወጣት አስናቀ ማንኛውንም ሥራ ወጣቶች ለመጀመር ከማሰባቸው በፊት ምን ክፍተት አለ የሚለውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል በማለት ይገልጻል። ‹‹በሀገር ደረጃ ምን ችግር ወይም ክፍተት አለ የሚለውን መረዳት ያስፈልጋል። ክፍተቱን ከለዩ በኋላ ይህንን ክፍተት በመሙላት እንዴት ትርፍ ማግኘት ይቻላል የሚለው ተከትሎ የሚመጣ ጥያቄ ነው። ›› በመሆኑም አካባቢን እና ነባራዊ ሁኔታን ማጥናት አንዱ ሥራ የመፍጠሪያ መንገድ መሆኑን ጠቅሷል። በመረጡት የሥራ ሃሳብ ላይ ደግሞ ራሳቸውን ማብቃት ይጠበቅባቸዋል።

‹‹አሁን ላይ ያለንበት ወቅት ደግሞ የተለያዩ ጥናቶችን ኢንተርኔቶችን በመጠቀም በቀላሉ ጥናት ማድረግ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። ›› በማለት ጊዜው ያመጣቸው እድሎችን በመጠቀም የሥራ ሃሳቦች ማግኘት ብቻ ሳይሆን ወጣቶች ራሳቸውን ማብቃት ጭምር ይህንን መንገድ ይችላሉ።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You