ለተሸከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ ሊገጠም መሆኑን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያእቆብ በላይ ይህን ያሉት በቢሾፍቱ ከተማ ‹‹የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚዲያ ተቋማት ያላቸው ሚና›› በሚል መሪ ቃል በመጋቢት 5 እና 6 ተካሂዶ በነበረው የስልጠናና የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡
አቶ ያእቆብ እንዳሉት በጥፋተኛ አሽከርካሪዎች የሚደርሰውን አደጋው በከፍተኛ ደረጃ እያባባሰ ያለውን የፍጥነት ችግር መፍትሔ ለማበጀት የፍጥነት መገደቢያ (speed limiter) መመሪያ ወጥቶ ፀድቋል ያሉ ሲሆን መሳርያው እስከ ቀጣይ ሶስት ወራት ድረስ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባልም ብለዋል፡፡
የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያውን በተሸከርካሪዎች ላይ ለመግጠም ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ ኩባንያዎችን መለየቱንና መሳሪያውም በቅርብ እንደሚገባ የገለፀው ባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ የማሰልጠኛ ተቋማትን ፕሮፌሽናል ከማድረግ አንፃር የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ባለስልጣኑ የተለየ አሰራርን በመዘርጋት ባለፉት ሶስትና አራት አመታት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡
አቶ ያዕቆብ አክለውም ከዚህ በፊት የነበረው የመረጃ ስርዐት ጥፋተኛ አሽከርካሪዎችን መያዝ ላይ የዝርጋታ ችግር ነበረበት፡፡ በክልል ከተማ ውስጥ የተቀጣ አሽከርካሪ የአሽከርካሪ ሪከርድ በስርአቱ ያልቀረበ በመሆኑ ወደ ሌሎች ከተሞች በመሄድ ይሰራ ነበር አሁን ግን አገር አቀፍ የሆነ የመረጃ ቋት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያው በሌሎች ሀገራት ውጤታማ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ በኬንያ 33 በመቶ በላይ አደጋውን ቀንሷልም ብለዋል፡፡
በዳግማዊት ግርማ