ሰሞንኛው የብልጽግና ክራሞት
ገዢያችን ብልጽግና ፓርቲ ጉባዔውን “በሰላም አጠናቆ” ገና ከጣመናው አላገገመም፡፡ “እንኳንም በሽልም ወጣህ” ብለን መልካም ምኞታችንን ብንገልጽ ዘግይቷል አያሰኝም፡፡ የፓርቲው ቤትኞች ስለ ወደፊቱ የሥልጣን ማረፊያቸው እየተጨነቁ፤ እኛ ግፉዓን ተገዢ ዜጎች ደግሞ ፈተና ስለተሞላው ኑሯችን “ምን በጎ ነገር ይወሰንልን ይሆን?” በማለት የጉባዔውን መጠናቀቅ ስንጠብቅ የሰነበትነው ልክ እንደ ርሃብ ቀን ሰብል በመጓጓት በሚዲያዎች ላይ አፍጥጠን ነበር፡፡
በተለይም ለፖለቲካው ሠፈርተኞች የብልጽግናው ትልቁ ሰውዬ፤ ለእኛ ለተራ ዜጎች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ብቅ ባሉ ቁጥር “ስለ ወሰኗቸው ውሳኔዎች መልካም የምሥራች” ያሰሙናል ብለን ጆሯችንን ቀስረንና ልብ ተቀልብ ሆነን ስናደምጣቸው የባጀነው በትልቅ ጉጉት መሆኑን ጫን ብለን እንገልጻለን፡፡
አብዛኛው ሕዝብ ፊት ከነሳቸው ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋር ያለ አስታራቂ ሽማግሌ ወዶና ፈቅዶ ዐይንና ጆሮውን በአትኩሮት ካፈጠጠባቸው አጋጣሚዎች መካከል ምናልባትም ብልጽግና ፓርቲ ጉባዔውን ባካሄደባቸው ቀናት ስለመሆኑ በጥናት ባይረጋገጥም ለሙያው ቅርበት ያለን ዜጎች መገመታችን አልቀረም፡፡
በርካታ ተራ ዜጎችና በቀለም ቆጠራ የገፉ “አንቱዎች” ጭምር በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ ስለተላለፉት ውሳኔዎች “ሺህ ቢታለብ ያው በገሌ” እንዳለችው ድመት፤ አዲስ ነገር አላገኘንበትም ብለው በወዳጆች ጨዋታ መካከልም ይሁን በይፋ ሲከራከሩ ተደምጠዋል፡፡
አንዳንዶችም ተስፋ እንዳጫረባቸው በግልጽ ሲመሰክሩ ሰንብተዋል፡፡ በተለይም የፓርቲው ትልቁ ሰውዬ ሀገራዊ አበሳዎቻችንን (ሌብነቱን፣ ሙስናውን፣ ከዕለት እንጀራችን ጋር የተያያየዘውን የኢኮኖሚ ጡዘትና የመጻኢው የሀገሪቱን ዕድል ፈንታ ወዘተ.) አስመልክቶ በድፍረት የዳሰሷቸው ጉዳዮች በእጅጉ አርክቶናል በማለት ምስጋናቸውን በየሚዲያዎቹ ጭምር በግላጭ ያደረሱም ብዙዎች ናቸው፡፡
“ከዳዴ እንፉቅቅ ካልወጣውና የወተት ጥርሱን ገና ካልነቀለው የሦስት ዓመቱ ጨቅላ ፓርቲ ከዚህ የላቁና እጅግ የገዘፉ የተግባር ውሳኔዎች መጠበቁ የዋህነት ስለሆነ ጊዜ ሰጥተን በትዕግሥት ልንጠብቀው ይገባል” በማለትም አቋማቸውን በድፍረት የገለጹ አልጠፉም፡፡
“ፓርቲው በእስከ ዛሬው ጉዞው ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለመጽናትና አገሪቱንም ከበርካታ አደጋዎች ለመታደግ በመቻሉም ‘የልጅ አዋቂ’ ልንለው ይገባል” እያሉ የተከራከሩለት ወገኖች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለሒስ የሚቸኩሉት “የተገፋን ባይ የሌሎች ፓርቲዎች ልጆችም” ብልጽግና ፓርቲ የተደራጀው የኢህአዴግ ቤትኞችና ገመና አዋቂ በሆኑ “አልጋ ወራሾች” መሆኑን በማስታወስ እንደ አዲስና ተቋቋሚ ጎጆ ወጭ “ሙሽራ” ሊታይ አይገባም በማለትም የሞገቱ ብዙዎች ናቸው፡፡
የመከራከሪያዎቹ ዓይነት ደርዛቸው ብዙ፤ ተጠየቃቸው ዝንጉርጉር ስለሆነ ሁሉንም ለመዳሰስ የጋዜጣው ዓምድ ጥበት ባያወላዳን ኖሮ ብዙ ጉዳዮችን መዳሰስ ይቻል ነበር፡፡ የብልጽግናን አፈጣጠር በተመለከተና የሦስት ዓመቱን የፓርቲውን ዜና መዋዕል አስመልክቶ አንድ ጨዋታ አዋቂ ወዳጄ ያጋራኝን ምልከታውን ማስታወሱ ለትምህርትም ይሁን ለተዝናኖት ያግዝ ይመስለኛል፡፡ ይህ ወዳጄ ፓርቲውን ያመሳሰለው ሶምሶንን ከተገዳደረው አንበሳ ጋር ነበር፡፡ ታሪኩ የሚገኘው በቅዱስ መጽሐፍ፤ “መጽሐፈ መሳፍንት ምዕራፍ አስራ አራት” ውስጥ ነው።
ሶምሶን በጉዞ ላይ እያለ ጠግቦ የሚያገሳ አንድ የአንበሳ ደቦል ወደ እርሱ እየተንደረደረ ሲመጣ ያስተውላል። አንበሳው እያገሳ ወደ እርሱ መሮጡን ቢያስተውልም ወላጆቹ በስለት ያገኙት ልዕለ ሰቡ (Superman) ሶምሶን ፍርሃት ይሉት ስሜት ዝርም አላለበትም፡፡ የእግዚሃር ብርቱ መንፈስ ስለወረደበትም ምንም የጦር መሳሪያ ወይንም ስለት በእጁ ሳይዝ ያንን የአራዊት ንጉሥ አንበሳ በራሱ ጡንቻ ቆራርጦ በመጣል የመንፈሳዊ አቅሙን የሥልጣን ብርታት አስመሰከረ፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላም ሶምሶን በዚያ መንገድ ሲያልፍ ቆራርጦ ከጣለው የአንበሳ ሬሳ ውስጥ ንብ ሰፍሮበት፤ ወለላ ማርም ጢም ብሎ ሞልቶበት ያገኘዋል፡፡ በዚህ ተዓምር ሶምሶን ምን እንደተሰማው ቅዱስ መጽሐፍ አብራርቶ ባይገልጽልንም የማሩን ወለላ ለራሱ እስኪበቃው ድረስ ከተመገበ በኋላ የተረፈውን ለእናትና አባቱ ወስዶ እንዳበላቸው በታሪኩ ወስጥ በዝርዝር ተገልጧል፡፡
“ከበላተኛ ውስጥ መብል ወጣ፤ ከብርቱውም ውስጥ ጥፍጥ ወጣ” የሚል እንቆቅልሽ እንደተመሳጠረበት ጭምር ጣፋጩ ታሪክ እያማለለ ያጓጉዘናል፡፡ በሶምሶን ጡንቻ እንደተገደለውና የማር ወለላ ከበድኑ ውስጥ እንደወጣው ተዓምረኛ አንበሳ ሁሉ “ያለምንም ደም መፋሰስ” ጥበብ በታከለበት የፖለቲካ ጡንቻ ከተዘረረው የኢህአዴግ ግምባር ውስጥ የብልጽግና ፓርቲ መወለዱን እያነጻጻረ የተረከልኝ ያ ወዳጄ፤ ጨዋታው እየጣመኝ እንዳጣጣምኩ ባልመሰክር ውለታ በል እሆናለሁ፡፡
ስለ ሶምሶን አንበሳና ከበድኑ ውስጥ ስለወጣው የማር ወለላ ጉዳይ ሥነ መለኮታዊ መነታረኪያውንና የሥነ አፈታት ምሥጢሩን ለጊዜው ለባለሙያዎች በመተው ተመሳስሎው ብቻ ትኩረት እንዲደረግበት ጸሐፊው ዳግላስ በትህትና ያሳስባል፡፡ ያ ጓዴ ይህንን መሰል ሃሳቡን ያጋራኝ “ዴሞክራሲያዊ መብቱን” በመጠቀም ስለሆነ ፊት ሊጠቁርበትም ሆነ ጥርስ ሊነከስበት ይገባል ብሎም አያምንም፡፡
“በአግባቡ ልትተቹኝ መብታቸሁ ነው!” ብሎ ያደፋፈረን ብልጽግና ራሱ ስለሆነ ለወደፊቱም ቢሆን በቃሉ እንደሚገኝ እምነታችን ነው፡፡ ብሩህ ተስፋና ርእይ ሰንቆና ከፍተኛ የሕዝብ ተቀባይነት ተጎናጽፎ በዕልልታ ጭምር ታጅቦ “ከሟቹ ኢህአዴግ ውስጥ እንደ ሶምሶን ማር” ብቅ ያለው “ተዓምረኛው” ብልጽግና ፓርቲ ክፉ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች የገጠመው ገና ከጠዋቱ ነበር፡፡
ስለዚህም ይመስላል የፓርቲው አንደኛ ጉባዔ “ከፈተና ወደ ልዕልና” በሚል መፈክር ደምቆ የተካሄደው፡፡ በዚያም ተባለ በዚህ ብልጽግና የሀገሪቱ ገዢ፣ የፖለቲካው ሻምፒዮን በመሆን ይድላውም ይቆርቁረው ብቻ በሥልጣኑ ላይ ተዳላድሎ ከተቀመጠ ሦስት ተኩል የልደት ሻማውን አብርቶ አንደኛን ጉባዔውን አካሂዶ በስኬት አጠናቋል፡፡
ለመንበረ ሥልጣኑ መደላድል ዕውቅና የሰጠነውና “አንተ ምራን” ብለን ቀኝ እጃችንን የዘረጋንለት እኛ “ሕዝብ” በሚል የጥቅል ስም የምንሰፈረው ሚሊዮን ዜጎች መሆናችን ግን ፍጹም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ዘንግተነዋል ቢሉንም “በሕግ አምላክ!” ብለን እንሞግታቸዋለን።
በብልጽግና አገዛዝ ላይ ብዙ አስተያየቶችና አቃቂሮች ቢዘንቡም በኮንትራት የሰጠነው የአምስት ዓመቱ ጉዞ ገና መጀመሩ መሆኑ መዘንጋት አይኖርበትም፡፡
እግር በእግር እየተከታተልን በማረቁ ላይ ካልበረታን በስተቀር አንገዛልህም ብለን ማቅማማቱ ፋይዳ ቢስ መሆኑን እኛ ተራ ዜጎች ብቻ ሳንሆን “በፖለቲካ የሰከሩትም” ቢሆኑ ቢረዱት አይከፋም፡፡ “ማርያምን ትወዳታለህ?” ተብሎ የውስጠ ወይራ ይዘት ያለው ጥያቄ የቀረበለት አንድ ብልህ ባለ አገር፤ “ወዳጄ ሆይ ወድጄ ነው እመቤቴ ማርያምን የምወዳት፤ ከግንድ የሚያላጋ ልጅ ስላላት ነው፡፡” በማለት ሰጠ የሚባለው መልስ ለብልጽግናም ይሰራ ይመስለናል፡፡ እኛም “ብልጽግናን የምንወደው ወደን ነው” ብንልስ፡፡
”ሕዝብ የተቀየማቸውን፤ ፓርቲው አያባብላቸው!‘
ብልጽግናም ሆነ የቀደምቱ የኢህአዴግ ችግር ሕዝብን ያስቆጡና በአገልግሎት አሰጣጣቸው ያስከፉ “ልጆቻቸውን” ከማረቅና የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ከብዙኃን ጋር እልህ የተጋቡ ይመስል አቅመ ቢሶቹን እሹሩሩ እያሉ በአንቀልባ ማዘል እስኪቀራቸው ድረስ የሚፈጽሙት ተግባር በእጅጉ የሚያሳዝን ነው።
ለምሳሌ፡- በከፍተኛ ስፍራ ተሹሞ “ካብ አይገባ ምንትስ” የሚሉት ዓይነት መሆኑ እየታወቀና ተደነቃቅፎ ማደነቃቀፉን እንኳን በመንግሥት ዐይን ቀርቶ ለሕዝቡ ለራሱ ግልጥ ሆኖ እየታየ ይብስ ብሎ በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን እንዲወክል ሲሾም ይስተዋላል፡፡
ይህንን መሰሉን ሰው ገለል አድርጎ ከማለዘብ ይልቅ ወደ ተሻለ ከፍታ ማስፈንጠሩን በቀዳሚው ሥርዓት ቆሽታችን እየደበነ እናስተውል ነበር፡፡ “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” እንዲል ብሂላችን ብልጽግናም ይህንኑ ፈለግ ሲከተል ዕለት በዕለት እያስተዋልን ነው፡፡
ሕዝቡ ለሁልጊዜ “ጓያ እንደሰበረው ሰነፍ ሰው” ቆይ ብቻ እያለ የሚኖር አይመስለንም፡፡ ምንም አንኳን መከራን ለመቀበል የኢትዮጵያዊያን ጫንቃ ተላምዶታል ቢባልም እስከ መቼ? ምንም ትከሻው ሰፊ ቢሆን ሕዝብ እኮ የትዕግሥት ገደብ አለው፡፡ ብልጽግና ሆይ ምርር ብለህ ስትናገር እኛ በትዕግስት እንደሰማንህ አንተም ምሬታችንን ልብ ተቀልብ ሆነህ ለማድመጥ አትሰልች ወይንም አትከፋ፡፡
ይህ የመጀመሪያው ኮስትር ያለ ትዝብታችን ነው፡፡ ከአፍሪካዊያን ብጤዎቹ ጋር ተነጻጽሮ የብልጽግና ፓርቲው ግዙፍነት የተገለጸበት የአስራ አንድ ሚሊዮን አባላቱ ጉዳይም ብዙዎችን ሲያስገርም ከርሟል፤ በርካቶችንም አስደንግጧል፡፡
ቁጥሩ እርግጠኛ ይሁንም አይሁን፤ የአባላቱ የብቃትና የጥራትም ጉዳይም “እንደተከደነ ይብሰልና” ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ሠራዊት ወላጅ መሆን “የመንታ እናት ተንጋላ ትሙትን” አያስተርትም? “የተወዳደርኩት ለሥልጣን አሸናፊነት ነው” የሚል ፓርቲ ነገ ጠዋት የተጠቀሰው ሚሊዮን ሰልፈኛ ለእኔ የሚገባው ስልጣን የትኛው ነው? ብሎ ቢጠየቅ መልሱ ምን ሊሆን ይችላል? ይሄኛው ጥያቄ ፊት ሊያስጠቁር ስለሚችል በሌላ ፈርጁ ብንመለከተውስ፡፡ ገና በጮርቃ ዕድሜ ላይ በሚገኝ ፓርቲ በምትመራ አገር ይሄን ያህል ቁጥር ባለው ካድሬ ወረራ መፈጸሙ አንድምታው ምን ሊሆን ይችላል።
የወደፊቱን ኑሯችንን ስናስብ ሊያስፈራን አይገባም? በምርጫ ውጤት ላይ በሚያመጣው ግዙፍ ተጽእኖስ የተፎካካሪ ተብዬ ፓርቲዎችን የነገ ተስፋ አያጨልምም? ሀሞታቸው ቀጥኖ ከጨዋታው ሜዳ እንዲወጡስ የቀይ ካርድ ሚና አይጫወትም? “ቢበዛና ቢያንስ ምን አገባችሁ?” እንደማንባል ተስፋ በማድረግ፤ የብልጽግና ልጆች ቁጥር እንደተገለጠው ነው ብንል አንኳን፤ ይህ ሁሉ ሚሊዮን ሠራዊት እስከ ዛሬ ለሕዝብ ምን ውለታ ዋለ? በመንግሥታዊና በአገልግሎት መስጫ ተቋማት እየተገኙ ሕዝቡ ለሚንገሸገሽባቸው ችግሮች የዐይን ምስክር በመሆን ግኝታቸውን ለፓርቲያቸው አካል አሳውቀው መፍትሔ አስገኝተዋል? በተገልጋይ እምባ ጥማቸውን የሚያረኩ “ሹመኞችና ምንደኞች” አደብ እንዲገዙስ መክረዋል፤ አስመክረዋል? ለመሆኑ ፓርቲው የእጃቸውን ንጽሕና የሚፈትሽበት አሰራርስ ዘርግቷል? አራገፍኳቸው ያላቸው አባላቱስ የተገመገሙት በናሙና የፍተሻ ስልት ነው ወይንስ የሁሉም ጓዳ ጎድጓዳቸው ተፈትሾ? ሌላው ትዝብታችን ነው፡፡
የሆነውስ ሆኖ ለመሆኑ አገር የምትመራው የፓርቲ ዩኒፎርም በለበሱ “ብፁዓን” ብቻ ነውን? “በተማርኩበት ሙያ አገሬን ላገልግል፣ በልምዴ የአገሬን ቀዳዳ ልድፈን ወዘተ.” ለሚሉ ባእድ ባለሀገሮች ብልጽግና ምን መልስ ይሰጣል? ከሚሊዮኖቹ አባላቱ የሚተርፍ ድርሻስ ሊኖር ይችላል? ቢሯቸውን በብረት አጥር ከርችመው፣ ከውስጥ ወደ ውጭ እንዳይታዩ መኪኖቻቸውን በጥቁር ግምጃ ጋርደው፣ የባለ ጉዳይን ጠረን ከማሽተት ይልቅ ስብሰባ እንደ ሱስ ሀራራ ለተጠናወታቸው የላይኞቹ ሹመኞች አቤት ባዩን ወይንም ምክር ላካፍል እችላለሁ የሚሉ ዜጎችን ነዎሩ ብሎ ለመቀበል ዝግጁ ናቸው? ወይንስ እንደ ሀቻምና አምና ምንም መሻሻል አልታየበትም? ሦስተኛውና በልባችን የከበደ ሌላው ሀዘን መሆኑ ይመዝገብልን፡፡
እንደ ትምህርት ዝግጅታቸውና ልምዳቸው አትዮጵያ ባለሙያ ልጆቿን የምትመዘግብበት ሮስተር ይኖራት ይሆን? ካለ አሰየው! ከሌለስ ምን አገደን? በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት ማን በምን የሙያ ዘርፍ ሰልጥኗል? እየተባለ ቢጠየቅ ክፋት ይኖረው ይሆን? ወይንስ አይቻልም? እነዚህን ባለሙያዎች ከፓርቲ ችሮታ ውጭ በየተቋሙ በመመደብስ ማሰራት አይቻልም።
ቀበሌዎች፣ ወረዳዎች፣ ክፍለ ከተሞችም ሆኑ ዞኖች ወይንም ሌሎች ተቋማት የሰው ኃይል ሲፈልጉና ለመፈለግ ሲያቅዱ መረጃው አይጠቅማቸው ይሆን? “ከፓርቲው ልጆች ውጭስ” ነፃና ንጹሕ ልብ ያላቸውን ባለሙያዎች ለማሰማራት ብልጽግና ፈቃደኛ ነውን? ጠይቁ እንሰማችኋለን ስለተባለ እንጠይቃለን፡፡
ሰምተው ሲመልሱም እናመሰግናለን፡፡ ትዝብታችንን ከቁብ ሳይቆጥሩ ቀርተው “አዳሜ ይጩኽ ምን እንዳያመጣ ነው” ብለው “ጩኸታችን የቁራ ጩኸት” እንዲሆን ከፈረዱብንም እንደለመድነው ጯኺ እስኪተካ እየጮኽን እንጠብቃለን፡፡
ከዛሬ ወደ ትናንት፤
መቼም ያለፈውን ሥርዓት በጭፍን ጥላቻ ማክፋፋት አገራዊ ባህላችን ስለሆነ እንጂ ዞር ብለን ብንፈትሽ በርካታ መልካም ተሞክሮዎችን መንቀስ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ “ዐይንህን ለአፈር” እያልን ስንረግመው የኖርነው የደርግ ሥርዓት ከቀበሌ አንስቶ እስከ ከፍተኛ መዋቅር ድረስ፣ በሕብረት ሱቆችና በፍርድ ሸንጎዎች ውስጥ ሳይቀር ዜጎችን በሕዝብ ምርጫ ያሳትፍ የነበረው የግድ የኢሠፓ አባላት ስለሆኑ ብቻ አልነበረም፡፡
እንዲያውም እውነት እንመስክር ከተባለ በስነ ምግባራቸው ለተከበሩ ዜጎች ቅድሚያ ይሰጥ እንደነበር ይህ ጸሐፊ ምስክር ነው፡፡ በ1979 ዓ.ም የኢሕዲሪ መንግሥት ከተመሰረተም በኋላ ከገጠር እስከ ከተማ በየደረጃው ለሚገኙ የአመራርና የአስተዳደር ቦታዎች ያለምንም የፓርቲ ወገንተኛነት የመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው ዜጎች እንዲሰማሩ ተወስኖ በወቅቱ የአገሪቱ መከራዎች በመብዛታቸው ዕቅዱ በከፊል ብቻ ተፈጽሞ መክሸፉ እንጂ ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡
በቅርቡ ከአንድ የወቅቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን ጋር ስንጨዋወት አብዛኞቹ ሚኒስትሮችና ከዚያ በታች ያሉ ሹሞች ወደተለያዩ ኃላፊነቶች ይመደቡ የነበረው በብቃታቸው እንጂ የፓርቲ አባላት ስለሆኑ ብቻ እንዳልሆነ አረጋግጠውልኛል። ይህም ጸሐፊ በአብነት የሚጠቅሳቸው ጥቂት ሰዎች በአቅራቢያው ዛሬም ድረስ እንደሚገኙ ያረጋግጣል፡፡ ሰፊ ርዕስ፤ ውሱን አምድ… ቀሪው ትዝብትና አስተያየት በይደር ይተላለፍልን፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2014