እንደምን አላችሁልኝ ውድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አንባቢዎች:: በዛሬው ዝግጅቴ ከናንተ ጋር ቆይታ የማደርገው፣ በፈረደበት ሶሻል ሚዲያ ከሰሜን አሜሪካ እስከ አውሮፓና ኢትዮጵያ ድረስ ሲደሰኮርለት ለነበረው የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ትንሽ ነገር ማለት ፈልጌ ነው::
ሁለት የሚተዋወቁ እናቶች ስድስት ኪሎ አካባቢ በድንገት መንገድ ላይ ይገናኙና ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ፤ አንደኛዋ እናት “እንኳን ደስ ያለዎት ልጅዎት ዩኒቨርሲቲ ገባልዎት አይደል?” ሲሉ ይጠይቋቸዋል:: እናትም ድንግጥ ብለው “ልጄማ ገና ዘጠነኛ ክፍል ነው፤” ይላሉ::
ጓደኛቸው ደረታቸውን በእጃቸው እየመቱ ውይ አፈር በሆንኩኝ፣ እኔኮ በቀደምለት ዱላ ይዞ ሳየው ዩኒቨርሲቲ የገባ መስሎኝ ነው ብለው እርፍ!።ምናልባት ቀልዱ ሊያስቀን ይችላል::
ነገር ግን የነገ ኢትዮጵያን ተረካቢ አዲስ ትውልድ መልኩንም፣ ቅርፁንም፣ ቀይሮ “ባለ ዲግሪው መባል .. ቀርቶ ባለ ዱላው “ ተማሪ እየተባለ ሲጠራ መስማት ያሳዝናል:: ውድ አንባቢዎች ለመሆኑ ትምህርት ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት ወደ ዋናው ሃሳቤ ለመግባት ወደድኩ።
በርግጥ የአለም ምሁራን እንደሚስማሙበት ትምህርት ማለት ምን ያህል ሸምድደን በአእምሮአችን ይዘነዋል? አልያም ምን ያህል የመፃህፍቱን ክፍሎች አንብበናል? ሳይሆን፤ የምናውቀውንና የማናውቀውን ምን ያህል መለየት ችለናል የሚለውን መመለስ ስንችል ነው።
የትምህርት ዋናው ተግባር መሆን ያለበት አንድን ሰው እንዴት በትኩረት እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማሰብ እንዲችል ማድረግ ነው።
ትክክለኛ ትምህርት ከግለኝነት እጅጉን በላቀ ሁኔታ ከራስ ወዳድነት አውጥቶ ስለ ሁሉም ሰብዓዊ ፍጥረት ማሰብ እንድንችል ማድረግ የሚያስችለን ስርዓት መሆን አለበት። በመሆኑም ትምህርት ማለት “ወርቃማውን የነፃነት በር መክፈቻ ቁልፍ ነው”።
በእርግጥ ሐገራችን ኢትዮጵያ ለአለፉት 27 የጨለማ አመታት ዝግ አዕምሮ ባላቸው ፅንፈኛ የፖለቲካ ጋንግስተር በተገነባ ስርአት ትመራ እንደነበረና ታሪኳን ሲያንቋሽሹና ሲደልዙ የነበሩ ቅጥረኛ ባንዳ ምሁራን የነበሩባት ሐገር እንደነበረች ጠንቅቀን እናውቃለን::
በወቅቱ የዩኒቨርሲቲዎች ቅጥር ግቢ የምናያቸው ፅንፍ የረገጡ ትንኮሳዎች ዛሬና ትናንት የተፈጠሩ አይደሉም።ይልቁንም በተለይ በወጣቱ አዕምሮ ላይ የዘረኝነት ቁልፍ ቆልፎ ለ27 አመት በየክልሉ ትምህርቱ ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር ተጣብቆ ከታችኛው የትምህርት ደረጃ ጀምሮ ለዓመታት ሲዘራ የነበረው የጥላቻ ፖለቲካ ትርክት ውጤት ፍሬዎች ናቸው፡፡
ይህን ትውልዱን ያኮላሸ ስርአተ ትምህርት ነገ ዛሬ ሳንል አረሙን ከስር ነቅለን ጥለን አጉራ ዘለል ፅንፈኛ የፖለቲካ ታፔላ ተሸካሚዎችን ከየኒቨርሲቲዎቻችን ቅጥር ግቢ በብሔራዊ ምክክር መጥረጊያ ጠራርገን በአስቸኳይ ካላፀዳን፤ ወደፊት በመማር ማስተማሩ ተግባር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አስተማማኝ ሠላም የማምጣቱ ጉዳይ ምኞት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ያሳስበኛል::
ትምሕርት የሰውን ልጅ ወደ ፈጠራና ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እንዲያመራ የሚያደርገው ሲሆን፤ የፖለቲካ ፍልስፍናው የጦር መመሪያና የውዝግብ መፍጠርያ፣ ወይም ደግሞ የዘር ፖለቲካ መቋጠሪያ ፖሊሲ ማውጫ ሳይሆን የጦርነትንና የህብረተሰባዊ ውዝግብን ዋናውን ምክንያት መፍትሔ መፈለጊያ ዘዴ ነው። ምክንያቱም በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚነሱት ግጭቶችና ጥቃቶች በቀላል የፅንፈኛ ፖለቲከኞች ትንኮሳ የሚጀመሩ ቢሆንም፤ የሚያስከትሉት ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም።
የሚደርሰውን ጉዳትም ለመከላከል ተቀናጅቶ በአንድነት የሚሰራ የፀጥታ አካልና ጠንካራ የዲስፕሊን ሕግ ከሌለን ወደፊትም የከፋ ሁኔታ መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡
ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ታዳጊ ወጣቶችን በአጭር እንዲቀጩ፣ እፅዋቱ እንዲቆረጡ እንጂ እንዲተከሉ ስለማይፈልጉ ሐገር እንደ ሐገር እንዲረጋጋ እንዲቀጥል ሳይሆን ታሪክ እያበሻቀጡ እርስ በእርስ ወጣቱን በማጋጨት እርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ስለሚፈልጉ ሰይጣናዊ ስራ ስለሚሰሩ ትውልድ አምካኝ ጅላንፎ ፖለቲከኞች ላይ መንግስት ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን መውሰድና አደብ ማስገዛት ይኖርበታል፡፡ ጤናማ ማህበረሰብ ለማምጣት ዲሞክራሲ ያለገደብ አናርኪዝም ነው::
መንግስት እንደመንግስትነቱ ትልቁን የታሪክ ኃላፊነቱን ቢኖርበትም እኛ ደግሞ ልጆቻችን ላይ የምንረጭባቸውን የፅንፈኝነት መርዝ አቁመን በሚረባውም በማይረባውም አጣና እየቆረጥን በማደባደብ የሐገርና የሰላማዊ ህዝብ ስጋት ላለመሆን እንደ ዜጋ ኃላፊነቱን ካልወስድን በስርአተ ትምህርትና በፅንፈኛ ፖለቲከኞች ብቻ እያሳሰብን የምንፈልጋት አገር መገንባት አንችልም፡፡
ስለዚህ የአስተሳሰብ አድማሳችንን ሊያዳብረውና ወደ አርቆ አሳቢነት ቡድን-አልባ የሆነ ትግል ለማራመድ እንድንችል አስተሳሰባችንን እንድናዳብርና የአገራችንን የህብረተሰብ አወቃቀርና የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ በሰፊው እንድናጤን የሚያስችል ዕውቀት ለማዘመን በቅድሚያ አስተሳሰባችንን መቀየር ያስፈልገናል።
ይህን ማድረግ ካቃተን ግን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በመሆን ብቻ የምናመጣው ለውጥ የለም:: ይህን አዲስ ትውልድ ስለ አገሩና ስለወገኑ ከዘርና ከአጥንት ቆጠራ ባለፈ ራሱን ከመንደር ፅንፈኝነት ነፃ እንዲያወጣ የትምህርት ፖሊሲያችንን ቀይረን በመደመር እሳቤ አንድ መሆናችንን ልናስተምራቸው የግድ ነው::
የቅርፅ ልዩነቶች ካልሆነ በቀር መሰረታዊ የሆነውን የሰው ልጆች ፍላጎታችን ተመሳሳይነትና ተፈጥሯዊ የሆነ ስብዕና ያለው በታሪክ ደግሞ አብረን የተገመድን እንደሆን በደም የተሳሰርን ነገርግን በቋንቋ የተለያየን ኩሩ ባህል ያላን አለምን ያስደመምን ህዝቦች እንደሆን ልጆቻችንን በቅጡ ማስተማር ይኖርብናል::
ከዚያም ባለፈ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ትልቅ የሞራል መንፈስ የሚሰጠው እግዚአብሔር መሆኑን በመግለፅ የምናምን ፍርሐተ እግዚአብሔር ያደረበን ህዝቦች እንደሆን፤ በተፈጥሮ አንድነትና ልዩነት አንዱ ዘር ከሌላው ዘር ሳንነጣጠል ያለንና የነበርን፤ አንዱ ብሔረሰብ ከሌላው ብሔረሰብ የተዋለድን ስለሆነ የሚወርሰውና የሚጋራው ባህሪ በትክክል እንዳለን ለልጆቻችን ልናረጋግጥላቸው ይገባል::
ኢትዮጵያውያን በልዩነትና በአንድነት መካከል ባሉት ባህሪያት በመጣጣም፤ በፍቅርና በአንድነት በዘለቄታ አብረን የኖርን መሆናችንን የዘመናት ታሪካችንን እንዲፈትሹና እንዲመራመሩ የዘጋነውን የታሪክ ዲፓርትመንት (ትምህርት ክፍል) መክፈትና እድሉን ማመቻቸት ተገቢ ነው::
ወደፊትም በትምህርት ተቋማት ውስጥ የችግሮችን መንስኤ የሚያጠኑ ኃላፊነት የሚሰማቸውን ምሁራኖችን በማስጠናት የአገርን ሰቆቃ፤ የወጣቶችን ስቃይና መንገላታት፤ የእናቶችን ለቅሶና ሀዘን የሚሰጠውን ከባድ ትርጉም ወጣቱ ትውልድ እንዲገባውና ስርአት እንዲይዝ ማድረግ ይቻላል።ለዛሬው አበቃሁ፤ ቸር ሰንብቱ!
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን መጋቢት 14 /2014