ቤኒሻንጉል ክልል ከሌሎች ክልሎች ለየት የሚያደርገው የኢትዮጵያውያን አሻራ የሰፈረበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ መገኛ መሆኑ ነው። ክልሉ ከዚህም በላይ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉት መሆኑ የተረጋገጠለት ነው። ነገር ግን ላለፉት 27 ዓመታት እንደአንዳንዶቹ ክልሎች ዋና እና ወሳኝ ሳይሆን እንደጥቂቶቹ አጋር የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በአገሩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውሳኔዎች ላይ የበይ ተመልካች ሆኖ ጊዜዎችን እንዲያስቆጥር ተገዶ ቆይቷል።
ከሶስት ዓመት ወዲህ በተከሰተው ለውጥ ደግሞ እንደ ሌሎቹ ፖርቲዎች ሁሉ በጉባኤ የመሳተፍ፤ በአገር ጉዳይ ላይ ሃሳብ የመስጠት፤ የመምረጥ የመመረጥ እድልን አግኝቶ በአሁኑ ወቅት እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ድረስ የደረሰ የኃላፊነት ቦታ ያገኘ ሆኗል።
እኛም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከሆኑት ከአቶ ኢሰቅ አብዱልቃድር ጋር ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ባለፉት 27 ዓመታት እንደ ክልል በአገር ጉዳይ ላይ ትሳተፉ የነበራችሁትን ሁኔታ በሚመለከት እንዴት ያስታውሱታል?
አቶ ኢሰቅ ፦ ባለፉት ዓመታት በተለይም በኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን እኛን ጨምሮ አራቱ ክልሎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን ሳይችሉ ቆይተዋል። በሌላ በኩልም የክልሉ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ብቻ በጉባኤዎች ላይ ተገኝተው ሌሎች የሚሉትን ብቻ ከማዳመጥ ወጪ ሃሳብ የመስጠት የመቀበል ድምጽ የመስጠትም ሆነ በጠቅላላው ምንም ዓይነት ተሳትፎን ማድረግ አይፈቀድላቸውም ነበር።
ይህ ሁኔታ ደግሞ በአንድ አገር ላይ ሁለት አይነት ዜጋ ያለ እንዲመሰል አድርጎት ቆይቷል። በወቅቱ አጋር ክልሎች የበይ ተመልካች ሆነው እንዲቆዩ ከመደረጉም በላይ፤ ወሳኝ በሆኑ አካላት ይፈለጉ የነበሩ ሀብቶቻቸው መሬታቸው እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብታቸው ለመቀራመት ሲያስቡ ብቻ አሉ ይሉ ነበር።
እንደአገር በሚወሰኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ድምጻችን የሌለ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ እነሱ ተወያይተው ጨርሰው በእኛ ጉዳይ ሁሉ ወስነውልን የሚያወርዱልንን መመሪያ መፈጸም ካልሆነ በቀር ሌላ ተሳትፏችን ተገድቦ ኖሯል።
በተለይም እንደዚህ ባለው ታሪካዊና አገራዊ ጉባኤ ላይ የመሳተፍ እድል አልነበረንም። አልፎ አልፎ ታዛቢ ተብለን እንጠራለን፤ እሱም ግን የይስሙላ ታዛቢነት ካልሆነ በቀር ሕጉና ደንቡ በሚፈቅደው አኳኋን እንድንታዘብ አይፈቀድልንም ነበር።
በአንድ አገር ውስጥ እየኖርን አንዱ ዜጋ ሌላው እንደሁለተኛ ዜጋ ታይቶ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ ብሎም በአገር ጉዳይ ላይ ተመካክሮ ተከራክሮ ተግባብቶ መወሰን የማይችልበት ሁኔታ ነበር። በእውነት በጣም አሳፋሪ እና አሳዛኝ ጊዜ አሳልፈናል። በጠቅላላው የነበረው አስተዳደር እጅግ ከባድ በአንድ አገር ውስጥ የምንኖርን ሕዝቦች የከፋፈለ ነበር::
ዛሬ ላይ ግን መብታችን ተከብሮ ከአጋርነት ወደማዕከል መጥተን እኛም እንደዜጋ በአገራችን ጉዳይ ላይ ያገባናል ብለን እኩል በጉባኤ ተሳትፈን ተከራክረን በሚተላለፉ ውሳኔዎች ላይ ሃሳብ ተለዋውጠን በሚያስማሙን ላይ ተስማምተን ልዩነቶቻችንን አስጠብቀን ወጥተናል:: ይህ ሁኔታ ደግሞ እጅግ የሚያስደስት ነው።
አዲስ ዘመን ፦ የነበረው የአጋርነት ቆይታ በክልሉ ሕዝብ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ኢሰቅ፦ ተጽዕኖው በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ሕገ መንግስቱ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ ቢልም በተግባር የነበረው ነገር ግን ከዚህ ፍጹም የተለየ እጅግም አሳፋሪ ነበር። ኢሕአዴግ የሚባሉት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች የራሳቸውን አደረጃጀት ከፈጠሩ በኋላ ሌሎች አጋር የምንባል ክልሎች ላይ በተለይም ቁልፍ በሆኑ የሥራ መደቦች ላይ ሲመድቡ የነበሩት የራሳቸውን ሰዎች ብቻ ነበር።
በዚህም ራሳችንን ለመምራት አይደለም የእነሱን አቅጣጫ ተቀብለን ካላስፈጸምን ራሱ ከባድ ሁኔታ ሲፈጠር ቆይቷል። በክልሉ በፖለቲካ በኢኮኖሚ እንዲሁም በማኅበራዊ ዘርፍ ላይ ያሉ ሥራዎች በሙሉ ይያዙ የነበሩት ኢሕአዴጎቹ በሚመድቧቸው አስተዳዳሪዎች ከመሆኑም በላይ፤ ርዕሰ መስተዳደር ተብለው የተቀመጡትን የክልሉን ሰዎች እናማክር በሚል እጃቸውን እየጠመዘዙ የራሳቸውን አጀንዳ ሲያስፈጽሙባቸው መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።
በዚህ ምክንያት ደግሞ በክልል ያለን የፖለቲካ ተሳትፎ የምናደረግ እንዲሁም ሕዝቡ በጣም ሰልችቶት ይህ መሰሉ ለውጥ እንዲመጣ ከልቡ ሲፈለግና ሲጥር ነበር። እንደ አገር ከመጣው ለውጥ ጋርም ቀድመን የተቀላቀልነው ቀድሞ አጋር ተብለን ተገፍተን የነበርን ክልሎች ነን። በዚህም ብልጽግና ሲደራጅ ብሔራዊ ድርጅቶች ይባሉ የነበሩት ሁሉ ድርጅታቸውን አፍርሰው ወደ ብልጽግና የተቀላቀሉበት አገራዊ ድርጅት እንዲፈጠር የሆነበት፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ያለምንም አድሎና መገለል አገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል አደረጃጀት የተፈጠረበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አጋር የምንባለውም ክልሎች ይህንን ስያሜ ትተን አንድ ሆነው ወጥተናል።
በዚህም ሕዝቡ ደስተኛ ሆኗል። በሌላ በኩልም ባለፉት ሶስትና አራት አመታት በርካታ ችግሮች ውስጥ እንድናልፍ የተገደድን ቢሆንም፤ የመጣንበት መንገድ ግን እንደአገር ወጥ የሆነ አደረጃጀትን የያዘ ሌሎች ክልሎችንም እንደራሳችን አድርገን ስናይ የነበረበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በእነዚህ ዓመታት አገራዊ የኢኮኖሚ የፖለቲካ ማኅበራዊ ሥራዎችን እየመራን የመጣንበት ሁኔታ ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ብልጽግና የራሱን ጉባኤ አላደረገም። እኛም እንድ አጋር መቆጠራችን ቀርቶ የተዋሀድነው ከጉባኤው ውጪ ነበር። በዚህ ደግሞ አንዳንድ ሰርጎ ገቦችም ነበሩ። በዚህ የተነሳ በውስጥም በውጪም በርካታ ችግሮችን ለማለፍ ተገደናል።
ሰሞኑን ያደረግነው ጉባኤ ፈተና የሆኑብንን ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት የሚደራጁ የጠራ አመለካከት ያላቸው የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በእኩል የሚያዩ፤ ሌብነትን የሚታገሉ ለአድሏዊነት ቦታ የሌላቸው ሰዎች እንዲፈጠሩ ከፍ ባለ ግምገማ በተቻለ መጠን የጠራ ነገር ይዘን ተመልሰናል።
ይህ ሲባል ግን ሁሉም ነገር መቶ በመቶ ከችግር የጸዳ ነው ለማለት አይደለም። ሾልከው የገቡ ይኖራሉ። ወደፊት እነሱን የማጥራት ሥራ እየተሠራ አገራችን አሁን ካለችበት ከፍ እንደትል ይሆናል። ከዛ ውጪ ግን እንደቀድሞው አንዱ ኢሕአዴግ ሌላው አጋር እየተባለ የበይ ተመልካች የሚያደርግ አደረጃጀት አይኖርም።
ብልጽግና ፓርቲም ጉባኤውን ሲያደርግ ከሁሉም የአገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ ሰዎች ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ አገርን የሚመሰል አደረጃጀት ተፈጥሯል። ይህም ትልቅ ሥራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከውህደቱ በኋላ እንደ ክልል በተለይም ሕዝቡ ላይ በተጨባጭ የታየውን ለውጥን እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?
አቶ ይሰቅ፦ ብልጽግና ፓርቲ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ላይ ባልነበረ ሁኔታ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድ አቅፎ የተደራጀ ነው። ሕዝቡ በጣም ደስተኛ ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ ያለፉትን 27 ዓመታት አጋር ሆኖ በመቆየቱ ያጣውንም ያገኘውንም ነገር በውል ስለሚረዳ ነው። ፓርቲው እንደቀደመው ጊዜ አንዱን እየገፋ ሌላውን የሚያቅፍ ሳይሆን ወጥነት ባለው አመለካከት በፍትሐዊነት የሚመራ መሆኑን ሕዝቡ እየተረዳው ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ብልጽግና ፓርቲ እንደ ዜጋ ቆጥሮ ማዋሀድ ብቻ ሳይሆን ጥያቄዎችን በመመለስ ለሕዝቡ ቃል የሚገባቸውን ነገሮች መሬት አውርዶ ተግባራዊ ያደርግ ዘንድ ብዙ እየጠበቀ ነው። ሕዝቡ በአሁኑ ወቅት እያነሳ ካለው ጥያቄ መካከል የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ሲሆን ይህ ሁኔታ ይቀረፍልኛል ብሎም እየጠየቀ ተስፋ እያደረገ ነው።
በክልሉ አሁንም የጸጥታ ስጋቶች አሉ። ሕዝብ ይፈናቀላል፤ ይገደላል፤ ከዚህ ጋር ተያይዞም ጉባኤው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መቶ በመቶ መሬት ላይ ወርደው ማየትን እንደሚፈልግ እየጠበቀ ነው። በመላው አገሪቱ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለመቀልበስም የተቀመጡ አቅጣጫዎች ስላሉ እነሱን ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ሕዝቡ እየጠበቀ ነው።
እስከ አሁን የተከማቹና ያልተፈቱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችም በክልሉ በመኖራቸው ከዚህ በኋላ እነሱንም ለመፍታት አመራሩ እንደ አመራር ሆኖ እንዲገኝ የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ። አመራር ሲባል በልኩ የሕዝቡን ስሜት የሚያዳምጥ ለሆኑና ለሚሆኑ ነገሮች ፈጥኖ ምላሽ የሚሰጥ መሆን አለበት በሚል እየተሠራ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡም ተስፋ ጥሎ የሚጠባበቀው ይህንን ነው።
ሕዝቡም የራሱን፤ መንግሥትም የመንግሥትነት ሚናውን እየተወጣ ሕዝቡ በተረጋጋ ሁኔታ ኑሮውን እንዲኖር የሚያደርጉ ሥራዎችን በማከናወን የሕዝቡን ደስታ ወደ ምሉዕነት የመቀየርም ዕቅድ አለ። እስከ አሁን በክልሉ በታዩ ተጨባጭ ለውጦች ግን ሕዝቡ በጣም ደስተኛ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ ቀደም እንደ አጋር ከመታየት ባለፈ በየትኛውም ውሳኔን በሚፈልግ ነገር ላይ ተሳትፎ አልነበራችሁም። ከውህደቱ በኋላ በተለይም ከጉባኤው መጠናቀቅ ጀምሮ ወደ ፊት የመምጣት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የመሆን እድልን አግኝታችኋልና ይህ ለእርስዎ ምን ማለት ነው? ትርጉሙስ ምንድን ነው?
አቶ ኢሰቅ፦ ይህንን ሁኔታ በቀላሉ መግለጽ በጣም ይከብዳል፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት የይስሙላ አደረጃጀት የነበረበት በአንድ አገር ውስጥ እየኖረን አንዱ የአገሩ ጉዳይ የሚመለከተው ሌላው ደግሞ የማያገባው ሆነ መቆየቱ ያሳዝናል። ይህ ትልቅ ግፍ ሲሆን አሁን ላይ አንድ ሆነን ኢትዮጵያውያንን ዳር እስከ ዳር የሰበሰበ ፓርቲ ተመስርቶ ሁሉም ክልሎች በዛ ላይ ድርሻ እንዲኖራቸው ተደርጎ በሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም በአመራር ደረጃ የተመረጡ መሆኑ ጥሩና የወደፊቱን ጊዜም ብሩህነት አመላካች ነው። ይህንን አደረጃጀት መፍጠሩ ጥሩ ቢሆንም ነገር ግን ከዛ ባለፈ ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል።
ከዚህ ቀደም ሕዝቡ አጋር ተብለን የተገለልነው ለምንድን ነው? በአገራችን ጉዳይ ላይ አያገባችሁም ተብለን የተገፋነው ለምንድን ነው? የሚል ፖለቲካዊ ጥያቄ ነበረው። በአሁኑ ወቅት በሕዝቡ ዘንድ የነበረው የፖለቲካዊ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ መልስ አግኝቷል። ከዚህ ቀጥሎ የሚፈልገው ነገር ደግሞ የማኅበራዊው የኢኮኖሚው እንዲሁም የልማት ሥራዎች ተሠርተው ተጠቃሚ መሆንን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ ሕዝቡ የፖለቲካ ጥያቄው ቢመለስለትም አሁንም የመልማት ጥያቄው ደግሞ እንደቀጠለ ነው። ከዚህ በኋላ የህዝቡን ችግሮች አንድ በአንድ ለመፍታት በእናንተ በኩል ያለው ዝግጁነት እንዴት ይገለጻል?
አቶ ኢሰቅ፦ አሁን ሕዝቡ ትልቅ አደራ አሸክሞናል። ይህንን ኃላፊነት ደግሞ መወጣት የምንችለው እና ወደ ተግባር የምንቀይረው፤ አንዱ ጉባኤው ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመከተልና ወደ ክልላችን ተጨባጭ ሁኔታ በመተርጎም ሥራ ላይ በማዋል ይሆናል። በሌላ በኩል ሕዝቡ እያነሳ ያለው ምንድን ነው? ያማረሩት ነገሮች ምንድን ናቸው? የሚሉትን በመለየት ወደ ሥራ ለመግባትም በእኛ በኩል ሙሉ ቁርጠኝነት አለ።
በዚህ ሥራ ውስጥ በተለይም በአመራሩ በኩል የሚፈጠሩ ክፍተቶችን እየሞላን እየገመገምን ተልዕኳችንን የምንፈጽምበት እንደሚሆን ሁላችንም ተስማምተንና ተግባብተን ወደ ሥራ ገብተናል። በመሆኑም በሕዝቡ የሚመለሱ፤ በመንግሥት ትኩረት ሊያገኙ የሚገባቸው በማለት ከፋፍለን ሁሉም የድርሻውን እንዲወስድና በዛ ልክ እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ሥራም እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ክልሉ የሁሉም ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ያለበት የህዳሴ ግድብ የሚገነባበት አካባቢ በመሆኑ የብዙ ኃይሎች ፍላጎት አለበት። እንደው ዘላቂ እንዲሁም አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር ለማድረግ የደረሳችሁበት የዝግጁነት መጠን እንዴት ይገለጻል ?
አቶ ኢሰቅ፦ አዎ! የሰላሙ ጉዳይ ግንባር ቀደም የትኩረት መስካችን ነው። ምክንያቱም ለውጡን የማይፈልጉና የተለያዩ ሁኔታዎችን ተጠቅመው ለውጡን ለመቀልበስ የሚጥሩ ኃይላት ስላሉ እነሱን ማስቆም ይገባል። መንግሥትም እንደ መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራውን በጥንካሬና በቁርጠኝነት ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት መሥራት አለበት። በሌላ በኩልም ክልሉ የልማት ኮሪደር፣ የህዳሴው ግድብ የሚገነባበት በመሆኑ ብዙ ፍላጎቶች አሉ።
በተጨማሪ ጠረፍ ላይ ስለሆነ ከሱዳን በተለያየ መንገድ የሚገቡ ሰርጎ ገቦች በመኖራቸው ከውስጥም የግል ፍላጎት ያላቸው አካላት እየተደራጁ ሕዝቡን የሚያፈናቅሉበት ሁኔታ አለ። ይህንን እንግዲህ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ከጸጥታ አካላት ጋር ተነጋግረን ጸጥታ አካላቱ የራሳቸውን እቅድ አዘጋጅተው እኛም የሚጠበቅብንን ዝግጅት አድርገን ሥንሰራ ነበር።
አሁንም ጉባኤው ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች አንዱ የሕዝቡን ሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ በመሆኑ ከፌደራልና እስከ ክልሉ ጸጥታ አካላት ድረስ ተጣምረን ሕዝቡንም በማደራጀት የጸረ ሰላም ኃይሎችን እግር በእግር እየተከታተሉ የማጥፋቱን ሥራ ለመሥራት በቁርጠኝነት ተዘጋጅተናል። በተለይም ድንበር አካባቢ ላይ ከሱዳን ጋር አልፎ አልፎ ችግሮች ስለሚኖሩ ይህንንም ለመቆጣጠር መረጃን በተቀናጀ ሁኔታ እየተለዋወጡ ውጤታማ ሥራን ለመሥራት ታቅዷል።
አሁን እኛ ጋር ያለው ትልቁ ጫና ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ስለሆነ ይህንን አካባቢ ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን በመጠበቅና ሕዝቡም የራሱ መሆኑን ተረድቶ በአግባቡ እንዲጠብቀው ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በመሆኑም አካባቢውን ቀንና ሌሊት በመጠበቅ የሕዝባችን ደህንነት እንዲረጋገጥ ከማድረግ አንጻር ትልቅ ኃላፊነት እየተወጣን ነው። በቀጣይም አጠናክረን ለመቀጠል ዝግጁ ነን።
አዲስ ዘመን ፦መዋሀድ ማለት አንድ መሆን እንደመሆኑ፤ ከዚህ በኋላ ብልጽግና አንድ ሆኖ እንዲቀጥል በእናንተ በኩል ያለው ዝግጁነት ምን ይመስላል?
አቶ ኢሰቅ ፦ በነገራችን ላይ ውህደቱን ስንመኘው ደጋግመን ስንጠይቀው የነበረ ነው። የእኛ ክልል የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅር የሚኖሩበት ነው። ከዚህ ቀደምም አማራን፣ ትግሬን ፣ኦሮሞን ፣ ቤንሻንጉልና ደቡብን የሚወክሉ አደረጃጀቶች ነበሩ።
ነገር ግን ለክልሉ የፈየዱት ነገር አልነበረም። አሁን ግን እነሱን ሁሉ አፍርሰን አንድ ሆነን በአንድነት የቆምንበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ባለፈው 27 ዓመት በፖለቲካው መስክ የተሠራው ሥራ እንደ አገር ቀላል የማይባል ቁርሾን ያሳደረ ነው።
ይህንን የማስተካከል በተለይም የብሔር ጽንፈኝነትን የመዋጋት ሥራ በመሥራት የአንዱ ብሔር የራሱ እንደሆነ ጉዳቱም ጥቅሙም የጋራ መሆኑን ወንድማማችነት እህትማማችነትን ለማስፈን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ ሥራ የምንሠራበትና የተሻለች አገር ለመገንባት የምንጥርበት ሁኔታ እንደሚኖር እናምናለን።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::
አቶ ኢሰቅ፦ እኔም አመሰግናለሁ
ዕፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 /2014